Pages

Thursday, September 6, 2012

አሮጌውን ሰው አስወግዱ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

የዚህ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች በአዲሱ ዓመት በክርስትና ሕይወታቸው እንዲያድጉ እንጂ በፊተኛ ኑሮአቸው እንዳይመላለሱ ከጨለማ ሥራ ጋርም እንዳይተባበሩ ለማሳሰብ ነው፡፡ ይህን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈላቸው መልእክቱ ነው /ኤፌ.4፡23/፡፡ 

  ኤፌሶን በሮም መንግሥት ሥር ሆና ታናሽ እስያ በምትባል አውራጃ በኤጅያን ባሕር ዳር /በዛሬዋ ኢያዘሎክ-ቱርክ/ የምትገኝ ታላቅ የንግድ፣ የአምልኮና የወደብ ከተማ ነበረች፡፡ በከተማዋ አርጤምስ /በላቲኑ አጠራር- ዲያና/ ለምትባል አምላክ ትልቅ መቅደስ ታንጾ ነበር /ሐዋ.19፡24፡27/፡፡ የባሕር አሸዋ የድሮይቱን ከተማ ስለሸፈናት ዛሬ ሰው አይኖርባትም፡፡ 

   ምንም እንኳን ክርስትና ወደዚህች ከተማ የገባው በጵርስቅላና በአቂላ አማካኝነት ቢሆንም /ሐዋ.18፡18-19/ ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ የተቋቋመችው ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሦስተኛው ጉዞው ወደዚህች ከተማ መጥቶ ለሦስት ዓመት ያህል ወንጌል ካስተማረና ብዙ ሕዝብም ወደ ክርስትና ከመለሰ በኋላ ነው /ሐዋ.19፡8-27፣ 20፡31/፡፡ 

የኤፌሶን ከተማ ጢሞቴዎስ ጵጵስና የተሾመባትና በሰማዕትነት ያረፈባት፤ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሞትን ሳያይ የተሰወረባት፤ በኋላም በ431 ዓ.ም የንስጥሮስ ክሕደት በጉባኤ ተወግዞ የእመቤታችን ወላዲተ አምላክነት በይፋ የተመሰከረባት ከተማ ናት፡፡ 

ሐዋርያው መልእክቲቱን የጻፈላቸው ዋና ዓላማ አንደኛ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ምንም እንኳን አሕዛብ ቢሆኑም ከእስራኤል ጋር አንድ ሆነው በክርስቶስ ጸጋ መዳናቸውንና ሰማያዊ ክብር ማግኘታቸውን አውቀው በእምነታቸው እንዲጠነክሩ ለማድረግ ሲሆን /ምዕ.1-3/ ሁለተኛው ደግሞ በክርስትና ሕይወታቸው እንዲያድጉ እንጂ በፊተኛ ኑሮአቸው እንዳይመላለሱ ከጨለማ ሥራ ጋርም እንዳይተባበሩ ለማሳሰብ ነው /ምዕ.4-5/፡፡ እኛም እግዚአብሔር እንደወደደና እንደፈቀደ በሁለተኛው ዓላማ ላይ በማተኰር እንማማራለን፡፡ ማስተዋሉን ያድለን!!

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍና ቁጥር “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፤ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” ይላል /ኤፌ.4፡22-24/፡፡ 

   ምን ማለት ነው? አሮጌ ማለት ፊተኛ፣ የቀድሞ፣ የድሮ፣ የጥንት፣ ያረጀ ማለት ነው፡፡ ፊተኛ ኑሮ ማለትም የድሮ ባሕርይ፣ የቀድሞ ምልልስ ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ አሮጌነትን የተላበሰው በቀዳማዊ አዳም በደል ምክንያት ነው፡፡ ቀዳማዊ አዳም አስቀድሞ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረ ንጽሐ ጠባይዕ ነበረው፡፡ መተዳደሪያውም ጽድቅ ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህን እስከ መጨረሻ መጠበቅ አልቻለም፡፡ ሐዋርያው እንደነገረን  ዲያብሎስ ከቅንአት የተነሣ /ጥበብ.1፡24/ በእባብ አካል ተሰውሮ አዳምን በሚያታልል ምኞት ተፈታተነው /ዘፍ.3፡1/፡፡ ወደ እርሱ ፈቃድ ስቦም “አትብሉ” የተባሉትን የዛፍ ፍሬ ከሚስቱ ጋር እንዲበላ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ አዳም ከክብሩ ተዋረደ፡፡ አሮጌ ሆነ፡፡ ባሕርዩ ወደ ኃጢአት ያዘነበለ ሆነና በእርሱ ጠባይ
የሚወለደውም ሁሉ የኃጢአት ባርያ ሆነ፤ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የነበረው ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ ከመሆን ራቀ፤ ከፈቃደ እግዚአብሔር ይልቅ ከራሱ ጋር የሚነጋገርና የራሱንም ፈቃድ የሚፈጽም ሆነ /ሮሜ.5፡12/፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም የገባለትን ቃልኪዳን የሚፈጸምበት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ግን እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ከድንግል ተወለዶ ይህን አሮጌ ሰውነት አደሰለት /ገላ.4፡4/፡፡ በሰሌዳ ላይ የተሠራ ሥዕል ከውጭ በመጣ ቆሻሻ ሲዝግና ሲበላሽ ሥዕሉ የእርሱ የሆነ ሰው ሥዕሉ ያለበትን እንጨት ሳይጥል ሥዕሉን ያበላሸውን ቆሻሻ በማስወገድ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው እንደሚመልሰው ንጹሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ቃልም በአርአያው ተሠርቶ የነበረውን ሰው በኃጢአት በቆሸሸ ጊዜ ሥጋ ለብሶ አደሰለት፡፡ ጽድቅ ጐድሎት የነበረው አዳም ጽድቁን መለሰለት፡፡ እኛም ሐዋርያው፡- “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል” እንዳለን በ40ና በ80 ቀናችን ስንጠመቅ ታደስን፤ ክርስቶስን ለበስን፤ በእኛ ዘንድ የነበረው አሮጌው ሰውም ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ሞተ /ገላ.3፡27/፡፡

   ይህ ከሆነ ዘንዳ ሐዋርያው ተመልሶ አሮጌውን ሰው አስወግዱት፤ አዲሱን ሰው ልበሱት የሚለን ስለ ምንድን ነው? እርግጥ ነው በጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ጣፍጠን፣ ሰማያውያን ሆነን፣ የእግዚአብሔር የልጅነትን ሥልጣን በማግኘት በሐዲስ ተፈጥሮ መልካሙን ሥራ ለማድረግ ተፈጥረናል /ኤፌ.2፡10/፡፡ አሁን ኃጢአት ድል የሚነሣው የቀደመው አዳም ሰብእናችን፡ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልን በመላበስ፡ ኃጢአትን ድል የሚነሣ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “አሮጌውን ሰው አስወግዱ” ሲለን “ድጋሜ ተጠመቁ” እያለን ሳይሆን “በመንፈስ ቅዱስ በሰውነታችሁ ሠልጥኖ ያለውን የኃጢአት ልማድ አስወግዱ” ሲለን ነው፡፡ ይህም ከጥምቀት በኋላ ሌላ ከእኛ የሚጠበቅ ግዳጅ እንዳለ የሚያሳስበን ነው፡፡ እርሱም በውስጣችን ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በመታዘዝ የቀድሞውን የኃጢአት ልማዶቻችንን በማስወገድ ክርስቶስን መስለን መገኘታችን ነው፡፡ ሶርያዊው ቅዱስ ፊልክስዮስ ይህን “ሦስተኛው ልደት- The Third Birth” ብሎ ይጠሯል፡፡ 

  ሰው ከጥምቀት በኋላ በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መታዘዝ ሲጀምር ክርስቶስን ወደሚመስልበት የቅድስና ከፍታ ያድጋል፡፡ ነገር ግን በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ካልታዘዘና በቀድሞው ጠባዩ ከቀጠለ ምንም መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ያደረ ቢሆንም፣ ምንም ኃጢአትን ድል የሚነሣበት ሰብእና ገንዘቡ ያደረገ ቢሆንም፣ ምድራዊ መባሉ ቀርቶ ሰማያዊ ቢባልም፣ ፍጥረታዊ ሰው መባሉ ቀርቶ ክርስቲያን ቢባልም ይህ ሰው በአሮጌው ማንነቱ ውስጥ እንጂ አዲሱን ማንነቱ ውስጥ አይደለም ያለው፡፡ አንድ ሰው ከሰውነቱ የኃጢአትን
ፈቃድ አስወግዶ በጽድቅ ሕይወት በመመላለስ በእርሱ እግዚአብሔር መገለጥ ሲጀምር ያኔ ግን “በእውነት አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶታል” ይባልለታል፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ኃጢአትን ድል የምንነሣበትን ትጥቅ ታስታጥቀናለች፡፡ ትጥቁን ታጥቀን ኃጢአትን ድል የመንሣቱ ሓላፊነት ግን የእኛ ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን መጠመቁ ብቻ አያድነውም፡፡ የሚድነው በጥምቀት ባገኘው፣ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ጸጋ ተጠቅሞ  እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተመላለሰና አዲሱን ሰው ክርስቶስ ለብሶ በመገኘት ለዚህ ዓለም በመልካም ምግባሩ ብርሃን ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከልጅነት ጀምሮ የሚፈጸም ተግባራዊ የሆነ የክርስትና ሕይወት ምልልስን የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ግን አልረፈደም፡፡ ስለዚህ ለመዳን ከእግዚአብሔር ርቀን ለሰይጣን ፈቃዶች በመታዘዝ በሰውነታችን ያለመድናቸውን ኃጢአቶችንና የኃጢአት ፈቃዶችን ለማስወገድ ብንተጋ በውስጣችን ያደረው መንፈስ ቅዱስ አቅም ሆኖን እውነትን እየገለጥን አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለመልበስ እንበቃለን፡፡ 

  ተወዳጆች ሆይ! ሐዋርያው እንዴት ባለ የክርስትና ሕይወት እንመላለስ ዘንድ እንደሚፈልገን ታስተውላላችሁን? ይህን የሐዋርያው ቃል ስናስብና የእኛን ሕይወት ስናየው ምን ያህልም ከዚያ እንደራቅን ስናስብ ውስጣችን ይቃትታል፡፡ ዐይናችን በእንባ ይመላል፡፡ ምንም እንኳን በጥምቀት አዲሱን ሰብእናችን ብንለብሰውም እኛ ግን ወደ ቀደመ አሮጌ ሰብእናችን ወደ አሕዛባዊውም ኑሮ ተመልሰናል፡፡ አማናዊውን መና ትተን በግብጽ እንበላው የነበረውን ዓሣ፣ ዱባና ሽንኩርት እናስባለን /ዘኅ.11፡5/፡፡ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “ከእንግዲህ ወዲህስ ይህን አላደርግም” ብለን እንምላለን፡፡ ሆኖም ግን አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላን በየዓመቱ ወደዚያ ትፋታችን እንመለሳለን፡፡ 

  በመሠረቱ አዲስ ዓመት ሲባል አዲስ ማክሰኞና አዲስ መስከረም አይደለም፡፡ አዲስ የመነቃቃትና አዲስ የመታደስ መንፈስ እንጂ፡፡ እስራኤላውያን አዲስ ዓመት ሲገባ የሚያከብሩት የቂጣ በዓል አለ፡፡ ታድያ በዚህ ጊዜ ከሚያታዘዝዋቸው ትእዛዛት አንዱ እርሾ ያለበትን እንጀራ ማስወጣት ነው፤ ይህን ያላደረገ ሰው በድንጋይ ተወግሮ በእሳት ተቃጥሎ ይሞታል /ዘጸ.12፡15/፡፡ እርሾ መፃፃ ነገር ነው፤ እርሾ ቂም ነው፤ እርሾ በቀል ነው፤ እርሾ ክፋት ሁሉ ነው፡፡ በአጭሩ እርሾ የአሮጌው ሰው መገለጫ ነው፡፡ እኛስ አዲሱ ዓመት ሲመጣ ምን ያህል መፃፃ ነገራችንን እናስወግዳለን? ለምን ያህል ጊዜስ እናስወግደዋለን? ሐዋርያው ጳውሎስ ግን እየጠየቀን ያለው ለአንድ ሳምንት ወይም ለሁለት ሳምንት ሳይሆን “ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ” በማለት እስከመጨረሻ እንድናስወግደው ነው፡፡ 

  እኛ ግን ይህን ትተን ወደ ቀድሞ ሰብእናችን ተመልሰናል፡፡ በአዲሱ ሰዋችን ላይ የኃጢአት ሕንፃን እየገነባን እንገኛለን፡፡ የዘፈን፣ የስካር፣ ጣዖትን የመውደድ ሕንፃ በመገንባት አዲሱን ሰዋችን እያበላሸነው እንገኛለን፡፡ አሮጌውና ውራጁ ሊጠፋ ሲገባው በየዓመቱ እናድሰዋለን፡፡ ሐዋርያውም “ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ፡፡ ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ” ይለናል /ገላ.4፡11/፡፡
 ፍቁራን ሆይ! በዕድሜ ያረጀ ሰው አይታችኋል አይደል? በዕድሜ ያረጀ ሰው ቆዳው የተሸበሸበ ነው፤ ድምጹ ይቆራረጣል፤ መጋጥሞቹ በሪህና በቁርጥማት የሚሰቃዩ ናቸው፤ ብዙውን ጊዜ የሚናገረውን ስለማያውቅ ይዘባርቃል፤ ይረሳል፤ ዓይኑ በሞራ የተጋረደ ነው፤ ደም ግባት የለውም፤ ጉልበቱ የተዳከመ ነው፡፡ የአሮጌ ሰው ነፍስም እንዲህ የተጐሳቆለች ናት፡፡ የአዲሱ ሰው ነፍስ ግን ወጣትን ትመስላለች፡፡ ወጣት ደም ግባት አለው ነው፤ እርሷም ውብ ነች፡፡ ወጣት ሁል ጊዜ ዝግጁ ነው፤ እርሷም የሚመጣባትን ፈተና ለመዋጋት ዘወትር ዝግጁ ነች፡፡ 

  የአሮጌው ሰው ነፍስ እንዲህ ዓቅም ስለሌላት በቀላሉ ትወድቃለች፡፡ መዝሙረኛው “ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ” እንዳለ የአሮጌ ሰው ነፍስ ኃጢአት እንዳሻው ወደ ፊትና ወደ ኋላ ስለሚያወዛውዛት ሁል ጊዜ ለአደጋ የተጋለጠች ናት /መዝ.1፡4/፡፡ 

  በዕድሜ የሸመገሉ ሰዎች አስቀድመን ካልነው በተጫማሪ ብዙውን ጊዜ ጤና ስለሌላቸው ያስላቸዋል፤ ዓቅም ስሌላቸው አክታቸውን እንኳን መትፋት ይሳናቸዋል፤ በስንት ጥረትም በእጃቸው ይጠርጉታል፡፡ ያነጫንጫቸዋል፤ ትንሽ ነገር ያበሳጫቸዋል፤ ትንፋሽ ያጥራቸዋል፡፡ ከእኛ መካከል ምናልባት እንዲህ በጠና የታመመ ሰው ካለ እነዚህን ምልክቶች በቀላሉ ያውቃቸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ በሥጋ የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ የአሮጌው ሰው ነፍስ’ማ እንደምን ከዚህ የባሰች ትሆን?

 በሉቃስ ወንጌል ላይ የምናገኘው የጠፋው ልጅ እንዲህ ሆኖ ታሞ የገረጣ የከሳ ልጅ ነበር፡፡ ሲወስንና ሲለወጥ ግን ወድያው እንደ ቀድሞ ወጣት ሆነ፡፡ “ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁ” ባለ ጊዜ አሮጌው ሰውነቱ እየከሰመለት… እየጠፋለት… አዲሱ ሰውነቱ ደግሞ እየፋፋለት… መጣ /ሉቃ.15፡17/፡፡ በሐሳቡና በቃሉ ተግባር እየጨመረበት ሲመጣ ደግሞ የበለጠ እየወፈረ… እያገገመ… መጣ፡፡ “ወደ አባቴ ልመለስ” ብሎ እዚያ የቆየ አይደለም፤ ፈጥኖ ድሮ የሄደበትን መንገድ እየተወ… እየተወ… እየተወ… ወደ ቤቱ ተመለሰ እንጂ፡፡ 

  ተወዳጆች ሆይ! ከአባታችን ቤት በጣም ርቀን በአሕዛብ ሀገር ገብተን ቢሆንም ፀሐይዋ ገና አልጠለቀችምና አሁንኑ ወስነን እንመለስ፡፡ የመንገዱን ርዝማኔ እየታሰበን በዚያ የምንዘገይ አንሁን፡፡ እኛ ፈቃደኞች ከሆንን የሄድንበትን መንገድ ለመመለስ ከቀድሞ ይልቅ የቀለለና የፈጠነ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የሄድንበትን የእንግድነት ሀገር ወስኖ መልቀቅ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከሄድንበት የኃጢአት ሀገር ተመልሰን ከአባታችን ቤት እንግባ፡፡ አባታችን እኛን ለመቀበል ፍሪዳውን አርዶ ቤቱን አሰናድቶ እየጠበቀን ነውና ከዚያ የኃጢአት ሀገር ተሎ ለቀን እንውጣ፡፡ጤናን ከማጣት የተነሣ የገረጣውን ሰውነታችን በእንግድነት ሀገር ሳይሞት ፈጥነን እንመለሰው፡፡ 

   ተወዳጆች ሆይ! ሓኪሞች አንድ የታመመ ሰውን “ከአልጋህ ተነሥና ተመላለስ” ሲሉት መጀመርያ እንደሚፈራ ወደ አባታችን ቤት መመለሱን የምንፈራ አንሁን፡፡ ይህ ከአልጋ የሚነሣ ታማሚ የሚያበረታቱት ሐኪሞችና ቤተሰቦች በዙርያው እንዳሉ ሁሉ በከእኛ ጋርም መንፈስ ቅዱስና እልፍ አእላፍ መላእክት አሉ፡፡ ታማሚው አንዴ ከተነሣ በኋላ ዓቅምና ብርታት እያገኘ እንደሚሄድ ሁሉ እኛም አንድ ቀንና ሁለት ቀን መመለስን ስንጀምር በሦስተኛው ቀን የበለጠ እየበረታንና እየፈጠንን እንሄዳለን፡፡ የበለጠ በመጣን ቁጥር የአባታችንን ቤት አሻግረን ስለምናያት ጉልበት እናገኛለን፡፡ የተዘጋጀልንን ድግስ በሩቅ ስናይ ቁጥር የበለጠ ብርታት እየተሰማን እንመጣለን፡፡
   የጠፋው ልጅ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ስላባከነው ገንዘብ አባቱ አንዳች ስንኳ የጠየቀው አይደለም፡፡ የወቀሳ ቃል አልተናገረውም፡፡ ፊቱን አላጠቆረበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሮጦ ሄዶ አንገቱን አቅፎ ሳመው እንጂ፡፡ ከወቀሳ ይልቅ ባሮቹን ፈጥነው የተሸለ ልብስ እንዲያለብሱት፣ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ እንዲሰጡት አዘዛቸው እንጂ፡፡ የሰባውን ፍሪዳ አምጥተው እንዲያርዱለት አዘዛቸው እንጂ፡፡ ፍቁራን ሆይ! አባታችንም እንዲህ አዘጋጅቶ እየጠበቀን ነውና እንመለስ፡፡ በእንግድነት ሀገር ስለምን እየተራብን እንቆያለን? አባታችን እኮ ለገዛ ልጁ ስንኳ ያልራራለት ይልቁንም ስለሁላችን ቤዛነት ለሕማም ለሞት አሳልፎ የሰጠው አፍቃሪያችን ነው /ሮሜ.8፡32/! እንዲህ አሮጌው ሰብእናችንን አውልቀን ስንመለስ’ማ አባታችን እንዴት በእጅጉ አይደሰት?! እንኳንስ እርሱ የሰማይ መላእክትም በእኛ ምክንያት ሐሴት ያደርጋሉ፡፡ 
  እንግዲያውስ እንምጣና የተጨማደደውን አሮጌ ፊታችን እናድሰው፡፡ እንምጣና በበሽታ የተጠቃው አሮጌ ሰውነታችንን አውልቀን በሽታን የመቋቋም ዓቅም ያለው አዲሱን ሰውነታችን እንልበስ፡፡ እንምጣና ለይስሙላ ሳይሆን ለእውነት በሚሆኑ የጽድቅና የቅድስና ልብስ እናጊጥ፡፡ እንምጣና አክሊልን እንደለበሰ ሙሽራ በጌጥ ሽልማትም እንዳጌጠች ሙሽሪት የመዳንን ልብስ እንልበስ /ኢሳ.61፡10/፡፡ 

  “ይህን በስደት ሀገር ሆኜ፣ በዐረብ ሀገር ሆኜ እንዴት ማድረግ እችላለሁ?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲህ በስደት ሀገር ኖረው ይህን የፈጸሙት ሰዎች አሉ፡፡ ዮሴፍ ምንም እንኳን በገዛ ወንድሞቹ ተሸጦ ከከነዓን ርቆ በግብጽ ሀገር ቢኖርም በጴጢፋራ ቤት ሆኖ ይህን ከማድረግ ምንም አልከለከለውም /ዘፍ.39/፡፡ ወጣቱ ዳንኤል ከኢየሩሳሌም ርቆ በባቢሎን በምርኮ ቢኖርም ይህን ከማድረግ ምንም አልከለከለውም /ዳን.6/፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ከሚወዷት እናት ሀገራቸው ርቀው በስደት ሀገር ቢኖሩም እግዚአብሔርን ከማምለክ ምንም አልከለከላቸውም /ዳን.3/፡፡ የእነ ዮሴፍ አምላክ የእኛም አምላክ ነው፤ የእነ ዳንኤል ጌታ የእኛም ጌታ ነው፤ የሠለስቱ ደቂቅ ንጉሥ የእኛም ንጉሥ ነው፡፡ እንግዲያውስ እኛም ይህን ማድረግ ይቻለናልና እነዚህን ቅዱሳን አብነት አድርገን ወደ አባታችን ቤት እንመለስ /ዕብ.12፡1/፡፡

 ይህን እንድናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!  

1 comment: