Pages

Wednesday, September 26, 2012

መስቀል ኃይላችን ነው



ከጌታችን ስቅለት በፊት መስቀል መቅጫ ነበር፡፡ ሰውን በመስቀል መስቀል የጀመሩት ፋርሳውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎችኦርሙዝድየሚባል የመሬት አምላክ ስለበራቸው እርሱን ላለማርከስ ብለው ወንጀለኛውን ሁሉ ከመሬት ከፍ አድርገው ሰቅለው ይቀጡት ነበር፡፡ በኋላም ይህ አድራጎት በሮማውያን ግዛት ሁሉ ሕግ ሆነ፡፡
በኦሪቱ ሥርዓትም በመስቀል የሚቀጡ ርጉማን ውጉዛን ነበሩ፡፡ ከጌታችን ስቅለት በኋላ ግን የነጻነታችን አርማ የድል ምልክታችን ሆነ፡፡ ክርስቶስ ይህን መስቀል ዙፋኑ አድርጎ ሰላምን እኩልነትን አድርጓልና፡፡ ስለዚህ ካሉን ነገሮች ሁሉ መስቀል የላቀ ክብር አለው፡፡


በእኛ ዘንድ የሆነው ሁሉ የተፈጸመው በመስቀሉ ነው
፡፡ ማንም አዲስ ፍጥረት ቢሆን የመስቀል ምሥጢር በእርሱ ዘንድ አለ፤ ማንም ሥልጣነ ክህነትን የተሾመ ቢኖር የመስቀል ምሥጢር ከእርሱ ጋር አለ፤ ማንም ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚካፈል ቢኖር ከእርሱ ዘንድ ይህ ምሥጢር አለ፤ ማንም ሥራውን በሚያከናውንበት ቦታ ሁሉ የድላችን አርማ የሆነው ይህ መስቀል አለ፡፡ ስለዚህ መስቀል በልባችን ብቻ ሳይሆን በግንባራችን፣ በልብሳችን፣ በግድግዳችን፣ በመጽሐፋችን፣ በመስኮቶቻችን እና በቤት ዕቃዎቻችን ሁሉ በክብር እንቀርጸዋለን፡፡ የሀገራችን ክርስቲያናዊ ባሕል የሆነው ጥልፉ ዝምዝሙ፣ ጌጣ ጌጡ ሌላው ቀርቶ ሴቶች በግንባራቸውና በሌላውም አካላቸው በዚሁ መስቀል ቅርጽ ይጠቆራሉ፤ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ብቻ ሳይሆን ከሞቱም በኋላ ዐፅማቸው በሚያርፍበት መቃብራቸው ላይ ይህ መስቀል አለ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት መስቀል የሞትና የመከራ ምሳሌ መሆኑ ቀርቶ የትንሣኤና የሕይወት ምልክት መሆኑ ስለገባቸው ነው፡፡

ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰጠን መዳን፣ ነጻነት እና መልካሙን ሁሉ ምልክቱ መስቀል ነው እንላለን፡፡ ጌታ በዚህ መስቀል ለመታረድ እንደ በግ ተነዳ /ኢሳ.53፡7/፡፡ ስለዚህ የዚሁ መስቀል ዓለማ ስለገባን መላ ሰውነታችንን በትእምርተ መስቀል እናማትባለን፡፡ የዚሁ መስቀል ዓላማ ስለገባን መላ ሰውነታችን በትእምርተ መስቀል ስናማትብ ልባችን ሁሉ በሐሴት ይመላል፡፡ ነጻነትን የሚያጐናጽፉ ነገሮች በዚህ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ጳውሎስ በጥበብ ከባርነት አርነት ወደ ወጣንበት ምሥጢር ሲመራን ወደ መስቀሉ እና ወደ ክቡር ደሙ ይወስደናል፡፡ እንዲህም ይለናል፡- “በዋጋ ተገዝታችኋልና የሰዎች ባርያ አትሁኑ” /1ቆሮ.7፡23/፡፡ አዎ! “በመስቀሉ ላይ በተከፈለው ዋጋ ተገዝታችኋል እና የሰዎች ባርያ አትሁኑ” ይለናል፡፡
ስለዚህ ከሁሉም በፊት ይህንን ምሥጢር በልባችን በእምነት ተክለን በጣታችን አመሳቅለን እናማትባለን፡፡ ሐዋርያው እንዳለው ይህ የመስቀል አማናዊና ምሥጢራዊ ኃይል ላመን እንጂ ላላመኑ አልደረሳቸውም፡፡ እንዲያውም መስቀልን በመቅጫነቱ የሚመለከቱ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ በእርግጥም መስቀል ለሞት ለአጋንንት መቅጫ ሆኗል፡፡ በልባችን ተተክሎ በጣታችንም ስናማትብ የቆሰለበትን ምላጭ እያየ፣ የተገደለበትን ሰይፍ እየተመለከተ ርኩስ መንፈስ ወደ እኛ አይቀርብም፡፡ ወንጀለኞች በፈጸሙት ጥፋት አንገታቸው ሲቆረጡ ብንመለከት በድንጋጤ እና በፍርሐት የምንቀጠቀጥ ከሆነ ኃይሉ ሁሉ የመከነበት፣ አንገቱንም ሁሉ የተቆረጠበት መሣርያ በእጃችን ቢመለከት ሰይጣን እንዴት አይራድ? እንዴትስ አይፍራ? እንዴትስ አይንቀጥቀጥ?
ይህ መስቀል በአባቶቻችን እና በእኛ ዘመን ብዙ የተዘጉ በሮችን ከፍቷል፤ ብዙ መርዛማ መድኃኒቶችን አምክኗል፤ የብዙ መርዛማ ዕፅዋቶችን ኃይል ከንቱ አድርጓል፤ በመርዛማ እባብ የተነደፉ ሰዎችን ፈውሷል፡፡ ደግሞስ የሲዖል የምሥጢር ቁልፎችን ከሰባበረ፣ የገነትን በር ከከፈተ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስኬድ መንገድን ከቀየሰ፣ የዲያብሎስን ነርቭ ከቆረጠ፤ አሁን መርዛማ መድኃኒቶችን ቢያመክን፣ በመርዛማ እባብ የተነደፉትን ሰዎች ቢፈውስ ሌሎችም ተአምራት ቢያደርግ ምን ይደንቃል?
እኛ ግን ይህን ተረድተን በልቡናችን እንቀርጸዋለን፤ የነፍሳችን መዳኛ የሆነው ይህንን መስቀል በአንገታችን እናስረዋለን፡፡ ዓለምን ሁሉ የፈወሰ እና ያጣፈጠ፤ ስሕተትን ሁሉ ያስወገደ፤ እውነትን የመለሰ፤ ምድርን ገነት ያደረገ፤ ሰዎችን መላእክት ያደረገ ይህ የመስቀሉ ምሥጢር ታላቅ ነው፡፡ በዚሁ መስቀል ምክንያት ዲያብሎስ አስፈሪነቱ ቀርቷል፤ ሞት ወደ እንቅልፍ ተቀይሯል፤ በእኛ ላይ ነግሦ የነበረው የሞት ፍርድ ተወግዶ ከእግራችን በታች ተጥሏል፡፡
ማንም ወደ እኛ መጥቶ፡- “በዚሁ መስቀል ላይ የተሰቀለውን ታመልከዋለህን?” ቢለን በፍጹም ደስታ እና ሐሴት ተመልተን፡- “አመልከዋለሁ ብቻ ሳይሆን ይኸንን ማድረጌም መቼም አላቆምም” እንለዋለን፡፡ እንዲህ ስላልነው ቢስቅብንም ማንም ከላይ ካልተሰጠው በቀር ይኸንን ምሥጢር ማወቅ የሚችል የለምና እናለቅስለታለን፡፡ ምክንያቱም የሚስቅብን ገና ፍጥረታዊ እና የክርስቶስን መንፈስ ያልተቀበለ ሰው ስለ ሆነ ነው /1ቆሮ.2፡14/፡፡ ሕፃናት በዚሁ መስቀል ሲባረኩ ወይም ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሲካፈሉ ሊስቁ ይችላሉ፡፡ ይኸንን መስቀል የማያከብሩትም እንደ እነዚህ ሕፃናት እንደውም ከእነዚህ የባሱ አላዋቂዎች ናቸው፡፡ ሕፃናቶቹስ ካለማወቅ የተነሣ እንዲህ ያደርጋሉ፤ እነዚህ ሰዎች ግን ምንም ዕድሜን የጠገቡ ቢሆኑም የመስቀሉን ምሥጢር ለማወቅ ሕፃናት ናቸውና አያከብሩትም፣ ይስቃሉም፡፡
ስለዚህ እንመሰክራለን፡- መስቀል ክብራችን ነው፤ መስቀል አርማችን ነው፤ መስቀል ዘውዳችን ነው፤ በመስቀሉ መባረክን አናፍርም፤ በመስቀሉ ማማተብን አናፍርም!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

1 comment:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን
    መልካም የመስቀል በዓልን ለሚያምኑ ሁሉ እመኛለሁ ፡፡

    ReplyDelete