Pages

Thursday, September 27, 2012

የዕርቅ ቀን


    በእግረ ሕሊናችሁ ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 1010 ኪ/ሜ ልውሰዳችሁ፡፡ የጠቀስኩላችሁን ያህል ርቀት ስትጓዙ ዓድዋ ከተማ ትደርሳላችሁ፡፡ ዓድዋ ማለት “ኦድዋ” ከሚል የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ከበብዋት ማለት ነው፡፡ ከተማዋ ይህን ስም ያገኘችው ዙርያዋ በተስዓቱ ቅዱሳን ገዳማት የተከበበች ስለሆነ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አጠገብዋም ዓዲ አቡን - የአቡን ሀገር የምትባል ሌላ ከተማ አለች፡፡ እዚያ አከባቢ ብቻ የሚበቅል ቲማቲም መሰል አትክልት አለ፡፡ ስሙም “ጸብሒ አቡን” ይባላል፡፡ የአቡን ወጥ እንደማለት ነው፡፡
  ከከተማዋ 3.5 ኪ/ሜ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በእግር ስትሄዱ “ብዒቶ” የምትባል ትንሽ የገጠር መንደር ታገኛላችሁ፡፡ ተወልጄ ያደግኩት እስከ 12ኛ ክፍልም ድረስ ንግሥተ ሳባ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እየተመላለስኩኝ የተማርኩት እዚች የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ እዚች መንደር 25 የሚሆኑ የገበሬ አባዎራዎች አሉ፡፡ በዚህች መንደር አሁን ላይ ሆኜ ሳስተውለው በጣም የሚደንቀኝ ባህል አለ፡፡ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን (የመስቀል በዓል ዕለት) በተለየ ሁኔታ ይከበራል፡፡ አስቀድሞ ሕዝቡ ለዳቦና ለጠላ የሚሆን እህልና ጌሾ ያዋጣል፡፡ ከዚያም ከ25ቱ አባዎራዎች በዕጣ የደረሰው አንዱ አባዎራ እቤቱ ወስዶ እንዲያዘጋጅ ይሆናል፡፡
  ዕለቱ (መስከረም 17) ሲደርስ ከጧቱ 5 ሰዓት ጀምሮ የተዘጋጀውን ዳቦና ጠላ በመንደሩ እምብርት ወደምትገኘው ትልቅ የሾላ ዛፍ ስር ይመጣል፡፡ ከቀኑ 7 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ድረስ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እዚያ ዛፍ ስር ይሰባሰባል፡፡ ሁሉም ከተሰበሰቡ በኋላ የመንደሪቱ ሽማግሎች ይቆማሉ፡፡ ከዚያም የተጣላ ሰው ካለ ሕዝቡን ይጠይቃሉ፡፡ የተጣሉ ሰዎች ካሉም በየተራ እጃቸውን እያወጡ “እኔ ከእከሌ/ ከእከሊት ጋር ተጣልቻለሁ” ይላሉ፡፡ ያፈሩ ካሉም እንደተጣሉ የሚያውቁ ሌሎች ሰዎች ይጠቁሟቸዋል፡፡ ከዚያም በዳዩና ተበዳዩ ይቆማሉ፡፡ በዳዩም “እኔ እከሌን/ እከሊትን እንዲህ እንዲህ አድርጌ በድዬዋለሁ/ በድያታለሁና እነሆ በእናንተ ፊት ይቅርታ እጠይቀዋለሁ/ እጠይቃታለሁ” ብሎ ተናግሮ/ ተናዝዞ በተበዳዩ እግር ስር ይደፋል፡፡ ተበዳዩም “ይቅር ለእግዚአብሔር” ብሎ በዳዩን ዕቅፍ አድርጎ ይስሟል፡፡ አንዳንዱም በዕንባ የሚራጭ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሽማግሎቹና ሕዝቡ በአንድ ላይ ሆነው ያጨበጭባሉ፡፡ ሌሎችም ካሉ እንዲህ ባለ መንገድ ይታረቃሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላውና ዳቦው ለሕዝቡ ይታደላል፡፡ አጋፔ እንበለው ይሆን? ይህ ሲያልቅ እዚያ በፍቅር የባህል ዘፈን ሲዘፍኑ ያድራሉ፡፡
  አሁን ላይ ሆኜ ይህን ሳስበው “እርሱ ሰላማችን ነውና ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልን በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው” የሚለው የሐዋርያው ቃል ትውስ ይለኛል /ኤፌ.2፡14-16/፡፡ በእርግጥም በጌታ መስቀል ሕዝብና አሕዛብ፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት ታርቀዋል፡፡ የዚህች መንደር ገበሬዎችም በመስቀሉ መታሰብያ ዕለት በመካከላቸው ዕርቅን ይፈጽማሉ፡፡ ያለፈውን ትተው ዓመቱ በዕርቅ፣ በይቅርታ፣ በፍቅር ዕንባ ይጀምራሉ፡፡ አባቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ምንም ማንበብ ወደማይችለው ገበሬው እንኳን ሳይቀር በገቢር እንዴት እንዳሰረጹት ሳስብ እደነቃለሁ፡፡
  የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተብሎ ለሁለት የተከፈለው ቅዱስ ሲኖዶሳችን አንድ ለማድረግ አባቶች ከእነዚህ ገበሬዎች ምን ይማሩ ይሆን? የአንዲት እናት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሆነው ሳለ የእከሌ ቡድን የእከሌ ቡድን የሚባባሉ አገልጋዮች ምን ይማሩ ይሆን? በጐጠኝነት፣ በጐሳ፣ በብሔር ስም የምንጣላ ሰዎችስ? እንዲህ ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው  የተከበረ ባህላችንስ ልንጠብቀው፣ ልንንከባከበው አይገባም ትላላችሁን? እስኪ እናንተም ባደጋችሁበት ወይም በምትኖሩበት መንደር እንዲህ ያለ የተቀደሰ ባህል ካለ አካፍሉን!
 በዚህ አጋጣሚ ሳላውቅ በስሕተት አውቄም በድፍረት የበደልኳችሁን ሁሉ ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃችኋለሁ!
 መልካም የይቅርታ፣ የዕርቅና የፍቅር ዘመን ይሁንላችሁ!!!

1 comment:

  1. "አባቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ምንም ማንበብ ወደማይችለው ገበሬው እንኳን ሳይቀር በገቢር እንዴት እንዳሰረጹት ሳስብ እደነቃለሁ፡፡"
    እምነታችን የገባቸው ቀና ሰዎች እንዲህ ያስባሉ ፣ እነዲህም ይመሰክራሉ ፤ ሌሎች ደግሞ ዛፍ ሥር በመደገሳቸውና ተሰባስበው በማክበራቸው ለጣዖት /ለዛፍ/ እየደገሱ ነው እንደሚሉን አልጠራጠርም ፡፡ ግን አኩሪ ባህላችንን ማለትም የእምነታችን መገለጫ የሆነውን ልማድ እንዲህ በየአጋጣሚው ማስረዳቱ ስተው ለሚያስቱ መከላከያ መፍትሄ ፣ ለማናውቀውም ትምህርት ነውና ወንድሜ ጅምርህን ቀጥልበት ፡፡

    በተረፈ እርቅና ስምምነት ላልከው ፣ ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ባይነት ከንስሐ ቀጥሎ የእምነት ወይም የሃይማኖታችን የመጀመሪያው መገለጫ ስለሆነ እግዚአብሔር የሁሎችንም አባቶች ልብ ይመልስልንና ቀናውን መንገድ ያስቃኝልን ፡፡ ይህ ችግር በዚህ አጋጣሚ ካልተፈታ ግን ቤተ ክርስቲያናችን የሰሜንና ደቡብ ፣ የምስራቅና ምዕራብ ያህል ለዘለዓለም የማትገናኝ መሆኗ አይቀሬ ስለሚሆን ሁሉም በአዲሱ ዓመት በጥሞና ቢያስብበት መልካም ነው በማለት መልዕክትህን እጋራለሁ ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ለምእመኑም መጥፎ አርዓያ እየሆኑት ስለሆነ ሊያዝኑለት ይገባል ፡፡ ማንን አይቶ ይማራል ? ወይስ የወንጌል ቃል “መባሕን አስቀምጠህ ሂድና መጀመሪያ ታረቅ” የሚለው የጌታ ትእዛዝ እነርሱን አይመለከታቸውም ማለት ይሆን ? ወይስ በመስቀል ላይ የሞተልንን ጌታ ክደው አገልግሎታቸው ምድራዊ (ዓለማዊ) አድርገውታል ይባል ?

    የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እንዲፈጠር እግዚአብሔር ይርዳን

    ReplyDelete