Pages

Wednesday, July 17, 2013

ውሉደ ብርሃን ትሆኑ ዘንድ በብርሃን እመኑ - የዮሐንስ ወንጌል የ፵፯ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.፲፪፡፴፬-፶)

በገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ውሸት በእልፍ የሚያማምሩ ሕብረ ቀለማት ብትቀባም ውሸትነቷ ከመታወቅ አታመልጥም፡፡ ያረጀና ያፈጀ ግድግዳም ምንም ያህል በሚያምር ቀለም ቢቀባም አዲስ መሆን አይችልም፡፡ የሚዋሽ ሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ ምንም ያህል ውሸቱን እውነት በሚመስሉ ውብ ቃላት ቢያሽሞነሙነውም ውሸታም መሆኑ በቀላሉ ይታወቃል፡፡ በአይሁድ ሕዝብ ዘንድ የምናስተውለውም ይኸንኑ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን (በአሚን) ወደ እኔ እስባለሁ” ሲላቸው /ቁ.፴፪/ እነርሱ ግን መልሰው፡-እኛስክርስቶስ (በመሲሑ) ሞት እንደሌለበት፣ ለዘለዓለምም እንደሚኖር በኦሪት ሰምተናል /መዝ.፻፱፡፬፣ ኢሳ.፬፡፮፣ ሕዝ.፴፯፡፳፮፣ ዳን.፯፡፲፫-፲፬/፤ አንተስ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው እንደምን ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ክርስቶስስ ማን ነው?” ይሉታልና /ቁ.፴፬/። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አንቀጽ በተረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ይላል፡- “ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች መሲሑ (ክርስቶስ) ለመዘኑ ኅልፈት ለመንግሥቱም ሽረት የሌለበት ዘለዓለማዊ መሆኑን ከተለያዩ መጻሕፍተ ብሉያት ቢያነቡም፣ እዚያው ዘለዓለማዊነቱን ባነበቡበት ቦታ ላይም ለሰው ልጆች ሲል ስለሚደርስበት መከራ መስቀልና ስለ ትንሣኤው ጨምረው አንብበዋል፡፡ ‘ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም’ /ኢሳ.፶፫፡፯/፤ ‘ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከመሰማርያህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ ተኛህ እንደ ሴት አንበሳም አንቀላፋህ እንደ አንበሳ ደቦልም የሚቀሰቅስህ የለም’ /ዘፍ.፵፱፡፱/ እና የመሳሰሉት ቃላት ደጋግመው አንብበዋቸዋል፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ (መሲሑ) አይደለም ለማለት ስለፈለጉ ብቻ ‘እኛስ በመሲሑ ሞት እንደሌለበት፣ ለዘለዓለምም እንደሚኖር በኦሪት ሰምተናል’ ይላሉ፡፡ የመሲሑ ሞት ዘለዓለማዊነቱን የሚጻረር አስመስለው ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ አንዱን ጫፍ ብቻ በመያዝም ወደ ስሕተት ይነጉዳሉ፡፡ ‘ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ’ ሲላቸው ‘እሞታለሁ እሰቀላለሁ’ ማለቱ እንደሆነ ስለገባቸው ‘አቤቱ ሆይ! ስለመሲሑ የምናውቀው አሁን እንደነገርንህ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ይሞታል ይሰቀላል የምትለው መሲሕ ፈጽመን አናውቀውም (አንተን አናውቅህም) ይሉታል” ይላል /St. John Chrysostom, Homily LXVIII/፡፡ ዓምደ ሃይማኖት የተባለው ቅዱስ ቄርሎስም “ከመጻሕፍት ጥቅስ በመጥቀስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረው ትምህርት ሐሰት ነው ለማለት ይጥሩ ነበር” ይላል /St. Cyril of Alexandria, Commentary on The Gospel of John, Book 8/፡፡
     

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስስ ምን አላቸው? ሞቱ እንደ አንድ ተራ ሰው ሞት እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ለጥቂት ቀናት ስለ ሰው ልጆች ብሎ በምድር ልብ ቆይቶ እንደሚነሣ ለማሳየት ብርሃን እኔ ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” ይላቸዋል /ቁ.፴፭/ ቅዱስ ቄርሎስ ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስፍቶና አምልቶ ሊያስረዳቸው አልፈቀደም፡፡ ይልቁንም በእነርሱ የአረዳድ መጠን ሊጠቅማቸው ወደሚችለው ሐሳብ ይሄዳል እንጂ፡፡ በመሆኑም ወደ ስሕተት የመሄዳቸው ምሥጢር፣ መጻሕፍትንም ያለማወቃቸው ምንጩ ከእግዚአብሔር መራቃቸው እንደሆነ ይነግራቸዋል፡፡ ብርሃን ክርስቶስን በመካዳቸው እንደሆነ ያስረዳቸዋል፡፡ ቢያምኑበትም በጨለማ (ባለማወቅ) የተዋጠው ልቡናቸው በብርሃን ክርስቶስ ብርሃን ዕውቀትን እንደሚያገኝ ይነግራቸዋል” ይላል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ብርሃን እኔ ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” የሚላቸው ብርሃን እርሱን እንዲያምኑበት ለማቻኰል ነው ማለት ነው፡፡

  በመሆኑም ቀጥሎ፡- “ብርሃን ሳለ ተመላለሱ (እኔ በመካከላችሁ ሳለሁ በእኔ እመኑ)፤ በጨለማ የሚመላለስ ሰው ወዴት እንዲሄድ አያውቅምና (እኔ ከሞትኩ በኋላ እኔ የምሠራውን ሥራ ሠርቶ በእኔ ማሳመን የሚቻለው የለምና)” ይላቸዋል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በራሳቸው አረዳድ በፍኖተ ጽድቅ የሚሄዱ ይመስላቸው ነበር፤ ነገር ግን በፍኖት ጽልመት የሚሄዱ ነበሩ፡፡ በብርሃን ክርስቶስ ከማመን ይልቅ ሰንበትን ማክበር፣ ይህን ብላ ይህን አትብላ፣ ይህን ንካ ይህን አትንካ ማለት የሚያጸድቃቸው ይመስላቸው ነበር /ቈላ.፪፡፲፮/፡፡ ይህ ድርጊታቸውም ከሚታደጋቸው የእግዚአብሔር ጽድቅ ይልቅ ምንም ረብሕ የሌለውና የማይታደጋቸው የራሳቸውን ጽድቅ እንዲያቆሙ አደረጋቸው /ሮሜ.፲፡፫/፡፡ ወደ ስሕተት ነዳቸው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን፡- “ውሉደ የብርሃን (የእኔ ልጆች) እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ (እኔ ሳለሁ በእኔ) እመኑ፡፡ አንድም ውሉደ ብርሃን ትሆኑ ዘንድ ብርሃን ዕድሜያችሁ ሳለ በእኔ እመኑ፤ ከሞት በኋላ ሃይማኖትና ምግባር ይዞ መዳን የሚቻለው የለምና” በማለት በፍቅር ይጋብዛቸዋል /ቁ.፴፮፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/ ካለማወቅ ወደ ማወቅ እንዲሸጋገሩ ይጠራቸዋል፡፡
  ይህንን ብሎም ምን ተሰውሯቸው ሄደ /ቁ.፴፯/። ከእናንተ መካከል “እነዚህ ሰዎች እንደ ከዚህ በፊቱ ይወግሩት ዘንድ ድንጋይ አላነሡም፤ አልሰደቡትምም፡፡ እንዲህ ከሆነ ታድያ ስለምን ተሰውሯቸው ሄደ?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ሊቁ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ቅድም በጠቀስነው ድርሳኑ፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልብ የታሰበውን የሚያውቅ ማእምረ ኅቡአት ነው /ዮሐ.፪፡፳፬/፡፡ ምንም እንኳን ሰዎቹ በገቢር አንዳች ነገር ባይሉትም በማዕምቀ ልቡናቸው ግን በቁጣ ነደው እንደ ነበር አውቋል፡፡ በመሆኑም ድንጋዩን እስኪያነሡ ድረስ አልጠበቃቸውም፤ ተሰውሯቸው ሄደ እንጂ፡፡ የተሰወራቸውም ድንጋዩን ፈርቶ አልነበረም፤ በኀልዮ ላይ የገቢር ኃጢአትን ጨምረው ራሳቸውን እንዳይጐዱ ስለፈለገ ነው እንጂ” በማለት ጥያቄውን ይመልስልናል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም፡- “የሚሻላቸውን እንዲመርጡ ጊዜ ይሰጣቸው ዘንድ ተሰወራቸው” በማለት ይጨምርልናል፡፡
 በመቀጠልም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የሰዎቹ ልበ ደንዳናነት እንዴት እንደነበረ ይነግረናል፡፡ “በፊታቸው ይህን ያህል ተአምራት ቢያደርግም አላመኑበትም” በማለት፡፡ ምንም እንኳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ መንገድ ሊመልሳቸው፣ ይቅርም ሊላቸው ቢፈልግም እነርሱ ግን ይባስ ብለው ይቈጡት ነበር፤ ይገድሉትም ዘንድ ይሹ ነበር፡፡ ለእነርሱ ጥቅም ብሎ ያደረጋቸውን ተአምራት በስውር አላደረጋቸውም፤ በዓይናቸው እያዩት አደረጋቸው እንጂ፡፡ እነርሱ ግን ያምኑበት ዘንድ አልፈቀዱም፡፡ ለምን? ያልን እንደሆነም ወንጌላዊው እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “ነቢዩ ኢሳይያስ ‘አቤቱ ትምህርታችን ማን ይቀበለናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ (ኃይሉ፣ ሥልጣኑ) ለማን ተገለጠ?’ ብሎ /ኢሳ.፶፫፡፩/ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ አላመኑበትም ዳግመኛም ኢሳይያስ ራሱ፡-በዓይነ ልቡናቸው እንዳያዩ፥ በልቡናቸውም እንዳያስተውሉ፥ ወደ እኔ እንዳይመለሱም፥ ይቅር እንዳልላቸው፥ ዓይነ ልቡናቸው ታውሯል፤ ልባቸውም ደንድኗል /ኢሳ.፮፡፱/ ብሏልና ስለዚህ ማመን ተሳናቸው። ነቢዩ ኢሳይያስ ይህንን የተናገረው የእግዚአብሔር ጌትነቱን ቢያውቅ ነው፡፡ ኢሳይያስ ይህን የእግዚአብሔር ጌትነት ሲያውቅ ከሰው ሹመት ሽልማት ሳይሻ ደፍሮ ተናገረ፡፡ አንድም እግዚአብሔር የሚያወርሰውን ክብር አውቋልና በመስቀል ይስቀሉኝ በመጋዝ ይተርትሩኝ ብሎ ሳይፈራና ሳያፍር ደፍሮ እንዲህ ብሎ ተናገረ” /ቁ.፴፰-፵፩፣ኢሳ.፮፡፩፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
  ከእናንተ መካከል፡- “ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ያየው የማንን ክብር ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም፡- “የእግዚአብሔር አብ ክብር ነዋ!” ብለን እንመልስለታለን፡፡ “እንዲህ ከሆነ ታድያ ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ወልድ /ዮሐ.፲፪፡፵፩/፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር /፪ኛቆሮ.፲፪፡፩-፱/ የሚናገሩት ስለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ካለም፡- “ነቢዩም ይሁን ሐዋርያቱ የሦስቱም አካላት ዕሩይነት ለመናገር ስለሚሹ ነው፡፡ የአብ የሆነ ሁሉ አብ ከመባል በቀር የወልድ እንደሆነ፣ የወልድ የሆነ ሁሉም ወልድ ከመባል በቀር የመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ (በሌላ አገላለጽ ዕሩያን እንደሆኑ) ለማሳየት እንዲህ አሉ ብለን እንመልስለታለን” ይለናል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡   
   ተወዳጆች ሆይ! እዚህ ጋር አንድን ነገር ልናስተውል እንደሚገባን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይመክረናል፡፡ እንዲህም ይለናል፡- “ልጆቼ! እነዚህ ሰዎች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያላመኑት አስቀድሞ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ አያምኑበትም ብሎ ስለተነበየ እንዳይመስላችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ነቢዩ አያምኑበትም ብሎ የተነበየው እንደማያምኑ አስቀድሞ በትንቢት አጉሊ መነጽር ስላየ ነውና፡፡”
  ከእናንተ መካከል አንዱ፡- “ግን እኮ እነዚህ ሰዎች እንደማያምኑበት እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ እንዲህ ከሆነ ታድያ (ላይመለሱ) አስቀድሞ ነቢያትን፣ ቀጥሎ አንድያ ልጁን፣ ቀጥሎም ቅዱሳን ሐዋርያትን የላከላቸው ስለምንድነው?” የሚል ጥያቄ ሊያነሣ ይችላል፡፡ አባታችን ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ጥያቄውን ይመልስልናል፤ እንዲህ ይለናል፡- “ምንም እንኳን እግዚአብሔር እንደማያምኑበት ይባስ ብለውም ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ በትልቁ ደግሞ አንዲያ ልጁን እንደሚገድሉት ቢያውቅም እነርሱን ከመጥራት እጁ አላጠረችም፡፡ ይኸውም በኃጢአታቸው ለመሞታቸው ምክንያት እንዳይኖራቸው ነው፡፡ የሚያምኑበት ቢሆኑ ኖሮስ ነቢዩም አያምኑበትም ብሎ ትንቢት ባልተናገረባቸው ነበር” በማለት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስም፡- “እንደውም ነቢዩ አስቀድሞ እንዲህ መናገሩ ለእነዚህ ሰዎች ታላቅ ጥቅም ነበረው፡፡ ምክንያቱም ሰዎቹ ወደዚህ ኃጢአት ከመግባታቸው በፊት (አልሰሙትም እንጂ) በእዝነ ልቡናቸው እንዲሰሙት ማነቃቃቱ ነበርና” ይለናል፡፡ 
  አሁንም ከዚህ ጋር በተያያዘ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተደጋግሞ የሚጠየቅ ጥያቄ እናንሣ፡፡ “ቃሉ ሲናገር፡ ‘(እግዚአብሔር) በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ’ ነው የሚለው፡፡ ታድያ በዓይነ ልቡናቸው እንዳያዩ እንዳያስተውሉም ያደረጋቸው እግዚአብሔር ከሆነ ስለምንድነው እነርሱ ተጠያቂዎች የሚሆኑ?” የሚል፡፡ አዎ! ቃሉን ከአፍአ ስናየው “እንዳያስተውሉ ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው” የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያላመኑት ማመን ስላልወደዱ እንጂ እግዚአብሔር እንዳያምኑ ስላደረጋቸው አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው አንዳች ርዳታን አልጠየቁትም፡፡ ዓይነ ልቡናቸውን እንዲያበራላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን አልፈለጉም፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ስላልረዳቸውም እውነትን ከማየት ተከልክለዋል፤ ከድኅነት መንገድም ወጥተዋል፡፡ “ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ” ማለት ትርጓሜው ይኼ ነው፡፡ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ በማለት አምልቶና አስፍቶ ያብራራልናል፡- “ልጆቼ! ይህን ትረዱ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ ይህ አነጋገር የመጻሕፍት ልማድ ነው፡፡ መጽሐፍ ‘ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው’ /ሮሜ.፩፡፳፰/ ሲል እግዚአብሔር የማይረባ አእምሮ እንዲኖራቸው አደረጋቸው ማለት አይደለም፡፡ የሰዎቹ ፍላጐት እንደዚያ ስለሆነ እግዚአብሔርም ፍቃዳቸውን አይቶ ለፍላጐታቸው እንዲገዙ፣ ለፍቃዳቸውም እንዲታዘዙ ጥበቃውን አነሣባቸው ማለት ነው እንጂ፡፡… የምንጠፋው እግዚአብሔር እንድንጠፋ ስለወደደ አይደለም፡፡ የምንጠፋው በራሳችን ፈቃድ ነው /ኢሳ.፶፱፡፪፣ ሆሴ.፬፡፮/፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ’ማ ‘የሟቹን ሞት አልፈቅድም’ የሚል ነው /ሕዝ.፲፰፡፴፪/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዳን ላልወደዱ የኢየሩሳሌም ሰዎች በከተማዋ አንጻር ያለቀሰላቸውም ይህን የመሰለ ነው /ማቴ.፳፫፡፴፯/፡፡”
  ወንጌላዊው እየተደነቀ ይቀጥላል፡፡ “ከሕዝቡ አለቆች ያመኑበት ብዙ ናቸው ነገር ግን ፈሪሳውያን ከምኵራብ አውጥተው እንዳይሰዷቸው ስለፈሩ እምነታቸውን አልገለጡትም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከሚያወርሳቸው ክብር ይልቅ ውዳሴ ከንቱን፣ ከክርስቶስ ይልቅ ቤልሆርን፣ ከመንግሥተ ሰማይ ይልቅ ምኵራብን፣ ከወንጌል ይልቅ ኦሪትን ወደዋልና” በማለት /ቁ.፵፪-፵፫፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአንድ ወቅት ላይ፡- “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” ብሏቸው ነበር /ዮሐ.፭፡፵፬/፡፡
  አሁን ወንጌላዊው መደነቁን ገታ ያደርግና ከላይ ወደጀመረልን የጌታችን ትምህርት ይመልሰናል፡፡ እንዲህም ይለናል፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጮኸ፤ መዳናቸውን ሽቶ ነበርና ግን ደግሞ ምንም ልብ ሳይሉት መጥፋታቸው አሳዝኖታልና ጮኸ፤ እንዲህም አለ፡-በእኔ የሚያምን ሰው በእኔ ብቻ ያመነ አይደለም፤ በላከኝ በአባቴም አመነ እንጂ” /ቁ.፵፬/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ሲተረጕመው፡- “የጌታችን ንግግር እንዲህ ማለቱ ነበር፤” ይለናል፡- “አይሁድ ሆይ! ስለምን በእኔ ማመንን ትፈራላችሁ? አላወቃችሁትም እንጂ አውቃችሁትስ ቢሆን በእኔ ማመን ማለት በባሕርይ አባቴ ማመን ነው፡፡ እኔን መካድ ማለትም የባሕርይ አባቴን መካድ ማለት ነው” /Homily LXIX/፡፡
 ተወዳጆች ሆይ! አስተውለን ከሆነ ጌታችን ሲናገር “በእኔ የሚያምን” እንጂ “በቃሌ የሚያምን” አላለም፡፡ ይኸውም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ “በእኔ የሚያምን” ማለቱ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ማስረዳት ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ እንዴት? ያልን እንደሆነም “በቃሌ የሚያምን” ማለትስ ክርስቲያን አስተማሪዎችም ቢሆኑ ሊሉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከመምህራን ወገን አንዱ ስንኳ፡- በእኔ የሚያምን ሰው በእኔ ብቻ ያመነ አይደለም፤ በላከኝ በኢየሱስ ክርስቶስም አመነ እንጂ” ያለ የለም፡፡ አንድ መምህር ሊል የሚችለው አስቀድመን እንደተናገርን፡- “በማስተምረው ትምህርት (በቃሌ) የሚያምን የትምህርቱ ባለቤት በሆነው በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ማመኑ ነው እንጂ ባርያው በምሆን በእኔ ማመኑ አይደለም” ነው፡፡
   እንዳውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ዕሩቅ ብእሲ እየተናገረ አለመሆኑን የበለጠ የምናውቀው ቀጥሎ በሚናገረው ቃል ነው፡፡ እርሱስ ምንድነው?እኔንም የሚያይ የላከኝ አባቴን ያያል” /ቁ.፵፭/። ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር በእዝነ ሥጋ የሚሰማ፣ በዓይነ ሥጋ የሚታይ፣ በእደ ሥጋም የሚዳሰስ ነው ማለት ነውን? በፍጹም! ታድያ ምን ማለቱ ነው? ጌታችን እኔን የሚያይ የላከኝ አባቴን ያያል” ሲል ከባሕርይ አባቱ ጋር ስላለው ዕሩይነት (በባሕርይ፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣንና በመሳሰለ አንድ መሆናቸውን) ሲናገር ነው!   
    ጌታችን ትምህርቱን ቀጥሏል፤ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ በመምህርነት ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ (ሰው ሆኛለሁ)” በማለት /ቁ.፵፮/፡፡ በዚህ ንግግሩም ቢሆን ጌታችን የባሕርይ አምላክነቱን የገለጸበት ነው፡፡ እንዴት? ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “ብርሃን የሚለው ቃል በመጻሕፍተ ብሉያትም ይሁን በሐዲሳት በብዛት ለእግዚአብሔር አብ ተጠቅሶ የምናገኘው ቃል ነው፡፡ ጌታችንም አሁን እንደሰማነው ይህን ቃል ተጠቅሞበታል፡፡ ብጹዕ የሚሆን ጳውሎስም ከዚሁ ተነሥቶ ‘መንጸባረቅ’ ብሎ ለክርስቶስ ሰጥቶ አስተምሯል /ዕብ.፩፡፫/፡፡ ይህም እንደተናገርን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ጋር ያለውን ዕሩይነት የሚያስረዳ ነው፡፡ ጌታ ራሱን ‘ብርሃን’ ብሎ መጥራቱም ‘የሰው ልጅ በክሕደት፣ ባለማወቅ፣ በአጠቃላይ በክፉ ነገር እንዳይኖር በእኔ አምኖ እንዲድን፣ ካለማወቅ ወደ ማወቅ እንዲሻገር ሰው ሆኜ በመምህርነት ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ’ ሲል ነው” ይላል፡፡
  አሁን ደግሞ ነገሩ እንዳይጸንባቸው “የእኔን ቃል ሰምቶ ባላመነ እኔ አልፈርድበትም፤ አድነው ዘንድ ነው እንጂ ልፈርድበት አልመጣሁምና” ይላቸዋል/ቁ.፵፯/፡፡ “ጌታ ሆይ! እንዳስተማርከን አብ በአንድ ሰው ስንኳ የማይፈርድ ከሆነ /ዮሐ.፭፡፳፫/፣ አንተም በዓለም ላይ ለመፍረድ ካልመጣህ፣ ታድያ ሰው ላይ የሚፈርደው ማን ነው?” “በዚህ ሰዓት የእኔ ፈቃድ የሰው ልጅ በሙሉ እንዲድን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ይህ ሰዓት የምሕረት (የጸጋ) ዘመን ነው፡፡ ትምህርቴን ባልተቀበለኝ ግን አሁን የምናገራት ቃል በኋለኛይቱ ቀን ምስክር ሆና ትፈርድበታለች” /ቁ.፵፰/፡፡ ከላይ እያየነው እንደመጣን አይሁድ “ይሞታል ይሰቀላል የምትለው መሲሕ ፈጽመን አናውቀውም (አንተን አናውቅህም)፤ የባሕርይ አምላክ አይደለህም” ብለውታል /ቁ.፴፬/፡፡ ጌታችንም ወደዚህ ስሕተት የከተታቸው ምን እንደሆነ በመግለጽ በተለያየ መንገድ የባሕርይ አምላክነቱን ነግሯቸዋል፡፡ ይህን መቀበልም ሆነ አለመቀበል ደግሞ የእነርሱ ፈንታ ነው፡፡ ካልተቀበሉት ግን በእኔ የሚያምን ሰው በእኔ ብቻ ያመነ አይደለም፤ በላከኝ በአባቴም አመነ እንጂ” የሚለው ቃል ራሱ ምስክር ሆኖ በመጨረሻይቱ ቀን እንደሚፈርድባቸው ያስታውሳቸዋል፡፡
  “ምክንያቱም” ይላል ጌታ ሲቀጥል፤ “እኔ ከራሴ ብቻ አንቅቼ የማስተምር አይደለሁምና፤ የላከኝ አባቴ በእኔ ህልው ሆኖ የምናገረውን የማስተምረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ እንጂ፡፡ የአባቴ ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። የማስተምረውንም ከአብ በህልውና ያገኘሁትን አስተምራለሁ” ይላል /ቁ.፵፱-/። “በዚህ ንግግሩ” ይላል የመናፍቃን መዶሻ የተባለው ቅዱስ ቄርሎስ፤ “በዚህ ንግግሩ በሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለ እርሱ የተነገረውን ቃል ለአይሁድ ሕዝብ ያስታውሳቸዋል፤ በጥበብ ይገስጻቸዋል፤ ሕግ አፍራሽነታቸውንም ይነግራቸዋል፡፡ እናከብረዋለን ለሚሉት ሕገ እግዚአብሔር ምንም ግድ የሌላቸው መሆናቸውን ያስታውሳቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለ ክርስቶስ የተናገረው ቃል በሁሉም ዘንድ የታወቀ ቢሆንም እስኪ ሐሳቡን በትክክል ትረዱት ዘንድ ቃሉን ላስታውሳችሁ፡- ‘ከወንድሞቻቸው መካከል እንዳንተ ያለ (ሕግ ሰጪ፣ መካከለኛ የሚሆን) ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አኖራለሁ፤ እንዳዘዝሁትም ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረው ሁሉ ያን ነቢይ የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀለዋለሁ’ ይላል /ዘዳ.፲፰፡፲፰/፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ መልኩ እግዚአብሔር አብ ስንኳ የነገራቸውን ቃል ባለማክበራቸው አብን እየተቃወሙት እንደሆነ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ‘ትእዛዝ ሰጠኝ’ እያለ ከጥንት አንሥቶ ትንቢት የተነገረለት ሱባኤ የተቈጠረለት መሲሑ እርሱ ራሱ እንደሆነ እየነገራቸው ነው ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ነገሩን ለመረዳት ልበ ዝንጉዓን ቢሆኑም ቃሉን እንዲያስታውሱት ያደርጋቸዋል፡፡ ‘ምድር ሆይ ስሚ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ’ እንዲል /ኤር.፮፡፲፱/፣ ይህን ሕይወት የሆነው የእግዚአብሔር አብ መለኮታዊ ትእዛዝ በመተላለፋቸውም ቃሉ ራሱ በመጨረሻይቱ ቀን ምስክር ሆኖ እንደሚፈርድባቸው ይነግራቸዋል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው የአይሁድ ወቀሳ ሁለት ወገን ነው ማለት ነው፡፡ አንደኛው፡- ሕጉን ራሱ ባለማክበራቸው ሕግ ሰጪው አብን አለማክበራቸው እንደሆነ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትንቢት የተነገረለት ሱባኤም የተቈጠረለት መሲሑ እርሱ መሆኑን ለነገራቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያስተምራቸው ቃል የዝሆን ጀሮ መስጠታቸው፡፡” /St. Cyril of Alexandria, Commentary on John, Book 9/፡፡      
  ከእናንተ መካከል “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና የሚናገረውም የሚያስተምረውም ከአባቱ የተቀበለው ከሆነ ከመቀበሉ በፊት የሚናገረውንና የሚያስተምረውን አያውቅም ማለት ነውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ብሎ ይመልስለታል፡- “አይደለም፡፡ ይህ የጌታችን ንግግር ለአቅርቦት የተናገረው የትሕትና ንግግር ነው፡፡ ጌታችን ሲናገር በሰማዕያኑ መጠን ስለሆነ ነው እንጂ ከእርሱ የባሕርይ አምላክነት የማይሄድ አነጋገር እንደሆነስ ያውቃል” ይላል /Homily LXIX/፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አውግስጢኖስ የተባለ ሊቅ፡- “እግዚአብሔር ወልድ የአብ ቃሉና ጥበቡ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብም የአካላዊ ቃል ልቡናው ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የማያውቀው የእግዚአብሔር አብ ልቡና ደግሞ የለም /ማቴ.፲፩፡፳፯/፡፡ ስለዚህ የላከኝ አባቴ እርሱ የምናገረውን የማስተምረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ ሲል በአብ ልቡና የታሰበው በእኔ ቃልነት ያለው ነው ሲል ነው” ይላል፡፡ ሊቁ ሲቀጥል፡- “የእግዚአብሔር (የሥላሴ) ሐሳብ ሁሉ በአብ ልቡና፣ በወልድ ቃልነት፣ በመንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት ውስጥ እንዳለ እናምናለን” ይላል /St Augustine; On the Gospel of St John, tractate 54:7/፡፡   
  ስለዚህ የወልድ ከአብ መቀበል ልክ በእኛ ሥርዓት የጌታና የሎሌ ዓይነት አድርገን ልናየው የሚገባ አይደለም ማለት ነው፡፡
…ተመስጦ…

 ቸር ወዳጅ ሆይ! ምንም እንኳን በራሳችን ፈቃድ የተዳደፍን እኛን ለማንሣት ብለህ የባርያህን መልክ ይዘህ ብትመጣም ለዘመንህ ኅልፈት ለመንግሥትህም ሽረት የሌለብህ ዘለዓለማዊ ንጉሥ እንደሆንህ እናምናለን፡፡ በብርሃንህ ወደ ብርሃንህ ትመራን ዘንድ፣ በቅዱስ ሥጋህ በክቡር ደምህም ረጭተህ ውሉደ ብርሃን ታደርገን ዘንድ እንደመጣህ እናምናለን፡፡ አባት ሆይ! ታድያ ይህ ሳይገባን የሠጠኸን ቅድስና አሁን በተለያየ ምክንያት አሳድፈነዋልና በቸርነትህ ወልውለን፡፡ ተሰነካክለን ወደ ጨለማ ወድቀናልና አትተወን፡፡ ከአንተ የምናገኘውን ክብር፣ ከቅዱሳን መላእክትህም የምናገኘውን ሰማያዊ ውዳሴ ረስተን አክሊል ሽልማት ለሌለው ለዚህ ዓለም ከንቱ ውዳሴ እየባከንን ነውና መልሰን፡፡ እንደ ፈሪሳዊ ጥቅስ እየጠቀስን ለስሕተታችን ሽፋን እንዳንሰጥም እርዳን፡፡ ያሳየኸን ቸርነት፣ ያስለመድከን የዋኅነት፣ ያስተማርከን ቃልህ በመጨረሻይቱ ቀን መፈራረጃ እንዳይሆንብንም ጠብቀን፡፡ አሜን! 

No comments:

Post a Comment