Pages

Wednesday, August 14, 2013

የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡

፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያትገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ወአግኃሦ ለሱራፊ ዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡
  ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰው ኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡
 ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪም ያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡ ዕንቆ ጳዝዮን የተባለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፡- “እስመ ቀዳሚኒ ሔዋን ኮነት ድንግል ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያምሂ ድንግል አብሠራ ገብርኤል ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሀ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኵሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም - ቀድሞም ሔዋን ድንግል ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ፤ ድንግል ማርያም ግን ገብርኤል አበሠራት፡፡ ነገር ግን ሔዋንን አሳታት፤ የሞት ምክንያት የሚኾን ቃየልን ወለደች፤ ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ኹሉን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች፡፡ የሔዋንን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደኾነ አስረዳ፡፡ በዚያም አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ፡፡ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን ዕፀ መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደኾነ ገለጠ፡፡ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች ኹሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት  ገነት ገባ” ብሏል /ሃይ.አበ.፷፯፡፫-፭/፡፡
  ከባሕርያችን መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያጠፋልንን ጌታን ዘር ምክንያት ሳይኾናት ወለደችው፡፡ ስለዚህ ነገርሰውን የምትወድ ሰው የሚወድህ አቤቱ ክብር ላንተ ይገባል” እያልን እናመስግነው፡፡ኄር ዘበህላዌሁ ዘልማዱ ኂሩት - በባሕርይው ቸር የኾነ፤ ቸርነትን ማድረግም ልማዱ የኾነ” እያልን እናመስግነው፡፡ ኄር ዘበህላዌሁ ዘልማዱ ኂሩት ከሚባል ልጅሽ ጸንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፫. ዘር ምክንያት ሳይኾናት አምላክንወለደች ድንግል፣ የማኅፀንዋ ሥራ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለድንግል ለማኅፀኗ ሥራ አንክሮ ይገባል፡፡ ለዮሴፍ የነገረው መልአክ ሳይለወጥ ሰው የኾነ አካላዊ ቃል ከርሷ የሚወለድ በግብረ መንፈስ ቅደስ እንደኾነ መስክሯልና /ማቴ.፩፡፳/፡፡ ማርያም የዚህ ደስታ ዕፅፍ ድርብሚኾን ጌታን ወለደችው፡፡ ሴቶች ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፤ ይልቁንም ወንድ ትወልዳላችሁ ሲሏቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ እመቤታችን ግን ከዚሁ ኹሉ ያለፈ አምላክን ወልዷለችና ደስታዋ ዕፅፍ ድርብ ኾነላት፡፡ መልአኩ፡- “ልጅ ትወልጃለሽስሙም አማኑኤል ይባላል” አላት፡፡ማኑኤልም ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከኛ ጋራ አንድ ባሕርይ ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ወገኖቹን ከኃጢአታቸው ፍዳሚያድናቸው መድኃኒት ይባላል አላት /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ በመኾኑም በክሂሎቱ (በከሃሊነቱ) ያድነን ዘንድ፣ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ (እስከ ዕለተ ምፅአት ድረስ ክብር ይግባውና) ሰው የኾነ እርሱ አምላክ እንደኾነ በተረዳ ነገር አወቅነው፡፡ አምላክ ብቻ ቢኾን ባልታመመ ነበርና፤ ሰውም ብቻ ቢኾን ባላደነን ነበርና፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ከዚህ ጋር አያይዞ ፡- “ፍቁራን ሆይ! ምንም እንኳን ለዚህ ክብር የተገባን ኾነን ባንገኝም አባታችን በከኀሊነቱ እንዲሁ ከኀጢአታችን አድኖናልና ይህን ክብር፣ ይህን ጸጋ በፍጹም ልናክፋፋው (ልናቆሽሸው) አይገባንም፡፡ ልጅነት እንዲሁ ሳይሰጠን ለምረረ ገሃነም የተገባን የቁጣ ልጆች ከነበርን፤ ይህ ከኅሊናት በላይ የኾነ ጸጋ ከተቀበልን በኋላማ ፍዳችን እንደምን የበዛ አይኾን? ልጆቼ! ይህን የምለው እንዲሁ ለመናገር ያህል አይደለም፡፡ ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከተወለዱ በኋላ ብዙ ክርስቲያኖች በኀጢአት፣ በስንፍና፣ ለምግባርና ለትሩፋት ሳይሽቀዳደሙ ታክተው ስለምመለከት ነው እንጂ” ሲል ይመክረናል /St. John Chrysostom, Homily on the Gospel of St. Matthew, Homily IV/፡፡

  ወዮ! ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? ቃልን ወሰነችው፡፡ ለልደቱም ዘርዕ ምክንያት አልኾነውም፡፡ በመወለዱም ማኅተመ ድንግልናዋን አልለወጠውም፡፡ ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ድካም ሳይሰማውተወለደ እርሱ ፭ ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸምም ከድንግል ሕማም ሴቶች የሚሰማቸውን ሕማም ሳይሰማት እርሱን ሕፃናትን የሚሰማቸው ሕማም ሳይሰማው ተወለደ እንጂ፡፡
 ሰብአ ሰገል ሰገዱለት፡፡
Ø አምላክ ነውና አምላክ እንደኾነ ለማጠየቅ ዕጣን አመጡለት፡፡ ንጉሥ ነውና ንጉሥ እንደ ኾነ ለማጠየቅ ወርቅ አመጡለት፡፡ ማኀየዊ የሚኾን የሞቱ ምሳሌ ከርቤንም አመጡለት፡፡
Ø አንድምይኸን ወርቅ እንገብርላቸውነበሩ ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው፤ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ “ይኽን ዕጣን እናጥናቸው የነበሩ ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው፤ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ብትኾን በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀምሳለህ ሲሉ ከርቤ አመጡለት፡፡
Ø አንድም ወርቅ ጽሩይ ነውናጽሩየ ባሕርይ ነህ” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነውና “አንተም ምዑዘ ባሕርይ ነህ” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ ዳግመኛም “ከርቤተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለያየውን አንድ ደርጋል፡፡ አንተም ከማኀበረ መላእክትተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ” ሲሉ ከርቤ አመጡለት፡፡
Ø አንድም ወርቅ ጽሩይ ነውናባንተ ያመኑ ምዕመናን ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነውናባንተመኑ ምእመናንም ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ ዳግመኛም በዕለተ ሞቱ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ የኾነ አንድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፬. ከአዳም ጎን አንድ ዐፅም መንሣቱ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? “በእምነት ዓይን ከማየት በቀር ይህ ከኅሊናት በላይ የኾነውን ድንቅ ነገር በቋንቋ መናገር አይቻለንም” /St. John Chrysostom, Homily 15 on Genesis/፡፡ ከእርሱ (ከአዳም) ሔዋንን ፈጠረ፡፡ ፍጥረትንም ኹሉ ከአዳምና ከሔዋን ፈጠረ፡፡ እንዲህም አድርጎ የአብ አካላዊ ቃል ለኵነተ ሥጋ (ለሕማም ለሞት) ተሰጠ፡፡ ከልዩ ድንግልም ሰው ኾነና አማኑኤልም ተባለ፡፡ “ኦ ለዝንቱ መንክር ልዑል ላዕለ ኵሉ ሕሊናት ብእሲት ምድራዊት ወለደቶ ለእግዚአብሔር ቃል ዘኮነ ሰብአ… - ከኅሊናት ኹሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ሰው የኾነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፡፡ ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ፡፡ ከእርሷም እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ” /ሃይ.አበ.፵፯፡፪/፡፡
 ስለዚህ ነገር ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ በቅዱሳን ዘንድ ቸር ናትና እርሷን እንለምን፡፡ ለሊቃነ ጳጳሳት አስበ ጵጵስናችን (የጵጵስናችን ዋጋ) ይሰጠናል ብለው ደጅ የሚጠኑትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ነቢያት አስበ ትንቢታችንን ይሰጠናል ብለውይወርዳል፤ ይወለዳል” ብለው ትንቢት የተናገሩለትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሐዋርያት አስበ ሰብከታችንን ይሰጠናል ብለውውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ - መምህራነ ሐዲስ ሐዋርያት ለምእመናነ ሐዲስ ወረደ ተወለደ ብለው አስተማሩ” እንዲል /መዝ.፲፰፡፬/ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ዙረው ወረደ ተወለደ ብለው ያስተማሩለትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሰማዕታ ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከዓላውያን መኳንንት ገብተው አስበ ትዕግሥታችንን ይሰጠናል ብለው መከራውን ታግሠው የተቀበሉለትን፣ ምዕመናን አስበ ተጋድሏቸውን ይሰጠናል ብለው ከፍትወታት ከእኩያት ኃጣውእ የተዋጉለት ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳቸዋችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሰው ኹኖ አድኖናልና በጥበቡ እየሰፈረ የሚሰጠው፣ ዳግመኛም የጸጋው ብዛት የማይታወቅ የቸርቱን ብዛት መርምረን እንወቅ፡፡ ሰው ኹኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፭. ተናግሮ የማያስቀር፣ ምሎ የማይከዳ እግዚአብሔር፡-ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህ (ክርስቶስን) በዙፋንህ አስቀምጥልሃለሁ ብሎ ለዳዊት በእውነት ማለለት /መዝ.፻፴፩፡፲፩/፡፡ ዳዊትም ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ እንዲወለድ ባመነ ጊዜ  የአካላዊ ቃል ማደርያውን መርምሮ ያውቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ቀኖናም ገባ፡፡ ከዚህም በኋላ “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም - በኤፍራታ ተወልዶ፤ በጎል ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያቅስ ሰማነው” አለ /መዝ.፻፴፩፡፮/፡፡ ይህቺውም እኛን ስለማዳን ይወለድባት ዘንድ የመረጣት ቤተ ልሔም፣ ቤተ ኅብስት የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ከሰማይ የወረደው ኅብስት እርሱ ነውና /ዮሐ.፮፡፶፩/፡፡
 ከነቢያት አንዱ የሚኾን ሚክያስም ዳግመኛ እንዲህ አላት፡- “አንቺም የኤፍራታ ዕፃ የምትኾኝ ቤተ ኅብስት ቤተ ልሔም እመቤታችን ሆይ! በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት ብትበልጭ እንጂ አታንሺም፡፡ እሥራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ ንጉሥ ባንቺ ይወለዳልና እንዲህ እንደኾንሽ አትቀሪም፡፡ ንጉሥ ይወለድብሻል፤ ቅዳሴ መላእክት ይሰማብሻል፤ የብርሃን ድንኳን ይተከልብሻል፤ መቶው ነገደ መላእክት ደጅ ይጠኑብሻል፡፡ አሕዛብ ይገብሩብሻል” ብሏታል /ሚክ.፭፡፪/፡፡ ጀሮም የተባለ ቅዱስ አባት ይህን አንቀጽ ሲተረጕም፡- “ከሰማይ የወረደ ኅብስት /ዮሐ.፮፡፶፩/ የተወለደብሽ ቤተ ኅብስት ሆይ! ሰላምታ ይገባሻል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደብሽ ምድረ ፍሬ፣ ምድረ ምውላድ (ኤፍራታ) ሆይ! ሰላምታ ይገባሻል፡፡ በዘመነ ብሉይ ሚክያስ ነቢይ ስለ አንቺ ሲናገር እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበርና፡- ‘ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሕቲ እም ነገሥተ ይሁዳ -  አንቺም የኤፍራታ ዕፃ የምትኾኝ ቤተ ልሔም ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም /ማቴ.፪፡፮/፡፡ ኢይወጽእ ምስፍና ወምልክና እምአባሉ ለይሁዳ - በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም እንዲል /ዘፍ.፵፱፡፲/ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ከዲያብሎስ አስቀድሞ ቀዳማዊ የኾነ እሥራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣል (ይወለዳልና)” ብሏል /St. Jerome, Letter 108:10/፡፡
 ወዮ! ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ ክብር ይግባውና በአንድ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው የክርስቶስን ነገር የተናገሩ ሚክያስና ዳዊት የተናገሩት ነገር ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ሚክያስና ዳዊት ለተናገሩት ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋር ክብር ከሚገባው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፮. ለእሥራኤል የነገሠ ዳዊት ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፡፡ ዳዊት ታመመ፤ ቢታመም ዘመዶቹ ቀሳ አወጡት፡፡ ኢሎፍላውያን ይህን ሰምተው ቤተ ልሔምን አልፈው ሰፈሩ፡፡ ዳዊትም “ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ስለምን ከቤተ ልሔም የተቀዳ ውሀ ይጠጣ ዘንድ ወደደ?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ታምሞ ስለነበር የቤተ ልሔም ውሀ ደግሞ ማየ ፈውስ ናትና /፪ኛ ነገ.፳፫፡፲፭-፲፯፣ አንድምታውን ይመልከቱ/፡፡
 ስለኾነም የጭፍራ አለቆች አዲኖን ኢያቡስቴ ኤልያናም አፋ አፋቸውን ታጥቀው፣ ዘገራቸውን ነጥቀው፣ ራዋታቸውን ጭነውየማን ጌታ በውሃ ጥም ይሞታል?” ብለው ፈጥነው ተነሡ፡፡ በኢሎፍላውያን ከተማ ተዋጉለት፡፡ ይጠጣ ዘንድ የወደደውንም ውሀ አመጡለት፡፡ ብጹዕ ዳዊት ግን ስለ ርሱ ሰውታቸውን ለሞት አሳልፈው እንደ ሰጡ በየ ጊዜ የራዋቱን ውሀ አፈሰሰው፡፡ በማለፊያው ቀድተው የሰጡትን አልጠጣም፡፡የናንተን ደም መጠጣት ነው” ብሎ አፍሶታል፡፡ አንድም ውሀውን መሥዋዕት አድርጐ ለእግዚአብሔር አፈሰሰው፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ዳዊት ንጉሥ ሲኾን መሥዋዕት የሚኾን ላም በግ አጥቶ ነውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ በፍጹም! እግዚአብሔር የወደዱትን ቢተዉለት ስለሚወድ ነው እንጂ /መዝ.፶፬፡፮፣ ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ ፻፵፭/፡፡
  ዳዊት የወደደውን ውሀ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ስላፈሰሰውም ጽድቅ ኾኖ ተነገረለት፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ስለ ዳዊት ብለው ጣዕመ ዓለምን እንደናቁ፤ ዳዊትም ስለነርሱ አንድም ስለ እግዚአብሔር ብሎ ጣዕመ ማይን እንደናቀ ሰማዕታት ጣዕመ ዓለምን ናቁ፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ዳዊትን ብለው ደማቸውን እናፍስ እንዳሉ፤ ዳዊትም ውሀውን እንዳፈሰሰ፤ ሰማዕታት ስለ እግዚአብሔር ብለው ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ስለ ዳዊት ብለው መራራ ሞትን እንታገሥ እንዳሉ፡ ዳዊትም ጽምዓ ማይን ልታገሥ እንዳለ ሰማዕታት መራራ ሞትን ታገሡ፡፡ ቸር አባት ሆይ! እኛስ እንደ ሰማዕታት ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከዓላውያን መኳንንት ገብተን መከራውን ታግሠን ተቀብለን፤ እንደ ምዕመናንም ከፍትወታት ከእኩያት ኃጣውእ ተዋግተን ድል ነሥተን መዳን አይቻለንምና እንደ ቸርነትህ ብዛት ይቅር በለን፡፡ ቸርና ይቅር ባይ ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣ ለምኚልን፡፡
፯. ከሦስቱ አካል አንዱ አካል በእግረ አጋንንት መረገጣችንን መጠቅጠቃችንን አየና ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ
ሰው ኹኖ በድንግል ማኅፀን አደረ /ኢሳ.፶፱፡፮/፡፡ ባሕየ መላእክትን ባሕይ አላደረገም፤ ባሕርየ ሰብእን ባሕርይ አድርጎ በድንግል ማኅፀን አደረ እንጂ /ዕብ.፪፡፲፮/፡፡ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀርም እንደኛ ሰውነ /ዕብ.፬፡፲፬/፡፡ ሚክያስና ዳዊት በቤተ ልሔም ይወለዳል ብለው እንደ ተናገሩ በቤተ ልሔም ተወለደ፡፡ “ይሙት ቤዛነ በትስብእቱ ወየሀበነ መድኃኒተ ዘከመ መለኮቱ” እንዲልም እንደ አምላክነቱ አዳነን እንደ ሰውነቱም ቤዛ ኾነን /ኤፌ.፩፡፯/፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤  በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ኾናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ኾናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል” /ኤፌ.፪፡፲፩-፲፫/ እንዲል ወገኖቹ ያልነበርን እኛን ወገኖቹ አደረገን፡፡ ወገኖቹ ካደረገን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣ ለምኚልን፡፡
 ይኸን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ወደ ሰማይ ታርጋለች፡፡ እርሱም ተባርኮ እጅ ነሥቶ ይቀራል፡፡

አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስጨረሰን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!

10 comments:

  1. qale heiwet yasemalen

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሒወትን ያሠማልን በእውነት

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር ይስጥልን✝️

    ReplyDelete
  6. ቃለ ህይወት ያሠማልን

    ReplyDelete
  7. አሜን እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  8. ቃለ ሂዎት ያሰማልን

    ReplyDelete