Pages

Thursday, August 15, 2013

የዓርብ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ይህ ዕለት ለምስጋና አምስተኛ ለፍጥረት ስድስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ደናግልን አስከትላ መጥታለች፡፡


. ከሴቶች ተለይተሸ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ሌለብሽ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ቤዴ የተባለ ተርጓሜ መጻሕፍት ይህን አንቀጽ ሲተረጉመው፡- “የመጀመርያው የሰው ልጆች ስሕተት ከዲያብሎስ በእባብ አማካኝነት ወደ ሴት ተላከ፡፡ ሴቲቱም በትዕቢት መንፈስ ወደቀች፡፡ ዲያብሎስ በእባብ ገላ ተሰውሮ መጣና የመጀመርያዎቹ ወላጆቻችንን አታለላቸው፡፡ ኢመዋቲው ጸጋቸውን ገፈፈው፡፡ ስለኾነም ሞት በሴት ምክንያት ገብቷልና መድኃኒትም በሴት ምክንያት ይገባ ዘንድ ይገባው ነበር፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን ዲያብሎስ በእባብ ገላ ተሰውሮ አታለላት፡፡ ለሰውም ኹሉ የሞትን ጣዕም አቀመሰችው፡፡ ሌላይቱ ሔዋን ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ በተላከ መልአክ የዓለም መድኃኒት የኾነው ክርስቶስን አስገኘች” በማለት እመቤታችን ከሴቶች ኹሉ የመለየቷን ምሥጢር በጥልቀት አስተምሯል፡፡
 የማኅፀንሽም ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍሰ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ የሚላን ሊቀ ጳጳስ የነበረውና አምብሮስ የተባለው ሊቅ ይህን አንቀጽ ሲተረጕም፡- “እመቤታችን አመነች እንጂ አልተጠራጠረችም፤ በመኾኑም የእምነቷን ፍሬ አገኘች፡፡ “ወብጽዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃለ ዘነገሩኪ እም ኀበ እግዚአብሔር - ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገሩሽን ነገር እንዲደረግ የምታምኚ አንቺ ንዕድ ክብርት ነሽ” እንዲል /ሉቃ.፩፡፵፭/፡፡ እናንተ ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገርዋችሁን ነገር እንዲደረግ የምታምኑም ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ የሚያምኑ ነፍሳት አካላዊ ቃልን ይፀንሱታል፤ በግብራቸውም ይወልዱታል (ይገልጡታል)፡፡ እንግዲያውስ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርጉት ዘንድ እመቤታችንን ምሰልዋት፡፡ በፈጣሪያችሁ በመድኃኒታችሁ አምናችሁ ደስ ይላችሁ ዘንድ የእመቤታችንን ልቡና ገንዘብ አድርጉ /ሉቃ.፩፡፵፮-፵፯/፡፡ ምንም እንኳን ጌታችንን በሰውነቱ የምትወልደው (የወለደችው) እመቤታችን ብቻ ብትኾንም በእምነት በኵል ግን የኹሉም አማንያን ፍሬ ነውና” በማለት ይመክረናል፡፡
 አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ! የጽድቅ ፀሐይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካንቺ ተወልዶም /ሚል.፬፡፪/ በክንፈ ረድኤቱ (በሥልጣኑ) አቀረበን፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ፈጥሮናልና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡- “በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ ወጣን፡፡ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ውሉደ እግዚአብሔር ተባልን፡፡ ከምንም በላይ ግን ከኀጢአት ቀንበር ተላቅቀን በሐዲስ ተፈጥሮ ተፈጠርን፡፡ ሥርየተ ኀጢአትን ሰጠን፡፡ ከርኩሰት ኹሉ አነጻን፡፡ ከጸጋው የተነሣ ደቂቀ አዳም የነበርን መላእክት አደረገን፡፡ መላእክቱም ለእኛ በተደረገው ነገር ሐሴት አደረጉ፡፡ ወዮ! ገና ሰዎች ሳለን መላእክት መኾናችን እንደምን ይረቃል እንደምን ይደንቃል? ይህ ኹሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው” /Fr. Tadros Malaty, On the Book of Isaiah 40:31/፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ከፈጠረን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. አምላክን የወልድሽ እመቤታችን ሆይ! ፀሐይ ዘኢየዐርብ (የማይጠልቅ ፀሐይ) የተባለው የብርሃን ክርስቶስ እናቱ ነሽና በአፍኣ በውሰጥ በሥጋ በነፍስ አንቺን ብቻሽን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለንም፡፡ ልዑላን ከሚባሉ መላእክት አንቺ ትበልጫለሽ፤ ትሑታን ከሚባሉ ከደቂቀ አዳምም አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከኀሊናት ኹሉ በላይ ነሽ (ኅሊና የአንቺን ክብር ተናግሮ መጨረስ አይቻለውም)፡፡ ክብርሽን ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው? አንቺንስ የሚመስል ማነው? ሊቁ አባ ሕርያቆስም፡- “ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩ ጥልቅነት ይዋኝ ዘንድ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሠወሪያው ማዕበልም ያማታዋል” ይላል /ቅዳ.ማር.ቁ.፹፬/፡፡ መላእክት ያከብሩሻል፤ ያገኑሻልም፡፡ ሱራፌልም ያመሰግኑሻል፡፡ በኪሩቤል በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱ ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ አድሯልና፡፡ ክብር የክብር ክብር ያለው እርሱ፤ ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እርሱ የእኛን ሞት ነሥቶ የእርሱን ሕይወት ለኛ ሰጥቶ ካባቱ ጋራ አስታረቀን፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በ “በእንተ ልደት” ድርሳኑ ላይ፡- “ስለዚህ ሥጋዬን ተዋሐደ! ወንጌልን ሲያስተምር እሰማው ዘንድ ሥጋዬን በተዋሕዶ ገንዘቡ አደረገው! ሥጋዬን ወስዶም መንፈሱን ሰጠኝ፡፡ ሰጠሁ፤ ተቀበልኩም፡፡ የእኔን ወስዶ የራሱን ስለ ሰጠኝም ሕይወትን ገንዘብ አደረግሁ፡፡ እኔን ለመቀደስ ሥጋዬን ተዋሐደ የሚያድነኝ መንፈስ ቅዱስንም ሰጠኝ” ብሏል፡፡ ክብር የክብር ክብር ካለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፫. ድንግል ሆይ! የደናግል ኹሉ መመኪያቸው አንቺ ነሽ፡፡ ከእናንተ መካከል “መመኪያነቷ እንዴት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡-
   ፩ኛ) ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “ወበከመ አውፅአ ብእሲ ብእሲተ ዘእንበለ ብእሲት ከማሁ አውፅአት ብእሲት ብእሴ ዘእንበለ ብእሲ ወሀሎ ዕዳ ላዕለ ትዝምደ አንስት፤ ወበእንተዝ ኮነት ፈዳዪተ ዕዳሃ ለሔዋን - ለወንዶች የሚከፈል ዕዳ በሴቶች ላይ ነበረ፤ ያለ እናት ሔዋን ተገኝታ ነበርና፡፡ ስለዚህም የሔዋንን ብድራት ለአዳም ትከፍለው ዘንድ ድንግል ያለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) ክርስቶስን ወለደችው፡፡ አዳም ያለ እናት ሔዋንን ስላስገኘ እንዳይመካ ድንግል ያለ አባት ክርስቶስን ወለደችው፡፡ ድንቅ በሚኾን አንድነት ይህ አንድ የፍጥረት እኩልነት ይታወቅ ዘንድ” /ሃይ.አበ.፷፮፡፳፱/፤
  ፪ኛ) ቀድሞ ወንዶች ሴቶችን በእናንተ ምክንያት ከገነት ወጣን እያሉ ርስት አያካፍሏቸውም ነበር፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ብእሲ ወብእሲት አሐደ እሙንቱ በክርስቶስ - ወንድም ሴትም የለም ኹላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ብሎ እስኪያስተምር ድረስ /ገላ.፫፡፳፰/ በሔዋን ምክንያት ከገነት ብትወጡ በእመቤታችን ምክንያት ገነት መንግሥተ ሰማያት ገብታችሁ የለምን? ብለው የሚመኩ ኹነዋልና፤
  ፫ኛ) ደግሞ ለደናግላን አስበ ድንግልናቸውን (የድንግልናቸውን ዋጋ) ስለምታሰጣቸው ሊቁ “ምክሆን ለደናግል” ብሏታል፡፡

  ቅድመ ዓለም የነበረ እርሱ ሰው ኹኗልና (ካንቺ ተወልዷልና) የእኛን ሥጋ ነሥቶ የርሱን ሕይወት ሰጥቶ ከርሱ ጋራ አስተካከለን፡፡ በቸርነቱ ብዛት እንድንመስለው አደረገን /ፊል.፫፡፲-፲፩/፡፡ ከብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ክብር የክብር ክብር ካላቸው ከብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ንጉሥ በከተማው እንዲኖር ዘጠኝ ወር ካምስት ቀን ማኅፀንሽን ዓለም አንድርጎ ኖሮብሽልና አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ! ልዑል እግዚአብሔር የከተመብሽ ረቂቅ ከተማ ነሽ፡፡ በኪሩቤል በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱን በማኽል እጅሽ ይዘሽዋልና ልዑል እግዚአብሔር የከተመብሽ ረቂቅ ከተማ ነሽ፡፡ በቸርነቱ ብዛት ፍጥረቱን ኹሉ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግበው እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ፡፡ አንድምሰውን (ለመንፈሳውያን) ኹ ሥጋውን ደሙን ሰጥቶ የሚመግበው እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ፡፡ ይኸውም ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ነው፡፡ እንሰግድለት እናመስግነውም ዘንድ በሐዲስ ተፈጥሮ በጥንተ ተፈጥሮ ፈጥሮናልና ለዘለዓለሙ ይጠብቀናል /ዮሐ.፮፡፴፯/፡፡ ሰጊድ (አምልኮ) ከሚገባው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፬. ድንግል ማርያም ዕፍረተ ምዑዝ (መዓዛው የጣፈጠ) የተባለ ጌታችንን የወለደች ሙዳየ ዕፍረት (የሽቱ መኖርያ) /፩ኛ ሳሙ.፲፡፩ አንድምታው/፤ ዳግመኛም የማየ ሕይወት (የሕይወት ውኃ የክርስቶስ) ምንጭ ናት /መኃ. ፬፡፲፪ አንድምታው/፡፡ የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ኹሉ አድኗልና፡፡ ከእኛ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አጠፋልን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ኹሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና” እንዲል /ቈላ.፩፡፲፱-፳/ በመካከል ኾኖ በመስቀሉ አስታረቀን፡፡ ልዩ በኾነ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ልዩ በኾነ ትንሣኤ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ከእነ አልዓዛር ትንሣኤ የተለየ መኾኑን ለማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱም፡-
፩ኛ) እነ አልዓዛር አስነሺ ይሻሉ፤ እርሱ ግን “ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ” ብሎ እንደተናገረ /ዮሐ.፲፡፲፰/ የተነሣው በገዛ ሥልጣኑ ነውና፡፡  በተለያየ ሥፍራ “አብ አንሥኦ (አብ አስነሣው)፤ መንፈስ ቅዱስ አንሥኦ (መንፈስ ቅዱስ አስነሣው)” ቢልም አንድ ነው፡፡ ምክንያቱም ዕሪናቸውን መናገር ነውና፡፡  
፪ኛ) የእነ አልዓዛር ትንሣኤ በብሉይ ሥጋ ነው፤ የእርሱ ግን በሐዲስ ሥጋ ነው፡፡
፫ኛ) የእነ አልዓዛር ትንሣኤ ሞትን ያስከትላል፤ የእርሱ ግን ሞትን አያስከትልም፡፡
፬ኛ) የእነ አልዓዛር ትንሣኤ ትንሣኤ ዘጉባኤን ይጠብቃል፤ የእርሱ ግን አይጠብቅምና፡፡

 አዳምን ዳግመኛ ወደ ገነት ከመለሰ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፭. አንዳንድ ተረፈ ንስጥሮሳውያን እንደሚሉት ንጽሕት ድንግል ማርያም ላቲ ስብሐትና “ወላዲተ ሰብእ” አይደለችም፤ የታመነች አምላክን የወለደች ናት እንጂ፡፡ የመናፍቃን መዶሻ የተባለው፣ በተለይም የቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት የካደውን ንስጥሮስን የረታው ቅዱስ ቄርሎስ እሳተ መለኮት አምላክን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ የተሸከመች፣ በጀርባዋ ያዘለች፣ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የፈጠረውን ፍጥረት የሚመግበው አማኑኤልን የድንግልና ጡቶቿን ወተት የመገበችውን የወላዲተ አምላክን ክብር ያልተረዱትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን ሲወቅስ “ወለዛቲ እንተ መጠነዝ ዐባይ ጾረት መለኮተ እፎ ይከልእዋ እምክብራ ለወላዲተ አምላክ ወላዲተ አምላክኬ ቅድስት ድንግል - ይኸንን ያኽል ታላቅ ኾና መለኮትን የተሸከመችቱን የአምላክ እናት ክብርን እንደምን ይነፍጓታል፤ ይከለክሏታል፡፡ የአምላክ እናት ማለት ድንግል ማርያም ናታ” በማለት የተሰጣትን ክብር በማድነቅ አስተምሯል /ተረፈ ቄርሎስ/፡፡

እንዲህም ስለኾነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታመነች የምሕረት አማላጅ ናት፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች አማልዱኝ ቢባሉ ነገር አጽንተው ይመለሳሉ፤ እርሷ ግን “ማእምንት ሰአሊተ ምሕረት - የታመነች የምሕረት አማላጅ ናት” /ዮሐ.፪፡፩-፲፩/፡፡ ሰአሊተ ምሕረት ሆይ! ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከልጅሽ ዘንድ አማልጅን፡፡  ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፮. ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ አሰምታ ትናገር ነበር፡፡ አረጋዊው ዮሴፍ በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፀነሰች ሳያውቅ “ ወለተ እስራኤል መኑ ቀረፀ አክናፈ ድንግልናኪ” ቢላት “እኔስ ምልዕተ ክብር ሆይ! እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍሽ ነፍስ ነሥቶ አንድ አካል ይኾናል ብሎ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ ነገር በቀር ምን ምን የማውቀው እንደ ሌለኝ እግዚአብሔር ያውቃል” ብላ አሰምታ ተናገረች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “ዲያተሳሮን” በተባለ የወንጌል ትርጓሜ መጽሐፉ የእመቤታችንና የዮሴፍ ግንኝነት እንዲህ በማለት በጥልቀት ተንትኖታል፡- “የመሲሑ ልደት እንዲህ ነበር፡፡ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች /ማቴ.፩፡፲፰/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን ያለ ምክንያት አይናገረውም፡፡ አሕዛብ አማልክቶቻቸው እጅግ አሳፋሪ በኾነ ግንኝነት እኛ ከምናውቀው ተፈጥሮ ውጪ ልጅ ይወልዳሉ ብለው ስለሚያስቡ እንጂ፡፡ በመኾኑም እነዚህ አሕዛብ እንደሚያስቡት እመቤታችን ፀንሳ ተገኘች ተብሎ እንዳይታሰብ ወንጌላዊው “ሳይገናኙ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” አለ፡፡ የተወለደው በወንድ ዘር አይደለም፡፡ ማኅተመ ድንግናዋን ሳይለውጥ ገባ፤ አከበራት፤ ነፍስና ሥጋም ከእርሷ ነሥቶ ተዋሐደ፡፡
 አስቀድማ ለወንድ መታጨቷ፣ ባል (ጠባቂ) እንዳላት መደረጓ፣ ቀጥሎም መፅነሷ ልጇ ወዳጇ በዳዊት በትረ ሥልጣን ስለሚገባና የዳዊት ሥልጣንን የሚይዝ ደግሞም በእናቱ ሳይኾን በአባቱ ስም ስለሚጠራ ነው /ሉቃ.፩፡፴፪/፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ክፉዎች የፀነሰችው በሴሰኝነት ነው ብለው እንዳያስቡ ነው፡፡ እጅግ ጻድቅ ለኾነው ለዮሴፍ የመታጨቷ ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ዮሴፍ እመቤታችንን ፀንሳ ባያት ጊዜ እስክትወልድ ድረስ ተከባከባት፡፡ ከእርሷ ጋር በቤቱ ኖረ እንጂ አላባረራትም፡፡ ከማንምና ከምንም አስቀድሞ ከእርሷ የተፀነሰው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንጂ በዘርዐ ብእሲ እንዳልኾነ ምስክር ኾነ፡፡
 እመቤታችንም ያለ ታራሽ ልጇን ወለደችው፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን አዳም ከማንም ጋር ሳይገናኝ እንደወለዳት አሁንም ዮሴፍና እመቤታችን በግብር ሳይተዋወቁ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ወለደች፡፡ ሔዋን ነፍሰ ገዳዩን (ቃየልን) ወለደች፤ እመቤታችን ግን ወሀቤ ሕይወትን ወለደች፡፡ ቀዳማዪቷ ሔዋን የወንድሙን ደም የሚያፈስ ልጅን ወለደች፤ ዳግማዪቱ ሔዋን ግን ስለ ወንድሞቹ ደሙን የሚያፈስ ልጅን ወለደች፡፡ የቀዳማይቱ ሔዋን ልጅ (ቃየል) ምድር ተረግማ ኃይልዋን አልሰጥ ስላለችው ኰብላይና ተቅበዥባዥ ኾነ /ዘፍ.፬፡፩-፲፬/፤ የዳግማይቱ ሔዋን ልጅ ግን ያንን ርጋማን አስወገደው በመስቀል ላይም ጠርቆ አስወገደው /ቈላ.፪፡፲፬/፡፡ የእመቤታችን ፅንስ አዳምን ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ምድር እንደተገኘ ዳግማዊ አዳምም ያለ ዘርዐ ብእሲ በድንግሊቱ ማኅፀን እንደተገኘ ያስተምረናል፡፡ ቀዳማዊ አዳም በበደለ ጊዜ ወደ እናቱ ማኅፀን (ወደ ምድር) ተመለሰ፤ ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ያልተመለሰው ዳግማዊ አዳም ግን ቀዳማዊውን እንደገና ከእናቱ ማኅፀን እንዲወለድ አደረገው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተራራማው ሀገር ወደ ቤቷ በሄደች በተመለሰች ጊዜ የፀነሰችው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደኾነ ታስረዳው ነበር፤ ነገር ግን ከኅሊናት በላይ ስለኾነበት ነገሩ ረቀቀበት፡፡ ፊቷን ሲመለከታት ምንም ዓይነት የውሸት ምልክት አይታይባትም፤ ግን ደግሞ ሆዷ ገፍቷል፡፡ በመኾኑም ደግ ነውና ሊገልጥባት አልወደደም፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን ግን ከሌላ ወንድ ጋር ተገናኝታለች ብሎ ስላሰበ ወደ ቤቱ ሊወስዳት አልወደደም፡፡ በእነዚህ ኹለት ሐሳቦች እየተማታ ወደቤቱ ሊወስዳት እንደማይገባ ግን ደግሞ ነገሩንም ሊገልጥባት እንደማይገባ ወሰነ፡፡ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፡፡  በጣም በሚያደንቅ መንገድ መልአኩ “ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት - የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ!” አለው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ለቅድመ አያቱ ለዳዊት “እስመ እምፍሬ ከርሥከ አነብር ዲበ መንበርከ- ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህ ክርስቶስን በዙፋንህ አስቀምጣለሁ” ብሎ የማለለትን ቃል እንዲያስተውስ ነው /መዝ.፻፴፩፡፲፩/፡፡ መልአኩ ቀጠለ፤ እንዲህም አለው “ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ - የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከካህናት እጅ እንደተቀበልህ ከእደ መንፈስ ቅዱስ መቀበልን አትፍራ፤ ከእርሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንድምትወልድ ከረቀቀብህ እነሆ “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ” የሚለውን የነቢዩን ቃል አስታውስ /ኢሳ.፯፡፲፬/፡፡ ዳግመኛም ነቢዩ ዳንኤል “ተበትከ ዕብን ዓቢይ እምደብር ዘእንበለ እድ - ታላቅ ደንጊያ እጅ ሳይነካው ከተራራ ወረደ” ብሎ የተናገረውን ልብ በል /ዳን.፪፡፴፭/፡፡ ይህ የነቢዩ ዳንኤል ቃል ኢሳይያስ በአንድ ቦታ “ርእይዋ ለኰኩሕ ጽንዕት እንተ ወቀርክሙ ወአዘቅተ ዕምቅተ እንተ ከረይክሙ - ያለዘባችኋትን ጽኑ ዐለት እይዋት የቈፈራችሁትንም ጥልቅ ጕድጓድ አስተውሉ” ብሎ እንደተናገረው ያለ አይደለም ኢሳ.፶፩፡፩/፡፡ ምክንያቱም ኢሳይያስ የወንድና የሴትን ነገር አንሥቶ የተናገረ ሲኾን ነቢዩ ዳንኤል ግን “ዘእንበለ እድ - ያለ እጅ” ነው ያለው፡፡ ይኸውም ቀዳማዊ አዳም ለሔዋን አባቷም እናቷም እንደኾነ ኹሉ እመቤታችን ለጌታችን (በተዋሐደው ሥጋ) እናቱም አባቱም ነች፡፡
 ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለነበረ ነገሩን ሊገልጥባት አልወደደም፡፡ ደግነቱም (ጽድቁም) እንደ ሕጉ የኾነ ደግነት አይደለም፡፡ ሕጉ እንዲህ ያለ ነገርን ያደረገ ወንድ ወይም ሴት እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል ያዝዛልና /ዘዳ.፲፯፡፭፣፯ ፤ ዘዳ.፳፪፡፳፫-፳፬/፡፡ ዮሴፍ ግን በስዉር ሊተዋት (ሊለያት) አሰበ እንጂ ሊገልጥባት አላሰበም፡፡ ዮሴፍ ይህን የሚደርገው ነገሩ ረቅቆበት፣ ከሚያውቀው የተፈጥሮ ሂደትም ውጪ ስለኾነበት ነው፡፡ በመቀጠል የኾነው ኹሉ እግዚአብሔር እንዳደረገው ተገነዘበ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ ነገር አይቶም ሰምቶም ስለማያውቅ ግራ ተጋባ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እመቤታችንን ላለማመን ምንም የማይቻል ነበር፡፡ ምክንያም በጣም ብዙ አስረጂ ነገሮችን አስረድታዋለችና፡፡ የዘካርያስ ዲዳ መኾን፣ የኤልሳቤጥ መፀነስ፣ የመልአኩ ብሥራት፣ የብላቴናው ዮሐንስ በሐሴት መሞላትና መዝለል፣ የቀደሙ አበው ትንቢት እና ሌሎች ዮሴፍን ለማሳመን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይነግሩት ነበር፡፡ በመኾኑም ነገሩን ሳይገልጥባት በስዉር ሊተዋት (ሊለያት) ወሰነ፡፡ እመቤታችን የፀነሰችው በግብረ መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ቢያውቅ ኖሮ በስውር ሊተዋት ባላሰበ ነበር፡፡
 የኾነው የተደረገው ኹሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ መኾኑን አውቋል፡፡ ኾኖም ግን ሌሎች በዙርያ ያሉ ሰዎች ይህን ነገር ሊያምኑት ስለማይችሉ በስውር መተው የተሻለ የጽድቅ ሥራ መስሎ ታየው፡፡ ይኸውም በግብር እንዲገናኛት ሳይኾን እንዲያገለግላት፣ እንዲጠብቃት የሰጡት ካህናት ይህን የእግዚአብሔር ሥራ ሊያምኑት እንደማይችሉ ስለሚያውቅ ነው፡፡ “የመለኮታዊው ልጅ አባት ነኝ ብል ኃጢአት ነው” በማለት በስውር ሊተዋት አሰበ፡፡ ልጇ (ክርስቶስ) በድንግልና የተፀነሰ በድንግልናም የሚወለድ መኾኑን ቢያውቅም ይህን የሚጠረጥሩ ሰዎች እንዳይኖሩ ከእርሷ ተለይቶ መኖርን ፈራ፡፡ መልአኩም መጥቶ “ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ - ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ” አለው፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስም ከዚያ በኋላ በጽድቅ በንጽሕና ከእርሱ ጋር እንደኖረች ዮሴፍም እንደወሰዳት ይነግረናል፡፡ ለዚህም ነው ካህናት በኋላ ዘመን ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስን እመቤታችን ድንግል ናት ስላለ ወግረው የገደሉት፡፡ ዳግመኛም ካህኑ ዘካርያስ ጌታችን እንደተናገረው በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲገደል ያደረጉት፡ ሕፃናት በሄሮድስ ትዕዛዝ በሚገደሉበት ሰዓት ልጁ ዮሐንስን በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ስለሚወለደው ክርስቶስ ምስክር እንዲሰጥ ወደ በረሐ እንዲሸሽ በማድረጉ ነው /ማቴ.፳፫፡፴፭/፡፡
 አንዳንድ ልበ ስሑታን እመቤታችን ጌታን ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር በግብር ተገናኝታለች ለሚሉን እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- “ያቺ ማኅደረ መለኮት የኾነች ድንግል፣ ያቺ መንፈስ ቅዱስ የጸለለባት እመቤት እንደምን ሟች ከኾነ ዕሩቅ ብእሲ ጋር ተመልሳ በግብር ትገናኛለች ተብሎ ይታሰባል? እንደምንስ ዳግም በምጥ በጋር ትወልድ ዘንድ በግብር ተዋውቃለች ተብሎ ይታሰባል? እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሴቶች ኹሉ ተለይታ ንዕድ ክብርት መኾኗን መልአኩ ከተናገረ ከጥንት (ከእናቷ ማኅፀን) አንሥቶ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ንጽሕት ነበረች ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን በምጥ በጋር ከመውለድ የተለየች ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ዳግመኛ ከዮሴፍ ጋር በግብር ተዋውቃ በምጥ በጋር ትወልዳለች ተብሎ ፈጽሞ ሊታሰብ አይገባውም፡፡ በሰብአ ትካት ጊዜ ከኖኅ ጋር ወደ መርከብ የገቡ እንስሳት ስንኳ ከግብር የተለዩ ከነበሩ አማኑኤልን በግብር በማኅፀኗ የተሸከመች እመቤታችንማ ፈጽማ እንዲህ በግብር ተዋውቃለች ተብሎ ሊታሰብ አይገባውም፡፡ ከመርከቡ ውስጥ ከኖኅ ጋር የነበሩ እንስሳት በግብር ያልተዋወቁት ኖኅ ከልክሏቸው ነው፤ እመቤታችን ግን ከዚህ ግብር የተለየችው በፈቃዷ ነው፡፡ በንጽሕና በቅድስና እንደወለደች ኹሉ ንጽሕናዋና ቅድስናዋም እንደዚያ ኾኖ እንዲዘልቅ ፈቃዷ ነበር፡፡
  የአሮን ልጆች እግዚአብሔር ያላዘዘውን እሳት በእግዚአብሔር ፊት በማቅረባቸው በሞት ከተቀጡ /ዘሌ.፲፡፩-፪/ እመቤታችንማ እንዴት? ወይንን የሚነግዱ ሰዎች በወይኑ ላይ ውኃ ቢጨምሩበት ቅጣታቸው የበዛ ከኾነ እምቤታችንማ እንዴት? አንዳንድ ሰዎች የጌታ ወንድሞች ተብለው የሚጠሩ ልጆች ስላሉ እመቤታችን የወለደቻቸው ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ጌታችንም የዮሴፍ ልጅ መባሉን ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ይህም አይሁድ ብቻ ሳይኾን እመቤታችንም እንዲህ አድርጋ ትናገር ነበር፡፡ “እስመ ናሁ አቡከኒ ወአነኒ ሠራሕነ እንዘ ነሐሥሠከ- እነሆ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” እንዲል /ሉቃ.፪፡፵፰/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዮሴፍ እመቤታችንን ወደ ቤቱ እንዲወስዳት የነገረው አንደኛው፡ በሐሰት ሊከሷት የሚችሉትን ስዎች ጥርጣሬ እንዳይኖራቸው ለማድረግ፤ በተለይ ደግሞ ከመልአኩ ፀንሳ ተገኘች ብለው ሊገድሏት ከሚችሉ ሰዎች ሊጠብቃት ነው፡፡ በእነዚህ ሰዎች ዘንድ አንድ የተለመደ ወሬ  ነበር፡፡ ይኸውም “ድንግል በድንግልና ትወልዳለች፤ ድንግሊቱ በመውለዷ ምክንያትም ከተማይቱ ትጠፋለች፤ ክህነታችን ሀብተ ትንቢታችን ኹሉ ይወገዳል” የሚል ነው፡፡ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንድምትወልድ የተናገረው ኢሳይያስን በመጋዝ ተርትረው እንዲገደል ያደረጉት ለዚሁ ነበር /ኢሳ.፯፡፲፬/፡፡ 
 ድንግሊቱ የበኵር ልጇን ወለደች፤ ነገር ግን ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ … የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ (ዮሴፍ) በንጽሕና በቅድስና ከእርሷ ጋር ኖረ /ማቴ.፩፡፳፭/፡፡ ይህ ቃል የተነገረው ዮሴፍ እመቤታችንን ወደ ቤቱ ከወሰዳት በኋላ ነው፡፡ “ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ” ብሎ ቀጥሎም “የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ (በግብር) አላወቃትም” እንዲል /ማቴ.፩፡፳፬-፳፭/፡፡ በሌላ አገላለጽ ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ ነገር ግን በግብር አልተዋወቁም ማለት ነው፡፡ ወደ ቤቱ የወሰዳት ከፀነሰች በኋላም ቢኾን እጮኛዋ ስለኾነ ነው፡፡ የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ማለትም እንኳንስ በግብር ቀርቶ በሐሳቡም ከእመቤታችን ጋር ሌላ ነገር ለማድረግ አላሰበም ተብሎ ይተረጐማል፡፡ እስክትወልድ ድረስ ማለትም ሰዎች እመቤታችን የፀነሰችው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንጂ በዘርዐ ብእሲ እንዳልኾነ እንደተረዱ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
 ዳግመኛም የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ማለት ምንም እንኳ እመቤታችንና ዮሴፍ በፈቃዳቸው በንጽሕና በቅድስና ለመኖር ቢያስቡም ጸጋ መንፈስ ቅዱስም ረድቶዋቸዋል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተወለደ በኋላ ያለው ቅድስናቸው ግን የራሳቸው ነጻ ፈቃድ ነው፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በግብር እንዳይተዋወቁ ከልክሎዋቸው እንደነበርና ጌታ ከተወለደ በኋላ ግን በራሳቸው ምርጫ በንጽሕና በቅድስና እንደኖሩ ለመግለጽ “እስከ” በሚለው ቃል ነግሮናል፡፡ የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ በንጽሕና በቅድስና አብሯት ኖሯል፡፡ እንግዲህ እስከ የሚለው ቃል ስለተጠቀሰ ዮሴፍ ከዚያ በኋላ በግብር አውቋታል ተብሎ ድምዳሜ ሊወሰድ ይችላልን? እስከ የሚለው ቃል መጨረሻ የሌለው እስከ ነው፡፡ “ጌታ ጌታዬን፡- ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” ተብሎ ስለተጻፈ /መዝ.፻፲፡፩/ ጌታ ጠላቶቹ በእግሩ መረገጫ ከኾኑ በኋላ ይነሣል ማለት ነውን? … ከእናንተ መካከል “የጌታችን ወንድሞች እኮ ስማቸው በወንጌል የተጠቀሰ ነው!” የሚለኝ ቢኖር እኔም እንዲህ ብዬ እመልስለታለሁ “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሥር ለሚወደው ደቀ መዝሙር (ለዮሐንስ) የሰጣት ስለኾነ እነዚህ ልጆች ልጆቿ እንዳልኾኑ፣ ዮሴፍም ባሏ እንዳልኾነ ግልጽ ነው” /ዮሐ.፲፱፡፳፯/፡፡ እናትና አባትህን አክብር ብሎ ሕግን የሠራ ጌታ እንደምን እመቤታችንን ከልጆቿ አለያይቶ ለዮሐንስ ይሰጣታል ተብሎ ይታሰባል?” /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatesaron, pp 60-64/፡፡  

  የማይቻለውን ቻልሽ፡፡ ምንም ምን የሚወስነው የሌለውን ወሰንሽ፡፡ ምልዕተ ክብር ሆይ! በክብረ ወሊድ ላይ ክብረ ድንግልናን ደርበሽ ብትገኚ ላንቺ የተሰጠሸ ክብር ፍጹም ነው፡፡ የአካላዊ ቃል ማደሪያ ኹነሻልና፣ ምዕመናንን ሰብስባ የያዘቻቸውና ለሥላሴ ሰጊድን የምታስተምሪላቸው (አንድነት ሦስትነት በጐላ በተረዳ ነገር የታወቀብሽ) ጴጥሮስ በናሕሰ ኢዮጴ ያያት የቤተ ወንጌል ሰፊ መጋጃ አንቺ ነሽ /ሐዋ.፲፡፱-፲፮/፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “ሰላም ለኪ መንጦላዕተ ገርዜን - የበፍታ መጋረጃ ሰላምታ ለአንቺ ይገባል” ብሏል /የአባ ጊዮርጊሥ የሰባቱ ጊዜያት የሃይማኖትና የጸሎት መጽሐፍ ትርጓሜ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ገጽ ፻፷/፡፡  
  ሙሴ ያየውን ዓምደ እሳት የተሸከምሽ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፲፫፡፳፪/፡፡ ይኸውም ዓምደ እሳት ያልኩት ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰማይና ምድር ለፈጠረ ለእርሱ ማደሪያ ኾንሽው፡፡ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሽ ቻልሽው፡፡ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ለመወሰን የታመንሽ ነሽ፡፡ ከምድር ወደ ሰማይ ለመውጣት መሰላል ኾንሽ፡፡ በመሰላል የላዩ ወደ ታች ይወርዱበታል፤ የታቹ ወደ ላይ ይወጡበታል፡፡ የላዩ ወደታች እንዲወርዱበት መለኮትም ከአንቺ ትስብእትን ተዋሕዷል፤ የታቹ ወደ ላይ እንዲወጡበትም ትስብእት ከመለኮት ጋራ ለመዋሐዱ ምክንያት ኾነሻል፡፡ ድንግል ሆይ! ክብርሽ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጣል፡፡ ቅዱሳን፣ ሰብአ ሰገል /ማቴ.፪፡፪/፣ እነ በለዓም /ዘኅ.፳፬፡፲፯/፣ ሐዋርያት ደስ ብሏቸው ያዩት ኮከብ ካንቺ የተወለደ ምሥራቅ አንቺ ነሽ፡፡ ይኸውም በፃር፣ በጋር፣ በምጥ ትወልድ ዘንድ በሔዋን የፈረደባት ነው፡፡ አንቺ ግን ምልዕተ ክብር ሆይ! ደስ ይበልሽ የሚል ድምፅ ሰማሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ሔዋንበሕማም ለዲ” የሚል ድምፅ ሰምታ /ዘፍ.፫፡፲፮/ ምክንያተ ሞት ቃየልን አስገኘች /ዘፍ.፬፡፩-፰/፡፡ አንቺ ግንተፈሥሒ ምልዕተ ጸጋ” የሚል ደምፅ ሰምተሸ  ፍጥረትን ኹሉ የሚገዛ ንጉሥን ወለድሽልን /ሉቃ.፩፡፴፩/፡፡ ሄሬኔዎስ የተባለ ሊቅም ይህንን አንቀጽ በረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል፡- “እነሆ ጌታ የራሱ ወደኾኑት በግልጥ (በለቢሰ ሥጋ) መጣ፡፡ ትእዛዙን ተላልፎ በዕፅ የሞተውን አዳም በዕፅ (በመስቀል) ላይ ታዝዞና ካሣውን ከፍሎ፣ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ይመልሰው ዘንድ በራሱ ጥበብ ከፍጥረቱ ተወለደ፡፡ ለአንድ ወንድ የታጨችው ድንግል በምክረ ከይሲ ያመጣችውን ያለመታዘዝ ኃይል የእውነት መልአክ ለአንድ ወንድ ለታጨችው ድንግል ባበሠራት ጊዜ ፈራረሰ፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን ከእግዚአብሔር እንድትርቅና ቃሉን እንድትቃወም በክፉ መልአክ እንደተታለለች ኹሉ፣ ዳግማይቱ ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያምም ደጉ መልአክ ይዞት የመጣው መልካሙን ዜና እንድትቀበለውና እግዚአብሔርን በከዊነ ቃሉ እንደምትወልደው አመነች፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን እግዚአብሔርን እንዳትታዘዘው ክፉ መልአክ አታለላት፤ ወደቀችም፡፡ ዳግማይቱ ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን እግዚአብሔርን እንድትታዘዝ ቅዱስ መልአክ አሳመናት፤ እርሷም ሔዋንን ረዳቻት፡፡ ነገደ አዳም በአንዲት ድንግል አለመታዘዝ ምክንያት ሞት ተፈረደበት፣ ኾኖም በሌላይቱ ድንግል መታዘዝ ምክንያት ዳነ፡፡ የፍጥረት በኵር የሚኾን አዳም የበደለው በደል የእግዚአብሔር በኵር በሚኾን በወልደ እግዚአብሔር መቀጣት ተፈወሰ፡፡ የእባቡ ተንኰል በርግቡ የዋኅነት ተዋጠ፤ ለሞት ሲዳርገን የነበረው ቁራኝነትም ተሰበረ፡፡”
  ሰው ኾኖ ያዳነን መሐሪ ነው፤ ሰው ወዳጅ ነው፡፡ ድንግል ሆይ! በእንተዝ ንዌድስኪ - ስለዚህ ነገር መልአኩቡርክት አንቲ እም አንስት” ብሎ እንዳመሰገነሽ እኛምተፈሥሒ ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ- እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍሽ ነስቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይ ኹኗልና (ተፈሥሒ) ደስ ይበልሽ” ብለን እናመሰግንሻለን፡፡ ንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታቸን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
  ይኽን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ታርጋለች፡፡ እርሱም እጅ ነሥቶ ይቀራል፡፡

 አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡

15 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ-ሕይወት ያሠማልን!!!አምላክ በጸጋው ይጠብቅልን!!

    ReplyDelete
  3. ቃለ-ሕይወት ያሠማልን!!!አምላክ በጸጋው ይጠብቅልን!!

    ReplyDelete
  4. ቃለ ሕይወት ያስምዕ ለነ።

    ReplyDelete
    Replies
    1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

      Delete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  6. Kale hiwotin yasmalin

    ReplyDelete
  7. ቃለህወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  8. አሜን እግዚአብሔረ ይስጥልን ቃለ ህይወት ያሰማልን !

    ReplyDelete
  9. እግዚአብሔረ ይስጥልን ቃለ ህይወት ያሰማልን !

    ReplyDelete
  10. 🙏🙏🙏❤️

    ReplyDelete