Friday, December 13, 2013

ነቢዩ ዳንኤል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 “ዳንኤል” ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “እግዚአብሔር ፈራጅ ነው” ማለት ነው፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ አፍአዊ በኾነ ትርጓሜ (Literally) ስንመለከተው እግዚአብሔር በነቢዩ ዳንኤል አድሮ በአሕዛብ ላይ እንደሚፈርድ፤ በአሕዛብ ላይ ብቻ ሳይኾን የዋሐንን በሚከስሱ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ፤  አንድም እግዚአብሔር ጨቋኙን ንጉሥ አጥፍቶ ወደ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም ወገኖች ማለትም እስራኤልንና ይሁዳን ነፃ እንደሚያወጣቸው የሚያስረዳ ሲኾን፤ በምስጢራዊው መልኩ ግን የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዲያብሎስ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም ወገኖች ማለትም ሕዝብም አሕዛብም ከኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶ የክብርን ሸማ እንደሚያለብሳቸው/ሰን የሚያመለከት ነው፡፡ 

 መጋቢት ፳፫ የሚነበበው ስንክሳር እንደሚነግረን ነቢዩ ዳንኤል የዮናኪር የልጅ ልጅ ነው፡፡ ዮናኪር ማለት ደግሞ የንጉሥ ኢዮአቄም (፮፻፱-፭፻፺፯ ቅ.ል.ክ.) ልጅ ሲኾን የሠለስቱ ደቂቅ አባትም ነው፡፡ የትንቢተ ዳንኤል አንድምታ ትርጓሜ መግቢያ እንደሚተርከው ደግሞ የዳንኤል እናት፣ ሠለስቱ ደቂቅ እና ኢኮንያን የኢዮአቄም ልጆች ናቸው፡፡ ፮፻፭ ቅ.ል.ክ. ገደማ በይሁዳ ነግሦ የነበረው ኢዮአቄምን ጨምሮ ነገደ ይሁዳ ሲማረኩ ነቢዩ ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ አብረው ተማርኳል፡፡ የይሁዳ ምርኮ የተፈጸመው ሦስት ጊዜ ነው፡፡ አንደኛው በ፮፻፭፣ ኹለተኛው በ፭፻፺፯፣ ሦስተኛው ደግሞ በ፭፻፹፯ ቅ.ል.ክ.፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ዳንኤል የተማረከው በመዠመሪያው ዙር፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል ደግሞ በኹለተኛው ዙር ነው ማለት ነው፡፡
 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዳንኤል ስም የሚጠሩ ሌሎች ኹለት ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱም፡-
1.  የዳዊት ልጅ ዳንኤል /፩ኛ ዜና.፫፡፩/፤
2.  የኢታምር ልጅ ዳንኤል /ዕዝራ.፰፡፫/ ናቸው፡፡
በነቢዩ ዳንኤል ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
 ነቢዩ ዳንኤል በተማረከ ጊዜ ዕድሜው ገና ልጅ ነበር፡፡ ድርሳናት እንደሚናገሩት ዳንኤል የተወለደው በ፮፻፲፰ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚኽ ሲማረክ ገና ፲፪ ዓመቱ ነበር ማለት ነው፡፡
 ነቢዩ ዳንኤል ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር በተማረከ ጊዜ በቀጥታ የተሰጡት ኤስፋኔዝ ለተባለ የናቡከደነፆር የጃንደረቦች አለቃ ነበር፡፡ በኤስፋኔዝ አማካኝነትም የከለዳውያንን ትምህርት ተምረዋል፡፡ የከለዳውያን ትምህርት የተባለውም ባሕላቸው፣ የኮከብ ቈጠራ፣ ሒሳብ፣ አስማትና ሕልም መፍታትን ነው /ዳን.፩፡፫-፬/፡፡ ናቡከደነፆር እነዚኽ የአይሁድ ወጣቶች ሲያስተምርም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም፡-
1.  ኢየሩሳሌምን የወረራት እርሷንና ሕዝቧን ለማጥፋት ሳይኾን ሕዝቡ እርሱን ማለትም ናቡከደነፆርን አናገለግልም በማለታቸው ብቻ መኾኑን ለመግለጥ፤
2.  የነገሥታት ልጆች በቤተ መንግሥት መብታቸው ተጠብቆ ከተቀመጡ አያምፁም አያሳምፁም ብሎ በማመን፤
3.  አይሁድ የእነርሱ ሰዎች በቤተ መንግሥት በመኖራቸው መብታችን ይከበርልናል ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ፤
4.  ወጣቶቹ ማንነታቸውን እንዲዘነጉና በአዲሱ የባቢሎን ባሕልና ሥልጣኔ እንዲዋጡ ለማድረግ ነው እንጂ፡፡
   የጃንደረቦቹ አለቃ አስፋኔዝ ሥራውን የዠመረው የነቢዩ ዳንኤልንና የሠለስቱ ደቂቅን ስም በመቀየር ነበር፡፡ ይኸውም አኹን ካለው የኢትዮጳውያን ነባራዊ ኹኔታ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው፡፡ ልዩነቱ እኛ ወደ ባዕድ አገር ሳንኼድ በገዛ አገራችን ምዕራባዊ ባሕል መበከላችን፤ ክርስቲያናዊ ስማችንና ባሕላችንን ትተን የባዕድ ስምና ባሕልን መውረሳችን ነው፡፡ በመኾኑም ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፣ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያንም አብድናጐ አላቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ ዳንኤል - እግዚአብሔር ዳኛ ነው፤ አናንያ - እግዚአብሔር ሩኅሩኅና ደግ ነው፤ ሚሳኤል - እግዚአብሔርን የሚመስል፤ አዛርያ - እግዚአብሔር ይረዷል የሚል ስማቸውን ቀይሮ ብልጣሶር - የበአል መስፍን፤ ሲድራቅ - በፀሐይ አምላክ የተገለጠ፤ ሚሳቅ - በሻቅ (በውበትና በመሬት አምላክ) በኩል፤ አብድናጐ- የእሳት አምላክ አገልጋይ በማለት ጣዖታዊ ስያሜን ሰጣቸው፡፡
 እነዚኽ ወጣቶች የጃንደረቦቹ አለቃ አስፋኔዝ በሚመራው ትምህርት ቤት ሲማሩና ለንጉሡ አማካሪነት ሲሠለጥኑ ምግብና መኝታ ከቤተ መንግሥት ድርሻ ተሸንሽኖላቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ይኽን እንዲመገቡ የንጉሥ ትእዛዝ ቢኾንም ነቢዩ ዳንኤል ግን እንዳይረክስ በልቡ አስቦ እምቢ አለ፡፡ የጃንደበረቦቹ አለቃን አሳምኖም ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር የሚበሉትን ጥራጥሬና ውኃ ብቻ እንዲሰጣቸው ለመነው /ዳን.፩፡፰-፲፫/፡፡ አስፋኔዝም ያሉትን ከመረመረ በኋላ ሰጣቸው /ዳን.፩፡፲፬-፲፮/፡፡ እኛ ግን እንኳንስ በባዕድ አገር ኾነን በገዛ አገራችን የምንበላው ሳናጣም ላለመፆም የምናመጣቸው ምክንያቶች መብዛታቸው ቤቱ ይቁጠረው፡፡
 በነቢዩ ሳሙኤል አድሮ “የሚያከብሩኝን አከብራለኹ” /፩ኛ ሳሙ.፪፡፴/ ብሎ የተናገረው እግዚአብሔርም በባዕድ ምድር ለነገሥታት እንኳ ሳይንበረከኩ፣ ጣፋጭ ምግብ ሳያስጐመጃቸው፣ ልጅነታቸው ሳያታልላቸው እግዚአብሔርን ስለ አከበሩት፤ እርሱም ከኹሉም በላይ አልቆ አከበራቸው፡፡ በትምህርትና በጥበብ ኹሉ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው /ዳን.፩፡፲፯/፡፡ በሦስት ዓመት የትምህርት ቈይታቸው ነቢዩ ዳንኤልንና ሠለስቱ ደቂቅን የሚተካከል አልተገኘም፡፡ ዳንኤል ግን ከዚኽም በላይ ሌላ ጸጋ ተጨመረለት፤ እርሱም ሕልምንና ራዕይን ኹሉ የመተርጐም ጸጋ፡፡ ለዚኽም ነው ናቡከደነፆር ኹለት ጊዜ ሕልምን አይቶ መንፈሱ በታወከ ጊዜ አስማተኞችና መተተኞች ሕልሙንና ፍቺውን መናገር ሲያቅታቸው ዳንኤል ሕልሙንና ፍቺውን የተረጐመለት ፡፡ በዚኽም፥ እግዚአብሔር ከነቢዩ ዳንኤል ጋር ስለነበረ በስደት አገር እንደ ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ለሹመት በቃ፤ በባቢሎን አውራጃ ኹሉ ላይ ተሾመ፤ በባቢሎን ጠቢባን ላይ ዋነኛ አለቃ ኾነ፡፡ ዳንኤል ብቻ አይደለም፤ ሕልሙን ይተረጕም ዘንድ በጸሎት ይራዱት የነበሩ ሠለስቱ ደቂቅም በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ ተሾሙ /ዳን.፪ ሙሉው/፡፡
 ናቡከደነፆር በ፭፻፷፪ ቅ.ል.ክ. ላይ ከሞተ በኋላም የናቡከደነፆር የልጅ ልጅ የኾነው ብልጣሶር ወደ ንግሥና ሲመጣም ነቢዩ ዳንኤል በቤተ መንግሥት ነበረ /ዳን.፭/፡፡ እግዚአብሔር በነቢዩ ላይ አድሮም ሥራውን ይሠራ ነበር፡፡ ብልጣሶር፥ አባቱ (አያቱ) ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ባመጣቸው ንዋያተ ቅዱሳት አማካኝነት ከመኳንንቱ፣ ከሚስቶቹና ከዕቁባቶቹ ጋር ጠጡባቸው፡፡ ጠጥተውም ጣዖታትን ያመሰግኑ ነበር፡፡ ድንገትም የሰው እጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ “ማኔ ቴቄል ፋሬስ” የሚል ጽሕፈት ብለው ጻፉ፡፡ ነገር ግን ያነቡለትና ይተረጕሙለት ዘንድ ንጉሡ የጠራቸው አስማተኞችና ጠንቋዮች ጽሕፈቱን መተርጐምስ ይቅርና ማንበብም አልቻሉም፡፡ ያነበበለትና የተረጐመለት ነቢዩ ዳንኤል ነበር /ምዕ.፭/፡፡
 የባቢሎን መንግሥት በ፭፻፴፱ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ማብቂያ አግኝቶ በቂሮስ አማካኝነት የፋርስ መንግሥት ሲተካ፥ ነቢዩ ዳንኤል አኹንም በቤተ መንግሥቱ ከተሾሙት መሳፍንት አንዱ ነበረ /ዳን.፮/፡፡     
 በአጠቃላይ እግዘኢብሔር ጸጋና ጥበብን ስለ ሰጠው በባቢሎን፣ በሜዶንና በፋርስ ቤተ መንግሥታት ውስጥ ኾኖ ሕዝቡን ያገለግል የነበረ ታላቅ ነቢይ ነው፤ ዳንኤል፡፡ ለነገሥታቱ ታማኝነቱን ሳያጓድል ለእግዚአብሔርም ታማኝ ኾኖ አገልግሏል፡፡ ምንም እንኳን ጣዖታትን ከሚያመልኩ ነገሥታት ጋር ቢኖርም ለጣዖት የተሠዋው መሥዋዕት ሊበላ አልወደደም፤ ለጣዖታቱም ሊሰግድ አልፈቀደም፡፡ እግዚአብሔር ለነገሥታቱ ሊያስተላልፈው የፈለገው መልእክትም ምንም ሳያፍርና ሳይፈራ እንዲኹም ሳይሸራርፍ ይነግራቸው ነበር፡፡
 ነቢዩ ዳንኤል በነበረበት ዘመን የአሕዛብ ነገሥታት በጣም ገንነው የወጡበት ሰዓት ነው፡፡ ለእነዚኽ ነገሥታት በቀስታ እንኳን ቢኾን የእግዚአብሔርን ቃል ሊናገር የሚችል ሰው አልነበረም፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ግን ምንም እንኳን መጻተኛ ቢኾንም፣ ምንም እንኳን ምርኮኛ ቢኾንም እውነቱን ሳይሸፍንና ሳይሸራርፍ በትሕትናና በጥበብ ይነግራቸው ነበር፡፡ ስሕተታቸውን ይገልጥላቸው ነበር፡፡ የጣዖቶቻቸውን ከንቱነት ይነግራቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ፈጣሪነት ያስተምራቸው ነበር፡፡  
የነቢዩ ዳንኤል ልዩ ልዩ ጸጋና ጠባይ
1.  የጸሎት ሰው ነበር፡፡ መጽሐፍ እንደሚነግረን ነቢዩ ዳንኤል “በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት” ይጸልይ ያመሰግንም ነበር /ዳን.፮፡፲/፡፡ እኛ ግን ምን ያኽል ደካሞች እንደኾንን መመርመር ነው፡፡
2.  የጾም ሰው ነበር፡፡ እንደዉም በጦም ወራት ማለፊያ እንጀራ አለመብላት፥ ሥጋ ጠጅም አለመመገብ የጦም ወራት እስኪፈጸም ድረስም ቅቤን አለመቀባት ያስተማረው ይኸው ነቢይ ነው /ዳን.፲፡፫/፡፡
3.  ነቢይነትን ከአስተዳዳሪነት ጋር የደረበ ነበር፡፡ ለዘመናችን አስተዳዳሪዎች ትልቅ አርአያ ሊኾን የሚችል ድንቅ መሪ ነበር፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን በአሕዛብ ላይ የተሾመ ቢኾንም መንፈሳዊነቱን አላቀጨጨበትም፡፡ ይበልጥ ነጥሮ እንዲወጣ አደረገው እንጂ፡፡ የሚያስገድዱ ኹኔታዎች እያሉም ማንነቱን አላበላሸም፡፡
4.  ሕዝቡን በቅንነትና በመንፈሳዊነት አገልግሏል፡፡ ምንም እንኳን በኹሉም ላይ የተሾመ ቢኾንም ፊትን አይቶ አላዳላም፡፡
5.  ነቢዩ ዳንኤል ክብርና ጠላት ያልተለየው ሰው ነው፡፡ የእርሱ በቤተ መንግሥት መኖር ማንነታቸው የሚገልጥባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ የርሱ ንጽሕና የነርሱን ርኵሰት፣ የርሱ ጥበብ የነርሱን ማታለል፣ የርሱ እምነት የነርሱን ከንቱነት የሚገልጥባቸው ሰዎች በዳርዮስ ቤተ መንግሥት ስለነበሩ ዳንኤልን ለማጥፋት ምክንያት ይፈልጉ ነበር፡፡ ኾኖም አንዳች ስንኳ ስሕተት አላገኙበትም፡፡ ስለ ጸለየና ብቻ ግን ጠላቶቹ በተንኰል ወደ አንበሶች ጕድጓድ እንዲጣል አድርገዉታል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሰው ዳንኤል የማይታዩትን አናብስት (አጋንንት) በጸሎት አፋቸውን ስለዘጋው ግዙፋኑ አናብስት ሊበሉት አልተቻላቸውም፡፡ ይልቁንም የዳንኤልን እግር እየላሱ እጥፍጥፍ ብለው ተኝተው ተገኙ እንጂ /ዳን.፮/፡፡
6. ራዕይንና ሕልምን የመተርጐም ጸጋ ነበረው፡፡
7. የመሲሑን መምጣትና የዓለም መጨረሻ በግልጥ ተናግሯል፡፡
8.  ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን እንደሚገልጠው በፋርስ ግዛት ውስጥ በሱሳ ከተማ የሚገኘውን የታወቀ ሰገነት ንድፍ (Design) ከሠሩት ጠቢባን (Architects) መካከል አንዱ ነቢዩ ዳንኤል ነበር፡፡
ትንቢተ ዳንኤል
 የዚኹ መጽሐፍ ዋና ዓላማ እግዚአብሔርና ሕዝቡ በመጨረሻ እንደሚያሸንፉ መግለጥ ነው፡፡ ነቢዩ ስለ መሲሕ “የሰው እጅ ሳይነካው ከረዥም ተራራ የወረደ ድንጋይ መንግሥታትን ኹሉ ይፈጫል” በማለት ክርስቶስን በእብን፣ ድንግል ማርያምን በደብር መስሎ ተናግሯል /ዳን.፪፡፵፬-፵፭/፡፡ በመቀጠልም “በሌሊት ራዕይ አየኹ፡፡ እነሆ! የሰው ልጅ … የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር መጣ … ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ኹሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር፣ መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፡፡ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” በማለት የመሲሕን ሥጋዌና ዘለዓለማዊ መንግሥት ተናግሯል /ዳን.፮፡፲፫-፲፬/፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉን እንሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.  የዳንኤል ወደ ባቢሎን መማረክና መሾም /ምዕ.፩/፤
2.  ዳንኤል አንደኛውን የናቡከደነፆርን ሕልም መተርጐሙ /ምዕ.፪/፤
3.  ሠለስቱ ደቂቅ ወደ እሳት መጣላቸውና መዳናቸው /ምዕ.፫/፤
4.  ዳንኤል ኹለተኛውን የናቡከደነፆርን ሕልም መተርጐሙና የሕልሙ ፍፃሜ /ምዕ.፬/፤
5.  ዳንኤል በግድግዳ ላይ ስለ ብልጣሶር የተጻፈውን ጽሕፈት መተርጐሙና የቃሉ ፍጻሜ /ምዕ.፭/፤
6.  ዳንኤል ዳርዮስን እያገለገለ ሳለ የእርሱ በቤተ መንግሥት ውስጥ መኖር ማንነታቸውን የሚገልጥባቸው ሰዎች ወደ አንበሳ ጕድጓድ እንዳስጣሉትና እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንዳዳነው /ምዕ.፮/፤
7.  በምዕ.፪ የተገለጡት አራቱ መንግሥታት በአራት አራዊት መመሰላቸው፤ ግዛትና መንግሥትም የሰው ልጅ ለሚመስል (ለክርስቶስ) መሰጠቱ /ምዕ.፯/፤
8.  አውራ ፍየል (ግሪክ) አውራዉን በግ (ፋርስን) እንደሚያሸንፍ፤ የአውራው ፍየል ታላቅ ቀንድ (እስክንድር) እንደሚሰበር፤ አራት ቀንዶች (ከእስክንድር በኋላ የተነሡ አራቱ መንግሥታት) እንደሚወጡ፡፡ ከመካከላቸው ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደር ትንሽ ቀንድ በመቃብያን ዘመን ቤተ መቅደስን ያረከሰ አንጥያኮስ እንደሚጠፋ /ምዕ.፰/፤
9.  ዳንኤል ከምርኮ ስለ መመለስ ስለመጸለዩ፤ መሲሕ እስኪመጣ ድረስ ሰባ ሱባዔ እንደሚያልፍ ትንቢት መናገሩ /ምዕ.፱/፤
10.         ከታላቁ እስክንድር በኋላ በሶርያና በግብጽ መንግሥታት መካከል ስለሚደረገው ጦርነት፣ ስለ እግዚአብሔርም ሕዝብ መከራ ትንቢት መናገሩ /ምዕ.፲-፲፪/፡፡
ተረፈ ዳንኤል
ይኽ መጽሐፍ ዳንኤል ከጻፈው ተጨማሪ መጽሐፍ ነው፡፡ ይኽም በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ፮፡፬-፳፬ ያለውን ኃይለ ቃል በስፋትና በጥልቀት የሚተንትን መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ባለ አንድ ምዕራፍ ሲኾን ኹለት ዐበይት ታሪኮችን የያዘ ነው፡፡ እነርሱም፡-
1.  ፈሪሳውያንና ባቢሎናውያን ያመልኳቸው የነበሩ ጣዖታት ነቢዩ ዳንኤል እንዴት እንዳጠፋቸው የሚናገር /ቁ.፩-፳፰/፤
2.  ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ዳንኤልን ከአንበሶች ጕድጓድ መልአኩን ልኮ እንዴት እንዳዳነው በስፋት የሚያስረዳ ነው /ቁ.፳፱-፵፪/፡፡
መጽሐፈ ሶስና
ሶስና ማለት ከነቢዩ ዳንኤል ጋር በፋርስ በስደት ትኖር የነበረች ሴት ናት፡፡ ይኽቺ ሴት በዘመኑ እግዚአብሔርን እጅግ የምትፈራና የምታመልክ ሕጉንም የምታከብር ናት፡፡ በረበናተ አይሁድ የዝሙት ጥያቄ ሲቀርብላት ሕገ እግዚአብሔርን በማክበር አላደርገውም ብላለች፡፡ መምህራኑ ግን ይባስ ብለው በርሷ ላይ በሐሰት የዝሙት ወንጀል ከስሰው የሞት ፍርድ እንዲፈረድባት ያደረጓት ምስኪን ሴት ናት፡፡ የሞት ፍርዱም “በድንጋይ ተወግራ ትሙት” የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን በሃይማኖቷ ምክንያት የደረሰባትን መከራ እግዚአብሔር ሐዘኗንና ጸሎቷን ተመልክቶ ነቢዩ ዳንኤልን ልኮ አድኗታል፡፡ መጽሐፉ ባለ አንድ ምዕራፍ ሲኾን እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ ከሞት ፍርድ እንዴት እንዳዳናት ይገልጻል፡፡
ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ
 ይኽ መጽሐፍ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ፫ ላይ የተገለጠውን በዝርዝር የሚያትት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ባለ አንድ ምዕራፍ ሲኾን ሦስቱ ወጣቶች ማለትም አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል በሃይማኖታቸው ምክንያት ብዙ ችግር እንደደረሰባቸው፣ ለጣዖት እንዲሰግዱ እንደተገደዱ፣ እነርሱም አንሰግድም እንዳሉና፣ በእሳቱ ውስጥ በተጣሉ ጊዜ ለሃይማኖት አባት ለምሕረት አምላክ ለልዑል እግዚአብሄር ያቀረቡትን ጸሎትና ምስጋና የሚገልጽ ነው፡፡
የነቢዩ የመጨረሻ ዕረፍት
 መጋቢት ፳፫ የሚነበበው ስንክሳር እንደሚያስረዳው ነቢዩ ዳንኤል ያረፈው በ፭፻፴፬ ቅ.ል.ክ. ነው፡፡ ስንክሳሩ፡- “ዳንኤል የእስራኤል ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም እስከሚመለሱበት ጊዜ በባቢሎን ኖረ፡፡ እርሷም ፸ ዘመን ናት፡፡ ከዚኽም በኋላ በሰላም በፍቅር ዐረፈ” ይላል፡፡ ጠቅላላ ዕድሜው ፹፬ ነበር ማለት ነው፡፡ በስሙ የተሠራው ጽላት በሃገራችን በደባልነት በጣና ሐይቅ ይገኛል፡፡
ለሕይወት የሚቀርልን
  ተወዳጆች ሆይ! ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን ለማገልገል እንሸሻለን፡፡ በእጃችን ያለውን ጊዜ ሳንጠቀምበት ነገ ወይም ከነገወዲያ እናገለግላለን እንላለን፡፡ ሕፃን ኾኖ ማገልገል እንደማይቻል፤ ወጣት ኾኖ ክርስትያናዊ ኑሮን መመላለስ እንደሚከብድ፤ በባዕድ ሀገር ኾኖ እግዚአብሔርን ማምለክ የማይታሰብ አድርገን የምንገምት ብዙዎች ነን፡፡  ወዳጄ ሆይ! ላለማገልገልኽ ምክንያትን አትስጥ፡፡ ሕፃን ነኝ አትበል፤ ሠለስቱ ደቂቅም እንዳንተ ሕፃናት ነበሩና፡፡ ወጣት ነኝ አትበል፤ ዳንኤልም እንዳንተው ወጣት ነበርና፡፡ ያለኹበት ኹናቴ አኹን አይመችም አትበል፤ አራቱ ወጣቶች በባዕድ አገር ኾነው ለመጦም፣ በቀን ሦስት ጊዜ ለመጸለይ አልተመቸንም አላሉምና፡፡ የያዝኩት ኃላፊነት ለማገልገል ጊዜ አይሰጠኝም አትበል፤ አራቱም ወጣቶች በሐላፊነት ቦታ ተቀምጠው ሕዝባቸውን እያገለገሉ እግዚአብሔርን ከማገልገል አልተቈጠቡምና፡፡ እንኪያስ ጠበቢ እንዳለው “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪኽን አስብ፤” /መክ.፲፪፡፩/፡፡ ይኽን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን፡፡
ዋቢ ድርሳናት፡-
Ø የትንቢተ ዳንኤል አንድምታ መቅድም፤
Ø የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤
Ø ስንክሳር፤
Ø ትንቢተ ዳንኤል ከዘመነ ባቢሎን እስከ ዓለም ፍጻሜ፤ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት የተዘጋጀ፤
Ø መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ፤ በመምህር ቸርነት አበበ የተዘጋጀ፤

Ø The Book of Daniel By Fr. Tadros Malaty፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount