Wednesday, December 4, 2013

ነቢዩ ኢሳይያስ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ኅዳር ፳፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ኢሳይያስ የሚለው ስም በአይሁድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ እጅግ የተለመደ ስም ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንኳ ብያንስ ወደ ፯ የሚኾኑ ሰዎች በዚኽ ስም ተጠርተዋል፡፡
 “ኢሳይያስ፣ የሻያ” ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ፣ ኢያሱ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደኾነ መድኃኒት መባሉ ግን እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ ተልእኮውን የሚገልጥ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሊመጣ ያለው መሲሕ ማለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ ቀስ በቀስ አድጎ፣ የደቂቀ አዳምን ሕማም ተሸክሞ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአስደናቂ መጐብኘትን ጐብኝቶ እንደሚያድናቸው ስለሚናገር “ኢሳይያስ - መድኃኒት” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡

  ተመሳሳይ ስም ካላቸው ከሌሎች ሰዎች ለመለየትም “የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ” ተብሎ ተጠርቷል /ኢሳ.፩፡፩/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይኽ አሞጽ ነቢዩ እንዳልኾኑ ይስማማሉ፡፡ እናንቱም የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው ሶፊያ ትባላለች፡፡
  ኢሳይያስ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፡፡ ኢሳይያስ ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት ነበር፡፡ ሚስቱም ነቢይት እንደነበረች መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል /ኢሳ.፰፡፫/፡፡ መተርጕማን እንደሚናገሩት፡- “የኢሳይያስ ሚስት ነቢይት መባሏ የባለቤቷን መንፈሳዊ ሕይወት፣ ተጋድሎውን ትጋራ ስለነበርና በተልእኮው ኹሉ ትረዳው ስለነበረ እንጂ ራዕይን የማየት ትንቢትንም የመናገር ጸጋ ተስጥቷት ስለነበረ አይደለም” ይላሉ፡፡ ኢሳይያስ ከባለቤቱ ኹለት ልጆችን ያፈራ ሲኾን የልጆቹ ስያሜም ትንቢት አዘል ትርጓሜን የቋጠረ ነው፡፡ ታላቁ ልጅ “ያሱብ” ይባላል፡፡ “ያሱብ” ማለትም “ቅሬታዎቹ ይመለሳሉ” ማለት ነው /ኢሳ.፯፡፫/፡፡ ታናሹ ልጅ ደግሞ “ማኄር ሻላል ሐሽ ባዥ” ይባላል፡፡ ይኸውም “ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛም ቸኰለ” ማለት ነው /ኢሳ.፰፡፫/፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በቤተ ሰቡ በጣም ደስተኛ ነበር፡፡ ይመካባቸውም ነበር፡፡ “እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን” ማለቱም ይኽንን ያስረዳል /ኢሳ.፰፡፲፰/፡፡
 ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር በአካዝና በሕዝያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥት አማካሪ ነበር፡፡ በራሱ መጽሐፍ እንደነገረንም በዘመኑ የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ ይባላሉ /ኢሳ.፩፡፩/፡፡ የነቢይነትን ሥራ የዠመረውም ወዳጁ ዖዝያን በሞተ በዓመቱ ነው፡፡ ይኸውም በ፯፻፵ ዓ.ዓ. አከባቢ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ዖዝያንን ገስጽ” ሲባል ወዳጁ ስለኾነ ይሉኝታ ይዞት እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ከአፉ ላይ ለምፅ ወጣበት፡፡ ጌታም ተገልጦ፡- “የምትወደውና የምታከብረው ዖዝያን ሞተ፤ መንግሥቱም አለፈ፡፡ ሞት፣ ኅልፈት፣ በመንግሥቴም ሽረት የሌለብኝ እኔ አምላክኽ ብቻ ነኝ” አለው፡፡ ኢሳይያስ ይኽን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር፡- “ወደዚኽ ሕዝብ ማንን ልላክ?” አለው፡፡ ኢሳይያስም፡- “እኔ እሔድ ነበር፤ ግን በአፌ ለምፅ አለብኝ” ሲል መልአኩ በጉጠት አፉን ቀባውና ለምፁ ድኖለት ትንቢት ተናግሯል /ኢሳ.፮/፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ የነበረበት ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ግብረ ገብነታዊና ፖለቲካዊ ኹኔታ
  ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር የቤተ መንግሥትም አማካሪ ኾኖ እንደማገልገሉ መጠን የነገሥታቱን ብዕል፣ ለመጓጓዣ የሚገለገሉባቸው ሠረገላዎች፣ ለማዕድ የሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች፣ ሕዝቡን ንቀው የሚያዩበት ትዕቢታቸው፣ ከሚስቶቻቸው ጋር የሚያሳልፉት የቅንጦት ኑሮአቸውን ይመለከት ነበር፡፡ በየዕለቱ በሚዘጋጀው የእራት ግብዣ ልዑላኑ በከፍተኛ የወታደር፣ የሃይማኖትና የሲቪል አመራሮች ታጅበው የሚጠጡት ወይን፣ በመጨረሻም ሰክረው የሚያሳዩት አሳፋሪ ድርጊትን ያይ ነበር፡፡ ይኽ በእንዲኽ እንዳለ እነዚኽ ልዑላን ወደ ቤተ መቅደስ መጥተው የሚያቀርቡት የመሥዋዕት ብዛት፣ ከስግብግቦቹ የሃይማኖት መሪዎች የሚቀርብላቸው ውዳሴ ከንቱ፣ ከቤተ መቅደሱ መልስ በኋላ ደግሞ የሚያከናውኑትን አሕዛባዊ ግብር በአጽንዖት ይመለከት ነበር፡፡ ነቢዩ ሲመለከት የነበረው ይኽን የቤተ መንግሥቱና የቤተ ክህነቱ የቅንጦት ኑሮን ብቻ አይደለም፡፡ የመበለቶች፣ የወላጅ አልባ ሕፃናት፣ የድኾች፣ የችግረኞች ጩኸትም በነቢዩ ጆሮ ያስተጋባ ነበር፤ ወደ መንበረ ጸባዖትም ሲወጣ ያስተውል ነበር፡፡
 ነቢዩ ራሱ “ራስ ኹሉ (የቤተ መንግሥቱ አመራር) ለሕመም ልብም ኹሉ (የቤተ ክህነቱ አመራር) ለድካም ኾኗል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ (ከተራው ሕዝብ አንሥቶ እስከ አመራሩ ድረስ) ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም” ብሎ እንደገለጠው /ኢሳ.፩፡፭-፮/ የይሁዳ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ከነ ተራው ሕዝቡ ተበላሽቶ ነበር፡፡ ኹሉም በእግዚአብሔር ታምኖ ሳይኾን በሰው ክንድ ተደግፎ ይሰባሰባል፤ ግዑዛን እንስሳት እንኳ የጌታቸውን ጋጣ ሲያውቁ ሰዎች ግን ፈጣሪያቸውን ረስተዋል፡፡ አለቆች በግብዝነት፣ ጉቦን በመውደድ፣ ለድኻ አደጉ ባለመፍረድ፣ የመበለቲቱን ሙግት ባለመስማት ይታወቃሉ /ኢሳ.፩፡፳፫/፡፡ አንባቢ ሆይ! አኹን ያለውን የቤተ ክህነታችንና የቤተ መንግሥት ኹናቴ ከዚኹ ጋር ያገናዝቡ!!!
 በነቢዩ ኢሳይያስ ጊዜ የነበረውን ፖለቲካዊ ትኩሳት ስንመለከትም፥ ነቢዩ አገልግሎቱን በዠመረበት ወራት በኹለት ኃያላን መንግሥታት ማለትም በግብጽና በአሦር መካከል ውጥረት ነግሦ ነበር፡፡ ወደ አገልግሎቱ ማብቂያ አከባቢ ደግሞ በአሦርና በባቢሎን መካከል የነበረው ፍጥጫ ጣራ የደረሰበት ወራት ነበር፡፡ የእነዚኽ ኃያላን መንግሥታት መፈክር፡- “Power is the truth - እውነት ማለት ሥልጣን ነው” የሚል ነበር፡፡ በእነዚኽ ኃያላን መንግሥታት መካከል የነበረው ፍጥጫ በእስራኤልና በይሁዳን እንዴት ጫና እንዳሳደረ ለመረዳትም ፪ኛ ነገሥት ከምዕራፍ ፲፭ እስከ ፲፯ ያለውን ክፍል ማንበብ በቂ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለማየት ያኽልም፡-
Ø የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ምናሔ የአሦር ንጉሥ ለነበረው ለፎሐ መንግሥቱን ያጸናለት ዘንድ አንድ ሺሕ ሰቅል ብር ሰጥቶታል /፪ኛ ነገ.፲፭፡፲፱-፳/፡፡
Ø የዖዝያን (ይሁዳ ንጉሥ) ንግሥና ማብቂያ አከባቢ ቴልጌልቴልፌልሶር የተባለ የአሦር ንጉሥ ፋቁሔ የተባለው የእስራኤል ንጉሥ ነግሦ ሳለ ሃገሪቱን ወርሮ ነበር /፪ኛ ነገ.፲፭፡፳፱/፡፡ በይሁዳ ላይ ነግሦ በነበረው በአካዝ ላይም ዘመቱበት፡፡ ኢሳይያስም የራሱን ልጆች ምልክት እያደረገ አካዝ በእግዚአብሔር እንዲታመን እንጂ እንዳይደነግጥ መከረው፡፡ አካዝ ግን ጠላቶቹን እንዲቋቋምለት ለማድረግ ለአሦር ንጉሥ ግብር ይልክለት ነበር /ኢሳ.፯፡፩-፲፯፣ ፪ኛ ዜና ፳፰፡፲፮-፳፩/፡፡
Ø ፋቁሔም በኋላ በሆሴዕ ተገደለ፤ ሆሴዕም ነገሠ፡፡ በኋላ ላይ ግን የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር በሆሴዕ ላይ ዘመተ፡፡ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ግብርም አመጣለት፡፡ ነገር ግን ስልምናሶር ሆሴዕን ስላላመነው ወደ ወኅኒ አስገባው፡፡ ሰማርያንም (ሰሜናዊው ክፍል ይኸውም እስራኤል ያልነውን) ሦስት ዓመት ከበባት፤ ሕዝቡን ደግሞ ወደ አሦር አፈለሳቸው /፪ኛ ነገ.፲፯፡፫-፮/፡፡
Ø እስራኤልና ይሁዳ በአምላካቸው ከመታመን ይልቅ እግዚአብሔርን ወደሚያስቈጣ የፖለቲካ ስሌት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ሰማርያ (እስራኤል) ይሁዳን ለመውጋት ከሶርያ ጋር ስትወዳጅ፣ ይሁዳ ደግሞ እስራኤልን ለመውጋት ከአሦር ጋር ተወዳጅታ ነበር፡፡ እንደዉም አካዝ፡- “እኔ ባሪያህና ልጅህ ነኝ፤ መጥተህ ከተነሡብን ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር መልእክተኞችን ልኮ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል /፪ኛ ነገ.፲፮፡፯/፡፡ ከላይ እንደጠቀስነውም እንደ ማማለጃ ይኾን ዘንድ አካዝ በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ወስዶ ወደ አሦር ንጉሥ ገጸ በረከት አድርጎ ሰደዶለት ነበር፡፡ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ግን መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም /፪ኛ ዜና ፳፰፡፳-፳፩/።
  ነቢዩ ኢሳይያስ እንግዲኽ ይኖር የነበረው በእነደዚኽ ዓይነት ውስብስብ ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ በአንድ በኩል የወገኖቹ ፍቅር ልቡን ያቃጥሏል፤ የእስራኤልና የይሁዳ አለመስማማት ይባስ ብሎም እርስ በርስ ለመተላለቅ ከውጭ ኃይሎች ጋር መወዳጀታቸው ውስጡን ያቆስሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይሁዳ የእኅቷ የእስራኤልን ጥፋት እየተመለከተች ምንም አለመማሯ ይልቁንም ደግሞ ወደ ጥፋት ሸለቆ መንጐዷ እጅጉን አሳዘነው፡፡ አኹን ያለው የሃገራችን ኹናቴ አንባብያን ያገናዝቡት!!
 ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ጠቢብ ፖለቲከኛ በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተመራ በጊዜው የነበረውን ፖለቲካዊ ትኩሳት ከምንጩ የሚያውቅ ነበር፡፡ የመንግሥታቱን አካሔድ አይቶም የደማስቆና የሰማርያ ውድቀት እንዲኹም የአሦር መንግሥት መካከለኛ ምሥራቁን እንደሚቈጣጠረው ተንብዮአል /ኢሳ.፯/፡፡ ከዚያ በላይ አለፍ ብሎም የባቢሎን አደገኛነት በይሁዳ ላይም የሚመጣውን መዘዝ ተናግሯል /ኢሳ.፴፱/፡፡ ጨምሮም ኹሉም ወገኖቹ (እስራኤልም ይሁዳም) ከምርኮ እንደሚመለሱ ተንብዮአል፡፡
 ነቢዩ ኢሳይያስ የአሦር መንግሥት በኋላም የባቢሎን መንግሥት በእስራኤልና በይሁዳ ማየል እግዚአብሔር ለቁንጥጫ የተጠቀመበት ጥበብ እንደነበር ተረድቷል፡፡ የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌም በአሦር ሰዎች ትወረራለች ብለው አልመውም አስበውም አያውቁም፤ ነቢዩ ግን ይኽ ኹሉ እንደሚኾን በትንቢት መነጽር አስረግጦ ነገራቸው፡፡ ይኽ ኹሉ የመኾኑ ምስጢርም ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና ከውጭ ኃይላት ይልቅ በእርሱ እንዲታመኑ ለማድረግ እንደኾነ ነግሯቸዋል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግራቸው ከንስሐ ውጪ ሌላ መፍትሔ እንደሌለው ይነግራቸው ነበር፡፡
 ነቢዩ እውነትን የማይሸፋፍን፣ ለማንም የማያዳላ መምህር ወመገስጽ ነበር፡፡ ምንም ሳይፈራና ሳያፍር አካዝን፡- “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፤” ብሎታል /ኢሳ.፯፡፲፫/፡፡ ሕዝቡን “በደል የተሞላበት ሕዝብ” /ኢሳ.፩፡፬/፤ ልዑላኑን “የሰዶም አለቆች” /ኢሳ.፩፡፲/፤ በዚያ ሰዓት የነበሩት ጠላቶች (የሶርያው ንጉሥ ረኣሶንና የእስራኤሉ ንጉሥ ፋቁሔ) “ኹለት የእንጨት ጠለሸቶች” /ኢሳ.፯፡፬/ ብሎ ገስጾአቸዋል፡፡ ልቡ ደግሞ ስለ ሞዓብ ይጮኻል /ኢሳ.፲፭፡፭/፤ በባቢሎን መንግሥት ምክንያት ስለሚደርሰው ውድቀትም፡- “ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፤ መራራ ልቅሶ አለቅሳለኹ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ” እያለ መራራ ለቅሶን ያለቅሳል /ኢሳ.፳፪፡፬/፡፡
የነቢዩ ኢሳይያስ ልዩ ስብእናዎች
1.     ታላቅ ነቢይ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ካደረጋቸው ግብሮችና ከጻፈው መጽሐፍ ይዘት አንጻር ታላቅ ነቢይ ልንለው እንችላለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በጽናቱ ነቢዩ ዳንኤልን ይመስላል፤ በጨዋነቱ ነቢዩ ኤርምያስን ይመስላል፤ ጸዋትወ መከራን በመቀበሉ ነቢዩ ሆሴዕን ይመስላል፤ መምህር ወመገስጽ በመኾኑ ደግሞ ነቢዩ አሞጽን ይመስላል፡፡ ከኹሉም በተለየ ግን ምንም እንኳን ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንዲኽ ቢገስጻቸውም የድኅነት ተስፋም ይሰጣቸው ነበር፤ ተስፋውም ለእነርሱ ብቻ ሳይኾን ለደቂቀ አዳም በሙሉ የሚኾን ተስፋ ድኅነትን ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡
2.    እግዚአብሔር በሦስት መንገድ ኢሳይያስን አናግሮታል፡፡ በሚያስደንቅ ግርማ /ኢሳ.፮/፣ በጽኑ እጅ /ኢሳ.፰፡፲፩/፣ እንዲኹም በአባታዊ ንግግር /ኢሳ.፳፡፪/ አናግሮታል፡፡ እርሱም ይኽ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መልእክት በሦስት መንገድ አስተላልፎታል፡፡ በአደባባይ በሚደረግ ግልጽ ትምህርት፣ ለምልክትና ለተአምራት ሊኾን ራቁቱንና ባዶ እግሩን በመሔድ፣ እንዲኹም በጽሕፈት፡፡  
3.    ከቤተ ክህነቱ እስከ ቤተ መንግሥቱ ድረስ ኹሉም ሕይወቱ በተበላሸና አምልኮው ኹሉ ግብዝ በኾነበት ሰዓት ነቢዩ ኢሳይያስ ግን ግሩም የኾነውን መለኮታዊ ምስጢር ይካፈል ነበር፡፡ በዚኽም እግዚአብሔር አፍቃሬ ኃጥአን እንደኾነ፣ ድካማቸውን እንደሚረዳ፣ ድኅነታቸውንም አብዝቶ እንደሚሻ ይሰብክ ነበር፡፡


ትንቢተ ኢሳይያስ
  ትንቢተ ኢሳይያስ በዕብራይስጥ ትርጉሙ ሲታይ ከምዕራፍ ፴፮-፴፱ በስተቀር የግጥም (የቅኔ) መልክ ያለውና በአጻጻፉ እጅግ መሳጭ የኾነ መጽሐፍ ነው፡፡ በብዙ ሊቃውንት ዘንድም “የኢሳይያስ ወንጌል” እየተባለ ይጠራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ደግሞ “ደረቅ ሐዲስ” ይሉታል፡፡ ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና መውለዷን፣ ጌታችንም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን ከፅንስ ዠምሮ እስከ ዳግም ምፅአቱ ድረስ ምስጢረ ሥጋዌን የሚናገር ስለኾነ ነው፡፡
 ትንቢተ ኢሳይያስን የሚያነብ ሰው ሐዲስ ኪዳንን የሚያነብ ያኽል ይሰሟል፡፡ ጸሐፊውም (ኢሳይያስም) በዘመነ ሐዲስ የነበረና ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር ስር ቁጭ ብሎ የተማረ ደቀ መዝሙር ይመስሏል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና እንደሚወለድ /ኢሳ.፯፡፲፬/፣ አምላክነቱን /ኢሳ.፱፡፮/፣ የነገደ እሴይ ስር መኾኑ /ኢሳ.፲፩፡፩/፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያርፍበት /ኢሳ.፲፩፡፪/፣ ለአሕዛብ ፍርድን እንደሚያመጣ /ኢሳ.፵፪፡፩/፣ ትሕትናው /ኢሳ.፵፪፡፪/፣ ለኹሉም ተስፋ ድኅነትን እንደሚያመጣ /ኢሳ.፵፪፡፫/፣ ወደ ግብጽ እንደሚሰደድ /ኢሳ.፲፱/፣ መከራውና ስቅለቱ /ኢሳ.፶፫/፣ በትንሣኤው ለኹሉም ተስፋ ትንሣኤን እንደሚሰጥ /ኢሳ.፴፭፡፰-፲/፣ … አምልቶና አስፍቶ ተናግሯል፡፡ ጀሮም የተባለ የጥንቲቱ የላቲን ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ አባት ይኽን በተመለከተ፡- “ትንቢተ ኢሳይያስን ሳነብ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት የሚተርክ ወንጌላዊን አገኛለኹ፤ ከዚኹ ጐን ለጐንም ስለ መፃእያት የሚናገር ነቢይን አገኛለኹ” ማለቱም ይኽን የሚያስረዳ ነው፡፡ አውግሥጢኖስ የተባለው ቅዱስ አባት ወደ ክርስትና ከተመለሰ በኋላ ቅዱስ አምብሮስን አዘውትሮ የሚያነበው መጽሐፍ ምን እንደኾነ ሲጠይቀውም “ኢሳይያስን” ብሎ መመለሱም ትንቢተ ኢሳይያስ ምን ያኽል ግልጽና የተብራራ መጽሐፍ መኾኑን ፍንተው አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
 አንዳንድ የስነ መለኮት ምሁራን ትንቢተ ኢሳይያስን ከይዘቱ አንጻር በአጭር አገላለጽ ሲገልጹት “በአራት ርእሰ አንቀጾች መጠቃለል የሚችል ነው” ይላሉ፡፡ እነርሱም እግዚአብሔር፣ ሰው፣ ዓለምና ድኅነት በሚሉ ናቸው፡፡ ይኽን ሐሳብ በአንድ ዓረፍተ ነገር እንግለጸው ቢባል እንደሚከተለው ይኾናል፡- “የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ኃጢአትን ይጸየፋል፤ ይኽ ኃጢአትም የሰውን ልጅ በሙሉ ያደከመና መላውን ዓለም ከፍርድ በታች እንዲኾኑ ያደረገ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ይኽን ፍርድ በራሱ ተሸክሞ ይቀድሰንና ያከብረን ዘንድ ፍጹም ሰው ኾነ፡፡”
ትንቢተ ኢሳይያስን በሦስት ክፍል መክፈል እንችላለን፡፡
1.     የመዠመሪያው ክፍል (ምዕራፍ ፩-፴፭) በኢሳይያስ ዘመን በኾኑት ድርጊቶች ምክንያት የተጻፈ ነው፡፡ ይኽ ክፍል እግዚአብሔር የሰው ልጆችን (ሕዝብንም አሕዛብንም) በሙሉ እንደተቈጣ፤ የሰው ልጅ በሙሉ ጽቅድ ስለጐደለውም መለኮታዊ ቅድስና እንደሚያስፈልገው የሚገልጽ ነው፡፡
2.    ኹለተኛው ክፍል (ምዕራፍ ፴፮-፴፱) ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ በኾነው በባቢሎን ምርኮ ምክንያት ተጽፏል፡፡ ይኽ ክፍል ቅዱስ እግዚአብሔር በጠላቶቹ (ዲያብሎስና ሠራዊቱ) ድል እንደሚያደርጋቸው የሚናገር ነው፡፡ ይኽ ክፍል በዳዊት ልጅ፣ በሚመተውና በሚነሣው (በሞተውና በተነሣው) መሲሕ እኛ የምንቀዳጀውን ድል አብሮ ይናገራል፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ትሞታለኽ ተብሎ እንደገና ፲፭ ዓመት በዕድሜው ላይ መጨመሩ ይኽን ምስጢር የሚያስረዳ ነው፡፡
3.    ሦስተኛው ክፍል (ምዕራፍ ፵-፷፮) ደግሞ የጽዮንን ዘለዓለማዊ ክብርን ያሳያል፡፡ በዚኽም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘው ድኅነት እንደምን ለሰው ልጆች ዕረፍትን እንደሚሰጥ የሚናገር ነው፡፡  

ነቢዩ ኢሳይያስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤት ክርስቲያን
  ነቢዩ ኢሳይያስንና ኢትዮጵያውያን ነጣጥሎ ማየት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ በሃገራቸው በሌላ ሃገር ሲሔዱም ከልብሳቸውና ከስንቃቸው ጋር ይዘዉት እየሔዱ ያነቡት እንደነበር ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ምስክራችን ነው /ሐዋ.፰፡፳፮-፵/፡፡ በዘወትር ጸሎታችን ውስጥ፡- “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ” የምንለውም ከትንቢተ ኢሳይያስ በቀጥታ የተወሰደ ነው /ኢሳ.፮/፡፡ በየቀኑ ለእግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን በሚቀርበው የቅዳሴ፣ የሰዓታት፣ የማኅሌት ምስጋናና ጸሎት ትንቢተ ኢሳይያስን ሳያነሣ አያልፍም፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴአችን፡- “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ መዠመሩ፤ በፍሬ ቅዳሴአችን ዲያቆኑ፡- “አውሥኡ” ሲል “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ሳይል የሚያልፍ ሊቅ የለም፡፡ ሰዓታቱ በብዛት “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ዘበተዋሕዶ ይሤለስ” እያለ ይፈጽማል፡፡ የማኅሌቱ ምስጋና መዠመሪያም ካህኑ ከማዘከሩ በፊት “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ብሎ አመስግኖ አዘክሮ ይዠምራል፡፡ ኪዳንም “ቅዱስ እግዚአብሔር፥ ቅዱስ ኃያል፥ ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት” ብሎ ይዠምራል፡፡ በአጠቃላይ ትንቢተ ኢሳይያስና ኢትዮጵያውያን የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታ ናቸው፡፡   

የነቢዩ የመጨረሻ ዕረፍቱ
  ነቢዩ ኢሳይያስ በዚኽ አገልግሎቱ፥ የአይሁድ ትውፊት እንደሚያስረዳው እስከ ፮፻፹፰ ዓ.ዓ. ቀጥሏል፡፡ ይኽም ማለት በነቢይነት ከ፶፪ ዓመት በላይ አገልግሏል ማለት ነው፡፡ መስከረም ፮ ቀን የሚነበበው ስንክሳርም “ትንቢት እየተናገረ የኖረበት ዘመን ፸ ዘመን ከዚያም በላይ ይኾናል” ይላል፡፡ 
 ስንክሳሩ እንደሚነግረን ነቢዩ ኢሳይያስ የሞተው በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሡ ምናሴ ላይ ትንቢት ስለተናገረ ነው፡፡ ንጉሡ ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ስለገሠፀው ተቈጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሰነጠቀው፡፡ ምስክርነቱንም በዚኽ ፈጸመ፡፡ ሊቃውንት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በመጋዝ ተሰነጠቁ” ያለው ነቢዩ ኢሳይያስን ነው ይላሉ /ዕብ.፲፩፡፴፯/፡፡ 
  ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ እኛንም በጸሎቱ ይማረን፤ በረከቱም ከኹላችን ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን!!!
ዋቢ ድርሳናት፡-
©     የትንቢተ ኢሳይያስ አንድምታ መቅድም፣ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የተዘጋጀ፤
©     የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣
©     ስንክሳር፣
©     A Patristic Commentary on The Book of Isaiah by Fr. Tadros Y. Malaty፡፡    


No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount