Pages

Thursday, January 2, 2014

ነቢዩ ዕንባቆም

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፲፰ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ዕንባቆም ማለት ማቀፍ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን በጸሎት አቅፎታልና እንዲኽ ተብሏል፡፡ ሊቃውንት እንደሚመሰክሩት ነቢዩ ዕንባቆም ያላ ገባ ድንግል ሲኾን የቤተ መቅደስ ዘማሪ ነበር /ዕን.፫፡፩/፡፡
 ከመጽሐፉ መረዳት እንደምንችለው ነቢዩ ራዕዩን ሲያይ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ይካኼድ ነበር /፪፡፳/፤ የመዝሙርና የምስጋና አገልግሎትም ይካኼድ ነበር /፫/፡፡ ከለዳውያን ዓለሙን ኹሉ እንደሚቈጣጠሩና ምርኮኞችን እንደ አሸዋ እንደሚሰበስቡም ተናግሯል /፩፡፮-፱/፡፡ ከለዳውያን ማለት ደግሞ ከባቢሎን በስተደቡብ የነበሩ ሕዝቦች ሲኾኑ ዋና ከተማቸው አብርሃም ይኖርበት የነበረ ዑር ነው /ዘፍ.፲፩፡፴፩/፡፡ እነዚኽ ከለዳውያን ከባቢሎን መንግሥት ጋር ተባብረው የአሦርን መንግሥት ድል ያደረጉ ናቸው፡፡ እነ ናቡከደነፆርም ከለዳውያን ናቸው፡፡ ከለዳውያን ማለት ትርጉሙ “የበአል (የጣዖት) ካህናት” ማለት ሲኾን በጥንቁልና ሥራቸው የታወቁ ናቸው፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ዕንባቆም የአሦር መንግሥት በባቢሎን መንግሥት ከመፍረሱ የነበረ ነቢይ መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ ብዙዎችም በ፮፻ ቅ.ል.ክ. ገደማ እንደነበር ይስማማሉ፡፡ ዘመኑም የኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት ነው፡፡
  ጥቅምት ፮ ላይ የሚነበበው ስንክሳር እንደሚነግረንም ነቢዩ ዳንኤል በሐሰት ተከስሶ ወደ አንበሳ ጕድጓድ ሲጣል የሚበላ ነገር አልሰጡትም ነበር፤ አንበሶች እንኳ ባይበሉት በረሃብ እንዲሞት በማሰብ ማለት ነው፡፡ በዚኹ ሰዓት ግን ለዳንኤል የሚበላ ነገርን ያመጣለት በኢየሩሳሌም ከትሩፋን ጋር ቀርቶ የነበረው ነቢዩ ዕንባቆም ነው፡፡ የወሰደውም የእግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡ ኼዶም በተዘጋው ጕድጓድ ገብቶ ለነቢዩ ዳንኤል ምግቡን ሰጠው፤ አጽናናውም፡፡ መልአኩም ዕንባቆምን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶታል፡፡
ትንቢተ ዕንባቆም
 ነቢዩ ዕንባቆም የይሁዳን ሕዝብ ክፋት እየተመለከተ፣ ባለጸጐች ድኾችን ሲበድሏቸው እያየ ያለቅስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ክፋትን እየተመለከተ በቅንነቱ የማይፈርድ መስሎትም ደጋግሞ ጠይቋል፡፡ ከዚኽ በኋላ ግን ከዚኽ በደላቸው የተነሣ እግዚአብሔር በከለዳውያን እጅ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ገለጠለት፡፡ ዕንባቆም እግዚአብሔር ከዚኽ ፍርዱ እንዲመለስ አጥብቆ ጸለየ፡፡ ይኽም ያደረገው ለምን እንደኾነ ስላልገበው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በጥበቡ ለምን አይሁድን በከለዳውያን (በባቢሎናውያን) እጅ አሳልፎ እንደሚሰጥ፥ ግን ደግሞ መልሶ እንደሚያድናቸው ገለጠለት፡፡ በመጨረሻም ይኸው ሲገባው እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግኖታል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ እንደሚከተለው ከፍለን ማየት እንችላለን፡-
1.     ጥያቄ፡- እግዚአብሔር በግፈኞች ላይ ለምን አይፈርድም? /፩፡፩-፬/፤
2.    መልስ፡- ከለዳውያን እልክባቸዋለኹ /፩፡፭-፲፩/፤
3.    ጥያቄ፡- እንዴት! ከእኛ የባሱ አይደሉምን? /፩፡፲፪-፲፯/፤
4.    መልስ፡- በተራቸው ክፉዎች ኹሉ ይፈረድባቸዋል፤ ጻድቅ (የእግዚአብሔር ሰው) ግን በእምነቱ ይድናል /፪/፤
5.    የዕንባቆም የጸሎት መዝሙር /፫/፡፡
ከዚኽ ምን እንማራለን?
©     እግዚአብሔር ምን ያኽል የፍቅር አምላክ እንደኾነና እንደምን ያለ አባት እንደኾነ እንማራለን፡፡ ምክንያቱም ዕንባቆምን ሲያናግረውና ሲመልስለት የነበረው አንድ ሕፃን ልጅ የማያውቀውን ነገር ለአባቱ እንደሚጠይቀውና አባቱም እያባበለ እንደሚመልስለት ዓይነት ነው፡፡
©     ነቢዩ ዕንባቆም ሲያለቅስ እግዚአብሔር ለጥያቄው መልስ ሰጥቶታል፡፡ ይኸውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና” እንዳለው ነው /ማቴ.፭፡፬/፡፡
©      ነቢዩ ዕንባቆም፥ እግዚአብሔር ለምን በከለዳውያን (በባቢሎናውያን) እጅ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ሲነግረው በጸሎት ዘምሯል፡፡ ዛሬም በኃጢአታችን ምክንያት ስለደረሰብን ኹሉ ብናለቅስና ብናዝን ከደረሰብን መከራ ዠርባ ያለችውን ድንቅ የእግዚአብሔርን እጅ እንመለከታለን፤ መጽናናትንም እናገኛለን፡፡ ከነቢዩ ዕንባቆም ጋር ኾነንም፡- “የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለኹ፡፡ ምንም እንኳን በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ (ፍሬ) ባይገኝ፣ የወይራ (የዘይት) ሥራ ቢጐድል፣ ምድርም የዘሩባትን ባታበቅል የተከሉባትን ባታጸድቅ፣ በጐች ከበረቱ ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር (አምኜ) ደስ ይለኛል፡፡ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለኹ፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፡፡ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስኼደኛል” እያልን እንዘምራለን /ዕን. ፫፡፲፮-፲፱/፡፡  
ከመከራችን ዠርባ ያለችውን የእግዚአብሔር ጣት እንድንመለከትና በዚያም ደስ ብሎን በልዕልና በቅድስና እንድንኼድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን!!!!!!!!!!!!!

No comments:

Post a Comment