Pages

Thursday, January 2, 2014

ነቢዩ ሶፎንያስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፳፩ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ሶፎንያስ ማለት “እግዚአብሔር ይሰውራል፣ እግዚአብሔር ይጠብቃል፣ እግዚአብሔር ይከልላል” ማለት ነው፡፡ “እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ኹሉ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቊጣ ቀን ትሰወሩ ይኾናል” እንዲል /፪፡፫/፡፡

 ነቢዩ ሶፎንያስ የነቢይነቱን አገልግሎት የዠመረው በይሁዳ የአሞጽ ልጅ ኢዮስያስ (ከ፮፻፵-፮፻፱ ከክ.ል.በ.) መንገሥ በዠመረ ጊዜ ነው /፩፡፩/፡፡ በዘመንም ከነቢዩ ኤርምያስ ጋር ይገናኛል፡፡ ንጉሥ ኢዮስያስ የእግዚአብሔርን ቤት ሲያሳድስ ታላቅ ሚና ተጫውቷል፤ ነቢዩ ሶፎንያስ፡፡
በነቢዩ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
 ትንቢተ ሶፎንያስን ማንበብ ስንዠመር ነቢዩ ሶፎንያስ የንጉሥ ሕዝቅያስ ዘር እንደኾነ እናነባለን፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ደግሞ ሦስት ልጆች ነበሩት፡፡ ሦስቱም በተራ በተራ ኾነው ወደ ንግሥናው ዙፋን ወጥተዋል /፪ኛ ነገ. ፳-፳፩/፡፡ ኹለቱ ክፉዎችና ጣዖታውያን ነበሩ፡፡ ኹለቱም በነገሡበት ወራት ጣዖተ አምልኮ፣ ክፋት፣ ብልሹነትና ማኅበራዊ ቀውስ በእያንዳንዱ እስራኤላዊ ሰፍኖ ነበር፡፡ ባለጠጋው ድኻውን ይበድል ነበር፡፡
 ከእነርሱ በኋላ ወደ ንግሥና የመጣው ወንድማቸው ማለትም ኢዮስያስ ግን መልካም ንጉሥ ነበር፡፡ መልካም ነው እንዲባል ካደረጉት ነገሮች አንዱም ገና በ፲፮ ዓመቱ ወደ ዙፋን ሲወጣ ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የእግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ብዙ ይደክም ስለ ነበር ነው /፪ኛ ዜና ፴፬-፴፭/፡፡ 
 በዚኽ አምልኮተ ጣዖትን የማስወገድ ሥራና ቤተ እግዚአብሔርን የማሳደስ ወቅት ሕዝቡ ከአንድ በላይ በኾኑ ቡድኖች ተከፋፍሎ ነበር፡፡  ምንም እንኳን አብዛኛው ሕዝብ ከንጉሡ ጋር ቢተባበርም መመለሱ ግን አፍኣዊ ነበር እንጂ ውሳጣዊ (ከልብ) አልነበረም፡፡ በቤተ መቅደስ ሔደው መሥዋዕት ስላቀረቡ ብቻ እግዚአብሔርን ከልባቸው ያመለኩት ይመስላቸው ነበር፡፡ ጥቂት ቅሪቶች ግን መመለሳቸው ከልብ ነበር፤ ራሳቸውን በቃለ እግዚአብሔር ይመዝኑ ነበር፤ የእግዚአብሔር ክብርንም ይሹ ነበር፡፡
ትንቢተ ሶፎንያስ
 የትንቢተ ሶፎንያስ ዋና ዓላማ ንስሐ ብቸኛውና አማራጭ የሌለው የመዳን መንገድ መኾኑን መግለጽ፣ አለቆቹንና በየትኛው ደረጃ ያለውን ሰው መገሰጽ፣ እንዲኹም በይሁዳ ላይ ሊመጣ ያለውን ቊጣ (በከለዳውያን እጅ ወደ ምርኮ መኼድ) ማሳወቅ ነው፡፡
 ምንም እንኳን መጽሐፉ የሚዠምረው ሊመጣ ያለውን ፍርድ በማሳወቅ ቢኾንም የሚጨርሰው ግን በምስጋና ነው፡፡ ይኸውም በአብዛኞቹ የነቢያት መጻሕፍት የምናስተውለው አካኼድ ነው፡፡ አብዛኞቹ ነቢያት አስቀድመው የእግዚአብሔር ፍርድ ምን እንደኾነ ይገልጣሉ፤ በመጨረሻም ለኹሉም ተስፋ ድኅነትን ይሰጣሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ይኸው ድኅነት ሊመጣ ካለው መሲሕ ጋር በማያያዝ ነው የሚነግርዋቸው፡፡ ትንቢተ ሶፎንያስም አካኼዱ እንዲኽ ነው፡፡ አስቀድሞ የሰው ወዳጁ እግዚአብሔር ሐዘን እንደምን እንደኾነ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን እንዲኽ እያፈቀራቸው እነርሱ ግን በኃጢአት በበደል በመውደቃቸው እጅግ እንዳዘነ ይገልጣል፡፡ በመጨረሻ ግን እንደተናገርነው በሐሴት በደስታ ይጨርሳል፡፡
 ትንቢተ ሶፎንያስ አስቀድሞ በይሁዳ መንግሥት ላይ ሊመጣ ያለውን የእግዚአብሔርን ፍርድ ያሳውቃል፡፡ በመቀጠል በትውልድ ኹሉ ላይ የሚታየውን የእግዚአብሔር ትዕግሥት እንደምን ጥልቅ እንደኾነ ይናገራል፡፡ ቀጥሎም ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ በሚያሳዩት ልክ ያልኾነ አያያዛቸው አሕዛብም ጭምር እንደሚፈረድባቸው ይናገራል፡፡ በመጨረሻ ግን መጽሐፉ ስለ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም፥ ሕዝብም አሕዛብም አንድ አድርጋ ስለምትሰበስበው ቤተ ክርስቲያን ያበሥራል፡፡
  ነቢዩ ሶፎንያስ የንጉሥ ቤተ ሰብ እንደመኾኑ በቤተ መንግሥቱ አከባቢ የነበረውን ብልግናም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምንም ሳይፈራና ሳያፍር መናገሩም ስለዚኹ (ንጉሣዊ ቤተ ሰብ በመኾኑ) ነው፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.     አብዛኞቹ አይሁዳውያን ልክ እንደ ሰሜናዊው ክፍል “እግዚአብሔር ለምርኮ አሳልፎ ይሰጠናል” ብለው አስበዉም አልመዉም አያውቁም፡፡ ይኽን ያሉበት ምክንያት ደግሞ ይሁዳ የዋናው ቤተ መቅደስ መናኸርያ በመኾኗ፣ ከተማይቱ በተለያየ ጊዜ የእግዚአብሔር ከተማ መኾኗ ስለተገለጸ እግዚአብሔር ሊያፈርሳት አይችልም ሕዝቡንም ለጠላት አሳልፎ አይሰጥም የሚል አጉል የኾነ እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡ ከዚኽም የተነሣ አምልኮተ ጣዖትን ከአምልኮተ እግዚአብሔር ጋር ቀላቅለው ያስኼዱ ነበር፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው ሕዝብ ከንጉሥ ኢዮስያስ ጋር ቢተባበርም፥ መመለሱ አፍኣዊ እንጂ ውሳጣዊ (ከልብ) አልነበረም ያልነውም ስለዚኹ ነው፡፡ ነቢዩ ሶፎንያስ ግን፥ በዚኹ በአንደኛው ምዕራፍ፡- “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧል” በማለት ይሁዳ ወደ ምርኮ እንደምትኼድ ቤተ መቅደሱም እንደሚፈርስ አስረግጦ ይነግራቸው ነበር /ምዕ. ፩/፤
2.    በምዕራፍ አንድ ላይ እግዚአብሔር እስራኤልንና ይሁዳን ከመቅጣት እንደማይመለስ ተናግሯል፤ ምክንያቱም ክፋትን ስለሚጠላ፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ሕዝቡን ለመገሰጽ አሦርንና ባቢሎንን ቢጠቀምም አሦርና ባቢሎን መታበይ ከዠመሩ፣ ሕዝቡን ባልተፈለገ መንገድ የሚያንገላቱ ከኾነ ግን እንደሚፈርድባቸው በኹለተኛው ምዕራፍ ይናገራል /ምዕ. ፪/፤
3.    በክፋቷ ስለቀጠለች፣ ለእግዚአብሔር ድምጽ ጆሮዋ ስለተደፈነ፣ የእግዚአብሔርን ቁንጥጫ አልቀበል ስላለች፣ ራሷን ወደ አምላኳ ለማቅረብ ስላልወደደች፥ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን “ዓመፀኛይቱ ከተማ፣ የረከሰች ከተማ፣ አስጨናቅይቱ ከተማ” ብሎ ይጠራታል፡፡ እንዲኽ በመኾኗም ከሌሎች አገራት ጋር የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሷ ላይ እንደሚመጣ፣ በእርሷ ፈንታም ሌላ አዲስ ኢየሩሳሌም እንደምትመሠረት፣ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሕዝብም አሕዛብም እንደሚሰበሰቡና በንጹሕ ልቡናቸውም እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ፤ እግዚአብሔርም በመካከላቸው እንደሚያድር በምዕራፍ ሦስት ላይ ይናገራል፡፡ እርሷም ቤተ ክርስቲያን ናት /ምዕ. ፫/፡፡  
እኛስ ከዚኽ ምን እንማራለን?
üእግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነው፡፡ ካህናተ እግዚአብሔር ከካህናተ በኣል ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው ፈጽሞ አይሻም፡፡ እንኳንስ እግዚአብሔር ይቅርና ሰውም የገዛ ንብረቱ ከሌላ ሰው ንብረት ጋር እንዲቀላቀል አይሻም፡፡ አንድ ባል ሚስቱ ከሌላ ወንድ ጋር አላስፈላጊ ነገር እንድታደርግ አይሻም፡፡ ካደረገች ግን ይፈታታል፡፡ እግዚአብሔርማ እንዴት?  
üእግዚአብሔር ስነ ፍጥረትን የፈጠረው በእነርሱ አልፈን ወደ ፈጣሪያቸው እንድንዘልቅ እንጂ በእነርሱ ላይ እንድናቆም አይደለም፡፡ ጣዖት የሚፈጠረው ግን እንዲኽ ያደረግን እንደኾነ ነው፡፡ እናም በስነ ፍጥረታቱ ላይ ስናቆም እግዚአብሔርን እንዳንመለከት ከልክለውናልና እነዚኽን ማሰናከያዎች ከፊታችን ያስወግዳቸዋል፡፡ እንኳንስ ስነ ፍጥረታት ይቅርና የገዛ አካላችንም ጣዖት ከኾነብንና እግዚአብሔርን ከማየት ከጋረደን ያጠፋቸዋል /ኢሳ.፫፡፲፮- ፍጻሜ/፡፡  
üእግዚአብሔር ምድር ብቻ እንድንኾን አይፈልግም፤ እንደተፈጠርንበት ዓላማ ሰማያውያንም ጭምር እንጂ፡፡ ሰማያውያን ስንኾን እግዚአብሔር ከእኛ ቤት (ከሰውነታችን) ያድራል፡፡ ብቻውን ሳይኾን ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ያድራል፡፡ ምድራውያን ብቻ የኾንን እንደኾነ ግን ቤታችን የሸረሪት ድር ማድሪያ ይኾናል (የዲያብሎስና የሠራዊቱ ማፈንጫ ይኾናል)፡፡
üንስሐ ሊመጣ ካለው የእግዚአብሔር ቊጣ ይሰውራል፡፡ ንስሐ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ዝቅ ብሎ በባሮቹ ቤት (በእኛ) እንዲያድር ያደርጓል፡፡ ንስሐ ጸጋ እግዚአብሔር በእኛ ላይ እንዲትረፈረፍ ያደርጋል፡፡ የንስሐ ትልቁ ዕንቅፋት ግን ተዘልሎ መቀመጥ ነው፡፡ የንስሐ ትልቁ ማለቆ እግዚአብሔር ለሕይወታችን እንደሚያስፈልገን ሳይሰማን ሲቀር ነው፡፡
üእግዚአብሔር ሲቀጣ ሰው እንደሚቀጣ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቅጣት የፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቁንጥጫ የአባትነት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ተግሳጽ አሮጌይቱን ኢየሩሳሌም ከማንነታችን ነቅሎ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ለመገንባት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ተግሳጽ አንካሳው ልባችንን ለማቅናት ነው፤ ጠላትን ለመጣል ነው፤ ክፉውን እንዳናይ ነው፤ ስድብን ለማራቅ ነው፤ ከምርኮ ለመመለስ ነው፤ ለከበረ ስምና ለምስጋና ነው፡፡
…ተመስጦ…
  ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለኽ በቅዱሳን መላእክትና ሰዎች የምትመሰገን ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ሆይ! እጅግ ደንዳኖች ብንኾንም ስላልተውከን እናመሰግንኻለን፡፡ ወደ ዕቅፍኽ እንድንመለስ በማሳጣትም ጭምር ስለምትጠራን እናመሰግንኻለን፡፡ ጸጋኽን ለመስጠት በምስጢራዊቷ የተግሳፅ እጅኽ ስለምትጠራን እናመሰግንኻለን፡፡ ንስሐ ገብተን ከአንተው አከባታችን ጋር እንድንታረቅ በሚያስደንቅ አጠራር ሹክ ስለምትለን እናመሰግንኻለን፡፡ ማንንም ስለማትንቅ እናመሰግንኻለን፡፡ በርኽ ኃጥአንን ለመቀበል ዘወትር ክፍት ነውና እናመሰግንኻለን፡፡

 ቸርና ሰው ወዳጅ ሆይ! ወዳንተ የማንመለሰው ስላልወደድን አይደለም፤ ብርታቱ ስለሌለን እንጂ፡፡ እንኪያስ አትተወን፡፡ ሰማያዊው ሙሽራችን ሆይ! አሮጌይቱን ኢየሩሳሌም ከማንነታችን አስወግድልና አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ሥራልን፡፡ አማኑኤል ሆይ! ከእኛ ጋር ኹንና ኹለንተናችንን ሰርግ ቤት አድርግልን፡፡ ሰርግ ቤት ኾነንም ከቅዱሳን ኹሉ ጋር እንድናመሰግንኽ ፍቀድልን፡፡ አሜን!!!

No comments:

Post a Comment