Pages

Thursday, January 2, 2014

ነቢዩ ዘካርያስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፳፫ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ዘካርያስ” ማለት “ዝኩር፣ ዝክረ እግዚአብሔር - እግዚአብሔር ያስታውሳል” ማለት ነው፡፡ ይኸውም በምርኮ የነበሩትን አይሁድ እግዚአብሔር እንዳሰባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በምስጢራዊ መልኩ ግን እግዚአብሔር ኹል ጊዜ በእኛ ውስጥ ያለችውን ቤተ መቅደስ (ነፍሳችንን) እንድናንፃት እንደሚያሳስበን፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎአችን ኹሉ እንደሚረዳን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

 በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የተጠሩ ከ፴ በላይ ሰዎች አሉ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ በፄዋዌ አገር በባቢሎን የተወለደ ሲኾን አባቱ በራክዩ በባቢሎን ስለሞተ ከአያቱ ሐዶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶአል፡፡ በመኾኑም እርሱና አያቱ በዘሩባቤል መሪነት ከመዠመሪያዎቹ ተመላሾች ጋር ከምርኮ ተመልሰዋል /ነህ.፲፪፡፩፣፬፣፯/፡፡ ትንቢቱንም የዠመረው በ፭፻፳ ቅ.ል.ክ. ላይ ነው፡፡ ከነቢዩ ሐጌ ጋር ማለት ነው፡፡
 ዘካርያስ የገዥው ዘሩባቤል፣ የነቢዩ ሐጌና የሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ወልደ ዮሴዴቅ የዘመን ጓደኛ ነው /ዘካ.፫፡፩፣ ፬፡፮፣ ፮፡፲፩/፡፡ እንደ አይሁድ ትውፊት ነቢዩ ዘካርያስ የነቢዩ ሐጌ የቅርብ ጓደኛ ሲኾን መቃብራቸውም ጐን ለጐን ነው፡፡
በነቢዩ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
 በ፭፻፴፰ ቅ.ል.ክ. ላይ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ አንድ አዋጅ አስነግሮ ነበር፡፡ አዋጁም አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የሚፈቅድ ነበር /ዕዝራ ፩፡፩-፲፩/፡፡ ነገር ግን አይሁዳውያኑ፥ በባዕድ አገር ኼደው ለመኖር የተገደዱ ስደተኞች እንደመኾናቸው ራሳቸውን ለማስተዳደር በጣም ይለፉ ነበር፤ ብዙ ሀብት ንብረትም አፍርተው ነበር፡፡ በመኾኑም ብዙዎቹ በጠላት ተወርራ ባዶ ወደ ኾነችው አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ የተመለሱት ወደ ፶ ሺሕ የሚጠጉ ብቻ ናቸው፡፡ እነዚኽ የተመለሱትም በ፭፻፴፮ ቅ.ል.ክ. ላይ የቤተ መቅደሱን ሥራ ዠምረዋል /ዕዝ.፫፡፲፩-፲፫/፡፡ ነገር ግን ወደ አገራቸው ሲገቡ አገራቸው ባድማ ኾና ስለነበር፣ የዘር ፍሬ በአገሩ ስላልነበረ፣ እንዲኹም ሳምራውያን ስለተቃወሟቸው /ዕዝ.፬/ የቤተ መቅደሱን ሥራ ለ፲፭ ዓመት አቆሙት፡፡ በ፭፻፳፩ ቅ.ል.ክ. ላይ ግን እግዚአብሔር ነቢዩ ሐጌንና ነቢዩ ዘካርያስን ልኮ የተዠመረውን ቤተ መቅደስ እንዲያጠናቅቁት አሳሰባቸው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ ይኽ ዓመት ዳርዮስ ወደ ንግሥና የመጣበት የቤተ መቅደሱም ሥራ እንዲጠናቀቅ ያዘዘበት ነው፡፡ በዙርያ የነበሩት የፋርስ ነገሥታት ይኽን ቢቃወሙም ዳርዮስ ይኽን እንዲተዉ አዝዟል /ዕዝ.፮፡፮-፲፪/፡፡
 ከአፍአዊው ተግዳሮት በተጨማሪ ውሳጣዊ የኾነ ፈተናም ነበር፤ ቤተ መቅደሱ እንዳይሠራ፡፡ ይኸውም የቤተ መቅደሱ ሥራ ለ፲፭ ዓመታት ስላቆመ በሕዝቡ ዘንድ “እግዚአብሔር ባይፈቅድ ነው” የሚል ስሜት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይኼ አስተሳሰብ ግን ሕዝቡ የራሳቸውን ቤት ለመሸላለም ያመጡት ምክንያት እንጂ ትክክል አለመኾኑ እግዚአብሔር በነቢያቱ አድሮ ነግሯቸዋል /ሐጌ.፩፡፬/፡፡
ትንቢተ ዘካርያስ
ትንቢተ ዘካርያስ ከደቂቀ ነቢያት መጻሕፍት ትልቁ ነው፤ ባለ ዐሥራ አራት ምዕራፍ፡፡ በውስጡም በጣም ብዙ ኅብረ አምሳሎችን የያዘ ሲኾን በአጠቃላይ ሊመጣ ካለው የመሲሑ ዘመን ጋር የተሰናሰለ ነው፡፡ አንባብያን ይኽን ማመሳከር እንዲችሉ ለናሙና ያኽል በእያንዳንዱ ምዕራፍ የተጠቀሰውን ኅብረ አምሳል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
Øምዕራፍ አንድ ላይ ዲያብሎስ እኛን ለመጣል ተነሣስቶ እንደነበርና ጌታችን ግን እኛን ለመርዳት የጠላትን ቀንድ ለመጣል እንደሚመጣ ይገልጣል፡፡
Øምዕራፍ ኹለት ላይ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጽዮን መጥቶ አማኑኤል እንደሚባልና በመሞቱም ለሕዝብና አሕዛብ መጠጊያ እንደሚኾን ተጽፏል፡፡
Øበምዕራፍ ሦስት ላይ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እንዲኹም ወደዚኽ ምድር መጥቶ የሰዎችን ኃጢአት እንዴት እንደሚያስወግድ ተተንብዮአል፡፡
Øምዕራፍ አራት ላይ ስለ ሐሳዊ መሲሕና ስለ ጌታችን ተነግሯል፡፡
Øምዕራፍ አምስት ላይ በዳግም ምጽአት ላይ ሊኾን ያለው ፍርድ ምን እንደሚመስል በግልጥ ያሳያል፡፡
Øምዕራፍ ስድስት ላይ “የእግዚአብሔር ቊጥቋጥ” የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ስላለው አኳኃኑን ያስረዳል፡፡
Øምዕራፍ ሰባት ላይ እግዚአብሔር (አይሁዳውያኑን) ሲጠራቸው እንዳልሰሙ ኹሉ እነርሱም ሲጠሩት እንደማይሰማቸውና በሮማውያን እጅ እንደሚበትናቸው አገራቸውም ባድማ ኾና እንደምትቀር ይገልጣል፡፡
Øምዕራፍ ስምንት ላይ ስለ መንፈሳዊቷ ኢየሩሳሌም ይናገራል፡፡
Øምዕራፍ ዘጠኝ ላይ በግልጥ ስለ ሆሣዕና ይናገራል፡፡
Øምዕራፍ አሥር ላይ ምእመናን በክርስቶስ ኢየሱስ ኃይል ኹሉንም ነገር ድል እንደሚያደርጉ ይገልጣል፡፡
Øምዕራፍ አሥራ አንድ ላይ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠላሳ ብር ሚዛን እንደሚሸጥ በግልጥ ይተነብያል፡፡
Øምዕራፍ አሥራ ኹለት ላይ ክርስቶስን ከማመን የራቁ አይሁድ እንደምን ያለ መከራ እንደሚደርስባቸው ያስረዳል፡፡
Øምዕራፍ አሥራ ሦስት ላይ ግልጽ በኾነ አነጋገር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚደርስበት ጸዋትወ መከራ ይናገራል፡፡
Øምዕራፍ አሥራ አራት ላይ ደግሞ በስቅለት ጊዜ ስለሚኾነው ክስተት እንዲኹም በዚያ አንጻር ስለ ዳግም ምጽአት ይናገራል፡፡
 ከዚኽም የተነሣ ትንቢተ ዘካርያስ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በጣም ተደጋግሞ እንዲነሣ (እንዲጠቀስ) ምክንያት ኾኗል፡፡ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.     የንስሐ ጥሪ /፩፡፩-፮/፤
2.    ንጉሠ ሰማይ ወምድር የኾነ እግዚአብሔር ጽዮንን ለመሥራትና ለማንጻት ያለው ሐሳብ /፩፡፯-፮፡፲፭/፤
3.    በኢየሩሳሌም መፍረስ ጊዜ የተደነገጉ የፆም ቀናት ተለውጠው የደስታ በዓላት እንዲኾኑ የተሰጠ ትእዛዝ /፯-፰/፤
4.    እግዚአብሔር ለመፍረድም ኾነ ለማዳን ታላቅና ቅን ስለመኾኑ /፱/፤
5.    ስለማይረቡና ስለ መልካሙ እረኛ /፲-፲፫/፤
6.    እግዚአብሔር በምድር ኹሉ ላይ ስለመንገሡ /፲፬/፡፡
እኛስ ከትንቢተ ዘካርያስ ምን እንማራለን?
©     መጽሐፉን በጥንቃቄ የሚያነብ ሰው እግዚአብሔር በምርኮ (በዲያብሎስ) ለምትፈተን ነፍስ ረዳቷ እንደኾነ ይገነዘባል፡፡ በየትኛውም ዓይነት ፈተና ውስጥ ብንኾንም እግዚአብሔር አይረሳንም፡፡ እኛ እስካልረሳነው ድረስ እግዚአብሔር ፈጽሞ አይተወንም፡፡ አንድ ቀን እንደምንመለስ በማሰብም ይጠብቀናል፡፡ ከተጠቀምንበትም የመውጫውን ቀዳዳ ያሳየናል፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ … እኔም ወደ እናንተ እመለሳለኹ” ሲልም ይኽን ድንቅ ፍቅሩ የሚያስገነዝብ ነው /፩፡፫/፡፡
©     እግዚአብሔር በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል /፩፡፲፮/፡፡ ከእኛ ጋር ለመታረቅ ባለጠጋ ሲኾን ስለኛ ድኻ ኾኗል፡፡ ንጉሥ ሲኾን ስለ እኛ አርአያ ገብርን ነሥቶ መጥቷል፡፡ በእኛ ዘንድ የነበረው ግማት ተወግዶ መዓዛ መለኮቱን ያድለን ዘንድ በቊጣ ሳይኾን በምሕረት ጐብኝቶናል፡፡ ዛሬ ዕርቅን የማንወድ ከኾነ ግን ዕርቁ ለእኛ አልሠራም፡፡ ድኾች ወገኖቻችንን የማንጠይቅ ከኾነ ግን ባለጠግነቱ ለእኛ አልደረሰም፡፡ ዝቅ ማለትን በእኛ ዘንድ ቦታ ከሌላት ንጉሥ ክርስቶስ ወደ ቤታችን አልገባም፡፡ ከኃጢአት ካልራቅን አኹንም ከነግማታችን ነን፡፡ በምሕረት ወደ እኛ ቢመለስም ለዚኽ ያልተገባን ኾነን ተገኝተናልና ቤታችን ገና አልተሠራም፡፡
©     ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን ገና የክርስቶስ ማደርያ ካልኾነ “አማኑኤል - እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” አልኾነም፤ መንፈስ ቅደስ አጥር ቅጥራችን አልኾነም /፪፡፭፣ ፲/፡፡
©     ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው መውደቅ አዳማዊነት ነው፤ መነሣት ግን ክርስቶሳዊነት ነው፡፡ እናም ወድቀን የማንቀር ከኾነ ግን ንጉሥ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ወደ ቤታችን ይገባል /፮፡፲፪/፡፡ ምንም እንደ አህያ (ወራዳ) ብንኾንም በእኛ ላይ ነግሦ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” ተብሎ ለመመስገን አይጠየፈንም /፱፡፱/፡፡

  ዘወትር ለማይጠየፈን፣ ከነ ኃጢአታችን ለሚወደን፣ ዘወትር በፍቅር ለሚጠራን ወዳጃችን፣ እድፋሙን ልብስ (ኃጢአታችንን) ተሸክሞ ወደ መስቀል ለወጣው ለታላቁ ሊቀ ካህናችን /፫/፣ በማይተመን ዋጋ እኛን ለመግዛት በሠላሳ ብር ለተሸጠው ቤዛችን /፲፩፡፪/፣ በቊስላችን ላይ ዘይት ያፈስልን ዘንድ ጐኑን በጦር ለተወጋው አፍቃሪያችን /፲፪፡፲/፣ በፈቃዳችን በጠፋን ጊዜ በምሕረቱ ላሰበን አምላካችን ኃይል፣ ክብርና ምስጋና ለዘለዓለሙ ይኹን አሜን!!!  

No comments:

Post a Comment