Pages

Thursday, January 2, 2014

ነቢዩ ሚልክያስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፳፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሚልክያስ” ማለት “መልአክ፣ ሐዋርያ፣ መልእክተኛ” ማለት ነው፡፡ ጥር ፰ ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንደሚያስረዳው ነቢዩ ሚልክያስ የተወለደው ሕዝቡ ከፄዋዌ (ከምርኮ) ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡ ከሕፃንነቱ አንሥቶም የእግዚአብሔርን መንገድ የሚወድ ነበር፡፡ ሕዝቡም ይኽን አካኼዱን አይተው እጅግ ያከብሩት ነበር፡፡ ይኽን መልካምነቱንም አይተው “ከእግዚአብሔር የተላከ ነው” ሲሉ ስሙን ሚልክያስ ብለው ጠሩት፡፡

 ነቢዩ ሚልክያስ ከጸሐፍት ነቢያት የመጨረሻው ነቢይ ነው፡፡ ከሐጌና ከዘካርያስ በኋላም በነቢይነት አገልግሏል፡፡ ከ፬፻፶-፬፻ ቅ.ል.ክ. ላይ እንደነበረም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ዕዝራና ነህሚያ ቤተ አይሁድን በሚስተካክሉበት ጊዜ ሚልክያስም ተባባሪያቸው ነበር፡፡
በነቢዩ ዙረያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
  በምርኮ የነበሩት አይሁድ በ፭፻፴፰ ቅ.ል.ክ. ላይ ከምርኮ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ከኹለት ቡድን ተከፍለዋል፡፡ አንደኛውና የሚበዛው ቡድን ወደ ተስፋይቱ ምድር መመለስን ያልወደደና በባቢሎን አገር በሀብትና ንብረት የተደራጀ ነው፡፡ ይኼ ቡድን ምንም እንኳን በባዕድ አገር የሚኖር ቢኾንም ባርነቱ የተመቸው ይኽንንም ዓለም የወደደ ነው፡፡ ይኼ ቡድን እግዚአብሔር ለአባቶቹ የገባውን ቃል ኪዳን ለመካፈል ያልፈለገ ቡድን ነው፡፡ በሕገ ኦሪቱ መሠረት እግዚአብሔርን እያመለከ ለመኖር ያልፈቀደ ቡድን ነው፡፡
 ኹለተኛውና የሚያንሰው ቡድን ደግሞ ወደ ተስፋይቱ ምድር የተመለሰው ነው፡፡ ይኼ ቡድን ከምርኮ ሲመጣ የኢሩሳሌምን አጥር፣ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት፤ እንዲኹም የቀድሞውን አምልኮተ እግዚአብሔር ለመመለስ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእነዚኽም መካከል ቤታቸውን ለመሸላለም “የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን ገና ነው” የሚሉ ነበሩ፡፡ አኹንም ከእነዚኽ ከተመለሱት ቅሪቶች መካከል ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ቢያከናውኑም አካኼዳቸው ግን ከልብ አልነበረም፡፡ መሥዋዕታቸው የቃየን መሥዋዕት ነበር፡፡ ሲዠምር “የእግዚአብሔር ማዕድ አስናዋሪ ነው” ይላሉ፡፡ በፊቱ የተዘጋጀ እኽሉም “አባር የመታው እንክርዳድ ነው” ይላሉ፡፡ እነርሱም ለመሥዋዕት ዕውሩን አንካሳውን እንስሳ ያመጣሉ /፩፡፰/፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ የተላከበት ምክንያትም ይኽን አካኼዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለማሳሰብ ነበር፡፡
 ነቢዩ ሚልክያስ በነገሥታቱ ዘመን እንደነበረው ዓይነት ስብከት አልሰበከም፤ የባዕድ አምለኮ ዐፀዶችን እንዲያፈርሱም አልተናገረም፡፡ ልክ እንደ ዕዝራ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አላሳሰባቸውም፤ ልክ እንደ ነህምያም የኢየሩሳሌምን አጥር ቅጥር እንዲሠሩ አላሳሰባቸውም፡፡ ወደ ውሳጣዊ ሕይወታቸው ዘልቆ በቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው አሳሰባቸው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር በእውነትና በመንፈስ የሚያመልኩት አምላክ ነውና ከምንም በፊት ውሳጣዊ ማንነታቸውን ወደ አገራቸው ወደ ሰማይ እንዲመልሱ፣ የነፍሳቸው የኢየሩሳሌምን አጥር ቅጥር እንዲሠሩ ነበር ያሳሰባቸው፡፡
ትንቢተ ሚልክያስ
 ትንቢተ ሚልክያስ እጅግ መሳጭና የእግዚአብሔር ፍቅር እንደምን ጥልቅ እንደኾነ የምናነብበት መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በሙሉ ያለማዳለት ይወዳል፡፡ እግዚአብሔር ሲወድ አንዱን በመጥላት ሌላውንም በመውደድ አይደለም፡፡ ያለ ማዳላት ኹላችንም ይወደናል እንጂ፡፡ ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠሉ የሚኾኑት ከራሳቸው ክፋት የተነሣ ነው፡፡ ሕጉንና ትእዛዙን ሳያከብሩ ሲቀሩ እግዚአብሔር አይቀበላቸውም፡፡ አፍአዊ በኾነ አምልኮ እግዚአብሔርን መቅረብ ወደ ሕይወትም መጋበዝ አይቻልምና እነዚኽ ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት የሌላቸው ይኾናሉ፡፡ በትንቢተ ሚልክያስ የምናገኘው አንዱ አንኳር ነጥብ ይኸው ነው /፩፡፪-፭/፡፡
 ነቢዩ ሚልክያስም ለዚኹ ኹሉ ችግር መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ እንደኾነ ይሰብካል፤ ይኽ ከእግዚአብሔር የተቀበለውንም መልእክት ለሕዝቡ ያስተላልፋል፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለኹ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት /፫፡፯/፡፡ ይኽ ለሰው ኹሉ የተከፈተ በር ነው፡፡ የእኛ ደንዳናነት ካልኾነ በስተቀር ይኽን የድኅነት በር መዝጋት የሚችል አካል የለም፡፡ እንኳንስ ፍጡር ይቅርና እግዚአብሔርም ቢኾን ስለማይችል ሳይኾን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ይኽን በር በማንም ሰው ፊት አይዘጋውም፡፡ እግዚአብሔርስ እርሱ እንዳይገባ የዘጋንበትን በር እንድንከፍትለት ያንኳኳል እንጂ አይዘጋውም፡፡ “ወድጃችኋለኹ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” /፩፡፪/፡፡
 ትንቢተ ሚልክያስን ገና ማንበብ ስንዠምር ከምርኮ የተመለሰው ሕዝብ አንድን ነገር ጠብቆ እንደመጣ እንገነዘባለን፡፡ ሕዝቡ አፍአዊ የኾነ በረከትን ሽቶ እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ ከዚኽ በፊት ነቢያቱ ስለ መሲሑ የተናገሩት ኹሉ በጊዜአቸው የሚፈጸም መስሎአቸው እንደ ነበር እናስተውላለን፡፡ የዳዊት ድንኳን እንደገና በዘመናቸው እንደምትሠራ፥ ፈርሶና ተዳክሞ የነበረው መንግሥታቸውም እንደገና አንሰራርቶ በዓለም ላይ ገናና መንግሥት እንደሚኾን ገምተው እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ እነርሱ እንዳሰቡት አፍአዊ የኾነ ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ግን ግርምት ይዞአቸው እግዚአብሔርን፡- “በምን ወደድኸን?” እንዳሉት እናነባለን /፩፡፪/፡፡ እንዲኽ ዓይነት የግርምትና የመደነቅ ንግግርም በብዙ ቦታ ላይ ሲናገሩት እናገኛቸዋለን፡፡ “ስምኽን ያቃለልነው በምንድነው?” /፩፡፮/፤ “ያረከስንኽ በምንድነው?” /፩፡፯/፤ “ያታከትነው በምንድነው?” /፪፡፲፯/፤ “የምንመለሰው በምንድነው?” /፫፡፯/፤ “የሰረቅንኽ በምንድነው?” /፫፡፰/፤ “በአንተ ላይ ድፍረት የተናገርነው በምንድነው?” /፫፡፲፫/፤ “ትእዛዙንስ በመጠበቅ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ኾነን በመኼድ ምን ይረባናል?” /፫፡፲፬/ እንዲል፡፡ እግዚአብሔር ግን እነዚኽ ሰዎች ምድራዊውን ሳይኾን ሰማያዊውን፣ ጊዜአዊውን ሳይኾን ዘለዓለማዊውን፣ አፍአዊውን ሳይኾን ውሳጣዊውን፣ ብልና ዝገት የሚያገኘውን ሳይኾን በሰማያዊው መዝገብ የተቀመጠውን እንዲሹ ይጠራቸዋል፡፡ ነውረኛ መሥዋዕትን እያቀረቡ እግዚአብሔርን ከመሸንገል ተመልሰው /፩፡፲፬/፣ የግፍ ሥራቸውን በልብስ መክደንን ትተው /፪፡፲፮/፣ “ክፉን የሚያደርግ ኹሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው” ፥ እንዲኹም “የፍርድ አምላክ ወዴት አለ?” /፪፡፲፯/፣ “የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዐን እንላቸዋለን” እያሉ /፫፡፲፭/ እግዚአብሔርን ከመፈታተን ተመልሰው ስሙን እንዲፈሩና የክፋት በረዶአቸው በጽድቅ ፀሐዩ እንዲቀልጥላቸው፥ በሕይወትም እንዲኖሩ ይጠራቸዋል /፬/፡፡
 በአጠቃላይ መጽሐፉ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ፥ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ … የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ኹሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያኽል መኾኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ …” እንዳለው /ኤፌ.፫፡፲፮-፲፱/  እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር እንደምን ጥልቅ እንደኾነ፣ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚከፍት የተትረፈረፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ልጆች እንደምን ብዙ እንደኾነ፣ ከአፍአ ሳይኾን ከልቡ የተመለሰ ሰው ምን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ድኅነትን የምትሻ ነፍስ መልስ የምታገኝበት ግሩም መጽሐፍ ነው፡፡ በውስጡም በዘመነ ሐዲስ ስለሚቀርበው ቊርባን /፩/፣ ስለ ጋብቻ ምንነት /፪/፣ እንዲኹም ስለ አስራት አሰጣጥ /፫/ በጥልቀት ያስተምራል፡፡
 መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1.  ምዕራፍ አንድን ስናነብ፥ ምንም እንኳን እግዚአብሔር አባታቸው መኾኑን ቢያውቁም፣ ምንም እንኳን እግዚአብሔር ጌታ እንደኾነ ቢረዱም በገቢር ግን የአባትነትም ኾነ እንደ ጌትነቱ የመፈራት ክብርን አለመስጠታቸው ይገልጣል፡፡ ነውረኛ የኾነ መሥዋዕትን በማቅረባቸው የእግዚአብሔርን ስም እንዴት እንደናቁት ያሳያል፡፡ በሌላ አገላለጽ የእምነትና የምግባር አንድነትን የሚያስረዳ እውነተኛና ተቀባይነት ያለው አምልኮ ምን እንደሚመስል የሚያረዳ ነው፡፡
2.  ምዕራፍ ኹለትን ስንመለከት ደግሞ የካህናቱን ኢሞራላዊነት ይናገራል፡፡ በዚኽ ድርጊታቸውም የእግዚአብሔርን ኪዳን እንዴት እንዳፈረሱት ለበረከት የኾነውም እንደምን ለመርገም እንዳደረጉት ያስረዳል፡፡
3.  ምዕራፍ ሦስትና አራት ላይ እግዚአብሔር እንደሚመጣና ሕዝቡንም ኾነ ቤተ መቅደሱን እንደሚቀድስ ይናገራል፡፡ ምዕራፍ ሦስት ላይ በመዠመሪያ ምጽአቱ ላይ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን (ቤተ መቅደሱን) በገዛ ደሙ ለመዋጀት እንደሚመጣና ሕዝቡም እርሱን ለመቀበል በገቢር እንዲመለሱ ሲጠይቅ በምዕራፍ አራት ላይ ደግሞ የጽድቅ ፀሐይ የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ ጨለማ የተባለውን ክፋት ከው ልጆች ለማራቅ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ በዚያ አንጻርም በሕያዋንና በሙታን ላይ ዳግም ለመፍረድ እንደሚመጣ ይገልጣል፡፡
እኛስ ከዚኽ ምን እንማራለን?
©     እግዚአብሔርን በከንፈራችን ሳይኾን በገቢር እንደምንወደው መግለጥ እንዳለብን፤ ንጹሕ መሥዋዕትም ይኸው እንደኾነ /፩/፤
©     እንዲኽ ካልኾነ ግን ብንጦምም፣ ብንጽልይም፣ ብንመጸውትም፣ ቤተ ክርስቲያን ብንመላለስም፣ መባ ብናቀርብም መሥዋዕታችን ኹሉ ፋንድያ እንደኾነ /፪፡፫/፤
©     ምንም ያኽል ኃጢአተኞች ብንኾንም ልንመለስ እንደሚገባን /፫፡፯/፤ እርሱም ከየትኛውም ዓይነት ኃጢአታችን እንደሚያነጻን፤ የእርሱ ገንዘብ እንደምንኾንና አንድ ሰው የሚያገለግለው ልጁን እንደሚምረው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደሚምረን /፫፡፲፯/፤
©     እንዲኽ ከተመለስን በኋላ የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ላይጠልቅ በሕይወታችን ላይ አብርቶ እንደሚኖር እንማራለን፡፡
…ተመስጦ…
 ቸርና ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ! በሕይወታችን እጅግ ጐስቋሎች ኾነን ስምኽን ብናቃልለውም ደካሞች ነንና በከንፈራችን ብቻ ሳይኾን በገቢርም እንድናውቅኽ እንድናመልክኽም እርዳን፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! እውነተኛ ካህናት እንድንኾን እርዳን፡፡ አባቶቻችን ካህናት ቅዱስ ሥጋኽና ክቡር ደምኽን ለምእመናን ለኹላችንም ሲያቀብሉ እኛም በክህነታችን ቁራሽ ዳቦና ኩባያ ውኃ ለድኾች መስጠት እንድንለማመድ እርዳን፡፡ የጽድቅ ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ቅድስናኽ እኛን ቢቀድሰን እንጂ ኃጢታችን አንተን አያረክስኽምና በእኛ ዘንድ እደር፡፡ በኹለንተናችን ላይም አብራ፡፡ ጨለማን ከእኛ ዘንድ አስወግድልን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን!!!

2 comments: