Pages

Sunday, March 16, 2014

መጻጉዕ ዘሰንበተ ክርስቲያን



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 7 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ሥጋችን በደዌ ተመትቶ መከራ በጸናብን ጊዜ፣ የኢዮብን ሥቃይ ማሰብ አቅቶን በደጅ ተንቀን በወደቅን ጊዜ፣ የምሬታችን ብዛት በአህዛብ ዘንድ ስድብ ሲሆንብን፣ በደጅህ ወድቀን የሚያነሳን ባጣን ጊዜ፣ የወለዱን እንኳን እኛን እስከመጨረሻው መሸከም ከብዷቸው በጣሉን ጊዜ፣ ሊሰሙን ያልወደዱ ነገስታት ሊጎበኙን ያልፈቀዱ ካሕናት በተሠበሰቡ ጊዜ፣ በቁስላችን ላይ ዘይትን በጥዝጣዜያችን ላይ መድኃኒትን የሚያፈሱልንን ባጣናቸው ጊዜ፣ አንተ ሳንጠራህ መጥተህ ሳንጠይቅህ ወደህ ሳንመካብህ መመኪያችን ሆነኸን ከሞት ጥላ በአባታዊ አጠራርህ ልጆቼ ብለህ ጠርተህልጆቼ መዳን ትወዳላችሁን?” ብለህ እንደ ታናሽ አስፈቅደህ መንጻትን በፈቀድን ጊዜ ከደዌያችን ሁሉ ጎንበስ ብለህ አጠብከን፡፡ ስለዚህም ማንም ሊሰጠን ያልፈቀደውን ሰላም ይልቁንም ማንም የሌለውን ሰላም ሰጠኸን:: በዚህ ሰላም ለሁላችሁ ሰላም ይሁንላችሁ!


 ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሠመይ ቤተ እግዚአብሔር ወማኅደሩ ለልዑል ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሠመይ ረሰየክሙ አንትሙ በዐተ ፊያት () አሕየዎ ኢየሱስ ለመጻጉዕ ለዘሰላሳ ወሰመንተ ክረምተ ሐመየሰንበት ጌታዋ፣ የምሕረት አባቷ፣ እርሱ ቤቴ የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት ቤት የልዑል ማደሪያ ትባላለች፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት አለ:: 38 ዓመት የታመመውን በሽተኛ ኢየሱስ አዳነው::” ዛሬ የአራተኛው ሳምንት የመጀመሪያ የጾም ቀን ነው:: ይህን ሳምንት መጻጉዕ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ለምን? ብንል ያው ከላይ ቅዱስ ያሬድ የዜማውን ድርሰት በምኩራብ ትውስታ ጀምሮ በሰንበት በዚያ ከሰራቸው ታላላቅ ተዐምራት አንዱ የሆነውን 38 ዓመት በሽተኛ መፈወስ ስለሚሰብክ ነው:: አመፅጉዐ - ታመመ አሳመመ ማለት ሲሆን መጻጉዕ የታመመ በሽተኛ እንደማለት ነው:: ስለዚህም ሳምንቱ መጻጉዕ ይባላል:: ከዚህ ከሰንበት ድርሰቱ ጥቂት የተመረጡ ቃላትን እየዘመርን እንቆያለን::

 በሰንበት ፈወሰ ዱያነ ወከሰተ አዕይንተ ዕውራንበሰንበት ድውያንን ፈወሰ፡፡ የዕውሮችንም ዐይን አበራ::” ይህች ሰንበት ሰው ሁሉ የሥጋውን አምሮት፣ የሰውነቱን እንቅስቃሴ፣ በፈቃዱም ያለፈቃዱም ለአምላክ በመገዛትም በልምድም ታስሮባት እንደ አምላክ አድርጔት ይኖር ነበር:: በተለይም የአይሁድ መምሕራን ጌታዋን ሳይሆን ቀኗን ያለፍቅር ይፈሯት ነበር:: ስለዚህም መልካም መስራትን እንጂ መታሰርን የማይፈቅደው ጌታ በዚህች ቀን የሽባውን እጅ ተረተረ፤ ዐይን በሌለበት ግንባር ጭቃን ቀብቶ ዐይንን ሰራ፤ በተለይም 38 ዓመት በደዌ የተያዘውን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው::

 አልጺቆ ኢየሱስ ኢያሪሆ ሀሎ ዕውር ዘይነብር ውስተ ፍኖት ወይቤሎ ለኢየሱስ ተሣሃለኒ እግዚእየ ዮም ይቤሎ ተኃድገ ለከ ኃጢአተከኢየሱስ ኢያሪኮ በደረሰ ጊዜ በመንገድ የተቀመጠ ዕውር ነበረ፡፡ ኢየሱስንም ዛሬ ይቅር በለኝ አለው:: ኢየሱስም ኃጢአትህ ተሠርዮልሃል አለው:: ሕዝቡ ሁሉ ይህን ታላቅ ተዐምር አይተው የሰንበት ጌታዋ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ሰላምን የሚሰጥ እግዚአብሔርን አመሰገኑ::”

 እንቀጥል! አብረን የቸርነቱን ስራ እናድንቅ: “አምላኩሰ ለአዳም ለእረፍት ሰንበተ ሠርዐየአዳም አምላኩ ለእረፍት ሰንበትን ሰራ፡፡ አይሁድም በምን ስልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፡፡ ኢየሱስም እኔ እሰራለሁ በሥራዬ እመኑ፤ የሰንበት ጌታዋ አንድ ልጅ እኔ ነኝ አላቸው:: ኃጢአትን ይቅር እል ዘንድ፣ በምድር ላይ ነፃነትን እሰብክ ዘንድየዕውራንን ዐይን አበራ ዘንድ ሥልጣን አለኝ አላቸው::” ከሥልጣኑ ሥር ምሕረትን እንለምን፤ ማዳኑን ለእኛ ገልጧልና::

 ንዑ ትሰምዑ ዘንተ ነገረኢየሱስ ያደረገውን ዕፁብ ድንቅ ተዐምር ትሰሙ ዘንድ :: ወደ ታንኳ ገባ፡፡ ባሕርን ገሰጸ፡፡ ነፋሳትን ገሰጸ፡፡ በደይን ያሉ ያርፉባት ዘንድ ሰንበትን አከበረ:: እሁድን ከፍ አደረገ፡፡ ዕውርንም አዳነ፡፡ ኃጢአት የሚሰረይበት ጾምን ሰጠን::” ከኃጢአት አርፈን እንውል ዘንድ የመፃጉዕን ነገር ገለጠልን፡፡ መፃጉዕን እምነቱ አዳነችው፡፡ በእምነት ያለን እኛን ምንኛ ያከብረን ይሆንወኀደገ ኵሎ መዐተከመዐትህን ሁሉ አስወግደህ በማዳንህ ይቅር በለን፡፡ ከትዕዛዝህ አታርቀን፡፡ የሰላም ንጉሥ መድኃኔዓለም ሰላምህን ስጠን::” አሜን!

No comments:

Post a Comment