Pages

Monday, March 24, 2014

ደብረዘይት ዘሠኑይ


በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 15 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 አስፈሪዋን ሰዓት እናልፍ ዘንድ ፍቀድልን:: በቀዳማይ ምፅአትህ በሥጋ ማርያም መገለጥህን አምነን በሕይወታችን አንተን መስለን በዳግማይ ምፅአትህም እንዳንተ የብርሃን ልብስን እንድንጎናጸፍ ፍቀድልን:: ያን ጊዜ ከሚያለቅሱትና ከሚተክዙት ሳይሆን የማይነገር ሰላምህን ከምትሠጣቸው አድርገን:: ዘላለማዊ ሰላሙን ይስጠን::


 አንቅሐኒ በጽባሕ ክስተኒ ዕዝንየበጠዋት ቀስቅሰኝ፤ የምሰማበት ጆሮዬን ክፈትልኝ፡፡ አምላኬ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ፤ የሚታወቅ ምሕረትህን በጠዋት (በማለዳ) አድርግልኝ::” እንቅልፍ አሸንፎኝ፣ ስንፍና እንደ ካባ በላዬ ሆኖ፣ ጽድቅን ማድረግ አቅቶኝ፣ በፍርድ ወንበር ስትቀመጥ ከሚፈረድብኝ አቤቱ ሁሉ በአንተ ነውና ለምሥጋና ለጾም ለጸሎት ለምጽዋት አበርታኝ::

  አፈቀርኩ እስመ ሰምዐኒ እግዚአብሔርየንጹሐንን ልመና የሚሰማ እግዚአብሔር የልመናዬን ቃል ሰምቷልና ወደድሁት::” በአንተ ዘንድ ንጹሕ የለም፤ ንጽሕና የአንተ ባህርይ ብቻ ነው:: ለእኛም ከአንተ ሳይከፈልብህ ታድለናለህ:: ስለዚህንጹሕ ሳንሆን ንጹሕ አድርገህ የልመናችንን ቃል ስማን” እያልን ከቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ከቅዱስ ያሬድ ጋር እናዜማለን::

  ዜመኛው ቤተክርስቲያንን እንደተለመደው ያወድሳታል፤ መስቀሉንም እንዲሁ:: “መስቀል ተስፋ ለእለ አልቦሙ ተስፋመስቀል ከዓለም ተስፋ ለሌላቸው ተስፋ ነው:: ያቺ መቅደስ የሰማዕታት የቅዱሳን ሁሉ እናት ናት::” በመስቀል የእኛን ዋጋ ባይከፍል ኖሮ ዛሬ ይህንን ባልጻፍኩ፤ በነፃነትም ባልሠበኩ ነበር:: ነገር ግን በተስፋ እንኖር ዘንድ ተስፋ በሚያስቆርጥ የመስቀል ሞት ተስፋችንን ቀጠለልን:: እኛ ታዲያ የኃጢአትን ስራ ሰቅለን በፍቅር ልንኖር ግዴታችን ነው::

  እምከመሰ አፍቀረነ እግዚአብሔር ወንሕነኒ ናፍቅር ቢጸነእንግዲህ እግዚአብሔር እኛን ከወደደን እኛም ወንድማችንን እንውደድ:: የእውነት ስራ በነገርና በአንደበት አይደለም:: ይህንን አስቡ ሌሎችን ግን አታስቡ፤ ሰላም ደኅንነት መፋቀር በመካከላችሁ ይብዛ::” እኛ በስሙ የተጠራን ካልተፋቀርን ዓለም እንዴት ሊድን ይችላል? እኛን የሚጠብቁ ብዙ ነፍሳት አሉ:: ያለፍቅር ግን ማንንም ልናሸንፍ አንችልም::

  እስመ አንተ ወወሀብከነ ሰላመከፍጥረት ሁሉ አንተ ሰላምን ሰጥተኸናልና አንተ የነገሥታትንና የመኳንንትን ቃል ስማ፤ ሁሉንም ሕዝብ ተቀበል፤ ምሕረትን የምታደርግ ይቅርታህን አሣየን:: ለካህናት ማየትን አስቀድም፤ በድንኳን ውስጥ የክህነትን ሥራ አሣያቸው፤ የተሠወረውንም ምስጢር ግለጥላቸው::” አንተን የሚያመሰግን የለም፤ ሁሉም የሥጋውን ነገር ብቻ ያስባል:: የምንመካባቸውን እነዚያን የሐዋርያት ልጆች ካህናት ስጠን፤ ያሉትን ለአንተ በመገዛት ይኖሩ ዘንድ ምሥጢርን አንተን ማወቅን ስጣቸው::

 አበው ቅዱሳን ዔሉ ውስተ አድባርቅዱሳን አባቶች በየዋሻውና በየተራራው በምድር ውስጥ ባለው ጉድጔድ ሁሉ ዞሩ፤ በቅዝቃዜ ራቁትን በመሆን በድካም ሰይጣንን አሸነፉት:: ነፃ የምታወጣ ጽዮን ቅድስት ኢየሩሳሌም ዋጋቸው ናትና አንተ ስጣቸው::” ከፍርዱ ቀን ሐዘን ዛሬ መራብን፣ መጨነቅን፣ መሠደድን መራቆትን መረጡ:: የአበው ሐዋርያትን ሕይወት ሕይወታቸው አደረጉ:: ሊሠጣቸው ያለውን መንግሥት ተስፋ አድርገዋልና::

  ኅዳጠ ሐሚሞሙ ወብዙኃ ይትፌስሑትንሽ መከራ ተቀብለው ብዙ ይደሰታሉ:: መንግሥተ ሰማያትን አገኙ፤ ወደ ቅድስት ሃገር ገቡ::” ወገኖቼ ቅዱስ ያሬድ ይለናል:- የዚህ ዓለም መከራ አያሣቅቃችሁ፡፡ ቢበዛ 80 ዓመት ነው:: ያኛው የሚመጣው አስፈሪ መከራ ቀን ግን ከጊዜ እይታ ውጪ ነው:: ዛሬ በምድር ላይ ያለው ሕማምና ፍርሃት ስቃይ ትንሽ ነው፤ ትንሽ ብቻ እንዲያውም ከሚመጣው ጋር ከተነፃፀረ ምንም ነው:: ታዲያ ምን ይበጃል? በትንሽ መከራ አልፎ ከጊዜ ቆጠራ ውጪ የሆነ ሥቃይን ማለፍ ወይስ ትንሽ ትንሽ ብቻ ተደስቶ ዘለዓለም መሠቃየት? ምርጫው የእኛ ነው፤ ቁርጥ ውሳኔው የእኛ ብቻ ነው::

 አስተጋብኦሙ እምበሀውርት ወእምጽባሕ ወእምዐረብ ወመስዕ ወባሕርከአሕጉር ከምስራቅና ከምዕራብ፣ ከመስዕ እና ከባሕር ሰበሰባቸው፡፡ ስለእርሱ ነፍሳቸውን አሳልፈው የሰጡትን በመስቀሉ ባረካቸው፡፡ ጸንተው ታግሰው ሥጋቸውን በእሳት ያቃጠሉ በራሳቸው ላይ ክብር ያላቸው ደናግል ከፍ ከፍ አሉ::

 እናዚም!በዕፀ መስቀሉ አስተጋብኦሙ ለቅዱሳን ጳጳሳትከእነርሱ እንደ አንዷ ሆና ክርስቶስ በመካከላቸው እያለ ጳጳሳትን በመስቀሉ ሰበሰባቸው፤ ሕይወትን የምታፈራ ሃይማኖትን ወሰኑ፤ ሥርዓትንም ሠሩ:: ክርስቶስ ለጻድቃኖች በነገሰላቸው ጊዜ ብርሃን የሆነች ሐዲስ ምድርን ያወርሳቸዋል፤ የንሥር ዐይን ያላያት ትዕቢተኞች ልጆች በእግር ያልረገጧት ምድር ያማረች ብርሕት የሆነች ጻድቃን የሚወርሷት ናት::” በጠባቧ በር እርሱ እያበራላቸው ገቡ:: ከሩቅ ጥቃቅኗን የሚያይ ንሥር ያላያት መታሠብ በሰው ሕሊና መሣል የማትችለውን ዓለም አወረሳቸው፤ የአባቴ ቅዱሳን አላቸው:: በትዕዛዙ ሁሉ የተገዙ ሆነዋልና:: አምላክነትን ባዕለጸጋነትን ሽተው ከትዕዛዙ ወጥተው ዕፀ በለስን አልቆረጡምና:: ዜመኛው ብዙ ይልላቸዋል:: እኔ ታዲያ በዚህች አጭር ጽሑፍ ማካተት አቃተኝ:: ስለዚህ ወደ መጨረሻ ቃሉ ዘለልኩ::

  አኃውየ በወርቅ ወኢ በብሩርወንድሞቼ በወርቅና በብር አይደለም፡፡ ወንድሞቼ ከእግዚአብሔር ዘንድ በመፈለግ ነው፤ መዓትና ጥፋትን የሚታገላት እርሱ ከኃጢአት ንጹሕ ነው::” ሰላሙን በመንግሥተ ሰማይ መቀመጡን ያድለን::

No comments:

Post a Comment