Pages

Monday, March 24, 2014

ደብረዘይት ዘሠሉስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 15 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በደሙ ፈሳሽነት በተሰቀለው መስቀል ባርኮ ድኅነትን በሰጠን፣ የአባቴ ቡሩካን ሊለን በታመነ፣ ከሚመጣው የልቅሶ ሕይወት እንወጣ ዘንድ በፍቅሩ በጠራን፣ በክርስቶስ ስም ሰላም ለእናንተ ይሁን::

 ወአንሰ በብዝኀ ምሕረትከ ዕበውዕ ቤተከእኔ በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት በመቅደስህ ፊት እሰግዳለሁ፤ አቤቱ በጽድቅህ ምራኝ::” ፍጹም ወደ ሆነችው ቤተክርስቲያን በሌሊት አንቅተህ ጠራኸን:: ነገር ግን እንገባ ዘንድ የተገባን አይደለንም፤ የአንተ ቸርነት ለሁሉ የተገባን፣ የአንተ ጸጋ ለሁሉ የተጠራን ያደርገናል እንጂ::


 እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን መድኃኒቶሙየቅዱሣን መድኃኒት ቤተክርስቲያን ብርሃን ናት፤ እኛ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች መከራን ብንመርጥ ክብርን እናገኛለን::” አንድ ጊዜ ለተሠጠ ለቤተክርስቲያን ራስ ራሳችንን እናስገዛ፤ ወደ እርሷ የሄደ ሁሉ አይደክምም::

 ከመ በጸጋ እግዚአብሔር ሃሎነ  በእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችን አለን፤ በመስቀሉ እንመካ፤ የእጁን ክንዶች በመስቀል ላይ ዘርግቷልና::” የእኛ እጆች ለምጽዋት እና ለጽድቅ ይዘረጉ ዘንድ በጸጋው በቸርነቱ ስለእኛ እጁን ለችንካር ሰጠ:: እኛ ደግሞ ከዜመኛው ጋር እናመሰግነዋለን፤ ስለሆነውም ሁሉ ምንም ልንከፍለው አንችልምና:: የሰነፎች ፊት ጻድቃን የሞቱ፣ የማይናገሩ ይመስላሉ፤ አንደበታቸው ከአምላካቸው ጋር ብቻ ነውና:: እግዚአብሔር ጻድቃኑን ካሕናቱን ያከብራል::

 ለካሕናት ሰመዮሙ መረግድካሕናትን የከበረ ድንጋይ ብሎ ጠራቸው:: እጃቸው እሳት ይዳስሳል፤ በአባቱ ፊት መስዋዕት ወልድን ይሠዋሉ፤ ማዕጠንታቸው ፈጽሞ ይወደዳል::” አቤቱ ነኩ፤ ልዑልን መስዋዕት አድርገው ለድኅነት አቀረቡ::

 ዕረፍቶሙ ለነፍሰ ጻድቃን ኃይል ወጸወንየጻድቃን ነፍስ እረፍት፣ ኃይልና መጠጊያ ክርስቶስ ነው:: እርሱን በመከተል ጻድቃን በክብር ከፍ አሉ፡፡ ጠራቸው፤ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ አላቸው፤ ምስክር የሆኑ ስለእርሱ ነፍሳቸውን አሳልፈው የሰጡ አሉ:: ኢየሩሳሌም ሃገራቸውን ዋጋቸውን ሰጣቸው፤ በየደረጃው እንደየተጋድሏቸው ክብር አወረሳቸው፤ ጥሩ ተጋድሎ ፈጽመዋልና ጻድቃን በክብር ከፍ አሉ:: የጻድቃን ነፍሶቻቸው የቅመም ተራራ ይባላሉ:: በጾምና በጸሎት የብርሃን ልጆች ጻድቃን የሕይወት ተስፋን ወረሱ::” ጥቂት ተጋድለው በእርሱ ፊት ደግሞ ምንም ተጋድለው በቸርነቱ ርስታቸውን አወረሳቸው፤ ተስፋ ወደገባላቸው ምድር ወሰዳቸው::

 እስመ ጽድቅ ቃሉ ለእግዚአብሔርየእግዚአብሔር ቃሉ እውነት ስለሆነ ለጻድቃን ሕይወትን አለበሳቸው፤ መንግሥተ ሰማያትን ብርሕት ዓለምን ሞት የሌለበትን አወረሳቸው:: ቁጥር ለሌለው ዘመን ይደሰታሉ::” ቃልህ እውነት ነው፤ እውነትህ ደግሞ ለእኛ ሕይወትን ይሰጠናል::

  ቦኡ ሰማዕት ጸባበ አንቀጸሰማዕት በጠባብ በር ገቡ፤ በሥላሴ ስም ሩጫቸውን ጨረሱ፤ የተመኙትን እና የፈለጉትን ፊት አገኙ፤ መንግሥተ ሰማያት ለእነርሱ ተዘጋጀ:: አባቶቻችን የዋሐን ጻድቃን እነርሱን ተከተሉ፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት በክብር ከፍ ከፍ አ፡፡ ወጣቶች ደናግል ይህን ዓለም ሃላፊ መሆኑን አውቀው ናቁት፡፡ ወርቅስ ከንቱ የሚያረጅ፣ ልብስም መሆኑን ተረድተው ተከተሉት፡፡ ሁሉን ነገር ለነፍሳቸው ቤዛ ሰጡ፤ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አላቸውና ጻድቃን በክብር ከፍ አሉ:: በሰማያት የሚኖር አባታቸው ለምስክርነት ይቆምላቸዋልና የብዙ ብዙ መላእክት ደስተኞች በዙሪያቸው ይቆማሉ::” ዜመኛው የጻድቃንን ሕይወት እንድንከተል ያዜማል::

  በመጨረሻም ዘመኑ ነውናንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነጾምን እንጹም፤ ወንድማችንን እንውደድ፡፡ እርስ በእርሳችን እንዋደድ፤ ጌታችን ጾምን ቀድሱ ሰላምን አድርጉ ብሏልና፡፡ በጾም በጸሎት ልዑልን እናገልግለው፤ በቀናች ሃይማኖት በልመና እና በስግደት በፊቱ እንቅረብ::” ሰላሙን እና ፍቅሩን ያድለን::

No comments:

Post a Comment