Pages

Tuesday, March 25, 2014

ደብረዘይት ዘረቡዕ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 16 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
                 
 ከሦስትነቱ በማይነጠል፣ የሞቱ በሚነሱም ጊዜ ዳግመኛ ወደ ሥጋ አዳራሽ በሚመልሳት፣ የፀሐይና ጨረቃን አካሄድ ወደ ምዕራብ በሚመልስ፣ የወይራውን ዛፍ በሚነቅለው፣ የተቀጠቀጠውንም ሸምበቆ በሚያጸናው፣ በውጪ ያለውን በሚያስባ፣ በውስጥም ያለውን በሚያስወጣ፣ በእግዚአብሔር ስም በሁሉ ላይ የሠለጠነ ነውና ለእርሱ ምሥጋና ለእናንተም ሠላም ይሁን::


 ቅዱስ ያሬድ ያዜማል! ያቺን የመጨረሻ ዕለት በዜማው ያስታውሰናል፤ ቤተክርስቲያንን መስቀሉን ያወድሳል፤ ጾማችንን በሠላም እንድንፈጽም ይመክረናል:: “ኢሳይያስኒ ይቤ ይኅድግ ኃጥእ ፍኖቶኢሳይያስ ኃጢአተኛ በኃጢአት መሄዱን ተንኮለኛም የተንኮል ምክሩን ይተው፡፡ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ይመለስ ይላል:: እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እኖራለሁ ምሕረቴንም ከእርሱ አልከለክልም አላርቅም ይላልና::” ጾማችን የሠመረ ይሆን ዘንድ አብረን ከዜመኛው ጋር ማዜም ብቻ ሳይሆን ያለፈውን ዘመን በኃጢአት የተመላለስንበትን ልንተው ይገባል:: ክፉንና ሥራውን እናርቅ፤ በእውነት በቅን ጾምን እንጹም::

 ዘትገብር የማንከ ኢታዕምር ፀጋምከቀኝህ የምትሰራውን ግራህ አትወቅ፤ የሥጋህ መብራት አይንህ ናት፡፡ ብትጾም፣ ብትጸልይ ከአፍህ ምግብ ለሌላቸው ስጥ፡፡ ረሃብተኛን ብታጠግብ ያን ጊዜ ብርሃንህ ይታያል፤ መሠረትህ አይናወጥም፤ ከጻድቃን ነፍስ ጋር በእርሱ ዘንድ መዝገብ አለህ:: በደስታ ለምነው በገሃድ ይደሰታሉ፤ ብርሃን ስለወጣላቸው መከራቸውን ይረሳሉ፤ ሙሉ ዘመናቸውን ለእርሱ ስለተገዙ ከፀሐይ ይልቅ ፊታቸው ይበራል::” ጾም ማለት በጾም ሕይወታቸውን የገፉትን በማጣት የኖሩትን መደገፍ ማለት ነው:: ከቤታችን ደጃፍ፣ ከቤተክርስቲያን በር የወደቁትን በአቅማችን ማንሳት ማለት ነው:: አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እስከፍጻሜ ድረስ:: ጌታ የሰጠንን ፍቅር ለእነርሱም ልንመግባቸው ይገባል::

  ርዕዩ ዘከመ ሜጠነ(ዘከመ አፍቀረነ) እግዚአብሔርእግዚአብሔር እንዴት እንደወደደን እንደመለሰን ተመልከቱ፡፡ ምሕረቱን በእኛ ላይ አሳየ፤ ስለ እኛ ታመመ፡፡ ጾመ፡፡ ልጁን ስለ እኛ አልማረም፡፡ ለሁላችን ነፍስ ልጁን ሰጠ፤ በመካከላችን ሠላምን አደረገ፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት አዳራሽ እንድንገባ ዳግመኛም ቸርነቱን እንድናይ በደስታው እንድንኖር ያድለን::” አቤት ወገኖቼ! ይህንን ልብ የሚነካ ዜማ በዕዝል ግዕዝ አራራይ ሲዜም ሁልጊዜ በዚያ ብሆን ከዚህ ያልሆነ ዜማ ዓለም ስለዜማ ባልተናገረበት ጊዜ ከላይ የወረደ የመላእክት ዜማ፣ ከላይ የወረደውን ቃል ከላይ በወረደ ዜማ መስማት ምንኛ ነፍስን ያለመልማት ምንኛ ያስደስታት:: ወደ ዘለዓለም መንግሥቱ ጠራን፤ ሸክማችንን አወረደልን፤ በመጨረሻዋ ሰዓት ዐርብ ዕለት ከእኔ ጋር ናችሁ፤ ያለፈው የውንብድና ሕይወታችሁ ዛሬ ተወገደ አለን:: ስሙ በእውነት ይመስገን፡፡ ሥጋችንን ለደላደለልን፣ ለጠቀመን ሁሉ ትልቅ ምሥጋናን እንሠጣለን:: ለእርሱ ምን ልንል ነው?

  ምሕረተ ነዳያን ወምስኪናን ቶስሕየነዳያንንና የምስኪናንን ምሕረት በልባችን ውስጥ ጨምር፡፡ ለሕዝብህ ሰላምህን ስጠን፡፡ ጎራችንንም መግቢያችንን መውጫችንን በሰላም አስጊጠን፤ የሰላም ንጉሥ ሠላምን ስጠን::” አሜን!

No comments:

Post a Comment