Pages

Sunday, March 30, 2014

ገብር ኄር ዘሰኑይ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 22 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ባሮችን የዋሃን በሚያደርገው፣ ቸርነት የባሕርዩ ሲሆን ከእርሱ ሳይከፈልበት እኛን ቸር የሚያሰኝ፣ የልዑላን ወዳጅ፣ የልባችንን ክፋት ሳይቆጥር የምናፈራውን ፍሬ በልባችን እርሻ የሚዘራ፣ ለዘመናት ያልተገራውን ማንነታችንን በቃሉ ዝናምነት በሚያረሰርሰው በእርሱ ስም ሰላምታዬ ይድረሳችሁ::


 አዕምሩ አዕምሩ ከመ በጽሐ ጊዜሁ ለነቂሕ እምንዋምከእንቅልፍ የመንቂያው ጊዜ እንደደረሰ ፈጽማችሁ እወቁ:: እንግዲህ ሕይወታችን ደርሳለች፤ ይህችም ተስፋችን ነች:: ሌሊት አለፈ፤ ቀንም መጣ፡፡ የጨለማ ስራን ሁሉ ከላያችን ላይ እናስወግድ፤ በብርሃኑ እንመላለስ::” ቅዱስ ያሬድ የድካማችንን እና የስንፍናችንን ነገር አስቀድሞ ተረድቶ ይሆን በሳምንቱ የመጀመሪያ የሥራ ቀን ከእንቅልፍ የመንቂያው የሥጋን ድካም የነፍስንም እንዲሁ ተው፤ በክርስቶስ ብርሃንነት ተመላለሱ የሚለን? በጠዋት ተነሱ፤ ድካምንም ወደማታመጣው ቤተክርስቲያን ገስግሱ፤ ቤተክርስቲያንን የያዘ ምንጩ ሙሉ በሆነ ጊዜ የሕይወት ውሃን ይቀዳል:: ዕዝራ ያያትን፣ ዳዊት የዘመረላትን በጠዋት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱሥ ስም እንሳለማት፤ አምላክ ሁልጊዜ ከእርሷ ጋር ነውና::

  ወትቤ ጽዮን ትረስዓኒኑ እግዚአብሔር ተኃድገኒኑጽዮን አለች፤ እግዚአብሔር ሆይ ትረሳኛለህን? ትተወኛለህን? ጽዮን ሆይ አልረሳሽም፤ ከሆዷ የወጡ ልጆቿን እናት ትረሳለችን? ግድግዳዎችሽን እኔ በእጄ አቆምኩ፤ ሰማይን ዘረጋሁ ምድርን መሠረትኩ፤ በመስክሽ መካከል ተመላለስኩ፡፡ የእስራኤል ቅዱስ ይላል፡- ጽዮን ሆይ ፈጽመሽ ተነሺ፤ ኃይልንም ልበሺ፤ ስምሽም ጽዮን ነው:: እናት ርግብ በክንፎቿ ልጆቿን እንድትሰበስብ ጽዮን ሆይ ልጆችሽን ምዕመናን የፈጠረሽ እንዲሁ ይሰበስባቸዋል አይተዋቸውም::

  ንሴፎ ንርከብ ብዕለ ጸጋከለምርጦችህ ያዘጋጀኸውን ለሁሉ የሰጠኸውን የጸጋህን ሃብት የምሕረትህን ብዛት ተስፋ እናድርግ፡፡ በሰቃዮችህ ሃገር በኢየሩሳሌም ረዳት አምላክ ትሆናቸው ዘንድ የመስቀልህን ኃይል አሳየህ፡፡አቤቱ ተስፋችን ምሉዕ ነው፤ በኢየሩሳሌም ጎልጎታ ሁሉን ለእኛ ስትል ፈጽመህ ተፈጸመ ብለሃልና::

 ጾም ቅድስት ትሜሕሮሙ ለወራዙት ጽሙናቅድስት ጾም ለወጣቶች ዝምታን ታስተምራለች፡፡ ይህች ጾም ቅድስት ናት፡፡ በዚህች ጾም ሙሴ ሕገ እግዚአብሔርን ተሰጠ፤ በዚህች ጾም ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በዚህች ጾም ዳንኤል ከአንበሶች አፍ ዳነ፤ በዚህች ጾም ሶስና ከአይሁድ መምህራን እጅ አመለጠች፤ በዚህች ጾም ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቆመ:: ጳውሎስም አለ: እንግዲህ ወንድሞቼ በጾምና በጸሎት ትጉ::” የኃጢአትን ስር ከወጣቶች የምታርቅ፣ ለሕጻናትም ይሁን ለአረጋውያን ትዕግስት የምታስተምር ጾም ናት::

 ኢያደሉ በውስተ ፍትሕበፍርዱ የማያዳላ፣ በክፉ ነገር የማይመልስ፣ ነገር ግን በየዋሕ ፍርድ ይፈርዳል:: በክንዱ ፈረደላቸው፤ በምሕረቱ አጸናቸው፤ በአፉ በከንፈሩም ቃል ገሠጻቸው:: የእውነት ፈራጅ በመንበርህ አለህ::” አቤቱ በፍርድህ ቅንነት የሞላ የምናመሰግንህን ስማን፤ በፍርድ ወንበር በተቀመጥክ ጊዜ ቸር አገልጋይ ተብዬ እጠራ ዘንድ አድርገኝ::

  በፍስሐ ወበሰላም ወበተፋቅሮበደስታ በሰላም በመፋቀር ጠብቀን፤ አቤቱ ተለመነን፤ ንብረታችንም በጸጥታ ይሁን፤ አቤቱ ይቅር በለን፤ ዓለምስ አታበሳጨን::” ሰላሙን ስጠን::

No comments:

Post a Comment