Pages

Friday, March 28, 2014

ገብር ኄር ዘሰንበተ ክርስቲያን



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 20 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በወለደ እና ባሰረጸ ግን ባልተወለደ በእግዚአብሔር አብ ስም፣ በተወለደ እና ባልወለደ በእግዚአብሔር ወልድ ስም፣ በሠረጸ ግን ባልተወለደ እና ባልወለደ በመንፈስ ቅዱስ ስም፤ በማይበደር ሦስት፣ በማይደኸይ ባዕለ ጸጋ፣ ሳይዘገይ ዓለምን ከሌለበት ባመጣ፣ የሃይማኖትን ኃይል በምዕመናን ልብ በሚያኖር፣ ለሁሉ ለእያንዳንዱ እንደየስራው በሚከፍል በእርሱ ስም ሰላምና ቸርነቱ ይብዛላችሁ:: (መጽሐፈ ምሥጢር)


 ዛሬ ስድስተኛውን የታላቁን ጾም ሳምንት እንጀምራለን:: እንደሌሎቹ ሳምንታት ሁሉ ታዲያ ይህንንም ሳምንት በታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ድርሰት በሆነው ጾመ ድጓ ስያሜ እንጠራዋለን:: ሊቁ ሲጀምር በተናገረው የድርሰቱ ቃል ተወስዶገብር ኄርእየተባለ ሳምንቱ ይጠራል:: መልካም አገልጋይ ማለት ሲሆን ማቴ፡ 2514 ባለው ታሪክ ተመስርቶ ዜመኛው የዛሬ አንድ ሺህ አምስት መቶ አመት ገደማ ወንጌሉን እያዜመ ከብሉይና ከሐዲስ ከአዋልዱ እያጣቀሰ ከልብ በማይወጣ ቅላጼ አስተምሮናል:: እኛም የአባታችን ልጆች ለመሆን የማንበቃ ቢሆንም ከእርሱ በረከት ያሳትፈን ዘንድ እየለመንን የተመረጡ ጥቂት ቀለማትን እንመለከታለን:: ከመልካም አገልጋዮች ከመላእክቱ ጋር ያሰልፈን::

 ገብር ኄር ወገብር ምዕመን ገብር ዘአስመሮ ለእግዚኡቸር እና የታመነ አገልጋይ፣ ጌታውን ያስደሰተ አገልጋይ፣ በአምልኮህ መልካም አደረግህ፡፡ ቸር አገልጋይ አንተ ምስጉን ነህ::” እንደምናየው የሰንበት ድርሰቱን ገብር ኄር ብሎ ይጀምራል፡፡ ከዚህም ስያሜውን አገኘ:: ስለዚህ አገልጋይ እያዜመ የሚነግረንን እንስማ፡፡አይቴ ተሃድር ጥበብጥበብ ወዴት ታድራለች? የምክርስ ሃገሯ ወዴት ነው? ባሕር አለች በእኔ ዘንድስ የለችም፤ ጥበብና ምክርስ እግዚአብሔርን መፍራት ከክፉ ነገር ሁሉ መሸሽ፤ ይህ በእውነት ዕውቀት ነው::” ቸር አገልጋይ ለመባል በእውነት ዕውቀት እና ጥበብ ያስፈልገዋል:: ጥበብ እና ዕውቀት የጎደለው ግን ክፉ ባሪያ ይባላል:: ስለዚህ ሊቁ ይመክረናል፤ በዜማ፡-ኢንኩን ከመ ገብር እኩይጌታውን እንደሚያስቆጣ ክፉ አገልጋይ አንሁን፤ ጌታውን እንደሚያስደስት ቸር አገልጋይ እንሁን፤ ሰንበትን ላከበራትና ለቀደሳት ምስጋናን እናቅርብ::” እናስ እንዲህ ያለ ሰው እንሆን ይሆን? በመጣስ ጊዜ ምግባር ያገኝብን ይሆን?

 መኑ ውእቱ ገብር ኄር ጠቢብጥበበኛ ቸር እና የታመነ አገልጋይ ማነው? እንዲህ ያለውን ሲሠራ ዋጋውን ያገኛል፤ ቸር አገልጋይ ምስጉን ነው:: በእውነት በጥበብ የሚጓዝ ጌታው ሲፈልገው በተገቢው ቦታ የሚገኝ እጁን ዘርግቶ የሚቆይ ጌታው ሊሠጠው ሲመጣ በዚያው ሊቀበል የሚገኝ ነው:: ጌታውስ ሰጥቶት የተቀበለውን ስለጌታው ክብር የፈጸመ ማነው? እርሱ ይሾማል::

 ገብር ኄር ወገብር ምዕመን ዘበውኁደ ምዕመነ ኮንከቸር እና የታመንክ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንክ ሆንክ በብዙ እሾምሃለሁ፤ እውነትን ወደድክ፣ አመፃን ጠላህ በሰላም ፊትህ ልቁም ከትዕዛዙም አታርቀኝ::” ዛሬ ማነው ትንሽ ሠጥቶ ብዙ የሚሾም? በጥቂት ሥራችን ብዙ የሚሸልመን ማነው? ስለብዙ ስራችን እንኳን ደሞዛችንን አጥተናል:: እርሱ ግን ይለናል በዜመኛው አፍ: እናንተ ያዘዝኳችሁን ስሩ እኔ ለእናንተ ሽልማትን ስጦታን አበዛላችኋለሁ::

 አንሥአ አዕይንቲሁ ወይቤሎሙ ብፁዓን እሙንቱ አበዊነአይኑን አንስቶ አላቸው አባቶቻችን እነርሱ የተመሰገኑ ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: በመልካም ስራ ለነፍሱ ቤዛ የሆናት፣ በምግባሩ ራሱን ዝቅ ያደረገ፣ በኃጢአት ስራ ፊቱን ያልመለሰ፣ ልቡ የጸሎት መመላለሻ የሆነ፣ ንስሐው ወደ ሰማይ ያረገለት፣ ኃጢአትን የተሻገራት፣ ስለ ተስፋ ነፍሱን የተወ፣ ጆሮው ያልሰማ ዐይኑ ያላየ፣ ይህንና ይህን ሲሰራ ጌታው ያገኘው ቸር አገልጋይ ምስጉን ነው::” አዎን ሊቁ ቸር አገልጋይ ይህ ነው ይለናል:: በሁሉ ነገሩ ዳግመኛ የወለደውን ዳግማይ አዳም ክርስቶስን የመሠለው እርሱ ምስጉን ቸር አገልጋይ ነው::

  ጹሙ ወጸልዩ ከመ አግብርት ተቀነዩጹሙ፤ ጸልዩ፤ እንደ አገልጋዮች (ባሮች) ተገዙ፤ በሚመሰገንበት ገንዘብ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አድርጉ፤ መልካም አስቡ፡፡ ሰንበቶቹን አክብሩ (ዓራራይ)፡፡ እንግዲህ እንደ ቸሮች አገልጋዮች ሁኑ፤ ወደ ሰማያዊት ሰርግ እስከሚገቡ ጌታቸውን እንደሚጠብቁ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች አማኞች ሁኑ፤ ሰንበትን ያከብሯታል::” የሰርጉን ቀን ከመብራት ጋር ሙሽራውን የጠበቁትን ምዕመናን ሁኑ፤ ምግባርን ሠርታችሁ ቸር የሕይወታችሁ ቤዛ የሕይወታችሁ አገልጋይ ሁኑ ይለናል::

 ብፁዕ ውእቱ ገብር ኄር ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይጌታው በበጎ ስራ መልካምን ሲያደርግ ሰንበትን ሲያከብር የሚያገኘው ቸር አገልጋይ ምስጉን ነው::” ተመልከቱ! መልካም አገልጋይ የተባለው ቆሞ የሚቀድሰው፣ ቆሞ የሚሰብከው፣ የሚያስተምረው፣ በቤቱ ሲሮጥ ሲያስተናግድ የምናየው ብቻ አይደለም:: ዜመኛው እንደሚለን ለጌታው የታመነ፣ በበጎ ስራው የጸና፣ አምላኩ በጠራው ጊዜ ስንቁን አዘጋጅቶ የጠበቀ፣ አምላኩ የሰጠውን የድኅነት ወንጌል ሳይቀብር በሕይወቱ ፍሬ አፍርቶ የተገኘ እንደሆነ ነው::

 ከመ ገብር ኄር ለእግዚአብሔር ተቀነዩ በኵሉ ጊዜበሁሉም ጊዜ፣ በሁሉም ሰዓት፣ በሁሉም ቀን፣ በሁሉም ሌሊት እንደ ቸር አገልጋይ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ በንጹሕ ልብ ጹሙ ጸልዩ፤ ሰንበትን በእውነት አክብሩ፤ ለወንድማችሁ መልካምን (በጎን) አስቡ፤ አባታችሁ ለእናንተ ያስባል፡፡ነፍሳችሁን ከኃጢአት ነፃ አውጧት::”

  የሰንበት ድርሰቱ ብዙ ቢሆንም ለዛሬ የተመረጡ ቃላቱን በእርሱ የፍጻሜ ቃላት ልሰናበት፡፡ንዕቀብ ጊዜሁ ለመርዐዊ ከመ ንባዕ ምስሌሁወደ ሙሽራው ደስታ እንገባ ዘንድ ጊዜውን እንጠብቅ፤ የዋሃንና ቸሮች እንሁን፤ ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን፤ ሰላምና ምክር በእናንተ ወንድሞቼ መኻል ይሁን፤ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠብቃችሁ:: ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልብ ያልታሰበውን የቅዱሳን የርስታቸውን ሀብት የሰላም ማደሪያ ይክፈላችሁ::” አሜን!

No comments:

Post a Comment