Pages

Tuesday, March 4, 2014

ቅድስት ዘረቡዕ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 25 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ
ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ
 ‹‹ ሐዋዘ ብርሃነ እግዚኦ ነግሐ ነቂሐነ እምንዋም ንጊሣ ለቤተክርስቲያን ኃበ የኃድር ብዕለ ስብሐቲሑ ንስአል እም ሐቤሁ ረድኤተ ወሕይወተ ኩሉ ዘጌሰ ወመጽአ ኢይጻሙ - አቤቱ ያማረ ብርሐንን ስጠን፤ ነጋ ከእንቅልፋችንም ነቃን፤ የምስጋናው ሐብት ወደሚያድርባት ወደ ቤተ-ክርስቲያን እንገስግስ፤ የሁሉ ህይወት ከሚሆን ከእርሱም እርዳታን እንለምን፤ ወደ እርሷ የገሰገሰ የመጣም አይደክምም፡፡›› ቀኑን ሰላም አውሎ ሌሊቱን ሰላም አሳድሮ ትናንት የነበሩት በሌሉባት ዛሬ ነገን ተስፋ እናደርግ ዘንድ ጠብቆ ለዚህ ያደረሰንን አምላካችንን አመስግነን ቅዱስ ያሬድ እንደሚነግረን ስለማይነገር ስጦታው የምንከፍለው የሌለን በቤቱ በመገስገስ ህይወትን ለምነን አመስግነን በደስታ እንኖር ዘንድ አምላኬ እና መድኃኒቴ በሚሆን በክርስቶስ የመድኃኒቴ ዘውድ በሚሆን በአባቱ የቅድስናዬ መገኛ በሚሆን መንፈስ ቅዱስ በከበረች እናቴ የገነት ሙሽራ ድንግል ማርያም እንዲሁም ሰላማቸው በበዛ በማኅበረ ጻድቃን ስም ሁሉ ሰላማችሁ ይብዛ እላለሁ፡፡


 ዛሬም እንደወትሮው ከዜመኛው ጋር በዚች አጭር ጽሁፍ በገለጠልን መጠን አምላክን እያመሰገንን እንቆያለን፡፡ ‹‹ብርሐነ ህይወት ዘኢይጸልም ጸግወነ እግዚኦየማይጨልም የህይወት ብርሀንን ስጠን፤ ከመገዛት ወደ ነጻነት ከጨለማ ወደ ብርሃን ምራን፤ በላይ በሰማይ በታች በምድር ከአንተ ሌላ አምላክ የለምና በነጋ ጊዜ ፍጹም ምስጋናን ወደ አንተ እንልካለን፡፡ እግዚአብሔር ሆይ እንዳንተ ይቅር ባይ ማን ነው?›› ቸርነቱ በዝቶ የሀጢአታችንን ተራራ እንደ ደን የሸፈነልንን በበደልና በኃጢአት ጨለማ ስንኖር ወደ ሚደነቅ ብርሃን ለጠራን ለዚህ ዓለም ነገር ለገንዘብ፣ ለምኞት፣ለዝሙት፣ ለዕውቀት፣ ለውዳሴ፣ ለውበት፣ ለሥልጣን፣ ተስፋ ላደረግነውና ለቀጠርነው ኃጢአት ሁሉ አውቀን የማናውቀውን ነገን ንስሀ እንገባለን በማለት ሳናውቀውም ለስጋችን አድልተን ባሮች በሆንን ጊዜ የሰላም አባት ድምጹን አሰማን፡፡እንግዲህ ባሮች አልላችሁም፤ አሁን ልጆቼ ናችሁ፤ ነጻነታችሁም በእኔ መታሰር ተቀይሮላችኋል፤ በላይም በአርያም በታችም በጥልቁም እኔ አምላካችሁ ነኝና ምስጋናን ለእኔ ስጡ” ይላል እያለ ቅዱስ ያሬድ በሚጥም ቃና እያዜመ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ይጠራናል፡፡

 በዘመኔ ሁሉ አቤቱ ማዳንህን እውነትህንም እናገራለሁ፡፡ ሁልጊዜም አመሰግንሃለሁ፡፡ አቤቱ ማረኝ፤ አቤቱ ይቅር በለኝ፡፡ በነጋም ጊዜ ይቅር ትለኝ ዘንድ ቃሌን ስማ” እያለ ፍጹም በሆነ ልብ መሰበር ያዜማል፡፡ የጾም ነገር የልብ መሰበር የስጋ መድከም የነፍስ ከፍታ ነው፡፡
 ማረን፤ አቤቱ ማረን፤ ይህ ሁሉ የሆነው ስለኛ በደል ነው፡፡ ነገስታት ቀንበር ቢያጸኑብን፣ የዓለም ውጣ ውረድ እንደ ውጋት ቢያስጨንቀን፣ ለነፍሳችን የሚሆን ጽድቅን መስራት ቢያቅተን፣ በቤትህ እለት እለት ባንመላለስ፣ ቃልህን በልባችን ባንጽፍ፣ ይህ ሁሉ ስለኛ ድካምና ኃጢአት ነውና ማረን እንበል ከዜመኛው ጋር፡፡ ለባህር ሰላምን የምትሰጥ፣ ማእበሉን ጸጥ የምታደርግ፣ የህይወታችንን ማእበል ጸጥ አድርግልን እንበል፡፡ ሀገረ እግዚአብሔር ጽዮን ቤተ-ክርስቲያንን አስባት፡፡

 ‹‹ወይእዜኒ አንትሙ አኃውየ ቀድሱ ጾመአሁንስ ወንድሞቼ በትዕግስት በሀይማኖት በምርጫ ጾምን ቀድሱ፤ የጾም ጥቅም ታላቅ ነውና፡፡ ቅድስት ጾም ከሀጢአት ነጻ ታወጣችኋለች፡፡›› የቸርነቱን ስራ ካዜመልን በኋላ ያው እንደተለመደው ዋናው ቁም ነገር ጾም ነውና ሰዓት በመቁጠር ደቂቃ በማሸጋሸግ ሳይሆን በጾሙ በመከራው ባሳየን ትእግስት እምነት እንጹም አለን፡፡ እንደዚያ ሲሆን የጾም ጥቅም ታላቅ ይሆናል፡፡

 ‹‹ጾም ልጓም ፍሬሐ ጥዑምጾም ልጓም ናት፤ ፍሬዋም ጣፋጭ ነው፡፡ ጾም ትንሽ አትምሰለን›› ይለናል ዜመኛው፡፡ ይህ ስለ እኛ የተጻፈ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ጾምን በልምድ እንጂ እንደ ህይወት የሚተገብረው ሰው አይታይም፡፡ የቁርሱን አሸጋሽጎ በምሳና በእራት የስጋውን አሸጋሽጎ በአሳታዲያ የተጾመው በምንድን ነው? የዚችን ጾም ጥቅም ማን ተረዳ? ለእኛ ብቻ ሳይሆን እንደተናገርነው ድሆችን የምናስብበት መሆን አለበት፡፡ የቁርሳችንን ለድሆች መስጠት አለብን፡፡ ያን ጊዜ ቁርሳችን የጾም ጊዜ ምጽዋት ሆነች ማለት ነው፡፡ የስጋ ሳይሆን የነፍስ ቁርስ አደረግናት ማለት ነው፡፡

 ዜማውን ቀጥሏል ኢትዮጵያዊው ቅዱስ! ስትጾሙ አስተውሉ ‹‹ ኅድጉ አበሳ ለቢጽክሙ እስመ እግዚአክሙ አርአያ ወሀበክሙየወንድማችሁን በደል ተውለት፤ ጌታችሁ ምሳሌ ሆኗችኋልና፡፡ ስለ እናንተ ታመመ፤ ጾመ፡፡ እርሱ ግን የሁሉ አባት ነው፡፡ እናንተስ የምድሩን ናቁ፤ በላይ ያለውን አስቡ፡፡ በዚያ ክርስቶስ ባለበት ለአገልጋዮች የሚገባን ሀብት አከማቹ፡፡ የቀደሙ አባቶች በሰላም በጾም ወደ ህይወት ገቡ፡፡ ሐዋርያው እንደተናገረው በስጋው የታመመ በመቅሰፍት መዓቱ ላይ ሰለጠነ፡፡›› እንዲሁ አትጹሙ ተብሏል፤ ሂዱ የተጣላችሁትን ታረቁ፤ ቅሬታችሁን አስወግዱ፤ የሰማይ አባታችሁ ህሊናን ያውቃልና ለዚህ ዓለም በተሰጠ ልቦና አትጹሙ፡፡ ታረቁ ለራሳችሁ ሰላምን ግዙ፡፡ ያን ጊዜም እንደቀደሙ አባቶች ወደ ፊቱ በሰላም ትቀርባላችሁ፡፡ ወደ እርሱ መሄድን ትናፍቃላችሁ፡፡ ፍርሃታችሁ ሞት አይሆንም፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ያሬድ ‹‹ ኢትፍርህዎ ለሞት ፍርህዋ ለሐጢአትሞትን አትፍሩ፤ ሀጢአትን እንጂ፡፡ ሞትስ ከላይኛው መንግሥት ኑሮ አይለያችሁምና፤ ከምድሩ እንጂ›› ያለን፡፡

 በመጨረሻም ከአባቴ ጋር እያዜምኩ እሰናበታችኋለሁ፡፡ ‹‹ኖላዊነ ሔር ዘኢትነውም ሰላመከ ሀበነ- የማትተኛ ቸር ጠባቂያችን ሰላምህን ስጠን›› ፡፡

 ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ፡፡ አሜን በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን፡፡ አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment