Pages

Monday, March 3, 2014

ቅድስት ዘሠሉስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ

ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

 ከልዑላን በላይ ልዑል፣ ከቅዱሳን በላይ ቅዱስ፣ የእርሱን ቅድስና ሌሎች ሲጠሩበት የእርሱ የማይከፈልበት፣ በአንድነት የሚመሰገን፣ በሦስትነት የሚቀደስ፤ ሠላምን በሞቱ፣ የገዛ ህይወትን በደሙ የመሰረተ፤ ቤቱን በማይፈርስ የሃይማኖት ምስክርነት ላይ ያነጸ፣ ቅዱሳን ተብለን ልንጠራ አባታችን ልንለው ሥልጣንን የሰጠን፣ ጸጋን ለሁሉ እንደችሎታ በሚያድለው አምላክ ስም ሁላችሁ በያላችሁበት ሰላሙ ይደረግላችሁ፡፡


 ዛሬ አባታችን እንደተለመደው የቅድስና ሳምንት ነውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እየቀደሰ ለእኛም የቅድስና መንገድ ልቡናን ነፍስን ደስ በሚያሰኝ ዜማው ያስተምረናል፡፡ ከድርሰቱ ጥቂት ቃላትን እነሆእነግረክሙ አኀውየ ጸጋ እግዚአብሔር ዘተውህበከብዙ መከራ ህማማቸው ይልቅ ደስታቸው የሚበዛ ስለሚሆን ለመቄዶንያ ቤተክርስቲያን የተሰጠውን ጸጋ እግዚአብሔር እነግራችሁ ዘንድ ወንድሞቼ ስሙኝ” 2 ቆሮ 8÷1-3፡፡ ከዚህ በፊትም እንደነገረን በዚህ ፆም ወቅት እና በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያንን ያወድሳል፡፡ከእናንተ ጋር ለዘላለም አለሁ” ያለው ክርስቶስ እርሱ ራሱ ነው፡፡ የሚኖረውም በእርሱ ስም በተመሰረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሚኖሩ ሁሉ ነው፡፡ ያኔም በመቄዶንያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ስለመከራቸው ሁሉ የመከራቸው ተቀባይ የሆነውን መከራቸውን ባርኮ የሰጣቸው ክርስቶስን አስበው ፍፁም እንደተደሰቱ በቤቱ ሆነን ስለሚመጣብን መከራ ሁሉ ዋጋችን እጥፍ ነውና እንደሰት እናዜምም ዘንድ ሊቁ ወንድሞቼ ስሙኝ ይለናል፡፡

 “… ዘአንቃህከነ እምንዋምከእንቅልፋችን ያነቃኸን፣ ለስግደት ወደተሰራች ወደዚች ቤተ ጸሎት ያስገባኸን፣ ታስተስርይልን ዘንድ ገንዘብህ አድርገን፡፡ ዋጋችንንም ስጠን፤ የሰራኸንን የእጆችህን ሥራዎች አታጥፋንበማለት ምስጋናውን ጸሎቱን ይቀጥላል፡፡ ሸክላ ሰሪ የሰራውን መልሶ እንዲያፈርስ የተሻለ ወይም የከፋ አድርጎ እንደሚሰራው የእጆችህ ሥራ ነንና እባክህ ለአንተ የምናስደስት እንሆን ዘንድ እንደገና ሥራን፡፡ እኛ ለራሳችን ምንም ነን፡፡ ባለን ነገር እንመካለን፡፡ በሀብት፣ በውበት፣ በሥልጣን፣ በዕውቀት፣ በኃይልሁሉም ግን የአንተ ናቸው፡፡

 “… ጥበብ ትሄይስጥበብ ከብዙ ሀብት ትሻላለች፤ ምጽዋትም ብዙ ወርቅ ከማከማቸት ትሻላለች፡፡በዚያ ሁሉ ሳይሆን አንተን መፍራት በሚሆን የጥበብ መጀመሪያ ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን የማስብበት ዕውቀትን ስጠኝ፡፡ ስለሆነው ሁሉንሴብሕ ወንዜምርበፆምና በጸሎት አመሰግናለሁ እዘምርምአለሁበማለት ከእርሱ ጋር ጌታን እንድናመሰግን ይጋብዘናል፡፡

 ናሁ በጽሐ ጊዜ ለተቀንዮለእግዚአብሔር የመገዛት ሰዓት እነሆ ደረሰ፤ በእግዚአብሔር ፊት የመስገድ የይቅርታ ጊዜ ነው፡፡ ወንድሞቼ ከክፉ እንራቅ፤ መልካምንም እናጽና፤ ጠላታችሁን አስደስቱ፤ በእርሱ ዘንድ መፋቀርን አጽኑ፤ ሁላችን ስንኖር ወደ ክርስቶስ ግዛት እንቅረብ፤ እንግዲህስ መልካም አድርጉ፤ እውነትንም ጠብቁ፡፡ እርስ በእርሳችሁ ተፋቀሩ፤ የእርሱ አንድ አካል ብልቶች ናችሁና፡፡ በመልካምና በቀና ምግባር እናመስግነው፡፡ የዚህ ዓለም ትካዜ አያሳስባችሁ፡፡ ትካዜያችሁስ ፆምና ጸሎት ይሁን፤ እግዚአብሔር ያንን ይወዳልናብሎ የዕለቱን መልዕክት በአንድ አንቀጽ ጠቀለለልን፡፡ የመገዛት ሰዓት፣ የፆም ሰዓት፣ የጸሎት ሰዓት፣ የስግደት ሰዓት፣ የምጽዋት ሰዓት ደረሰ አለን፡፡ በእውነት ይህ ሁሉ ሌላ ጊዜ አያስፈልግምን? አይደለም፡፡ እንደተለመደው የዛሬ መልዕክቱ ጠላታችሁን ውደዱ ሳይሆን ጠላታችሁን አስደስቱ ነው፡፡ መውደዳችንን በቃልና በጩኸት ሳይሆን በተግባር ግለጹ ይህም አሁን ነው ይለናል፡፡ በእውነት አሁን ብቻ ነውን? አይደለም፡፡ የአንዱ የቤተክርስቲያን ራስ የክርስቶስ አካል ሆናችሁ የተሰራችሁ ብልቶች ናችሁና እርስ በእርሳችሁ ተስማሙ፡፡ ብልት እርስ በእርስ ይፈላለጋልና፡፡ ዓይን ጆሮ አታስፈልገኝም አይልም፤ እጅም እግርን አልፈልግም አይልም፡፡ እነዚህ ተስማምተው ሲኖሩ ጤነኛ አካል ይኖራልና፡፡ ስለዚህም እርስ በእርስ እንደነዚህ አካላት በህብረትና በፍቅር ኑሩ ይላል ሊቁ፡፡ አሁን ብቻ ነውን? አይደለም፡፡ ይህንን ሁሉ ህይወት ሁልጊዜም ኑሩት፡፡ ይልቁንም አሁን በፆም ወቅት አብልጣችሁ ያዙት፡፡ እግዚአብሔር ያንን የሚወድ ነውና፡፡

 ምክርህን አባቴ ከአንተ በሆነ ከላይ በተቀበልከው ዜማ ብሰማ እኔም ባዜመው ቃላቶቼ ሁሉ ኃይል ባገኙ ነበር፡፡ ዓይኔም ዕንባን ባላቋረጠ፣ ልቤም ወደ አንተ ብቻ ነፍሴም ከመላእክቱ ጋር የወደፊት ተድላዋንና ህይወቷን በጎበኘች ነበር፡፡ የአንተ ምስጋና አያልቅም፡፡ፀሐይኒ አዕመረ ምዕራቢሁፀሐይም መግቢያዋን አወቀችብሎ ዜመኛው እንዳዜመ እና የዕለቱን እንደፈጸመ እንደ ፀሐይ የዕለቱን ከአንተ የተቀበልኩትን ዜማ ልኬን አውቄ ወደ ፍፃሜው አድርሼዋለሁ፡፡

 ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ፡፡ አሜን በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

1 comment:

  1. ዲ/ን ስመኝ
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ እግዚአብሔር ጸጋውን አብዝቶ ያድልልን፡፡

    ReplyDelete