Pages

Sunday, March 2, 2014

ቅድስት ዘሠኑይ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ
ጸልዩ ከምቅድመንባበ ዝንቱ ክርታስ

ይኄይሰኒ ሕገ አፉከ እምአእላፍ ወርቅ ወብሩር ወይጥእም እመዐር ወሶከር - ከብዙ ወርቅና ብር የአፍህ ህግ ይሻለኛል፡፡ እንደ ስኳርና እንደ ማር ይጥማልና፡፡በሚጥም አንደበቱ ጌታ አክብሮ አንደበቱን ያጣፈጠለት ዜመኛ የሰኞ ቅድስት ድርሰቱን ሲጀምር ባዜመበት ቃል ጀምረንንጉሰ ሰላም ሰላመከ ሀበነ - የሰላም ንጉሷ ሰላምህን ስጠንብለን እኛም ከእርሱ ጋር በማዜም በተሰጠን ሰላም ከዛሬ የድርሰቱን አንዳንድ ቃላትን እንላለን፡፡


 ዛሬ ቅዱስ ያሬድ ስለ ቤተክርስቲያን ቅድስናና በውስጧም ስላለን ስለእኛ በምስጋና መቀደስ ከሞላ ጎደል በድርሰቱ አስቀምጧል፡፡ ይህችን ቤተክርስቲያን አሁን እዚያው ሆኜ በአባቴ ዜማ እየቀደስኳት ከእርሷ እራስ ከሆነው አምላካችን ቅድስናን ባገኝ እወድ ነበር፡፡ በዚያ ባልሆንም በተሰጠኝ ኃይል መጠን ግን እዚህም ሆኜ ቢሆን ከአባቴ ጋር ማመስገን ነፍሴ ትሻለችና ከእናንተ ጋር ይኸው ጀመርን፡፡

 ነአኩተከ እግዚኦ አምላክነ - የቀን ጠባቂ ሌሊትን የምታኖረን በኪሩቤል ላይ ያለህ ወደ ታች የምታይ አቤቱ አምላካችን እናመሰግንሀለን፡፡እንደተናገርኩት አባታችን ሁለተኛ የጾሙን ሰኞ በምስጋና ጀምሮታል፡፡ ትናንት ቅድስት ያላትን ቅዱሳን ሁኑም ያለንን በቅድስና ጎዳና በምስጋና ሕይወታችሁን አድሱ እንጂ በማማረር አምላክን አታሳዝኑት ሲለን ነው፡፡

 ይቀጥልናነያ ጽዮን ቅድስት . . . መድሐኒት ቅድስት ጽዮን ሆይ ነይ ቅድስት ጽዮን ሆይ ነይ በሰማይ ያለህ አባታችን ምስጋና ይገባሀልእያለ የአባቷ ልጅ ለሆነችው ቤተክርስቲያን ጽዮንም እንዲሁ ምስጋናን ወደ ላይ ወደ አርአያም ይልካል፡፡

 ነግሀ ሰላመ ሃበነ . . . - ነጋ በጠዋትም ሰላምህን ስጠን በደስታ እና በፀሎት እንዋል፡፡ቀን ዛሬ ለእኛ የተሰጠች የእግዚአብሔር ፀጋ ናት፡፡ ይህችንም ስጦታ ከእርሱ ጋር በመነጋገር እንጂ እንደ ከንቱ ሰው አፍን ባለመከልከል እንዳንውል ከጠዋት ጀምሮ ቀኔን ሁሉ በፀሎት ካንተ በሚሆን ደስታ እውል ዘንድ ስጠኝ፡፡ደስ ያለው እርሱ ይዘምርያዕ 5÷13 በደስታ በዜማ በሆነ ፀሎት ቀኑን አሳልፍ ዘንድ ፍቀድልኝ ይላል ዜመኛው ደስታውን በዜማ እያሳለፍን፡፡

 ዓይ ይእቲ ዛቲ እንተ ታስተርኢ . . . ይህች ከሩቅ እንደ ብርሃን የምትታይ እንደ ፀሐይ የምታበራ ማን ናት? ቅድስት ሀገርን ሙሴ አያት እዝራም ተናገረላት ዳዊትም ዘመረላት፡፡ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሩቅ አይተው ዘመን ተሻግረውያቺ” ብለው ተመለከቷት፤ ተነበዩላት፤ ዘመሩላት፤ ቅዱስ የሆነው ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ራሷ ሆኗልና እንደ ጸሐይ ብሩህ ሆና ተገላጠችላቸው፡፡

 በውስጧ ያሉትም ስለዚህ ነገር ከቤተክርስቲያን ከራሷ ጋር እንዲህ እያሉ በዜመኛው ቋንቋ እንዲህ ያመሰግናሉ፡፡ ርእዩ ዘከመ አፍቀረነ ወሐረየነተመልከቱ እንዳፈቀረን፤ እንደመረጠን፤ ለዓለም ሁሉ መድሃኒት በእንጨት መስቀል የተሰቀለው ክርስቶስ አስቀድሞ መረጠን፤ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ስትል ታመሰግነዋለች፡- ቃልህ በእውነት ጣፋጭ ነው፡፡ ስለ ሐጥአን የተሰቀልህ ለአህዛብ ታበራለህ፡፡ ፅልመትን የምታስወግድ ብርሃንን የምትሰጥ አእምሮን የምታረጋጋ ከእኔ ዘንድ ያለውን አስቀድመህ ታውቃለህና የእያንዳንዱን ጸሎት ትሰማለህና ለእያንዳንዱም ፍላጎቱን ታድርግለታለህና ወደ አንተ የጸለየውን ስማ፡፡” እንግዲህ የዛሬ ምስጋናው ሁሉ ቅድስት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ሊቁ ይቀጥላል፡- ዘአኮ ፀሐይ ዘያበርህ ለኪ መዐልተ…- በቀን ፀሐይ የሚያበራልሽ አይደለሽም፡፡ በሌሊትም ጨረቃ የሚያበራልሽ አይደለሽም፡፡ ብርሃንሽ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ጨረቃሽ አይጨልምም፤ ፀሐይሽም አይጠልቅም፤ መሰረትሽም አይናወጥም፤ የመለኮት ማደሪያ ድንኳን፡፡”

 አቤት ሊቁ ያዜማል!ሁሉን ሲችል ታገሰ፤ ስለ ሰዎች ፍቅር ተሰቀለ፤ ያድነን ዘንድ ነፍሱን ስለእኛ ሰጠ፤ በመስቀሉ ተቤዠን፤ ለቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ወልዶናልና፡፡በጥምቀት ለቤተክርስቲያን ልጆች አድርጎ የሰጠን አባት አባት እንደሌለው ልጆች አልተዋችሁም ብሏልና ከጠላታችን ገድሎ ሳይሆን ሞቶ፤ ተዋግቶ ሳይሆን ተወግቶ፤ ሰቅሎ ሳይሆን ተሰቅሎ ልጅነታችንን አፀናው፡፡

 ስለዚህ ሊቁ ቀጠለንጊስ ቤተክርስቲያን . . . ወደ ቤተክርስቲያን እንገስግስ፡፡ አቤቱ አንተ ምስጉን ነህ ብላ ስታመሰግን እኛን ከእንቅልፋችን አነቃኸን ሰላምን ሰጠኸን ብርሀንንም አቀዳጀኸን፡፡በሞተ ሥራ ሳለን እኛን እንደምትፈርሰው የብሉይ ኪዳን ቤተመቅደስ ሳይሆን በደምህ ዘላለማዊ አድርገህ ወደ ሰራሀት ቤተክርስቲያን በጠዋት በልጅነት አንቅተህ በንስሀ አድሰህ ለምስጋና በሰላም ጠራኸን፡፡

 እንዲህ እያለ ይመጣና ይህን ሁሉ የምላችሁ ይላል ሊቁ ዘመኑ የጾም የመታረቅ ዘመን ነውና ፆሙን በቅድስት ቤት በቅድስና ታሳልፉት ዘንድ የማይመቻችሁ ደግሞ እንደ ዳንኤል መስኮታችሁን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከፍታችሁ የቅድስናን ነገር ትሰሩ ዘንድ ነው፡፡እስመ በጾም ወበጸሎት ወበምፅዋት ይድኀኑ . . . በጾም በጸሎትና በምፅዋት ከሞት ይድናሉ፡፡ ወደ መንግስተ ሠማያት ይደርሳሉ ለንስሀ ፆምን ለሰጠን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ግቡ ይህ ነው፡፡

 በጾም ወበጸሎት . . . በፆም በፀሎት በምልጃ በስግደት በእምነት ወደ ፊቱ እንቅረብ፡፡በእምነት ያለን በዚህ ወቅት በፆም እና በፀሎት በስግደትም በእርሱ ፊት ልንቀርብ ያስፈልጋል፡፡

  “. . . እስመ ተፋጥኑ ገቢረ ሰናየ . . . መልካምን ለመስራት ቸኩሉ፡፡የፆም ነገር በጎ ህይወትን በጎ ሥራን ሁሉ ማበርታት ማሳደግ ነውና ፆም ብቻውን ሳይሆን ከበጎ ሥራ ጋር ያዙ ይላል ዜመኛው፡፡

  በአባቴ ሰላምታ እንደጀመርኩ እንደ እርሱ እያዜምኩ በእርሱ ሰላምታ እጨርሳለሁ፡፡በተፋቅሮ ነሀሉ ኩልነ . . . ሁላችንም በመፋቀር እንኑር፤ ለሁሉም ራሳችንን ዝቅ እናድርግ፤ ወገቡን ታጥቆ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሰላምን አድርጎልንና፡፡በዚህ ሰላም አምላክ ጠብቆ በቅድስናም እርሱን መምሰልን ያጎናፅፈን፡፡

 ደካማ ስሆን ስላልተገባኝ ነገር ስለፃፍኩ ስለ እኔ ጸልዩልኝ አሜን፡፡ በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን በረከቱን ያሳድርብን አምላክ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment