Pages

Friday, April 18, 2014

በዓለ ትንሣኤ

በገብረ እግዚአብሔር
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፲፩ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የዚኽ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ክርስቶስን መስለው እንዲነሡ ማበረታታት ነው፡፡
 በክርስትና ታሪክ፥ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ትልቁና ጥንታዊው ነው፡፡ በዓሉ በዓቢይ ጾም፣ በሰሙነ ሕማማት፣ በአክፍሎት እንዲኹም ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለ የደስታና የሐሴት ወራት እንዲታጀብ መደረጉም ይኽን ታላቅነቱንና ጥንታዊነቱን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ምዕራባውያን ከትንሣኤ ይልቅ የልደትን በዓል በደመቀ አኳኋን ሲያከብሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ግን ትንሣኤን ርእሰ በዓላት አድርገው ያከብሩታል፡፡


 በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ንኡሰ ክርስቲያን የሚጠመቁትና ከቅዱሱ ምሥጢር ተካፋይ የሚኾኑት በዚኹ ታላቅ የትንሣኤ ዕለት ነበር፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ጥምቀት ማለት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መካፈል ስለኾነ ከዚኹ ምሥጢር ጋር ለማያያዝ ነው /ሮሜ.፮፡፬/፡፡ ብርሃን ክርስቶስ በጨለማ ለነበርን ኹላችን እንዳበራልን ለማስገንዘብም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰባስበው ሥርዓተ ቅዳሴን ይሳተፋሉ፤ ብዙ መብራቶችን በማብራትም ያከብሩት ነበር፤ ዛሬም እንዲኽ ይከበራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትኾን ከተሞችም በዚኹ የጧፍና የሻማ ሥነ ሥርዓት ይደምቁ ነበር /The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 551-552/፡፡
  የትንሣኤ በዓል መከበር የዠመረው ገና በመዠመሪያው ምዕተ ዓመት ላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት ወደ ምጸት እንዲስበው፣ አንዱ ክፉ ሰው ብዙውን በጐ ሰው ወደ ክፋት እንዲወስደው፣ ጥቂት ክፉ ግብር ብዙውን በጐ ግብር ወደ ክፋት እንዲለውጠው ስታውቁ “አንሳብም” ማለታችኁ በጐ አይደለም፡፡ እንዲኽም ከኾነ ብሉይ ግብርን፣ ብሉይ ኤጲስ ቆጶስን ከእናንተ አርቁ፡፡ ለሐዲስ ግብር ባለቤት፣ አንድም ለሐዲስ ኤጲስ ቆጶስ ማኅበር ቤተ ሰብ ትኾኑ ዘንድ፤ ገና ሐዲሳን ናችኁና፡፡ ብሉይ ግብርማ እንዳለፈ ለማጠየቅ ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቶ የለምን? አኹንም በዓላችኁን አድርጉ፤ ነገር ግን እውነትና ንጽሕና ባለው እርሾ ነው እንጂ በአሮጌው እርሾ፥ በኀጢአትና በክፋት እርሾም አይደለም” ሲል የተናገረው ለዚኹ ምስክር ነው /፩ኛ ቆሮ.፭፡፮-፰፣ አንድምታው/፡፡
 ከዚኽ በኋላ የተነሡት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በየድርሳናቶቻቸው ስለዚኽ በዓልና አከባበሩ ተናግረዋል፡፡ ዮስጢኖስ ሰማዕት በዓሉን “በዓለ ፋሲካ” ሲለው፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ደግሞ “የደኅንነታችን ቅዱስ ቀን፣ በዓለ ድኅነታችን” ይለው ነበር፡፡ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙም ዕለቲቱን “የዕለታት ንግሥት” በዓሉንም “የበዓላት በዓል፣ የክብራችን ኹሉ ክብር” ሲል ገልጧታል /The Coptic Encyclopedia, pp 1104/፡፡   
 ምንም እንኳን ሐዋርያት ሐዋርያነ አበውና ከዚያ በኋላ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር እንዲኽ ቢያስተምሩም ዝርዝር የኾነ ሥርዓት ግን አልወጣለትም ነበር፡፡ በመኾኑም በአከባበሩ ላይ የተወሰኑ ልዩነቶች እስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ይስተዋል ነበር፡፡ አንዳንዶቹ “በአይሁድ የፋሲካ ቀን ማለትም ኒሳን (በእኛ ሚያዝያ) ፲፬ ቀን ይከበር” ሲሉ፥ ሌሎቹ ደግሞ “ከኒሳን ፲፬ በኋላ ባለው እሑድ ማለትም ኒሳን ፲፮ መከበር አለበት” ይሉ ነበር፡፡ በአይሁድ ፋሲካ ቀን ይከበር የሚሉት የታናሽ እስያ ክርስቲያኖች (ከአንጾክያ ትምህርት ቤት) ሲኾኑ ከኒሳን ፲፬ በኋላ ባለው እሑድ ይከበር የሚሉት ደግሞ የእስክንድርያ ክርስቲያኖች (ከእስክንድርያ ትምህርት ቤት) ነበሩ፡፡ በመጨረሻ ግን በጉባኤ ኒቅያ ማለትም በ፫፻፳፭ ዓ.ም. በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አቈጣጠር እንዲከበር ሠለስቱ ምዕት ወስነዋል፡፡ ዕለቱ እሑድን እንዳይለቅ፣ ከአይሁድ ፋሲካ በኋላ እንዲከበር፣ ዕለቱ መቼ እንደኾነም የእስክንድርያው ፓትሪያርክ በሐሳበ ድሜጥሮስ እየሠራ እንዲያሳውቅ ወስነዋል፡፡ በዚኽም ውሳኔ መሠረት የፋሲካ በዓል ከዐዋድያት አንዱ ኾኖ በኢይዓርግና (ከሚያዝያ ፳፱ ወደ ላይ ሳይወጣ) በኢይወርድ (ከመጋቢት ፳፭ ወደ ታች ሳይወርድ) ተወስኖ ይኖራል /በዓላት ምን? ለምን? እንዴት? በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፣ ገጽ ፹፮፤ The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1226/፡፡
የትንሣኤ አስፈላጊነት
 ትንሣኤ ማለት ተንሥአ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲኾን መነሣት ማለት ነው፡፡ ይኸውም በተለይ ሰው ከፈረሰና ከበሰበሰ በኋላ አካል ገዝቶ ሕይወት አግኝቶ ለሚነሣው ትንሣኤ የሚነገር ቃል ነው፡፡
 ትንሣኤ ብለን ስንናገር የሥጋን መነሣት መናገራችን ነው፡፡ ምክንያቱም ነፍስ አትሞትምና፤ ለማይሞት አካል ደግሞ “ይነሣል” አይባልለትምና፡፡ ሥጋ ከመቃብር ከተነሣ በኋላ ከነፍስ ጋር ይዋሐዳል፡፡ ከዚያም በምድር ላይ የሠሩትን ሥራ አይቶ ክርስቶስ በፍርድ ዙፋኑ ተቀምጦ ይፈርድላቸዋል ወይም ይፈርድባቸዋል፡፡
 ትንሣኤ አስፈላጊ የሚኾንበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያኽልም፡-
1.     እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል፡፡ ቃሉም ለነፍስ ብቻ ሳይኾን ለሥጋም ጭምር ነው፤ ሰው ሲባል ነፍስ ብቻ አይደለምና፡፡ በመኾኑም ይኽ ሥጋ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የግድ መነሣት አለበት፡፡  
2.    እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ አክብሮና አልቆ ፈጥሮታል፡፡ በእነዚኽ ፍጥረታት ላይ ገዢና አለቃ እንዲኾን አድርጐታል፡፡ እንዲኽ ከብሮና ልቆ የተፈጠረው ሰውም እንደሌሎቹ ፍጥረታት በስብሶና ፈርሶ ይቀራል ተብሎ ሊታሰብ አይችልም፡፡ እንዲኽ ባይኾንስ ድሮውንም ሰው ከእነዚያ እንስሳት አይሻልም ነበር እንደ ማለት ነው፡፡
3.    ሰው ጽድቅ ሲሠራም ኾነ ሲበድል በነፍሱ ብቻ አይደለም፤ በነፍሱም በሥጋውም ነው እንጂ፡፡ ስለዚኽ በትንሣኤ ዘጉባኤ ጊዜ ሰው በነፍሱ ብቻ ሊፈረድለት ወይም ሊፈረድበት አይችልም፤ በሥጋውም ጭምር እንጂ፡፡ ይኽ ይኾን ዘንድም ሥጋ የግድ መነሣት አለበት፡፡
  ይኽን ያረጋግጥልን ዘንድም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኵራት ኾኖ ተነሥቷል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላንቀላፉት ኹሉ በኵራት ኾኖ ከተነሣ ያንቀላፉትም በተራቸው ተከትለዉት ይነሣሉ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለራሱ አይደለም፤ ለእኛ ነው፡፡ የተነሣውም ለምንም ለማንም አይደለም፤ እኛ እንድንነሣ ነው እንጂ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመዠመሪያይቱን የቆሮንቶስ መልእክት በተረጐመበት በ፴፱ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ያንቀላፉት ኹሉ የማይነሡ ከኾነ ክርስቶስ ለምን ተነሣ? ስለምን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ መምጣት አስፈለገው? ሙታንን ያነሣ ዘንድ ካልመጣ ስለምን ሟች ሥጋችንን ተዋሐደ? ነገር ግን ክርስቶስ ሥጋችንን የተዋሐደው እርሱ የሚያገኘው ነገር ኑሮ አይደለም፤ ስለ እኛ ረብሕ ነው እንጂ” ማለቱም ይኽን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ አዎ! ሥርየተ ኃጢአትን ያገኘነው ጌታችን ሲነሣ ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ ባይነሣ የኃጢአት መግነዝ አይፈታም፤ ሞት አይሸነፍም፤ መርገም አይወገድም፡፡ ነቢያት “ይነሣል” ብለው የተነበዩት ትንቢት ሐሰት ይኾናል፡፡ ሐዋርያት “ተነሣ” ብለው ያስተማሩት ትምህርት ከንቱ ይኾናል፡፡ በክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት የሞቱት እነ እስጢፋኖስ፣ እነ ያዕቆብ፣ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ በከንቱ ተጐዱ፡፡ እኛም በክርስቶስ ስላመንን ጐስቋሎች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ሳንታረቅ ታርቀናል ብለን አምነናልና፡፡
 ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ካልተነሣ ድሮውንም አልሞተም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ የእግዚአብሔር በግ ኾኖ መጥቷል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ የዓለምን ኃጢአት ያስገወደውስ እንዴት ነው? በሞቱ ነዋ! ሞቶም አልቀረም፤ በኵራት (የመዠመሪያ) ኾኖ ተነሥቷል፡፡ እኛም የመዠመሪያውን ትንሣኤ (ትንሣኤ ልቡናን) ተነሥተናል፤ ፍጹም ትንሣኤ ሥጋ ግን እርሱ በመጣ ጊዜ ይደረጋል /፩ኛ ቆሮ.፲፭፡፲፫-፳፬/፡፡ ፡፡    
 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የነተሣው ግን በኩር ሊኾነን ብቻ አይደለም፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ “ጽሞና በእንተ ትንሣኤ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደተናገሩት፡-
1.     ክርስቶስ የተነሣው ሕይወት በእርሱ ስለነበረች ነው /ዮሐ.፩፡፬/፡፡ ሕይወት ደግሞ ሞት አያሸንፈውም፡፡ መልአኩ፡- “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችኁ” ያለውም ስለዚኹ ነው /ሉቃ.፳፬፡፭/፡፡
2.    ክርስቶስ የተነሣው ብዙዎችን በቃሉ ብቻ እያዘዘ ስላነሣ ነው፡፡ ሞትን በጸሎት ሳይኾን በትእዛዝ ከሰዎች እንድትርቅ ያደረገ አምላክ እርሱማ እንደምን በኃይሉና በሥልጣኑ አይነሣ?
3.    ክርስቶስ የተነሣው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው /ማቴ.፲፮፡፳፩/፡፡ መልአኩም አስቀድሞ ጌታችን “እነሣለኹ” ብሎ የተናገረውን ቃል ለደቀ መዛሙርቱ አስታውሷቸዋል /ማቴ.፳፰፡፭-፮/፡፡
4.    ክርስቶስ የተነሣው የሞተውም በፈቃዱ ስለኾነ ነው /ዮሐ.፲፡፲፯-፲፰/፡፡ በፈቃዱ እንደሞተ በፈቃዱም ተነሣ፡፡
5.    ክርስቶስ የተነሣው ቀድሞውንም የሞተው ለካሣ ስለኾነ ነው /ሮሜ.፫፡፳፬-፳፭/፡፡ የሞተው እንደ እኛ ኃጢአት ስለነበረበት ሳይኾን የእኛን ኃጢአት ተሸክሞ ነውና፡፡
6.    ክርስቶስ የተነሣው ለዓይን ጥቅሻ ታኽል ቅጽበት ስንኳ መለኮታዊ ባሕርዩ ከሥጋው ስላልተለየው ነው፡፡
7.    ክርስቶስ የተነሣው የሞትን ኃይልና ሥልጣን ያጠፋ ዘንድ ነው /፩ኛ ቆሮ.፲፭፡፶፭/፡፡
8.    ክርስቶስ የተነሣው ደቀ መዛሙርቱን ለማጽናናትና ለመርዳት ነው፤ ክርስቶስ በደረሰበት መከራ ሞት ተስፋ ቈርጠው ነበርና፡፡
9.    ክርስቶስ የተነሣው ዕሩቅ ብእሲ እንዳልኾነ ያስረዳ ዘንድ ነው፡፡
10.  ክርስቶስ የተነሣው የቤተ ክርስቲያንን መሠረት (በክህነት አገልግሎት) ይመሠርት ዘንድ ነው /ዮሐ.፳፡፳፪-፳፫፣ Contemplations on the Resurrection, pp 47-55/፡፡   

ክርስቶስ በመነሣቱ የሰው ልጅ ምን ተጠቀመ?
የክርስቶስ ትንሣኤ እጅግ በጣም ብዙ ጥቅሞችን አምጥቶልናል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያኽልም፡-
©     የክርስቶስ ትንሣኤ ለክርስቲያኖች ትልቅ ተስፋን የሰጠ ነው፡፡ ሰው በዚኽ ምድር ላይ ተወልዶ በዚኽ ምድር ላይ በቃ የሚባልለት ፍጡር እንዳልኾነ አሳይቷል፡፡ በዘወትር ጸሎታችን፡- “የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፤ የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ አሜን” ብለን መጸለያችንም ስለዚኹ ነው፡፡ ሰው ከዚኽ ምድር በኋላ የሚቀጥል ሕይወት አለው፡፡ ሞትም ወደዚያ ሕይወት የሚያሻግር ድልድይ ነው፤ በምድራዊ ሕይወትና በሰማያዊው ሕይወት መካከል ኾኖ የሚሻግር ድልድይ፡፡ ማር ይስሐቅ፡- “ሞት የአላዋቂዎችን ልብ ያሸብራል፤ ቅዱሳን ግን ሕይወትን ስለሚናፍቁ ይናፍቁታል” ያለውም ስለዚኹ ነው፡፡ ሞትን የሚፈራ ኃጢአተኛ ሰው ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይኽ ኃጢአተኛ ሰው ሞትን የሚፈራው ሞት የሚያስፈራ ኾኖ ሳይኾን ከዚያ በኋላ ያለውን ፍርድ ስለሚታሰበው ነው፡፡
©     የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጆች መጽናናትን ያጐናጸፈ ነው፡፡ በዚኽ ምድር ስንኖር፥ ስግብግቦች የእኛ የኾነውን ነገር ለራሳቸው ወስደውብን ተሰቃይተን ይኾናል፡፡ መብታችንን ተጋፍተው ይኾናል፡፡ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ የሚሠራ ከልክለውን ይኾናል፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ለዚኽ ኹሉ መልስ አለው፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ለአልዓዛር ሕይወታችን መልስ አለው፡፡ ትንሣኤሁ ለክርስቶስ እነ ነዌ ቸል እንዳሉን እንደማይዘልቁ ይልቁንም መልሰው እንደሚለምኑን ያስረግጣል፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች በሙሉ እኩል እንደኾኑ አብሥሯል፡፡ እንዴት? በትንሣኤ ጊዜ ሃብታም የለም፤ ድኻም የለም፡፡ ጥቁር የለም፤ ነጭም የለም፡፡ ትልቅ የለም፤ ትንሽም የለም፡፡ ባርያ የለም፤ ጌታም የለም፡፡ ገዢ የለም፤ ተገዢም የለም፡፡ ወንድ የለም፤ ሴትም የለም፡፡ ኹሉም እኩል ነው እንጂ፡፡
©     በምድር ላይ እጅግ በጣም የምንወዳቸው ሰዎች ልናጣ እንችላለን፡፡ የምንወዳት እናታችን፣ የምናፈቅራት ሚስታችን፣ የምንወዳቸው ልጆቻችን ልናጣ እንችላለን፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ግን እነዚኽን መልሰን እንደምናገኛቸው አረጋግጦልናል፡፡
©     ሰው ከምድር አፈር የተፈጠረ ፍጡር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥጋችን ወደ ትቢያ የሚቀየርና የሚበሰብስ ቢኾንም ዳግም ይነሣል፡፡ በዚኽም የእግዚአብሔር ኹሉን ቻይነት እንረዳለን፡፡
©     ትንሣኤ፥ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅርና ቸርነት ያስረዳ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ስለ ፍቅሩ በአርአያውና በአምሳሉ ቢፈጠረውም በድሏል፤ ሞቷልም፡፡ እግዚአብሔር ግን ዝም አላለውም፡፡ ሰው እንደሞተ ይቅር አላለም፡፡ ዳግም ሕይወትን ሰጠው እንጂ፡፡ የሰጠው ሕይወትም ለጊዜው አይደለም፤ የዘለዓለም ሕይወት እንጂ፡፡
©     የክርስቶስ ትንሣኤ ደስታንና ሰላምን ለሰው ልጆች አምጥቷል፡፡ መስቀሉ የክርስቶስ መጨረሻ አልነበረም፤ የእኛ የሕይወት መዠመሪያ እንጂ፡፡ ሐዋርያት መከራ ሲደርስባቸው ደስ ሲላቸው የነበረው ይኽን ስላወቁና ስለተካፈሉ ነው፡፡ ዛሬ መከራው መከራ የሚኾንብን የኤማሁስ መንገደኞች ስለምንኾን ነው፤ መንገዱ ክርስቶስን ትተን በሌላ ፍኖት ስለምንኼድ ነው፡፡
  
እንዲኽ ከኾነ ታድያ የትንሣኤን በዓል እንዴት እናክብረው?
  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፡፡ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና፥ ሕይወታችኁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና፡፡ ሕይወታችኁ የኾነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችኁ” እንዲል /ቈላ.፫፡፩-፬/፥ በጥምቀት ውኃ ሞቱን በሚመስል ሞት ስንሞት፥ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ግብጻውያን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ አዲሱ ሰውነታችን ግን እስራኤላውያን ባሕሩ ተከፍሎላቸው እንደተሻገሩ ተሻግሯል (ተነሥቷል)፡፡ ብልየት ያለበት የቀዳማዊ አዳም ሰውነታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተቀብሮ አዲሱ ሰውነታችን ሕይወትን አግኝቶ ተነሥቷል፡፡ መሬታዊው ሰዋችን ሞቶ ሰማያዊው ሰዋችንን ለብሰን መንፈሳውያን ኾነናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን ተመልሰናል፡፡ አኹን ከእኛ የሚጠበቀው ይኽ ተፈጥሯችንን ሳናቆሽሽ መጠበቅ ነው፤ እንደተነሣን መዝለቅ፡፡ ይኽን ለማድረግም ከእኛ የሚጠበቀው ተራራ መውጣት ወይም ማፍረስ አይደለም፤ የእሳት ባሕር መሻገርም አይደለም፡፡ ይኽን ጠብቀን እንድንቈይ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ፈቃዳችንን ብቻ ነው፤ የሚሠራው እርሱ ነውና /ዮሐ.፲፭፡፭/፡፡ ይኽ በእኛ ዓቅም እንደማይቻል የሚያውቀው እግዚአብሔር መጽንዒ መንፈስ ቅዱስን ያደለንም ስለዚኹ ነው፡፡
  አዲሱን ሰውነታችን ለብሰን ከተነሣን በኋላ እንደ ቀድሞ ምልልስ የምንጓዝ ከኾነ ግን ተመልሰን ወድቀናል፤ አዲሱ ሰዋችንን አውልቀን አሮጌውን ሰዋችን ድጋሜ ለብሰነዋል፡፡ በእኛነታችን ውስጥ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሲመት፣ ፍትወትም ካለ አዲሱ ሰውነታችን ከእኛ ጋር የለም፤ ካልኾነም ታሟል፡፡ በኃጢአት የመቃጠል ስሜት፣ ዝሙት፣ ርኵሰትና ክፉ ምኞት ከእኛ ዘንድ ካለ አሮጌው ሰው ኾነናል፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ አላደረግንም፡፡ ፋሲካን ማክበራችንም ትርጕም የለውም፡፡ ለምን? ፋሲካ ማለት መሻገር ማለት ስለኾነ፤እግዚአብሔር ወልድ እኛን ከወደቅንበት አንሥቶና ተሸክሞ ከዚኽ ምድር ወደ ሰማያት ተሻግሯልና (ተነሥቶ ዓርጓልና)፡፡ ተወዳጆች ሆይ! የምናመልከውን አምላክ መስለን በሕይወት ካልተሻገርን የመሻገርን በዓል (ፋሲካን) ማክበራችን ምን ጥቅም አለው? ከጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን ሥራ፣ ከፍቅረ ዓለም ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ካልተሻገርን ፋሲካን ማክበራችን ምን ረብሕ አለው? እኛው ሳንነሣ የመነሣት በዓልን ማክበራችን ምን ጥቅም ይሰጠናል?
 ብዙዎቻችን ፋሲካን እናከብራለን፡፡ ነገር ግን በሕይወታችን ሳንሻገር ነው፡፡ ክርስቲያን ኾኖ ሰማያዊውን ፋሲካ ሳይኾን ምድራዊ ፋሲካን የሚያከብር ካለ ከጐስቋሎች ኹሉ ይልቅ ጐስቋላ ነው፡፡ ይኼ ማለት የዲያብሎስ ዓለም ተመችቶታል፤ ከዚኽም በላይ መሻገርን አይሻም ማለት ነው፡፡ ታድያ ከዚኽ የባሰ ጕስቁልና ምን አለ? እንኪያስ ተወዳጆች ሆይ! ፋሲካን እናክብር፡፡ እስከ አኹን በኃጢአት ውስጥ ካለን ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንምጣ (እንሻገርና) የመሻገርን በዓል እናክብር፡፡ ከክፉ ሥራ ወደ ጽድቅ ሥራ እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከኃይል ወደ ኃይል እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከሞት ሥራ ወደ ሕይወት ሥራ እንነሣና የመነሣትን በዓል እናክብር!!!
 ተወዳጆች ሆይ! ይኽን ዓለም (እኛን) የሚያሰነካክል ደግሞም የሚጥለን ፈርዖን (ዲያብሎስ) ተሰነካክሎ ወድቋልና ተነሥተን እንሻገር፡፡ ተሻግረንም ሰማያዊውን ፋሲካ እናክብር፡፡ በግብጽ የነበሩት እስራኤላውያን የበጉን ደም በጉበኑና በኹለቱም መቃን ሲቀቡት አጥፊው ከቤታቸው አልፏል /ዘጸ.፲፪፡፲፫/፡፡ ይኸውም በጉ በራሱ ያንን የማድረግ ኃይል ስለነበረው አይደለም፤ ደሙ የክርስቶስ አምሳል ስለነበር ነው እንጂ፡፡ እኛ ግን የአማናዊውን በግ /ዮሐ.፩፡፳፱/ ደም በልቡናችን፣ በአስተሳሰባችንና በሰውነታችን ኹሉ እንቀባና እንሻገር፡፡ ይኽን ስናደረግ በእባቡና በጊንጡ ማለትም በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ሥልጣን ይኖረናል /ሉቃ.፲፡፲፱/፡፡ የምንበላው በግ ራሱ ሕይወት ስለኾነ ሞት በእኛ ላይ አይነግሥም /ዮሐ.፲፬፡፮/፡፡ በዚኽ ዓለም ሳለን ከዚኽ ደስታ ተካፋዮች ከኾንን (የመዠመሪያውን ትንሣኤ ልቡና በንስሐ ከተነሣን) በሚመጣው ዓለምም ይኽን ደስታ ሊገለጽ በማይችል አኳኋን እንካፈላለን (ኹለተኛውን ትንሣኤ እንነሣለን) /ሉቃ.፳፪፡፲፭-፲፮/፡፡ ብንወድቅ እንኳን መልሰን በመነሣት የመነሣትን በዓል እናክብር፡፡ አለመነሣት የእኛ የክርስቲያኖች ተፈጥሮ አይደለምና ከተፈጥሯችን ውጪ አንመላለስ፡፡ 

ጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ወፍቅረ እግዚአብሔር፥ ወሱታፌ መንፈስ ቅዱስ የሀሉ ምስለ ኵልነ፡፡ አሜን /፪ኛ ቆሮ.፲፫፡፲፬/!!!

3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. በ/ዲብርሃኑ ኣድማስ ፹፮the oxford dictionary of christian church, pp 1226 የሚል ኣልገባኝም..ባማርኛ ነው በእንግሊዘኛ pls reaply me እግዚኣብሔር ያክብርልኝ

    ReplyDelete
    Replies
    1. 1. በዓላት ምን? ለምን? እንዴት? በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፣ ገጽ ፹፮፤
      2. The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1226/

      Delete