Pages

Monday, April 28, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - ክፍል ፩

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፲፱ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  የዚኽ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለው ወራት ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይቀዘቅዝ ማበረታታት ነው፡፡
  በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ባለው ወራት ረቡዕንና ዓርብን ጨምሮ አይጦምም፤ አይሰገድምም፡፡ ይኽም ሠለስቱ ምዕት በ፫፻፳፭ ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ሲሰበሰቡ በኻያኛው ቀኖኗቸው የወሰኑት ቀኖና ነው /ሃይ.አበ.፳፡፳፮፣ The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1250, 1738/፡፡ ይኽን ቀኖና ሲወስኑም ያለ ምክንያት አይደለም፤ ይኽ ወራት ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለውን ሕይወታችን የሚያሳይ ስለኾነ ነው እንጂ፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት ተብሎ የሚደረግ ጦምም ኾነ ስግደት የለም፡፡ ሥጋ ሙሉ በሙሉ በዲያብሎስ ከመፈተን፣ ከእግዚአብሔር ውጪ የኾነ ሌላ ሐሳብን ከማሰብ ነጻ የሚወጣበት ወራት ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ፈቃደ ሥጋ ከፈቃደ ነፍስ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ከድካሙ ነጻ ስለሚኾን እግዚአብሔርን ለማመስገን ትጉኅ ነው፡፡ እንደ አኹኑ እንቅልፍ እንቅልፍ አይለውም፤ ዘወትር የቅዱሳን መላእክትን ምግብ ለመብላት ማለትም ለማመስገን የተዘጋጀ ነው እንጂ፡፡


 ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለው ሕልውናችን በማያቋርጥ ብርሃን በደመቀችና በንጹሕ ፈሳሽ ውኃ በለመለመች፣ በማኅሌትና በይባቤ ድምፆችም በተመላች የተድላና የደስታ ዓለም መኖር ነው፡፡ በዚያ ፀዋትወ መከራ የለም፡፡ ብካይ፣ ልቅሶ፣ ሐዘን፣ በልብ መቆርቆር፣ መዋረድ፣ ነፍስን የሚያሳዝናትና የሚያስደነግጣት ፍርሐት የለም፡፡ በፊትኽ ወዝ መብላት መጠጣት፤ እሾኽም አመኬላም የለም፡፡ ምቀኝነትና መፎካከር የለም፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ሕማመ ሥጋ ሕማመ ነፍስ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ የለም፡፡ ብርሃን እንጂ ጨለማ፣ መዓልት እንጂ ሌሊት የለም፡፡ በሰማያዊው ሕይወታችን ደም ግባት ማሸብረቅ አለ፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ለዘለዓለም የማያልፈውን በጎ በጎውን ክብር ማግኘት ነው እንጂ መሻት፣ መሰልቸት፣ መራብ፣ ቁንጣን የለም፡፡
 ሠለስቱ ምዕት ይኽን ቀኖና ሲቈንኑ የትንሣኤያችን በኵር የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞታችንን በሞቱ ገድሎ ስለተነሣ በሐዘን ሳይኾን በፍስሐ በሐሴት እንድናከብረው፥ አንድም ሊመጣ ያለውን ሰማያዊ ሕይወታችንን ገና በዚኽ ምድር ሳለን በዓይነ ልቡናችን እንድናየው፣ እንድናስበው፣ እንድንለማመደው፣ ደግሞም ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንድንቻኰል ለማድረግ ነው፡፡
 ታድያ በዚኽ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች በእውነት በዚኽ ወራት ይኽን እናስባለን ወይ? ይኽን ተገንዘበን ወደዚያ ሕይወት ለመኼድ እንቻኰላለን ወይ? መንፈሳዊ ሕይወታችንስ ከማንኛውም ጊዜ በላይ የሚደክምበት ወራት አይደለም ወይ? ኹለት ወራት ጦመን ያገኘነውን ዕሴት በከንቱ የምናጣበት አይደለም ወይ? ለእግዚአብሔር ስትታዘዝ የነበረችውን ሰውነት ዳግም በዲያብሎስ አሽክላ የምትያዝበት ወራት አይደለም ወይ? ለኹለት ወራት ተዘግተው የነበሩት የምሽት ክበባትና የዳንኪራ ስፍራዎች ዳግም የሚከፈቱበትና ዲያብሎስ ያለምንም ከልካይ ነፍሳትን የሲዖል ሲሳይ የሚያደርግበት ወራት አይደለም ወይ? ለኹለት ወራት እንዳልሰገድን፣ እንዳልጦምን፣ ጧት ጧት ለኪዳን እንዳልገሰገስን ኾነን ፍጹም በኾነ መዘናጋት ተይዘን ዳግም ወደ ቀድሞ ኑሯችን የምንመለስበት ወራት አይደለም ወይ? ቅዱሳን አባቶቻችን ይኽን ቀኖና ሲቈንኑ ከላይ ያስቀመጥነውን ዓላማ ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ግን ይኽን እንዳንገነዘብ አድርጐናል፡፡ የዚኹ ወራት ዓላማ በጭራሽ እንድንስተውና እንደ ዕሪያ ወደ ቀድሞ ምልልሳችን እንድንመለስ አድርጐናል፡፡ እግዚአብሔር የሚመለከውና የሚመሰገነው በወቅት እስኪመስል ድረስ በዚኽ ወራት መንፈሳዊ ሕይወታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲደክም ያደርጓል፤ አድርጐታልም፡፡ በማስተዋል ሳይኾን በልምድ እንድንመላለስ አድርጐናል፡፡ ታድያ እስከ መቼ ድረስ ነው እንዲኽ የምንቀጥለው? እስከ መቼ ድረስ ነው ዲያብሎስ እያታለለን የምንኖረው? አንድ ሰው ዓይኑ ውስጥ ትቢያ ቢገባበት ለቅጽበት (ለሴኮንድ) ስንኳ ሊታገሥ ይችላልን? አይችልም! ታድያ ዲያብሎስ በዓይነ ልቡናችን ላይ ያስቀመጠውን ያለማስተዋል ግንድ መቼ ነው የምናስወግደው? እንዴት አድርገንስ መንፈሳዊ ሕይወታችንን በዚኽ ወራት በቀጭኒቱ መንገድ ማስጓዝ ይቻለናል? እንደምንስ የዲያብሎስን ተንኰል ከንቱ ማድረግ ይቻለናል? አንድ ክርስቲያን እነዚኽንና መሰል ጥያቄዎችን ሊጠይቅ ግድ ይሏል፡፡ እነዚኽን ጥያቄዎች ሲጠይቅ መፍትሔውም ምን እንደኾነ ለመገንዘብ አያስቸግረውምና፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment