Pages

Saturday, April 5, 2014

ኒቆዲሞስ ዘሰንበተ ክርስቲያን



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 27 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በሕልውና አንድ በሚሆን ሦስት፣ የማያገኙት ከፍ ያለ፣ የማያዩት የተሰወረ፣ የማይዙት እሳት፣ የማይዳስሱት መንፈስ፣ በማስተዋል የማይወስኑት ኃይል፣ የማይሾሙት ንጉሥ በሆነ በእግዚአብሔር ስም በመለኮቱ አምላካችን በቸርነቱም አባታችን ነው:: ለእርሱ ምሥጋና ይሁን:: በእርሱም የሆነ ሰላም ይብዛላችሁ::

 የዛሬዋ ቀን የጾሙ ሰባተኛ ሳምንት ናት:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ ይህ ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል:: ልክ እንዳለፉት ሳምንታት የዚህን መጠሪያ ያገኘው ታላቁ የዓለም የቤተክርስቲያን የዜማ እና መጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ በሆነው በቅዱስ ያሬድ ድርሰት ነው:: ከጾመ ድጔ ድርሰቱ:: በዚህ ሳምንት የሚዜመው ክፍል በሰንበተ ክርስቲያን (እሁድ) ሲጀምር ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበረ ብሎ የሚጀምር ሲሆን በድርሰቱ ሙሉ በየቦታው ይህንን እያነሳ ሊቁ ለልብ በሚስማማ ነፍስን በሚጥም የልባችንን ትርታ ጸጥ አድርገን የምናዳምጠውን ሰማያዊ ዜማ ያሰማናል:: እኛ ደግሞ ለጽሑፍ የሚስማማንን ዜማ በማይጮኸው በማይሰማው ብዕራችን የተመረጡ ቃላትን በዐይን እያነበብን በነፍስ እየዘመርን እንቆያለን:: የምንችል በሌሊት በቤቱ ተገኝተን ዜማውን በእሁድ እንድንሰማ እየጋበዝኩ የማንችል ደግሞ ይህንን እያነበብን ለጸሎት እንትጋ እላለሁ::

 ወሀሎ አሀዱ ብእሲ እምፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ ዘሖረ ኀቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ ወይቤሎ ለኢየሱስ ዕጔለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሣእነ በትንሣኤከከፈሪሳውያን ወገን የሚሆን ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ የሄደ ነው:: ኢየሱስንም እንዲህ አለው የአንበሳ ደቦል (ልጅ) ፈጽሞ ተኛህ (አንቀላፋህ) በትንሣኤህ (በምትነሳ ጊዜ) እኛንም አንሳን::” ከፈሪሳውያን ወገን የሚሆነው ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊነቱ በቀን ከመሄድ ፍርሃት የተነሳ ከልክሎት ይሆን ወይስ በንጹሕ ልብ ሊማር? የሆነው ሆኖ ግን መምህሩን ከሌሎቹ ይልቅ አውቆታል:: ትንሣኤውንና ትንሣኤ ሙታንንም ተስፋ አድርጔል:: ዜመኛው በየአንቀጹ ዜማውን የሚያነሳው (የሚጀምረው) ኒቆዲሞስ እያለ ነው:: በእርሱ የተገለጠውን የዳግም ልደት የክርስትና በር እንድናስተውል ይሆን? በሌሊት የሄደው ኒቆዲሞስ መምህር ከአብ ዘንድ ተልከህ እንደመጣህ እናምናለን፡፡

 ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህር አልቦ ዘይገብር ተአምረ ዘአንተ ትገብርከአብ ዘንድ መጣህ፤ መምህር ትሆነን ዘንድ፤ አንተ የምታደርገውን ድንቅ ማንም የሚያደርገው አይደለም::” ከአደነቀ በኋላ የኒቆዲሞስን ጥያቄ በዜማወይቤሎ ለኢየሱስ ብእሲ ዘስሙ ኒቆዲሞስ እፎ ይክል ሰብእ ደግመ ተወልደ እምድኅረ ልሕቀስሙ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ኢየሱስን እንዲህ አለው ሰው ካደገ በኋላ እንዴት ዳግመኛ ይወለዳል?” ዜመኛው ያደንቃል፤ አይሁድም በትንቢት ከገሊላ ሰው እንዴት ይወጣል ይላሉ::

 ቅዱስ ያሬድ ዳግም ስለ ኢየሱስ ሳይሆን ስለ ኒቆዲሞስብእሲ ምዕመን ዘተረክበ እምፈሪሳውያንየሚያምን ሰው ከፈሪሳውያን ተገኘ::” እያለ ያደንቃል:: የኒቆዲሞስ ጥያቄ መልስ አለው::

 እናዚም: “ይቤሎ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ አንተ ሊቆሙ ለእስራኤል ወዘንተ ነገረ ኢተአምርኢየሱስም ለኒቆዲሞስ እንዲህ አለው አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን ነገር አታውቅም? እኔ ከአብ ተላኩ፤ ስሜም እውነት ነው::” እንዲሁም “…አማን አማን እብለከ ዘተወልደ እምሥጋ ሥጋ ውእቱእውነት እውነት እልሃለሁ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው::” ይህ ከሰማይ እንደሆነ አቤቱ መምህር ሆይ እኔ አምናለሁ፤ ስለዚህ ይሰቀልን አላምንም::

 “…ድኅኑ አነ እምደሙከዚህ ሰው ደም እኔ ንጹሕ ነኝ፤ እኔ ግን እጠመቅ ዘንድ እሻለሁ::” ይህ አምላክ ወሰብእ የተስፋችን ፍጻሜ የሰንበት ጌታዋ በሀዲስ ኪዳናችንን ያደሰልን እርሱን ከእናንተ ጋር ልሰቅል አልተባበርም:: በህጉ ከእርሱ ጋር እርሱ በሰራት ቀን (ሰንበት) ደስ ይለኛል እንጂ::

 ወሃሎ አሀዱ ብእሲ እምውስቴቶሙ ወይቤሎሙ ኦሪትክሙኑ ትኴንና ለሰብእከእነርሱ ውስጥ የሆነ አንድ ሰው እንዲህ አላቸው ኦሪታችሁ አስቀድማ አንድ ሰው የሰራውን ሳትመረምር ትፈርዳለችን? … ዘይቤ ኒቆዲሞስ ስሙ ተአመነ እንዘ ይብል... ስሙ ኒቆዲሞስ የተባለው እንዲህ ሲል ታመነ የእስራኤል ንጉሥ ወደ እኛ የመጣውን አይሁድ በሙሴ ህግ በኦሪት አይሄድም አሉት፤ ኒቆዲሞስ መለሰ ጌታውንም አውቆ ደስ አለው መምህር ሆይ እኛ በአንተ እናምናለን::” እንግዲህ ጌታ እንዳለው የሰማነውን እንናገራለን፤ ያየነውን እንመሰክራለን፤ የዓለም ጌታ ደግሞ ሊወልደን ተወልዷል፤ ጥምቀትን ተጠምቆ ቀድሶልናል፤ ከሞተ የአይሁድ ስራችን ትተን በንጹሕ ልብ እንከተለው:: “…ነአምን ብከ ወበምጽአትከ አብራሕከበአንተ እናምናለን፤ በመምጣትህም አበራህልን፤ ሰላምንም ሰጠኸን::” ሰላሙ ይብዛልን::

No comments:

Post a Comment