Pages

Monday, April 7, 2014

ኒቆዲሞስ ዘሠኑይ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 29 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ሰው በመሆናችን ልንሸከመው የማንችለውን ፍቅር ሰጠኸን፤ በጨለማ ሆነን አንተን ስንናፍቅ የማይጨልም ብርሃንን በሕይወታችን አበራህልን፤ የልባችንን ፍሬ መራራነት ታገስከን፤ የማስመሰላችንን ድራማ ቸል አልክልን፤ ስምህን ባጎደፍነው መጠን ሳይሆን በማይለካው ፍቅርህ ንጽሕናን አለበስከን፤ ፍቅርና ሰላም የለም ብለን ተስፋ በቆረጥን ጊዜ ይህ ነው በማይባል ሰዓት ደርሰህ እኛ የምንገረምበት እኛነት አደልከን፤ ሰላምን አጎናጸፍከን፤ በዚህ ሰላም ለሁላችሁ ሰላም ይሁን::


 በአይቴ እንከ እረክቦ ይትረከብኑ እግዚአብሔርእንግዲህ እግዚአብሔርን በወዴት አገኘዋለሁ? ይገኛልን? ከብዙ በደሌ ብዛት የምጸልየውን ጸሎት ይሰማኛልን? አንተን በድያለሁና ነፍሴን ይቅር በላት፤ ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ አቤቱ ይቅር በለኝ::” ዜመኛው ቅዱስ አባት በማለዳ የሕይወትን ምንጭ እንደሰው ጆሮ የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ልመና የሚሰማውን ስለበደል ሳይሆን ስለ ቅጽበት መፀፀት እኛን የሚቀበለውን ይፈልገዋል፤ ይጠይቀዋል፤ ትሰማኛለህን? አገኝሃለሁን? ይለዋል::

 ከአገኘሁህስ፡-ስብሐተ ዘነግህ ንፌኑ ለከየጠዋት (የነግህ) ምሥጋናን እንልክልሃለን፤ ከመገዛት ጋር ምሥጋናን እናሳርጋለ::” ስምሽን ከፍ ከፍ ስላደረገው የእግዚአብሔር ሃገር ኢየሩሳሌም ሆይ በአንቺ ደስ ይለኛል፤ ጸሎቴን አብዝቶ የሚሰማኝን በአንቺ ዘንድ አግኝቸዋለሁና እያለ ቤተክርስቲያንን ማወደስ ይጀምራል::

  አንቀጸ መድኃኒት ቅድስት ቤተክርስቲያንየመድኃኒት መገኛ (በር) ቅድስት ቤተክርስቲያን በማዕከሏ መድኃኒታችንን እናድርግ፤ ቤተክርስቲያንን እንከተላት፤ መድኃኒት ወደብ ትሁነን:: ወደ እርሷ የሄደ አይደክምም::” እርሷ በተራሮች ራስ ላይ ተመስርታለች፤ በዕፀ መስቀሉም ተቀድሳለች፤ ግድግዳዎቿም የዕንቍ ናቸው፤ ነገሥታት ደቂቃን ሁሉ እኩል ይመኩባታል፤ የሁሉም እናታቸው ነችና:: እኛምበጽባሕ ትብጻሕ ጸሎትየ----- በጠዋት ጸሎቴ ወደ አንተ ትድረስ::” እያልን እንጸልይባታለን::

 ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ተጸፋእከ በውስተ አውድ ከመ ትቀድሳ በደምከ ክቡርስለ እርሷ ስለ ቤተክርስቲያን በክቡር ደምህ ትቀድሳት ዘንድ በአደባባይ በጥፊ ተመታህ:: የእስሩን ብዛት ተሸከመ፤ ርኩስ ምራቅንም ታገሰ፤ በደል ሳይኖርበት አምላክ በእንጨት መስቀል ተሰቀለ::” ቤተክርሰቲያን የእኛ መርከብ ትሆን ዘንድ የጥፋት ርኩሰትም እንዳይዘልቅባት በደሙ አነጻት፤ አጸናት፤ ስለእርሷ ሲል የኃጢአተኞችን ምራቅ የበደለኞችን ጅራፍ ታገሰ፤ ልንሸከም የማንችለውን የበደላችንን ክምር በእንጨት መስቀል አሳለፈልን፤ እርሷ መለያዋን መስቀል ስለፍቅሩ ብዛት በገዛ ደሙ ማሕተም አትሞ አጸደቀላት:: እንግዲህ ያለዋጋ እና ያለ ምንም ክፍያ እንኖርበት ዘንድ ውድ የደም መሠረት የደም ግድግዳ ተሰጠን፤ በሥጋ ሞተን ከዚህ ዓለም ከመነጠላችን በፊት በጌታዋ ዘንድ በጎ ማድረግን ጾምን ሥርዓትን ሁሉ መጠበቅ እንልመድ::

 አልቦ ዘአምጻእነ ወአልቦ ዘንነስእ እምዝንቱ ዓለምከዚህ ዓለም ይዘን የመጣነው ምንም የለም፤ ይዘን የምንሄደውም ምንም የለም፤ ዓለሙም ምኞቱም ሁሉም ሀላፊ ነውና:: አንተ ግን ለዘለዓለም ይቅር ባይ ነህ፤ ለዘለዓለም ትኖራለህ፤ የሰው ህግን አቃልልንበከመ ይቤ በወንጌል ዘሰ ገደፋ ለነፍሱ በእንቲአየ ይረክባበወንጌል እንደተባለ ነፍሱን ስለ እኔ የተዋት ያገኛታልሰላም ወተፋቅሩ ይብዛህ ማዕከሌክሙ አኀው------ ወንድሞቼ ሰላምና መፋቀር በመካከላችሁ ይብዛ::” አሜን!

No comments:

Post a Comment