Pages

Tuesday, April 8, 2014

ኒቆዲሞስ ዘቀዳሚት ሰንበት (ሆሳዕና)



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም፣ አንድ የናዝራውያን አምላክ፣ የማይለወጥ የሃይማኖት ምሰሶ፣ የማይፍገመገም የመርከባችን አለቃ፣ የማይጨልም የፋናችን ብርሃን፣ ከዘመናት በፊት በሕልውና አንድ የሆነ፣ በስምና በሥልጣን የሠለጠነ፣ የመለኮቱ አንድነት የማይለወጥ፣ የመንግሥቱ ስፋት የማይወሰን፣ የብልጥግናው ክብደት የማይለካ እርሱ በሰላም ይጠብቀን::


 ዛሬም ሆሳዕና በአርያም እያልን ከዜመኛው ጋር እንቆያለን:: የነገውን በዓል ዋዜማ እንደተመለደው በቀዳሚት ድርሰቱ አብሮን በአጭሩ ይቆያል:: “በበዓሎሙ ለአይሁድ ዐርገ ኢየሱስ ኢየሩሳሌምበአይሁድ በዓል ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ ብዙ ሕዝብም ተቀበሉት:: ጽዮን እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና የዋህ ዋጋውም ከእርሱ ጋር ያለ፤ ስራውም በፊቱ፤ ልብሱን በወይን የሚያጥብ፤ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም፤ የአህያውን ውርጭላ በዘይት ግንድ ያስራል::” በወይን ልብሱን የሚያጥበውን የያዕቆብን ልጅ የይሁዳን ልጅ በእንጨት መስቀል ሰቀሉት:: የአይሁድ በዓል ዛሬ ነው:: በዚህ ቀን ኢየሩሳሌም ሆይ ደስ ይበልሽ:: በእናንተ አንደበት ምሥጋናዬን ጨመርኩ ማንም በራሴ አመሰገንሁ አይበል:: የምሥጋናን መስዋዕት በእናንተ ያኖርኩ እኔ ነኝ እናም ማዳኔን ለዓለም ሁሉ ተናገሩ ሆሳዕና በሉ:: በቤቴ መለከትን ንፉ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል::

 ንጉሥ ዘይወጽእ እምይሁዳ እምድረ ሳይዳንጉሥ ከይሁዳ ከምድረ ሳይዳ የሚወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: በናዝሬት የተቀባው ሃገረ ኢየሩሳሌም ገባ:: ብዙ ሕዝብ ሕጻናት ወጣቶች ተቀበሉት፤ ሕጻናት በመስቀሉ ሕዝቡን አዳነ እያሉ አመሰገኑት::” የብርሃን መስቀል እነሆ አየሁ፤ የወይን ግንድን ይመስላል:: በተሰቀለው ብዙዎች ያምናሉ፤ ሆሳዕና መድኃኒታችን ይሉታል::

 እለ ነጸፉ ቆጽለ መቲሮሙዝንጣፊ ቆርጠው አነጠፉ፤ ልብስ ያላቸው ልብሳቸውን መንገዱ ላይ አነጠፉ:: በአይሁድ በዓል ወደ ደብረዘይት ደረሰ::” ምሥጋናን ከልባቸው የሚያውቁ እንደ አይሁድ ዳር ቆመው ከአንገት በላይ አያመሰግኑም፡፡ ክርስቶስ ይጎበኘው ዘንድ ልባቸውን ያነጥፋሉ፤ ራሳቸውን ፍጹም ለእርሱ ያስገዛሉ::

 ዓይ ውእቱ ዝንቱ ዘነፋሳት ይትኤዘዙ ሎቱይህ ነፋሳት የሚታዘዙለት ማነው? እርሱ ክርስቶስ ነው፤ ምሥጋና የሚከበው ሕጻናት ታዳጊዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ወስደው ክርስቶስን ከበቡት…፡፡” ያን ጊዜ ጌታ ሆሳዕናን በሰራ ጊዜ ሰማይ ታወከች፤ ንጉሧ በአህያ ተጭኖ አይታ፡፡ መላእክት ስለሆነው ሁሉ አደነቁ፤ ተደሰቱ፤ በምድር ያሉ የመዳናቸው ቀን ነውና መድኃኒት መድኃኒት እያሉ አመሰገኑ እያለ በድንቅ ዜማ ሊቁ ያስተምረናል::

 ወትቤ ጽዮን አርኅው ሊተ አናቅጸጽዮን አለች ወደ በሩ ግቡ፤ ከመንገዱ ድንጋዮችን ያስወግዱ፤ ሕዝቡም ይግቡ፤ ካሕናቱና ሌዋውያኑ ታቦቱን ይሸከሙ፤ መዘምራንም በእውነት::” ሕጉን ለሚጠብቁ መሪ ይሆናቸው ዘንድ በትሕትና በደካማዋ አህያ ሰላምን አመጣላቸው:: ኃያላን ነን እንደሚሉ እንደ ምድር ጦረኞች በፈረስ ተጭኖ ሰራዊተ መላእክትን አስከትሎ አልመጣም:: አዎ በአህያ በደካማዋ ሰላምን ሊሰብክ እንጂ፡፡ ስለዚህ ይላል ሊቁ፤ ከመዝሙረኛው አባቱ ከቅዱስ ዳዊት ጋር:: “በረዳን በወደደን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ፤ በታወቀች የበዓል ቀን በጽዮን መለከትን ንፉ:: በረከትን የሚያድለው ንጉሥ ወደ እኛ በትሕትና መጥቷልና::”

 ሆሳዕና በአርያም ለወልደ ዳዊት ለንጉሠ እስራኤል ዘይሁብ ዝናመለዳዊት ልጅ ለእስራኤል ንጉሥ ሆሳዕና በአርያም የበልግ ዝናምን የሚሰጥ፣ እንደ ቀድሞ የእህሉን አውድማ እና የወይኑን መጥመቂያ በበረከት ይመላል::” እኛነታችንን በሥጋ ወደሙ ይቀድስልን:: ሰላሙን ይስጠን::

No comments:

Post a Comment