Pages

Tuesday, April 8, 2014

ኒቆዲሞስ ዘዓርብ (ሆሳዕና)



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በአንድነት በሚመሰገን፣ በአንድነትም በሚለመን፣ በአንድነት በሚሰበክ፣ አንደበት ሁሉ የሚገዛለት፣ ጉልበትም ሁሉ የሚሰግድለት፣ ምሥጉን አምላክ በሆነ በእግዚአብሔር ስም፣ በመጽሐፍ ራስ ሁሉ ላይ በጥበብ ቁጥር በእርሱ ስምና በመስቀሉ ምልክት በማማተብ ሰላምታ ይድረሳችሁ:: (መጽሐፈ ምሥጢር)


 የሆሳዕናን ነገር ማወደስ ከጀመርን ዛሬ ሦስተኛ ቀናችን ነው:: ዛሬም እንዳለፉት ቀናት ሊቁ የሆሳዕናን ነገር እያነሳ ይዘምርልናል ያዜምልናል:: “ንስዕለከ እግዚኦ አምላክነ ናስተበቊአከ ሚጠነ ኀቤከአቤቱ አምላካችን እንለምንሃለን እንማልድሃለን ወደ አንተ መልሰን፤ ጳውሎስን በምርጫህ እንደመለስከው ትመልሰን ዘንድ እንማልድሃለን:: እኔ የሳትኩ ነኝ፤ አንተ ግን ወደ መንገድህ ልትመልሰኝ ትችላለህ::” ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕፃናት የዛፍ ቅርንጫፍ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ ያመሰግኑ ነበር:: ኢሳይያስም አሻግሮየእግዚአብሔር ሃገር ሆይ ዛሬ ብርሃንሽ ይብራ፤ ዛሬ ደስ ይበልሽ፤ ደሙን ስለ አንቺ የሚከፍለው መጥቷልና አደባባይሽን ተመልከቺ፤ በሕዝብሽ ደስታ በሕፃናትሽ ደስታ ደስ ይበልሽ፤ እነሆ በአንቺ ዛሬ የተፈጸመው በአንቺ የተገለጠው ለዓለም ሁሉ መድኃኒት የሚሆን አምላክሽ ነውና” ብሎ ተናገረ::

 ንፍሑ ቀርነ በጽዮን ቀድሱ ጾመበጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምን ቀድሱ፤ ምህላን ስበኩ፤ ሕዝብን ሰብስቡ (ጥሩ) ማኅበራችሁን ቀድሱ፤ ሊቃውንታችሁን ምረጡ፤ ጡትን የሚጠቡ ሕፃናትን ሰብስቡ (ጥሩ) ሙሽራው ከአዳራሹ ይውጣ፤ ሙሽራዋም ከመጋረጃዋ፤ ለጌታቸው የሚሰዉ ካህናት ያልቅሱ::” ዛሬ ታላቅ ቀን ነው፡፡ የዋሕ ንጉሥ በተናቀ ፍጥረት ላይ ሆኖ ተገልጧል:: እነሆ የመለከት ድምፅ ሁሉንም ይጥራ፤ ምሥጋናን የምታውቁ ይህንን ድንቅ ትገልጡ ዘንድ ንዑ ተሰብሰቡ፤ የምትዘምሩ ተናገሩ፤ የምትሰብኩ ስበኩ፤ የስብከት ርዕስ ይኸው ሊቃውንት ውጡ፤ ከቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ጋር ሆሳዕና በአርያም በሉ:: ሕፃናት ያውም የሚጠቡ በምሥጋና እንዳይበልጡን ከእነርሱ ጋር እናመስግን፤ የቢታንያ ድንጋዮች እንዳይበልጡን ንዑ እንሰብሰብ እናመስግን፤ ከጫጉላችን ከሠርጋችን ከምቾታችን እንውጣ አምላክን እናመስግነው:: የአይሁድ ካሕናት ዛሬ ያልቅሱ፤ ዛሬ ይዘኑ፤ በእነርሱም ግብር ያሉ ሁሉ እንዲሁ፤ የጌታቸውን መስዋዕት እንዲህ ባለ ሁኔታ ሆሳዕና እያሉ አልገለጹምና::

 በጺሖሙ ቤተ ፋጌ ሃበ ደብረዘይትየዘንባባ ዝንጣፊ ወዳለበት ደብረዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ደረሰ፤ በወይን ደም ልብሱን የሚያጥበውን ሆሳዕና በአርያም አሉት፤ተፈሥሒ ጽዮን ንጉሥኪ በጽሐ ንጉሥ ዘለዓለም ዘበብርሃኑ ሰደደየዘለዓለም ንጉሥ የሆነው ንጉሥሽ ደርሷል፤ ጽዮን ሆይ ደስ ይበልሽ:: በብርሃኑ ጨለማን አራቀ:: የጽዮን ሕፃናት በክብር በምሥጋና የተቀበሉት እንዲህ እያሉ፡- በሰማያት ለእግዚአብሔር ምሥጋና በምድርም ሰላም በስሙ ለዘለዓለም ኃጢአት ይቅር ይላል::” እገሌን ሄዳችሁ አህያዋንና ውርንጭላዋን ይፈልጋታልና በወይን ደም ልብሱን የሚያጥበው ንጉሥ ላክ ብሎሃል በሉት አላቸው::

 አልጺቆ ኢየሱስ ኢየሩሳልም ተሐውከት ኵላ ምድርኢየሱስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ ምድር ሁሉ ታወከች፡፡ ሕዝቡም እርስ በእርሳቸው ተባባሉ: ይህ በታላቅ ምሥጋና የሚገባው ማነው? እርሱ ናዝራዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ሰማያትና ምድር የሚያመሰግኑት የእግዚአብሔር ልጅ ነው::” እርሱ ሐሞትን ከከርቤ ጋር መራራውን ሊጠጣልን ሆሳዕናን ዞረ፤ አማጽያን ይሰቅሉት ዘንድ አመጽን ሊያስወግድ በአህያ ተጭኖ መጣ:: በኦሪት ዘልደት ልብሱን በወይን ያጥባል አልተባለምን? ዐይኖቹም ከወይን ይልቅ የሚያስደስቱ ናቸው አልተባለምን? ዳዊትም በአፉ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ብሎ አላመሰገነምን? ኢሳይያስስ ንጉሥሽ ስለመጣ ጽዮን ደስ ይበልሽ አላለምን? ዳግመኛም ወንጌል ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በምድር ሰላም በሰማያት ምሥጋና ሆነ አላለምን? እንግዲህ ዘካርያስም ንጉሥሽ ጽዮን ሆይ መጥቷል አለ፤ ይህ ሁሉ ዛሬ ሆነ:: ያድነን ዘንድ ወደ መስቀሉ በሆሳዕና ቀረበ::

 ዘበጦ ለሰይጣን በትዕምርተ መስቀልየአህያውን ውርንጭላ በወይን ሐረግ የሚያስረው በመስቀል ምልክት ሰይጣንን ቀጠቀጠው (ደበደበው)::” ይገርፉህ ዘንድ መጣህላቸው፤ ያራቁቱህ ዘንድ መጣህላቸው፡፡ አላወቁም፤ መድኃኒት ትሆንላቸው ዘንድ መጣህላቸው:: መላእክት ሆሳዕና እያሉ የሚዘምሩልህን ራስህን አድን ብለው ዘበቱብህ:: አብርሃም መስዋዕቱን ዘንባባ ይዞ ዞረው፤ እውነተኛ መስዋዕታችን አንተንም ዘንባባ ይዘን እንቀበልሃለን:: ሰላምን ትሰጣት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም የገባህ አምላክ ለእኛም ሰላማችንን ትሰጠን ዘንድ ፈቃድህ ይሁን::

No comments:

Post a Comment