Pages

Friday, May 16, 2014

ምክረ አበው ቁጥር 5



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
1.  ጥያቄ፡- “ለሰው አፍ ከኮሶና ከነገር ማናቸው ይመራል?"
      ምላሽ፡- "ሲገባ ኮሶ ይመራል፤ ሲወጣ ግን ነገር ይመራል፡፡
2.  ሐሳብህ ብዙ የሚመኝ አንዱን ይዞ የማይሠራ ሲሆንብህ ሰይጣን በጐም ሥራ እንዳትሠራ ባለመሥራትህም እንዳትደነግጥ መልካምን በማሳሰብ እየከለከለ በጥበብ ሰንሰለቱ እንዳሰረህ ዕወቅ፡፡ ስለዚህ አንተ አንድ ሁነህ ሐሳብህን ብዙ አታድርግ፡፡ የምትኖርበትን የማትለቀው አንድ ሥራ ያዝ እንጂ ምኞትህን በየቀኑ አትለዋውጠው፡፡ አንዱን መያዝ አንዱን መልቀቅ የዕብደትና የዝሙት ነውና፡፡
ስለዚህ ቀድሞ የዠመርከውን ትንሹን የበጐ ምኞትህን ሳትሠራው ደግሞ ሌላ ትልቅ አትመኝ፡፡ ምነው መልካም ሐሳብ ቢመኙት ከመሥራት ያደርሳል እንጂ ለምን ይጐዳል ትለኝ እንደሆነ ለሰብአ ዓለም የታዘዘውን ሳይሠራ የመናኒውን ሥራ ቢመኝ የቅርቡን ቤተ ክርስቲያን መሄድ ሳይሆንለት መልካም ሐሳብ ከሆነ ብሎ ኢየሩሳሌም መሄድ ቢመኝ እርሱም ሐሰተኛ ሐሳቡንም ሴሰኛ ያሰኘዋል እንጂ መልካም ሐሳብ ተብሎ ዋጋ አያሰጠውምና፡፡ የሚቻለውን በጐ ሥራ ቸል እያለ የማይሠራውን ማሰብ በእግዚአብሔር ማላገጥ ነውና፡፡ የሐሳብ መለዋወጥ ከምን ይመጣል ትለኝ እንደሆነ የሐሳብ ካንድ ቦታ አልቆምም የሚለው የእግዚአብሔር እጅ በመለየቱ ምክንያት ነው፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር ባልተለየ ጊዜ ከልብህ ውስጥ የሚቀመጠውን መንፈስ ቅዱስ የነፍስህን ልጓም ዛብ ይዞ ባንድ መንገድ ያስኬዳታል፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር ሲርቅህ ግን ነፍስህን ልጓም ዛብ ይዞ በአንድ መንገድ የሚያስኬዳት ባለቤት ታጣና በዚህ ብሄድ ጠላት ያገኘኛል፤ እንዲህ ብናገር እንዲህ ይመስልብኛል፤ እንዲህ ብሠራ እንዲህ ይጠፋብኛል እያለ ሐሳቦቹን ሁሉ የተከታተሉ ጌቶቹ ሆነው ሁሉም አዛዦች ይሆኑበትና ዙርያው ገደል ሆኖበት የሚፈራ አንድም የማይሠራ ይሆናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ሰው ሐሳቡም አንድ እንዲሆን በዚያው እንዲጸና ምን ማድረግ ይሻሏል ትለኝ እንደሆነም መዠመርያ ያሰበውን እሚያዘልቀው ሲሆን ቶሎ ሳይለውጥ ጠንክሮ ካሳቡ ጋር ይከራከር፡፡ በግድ ሊለውጥ የሚገባ የተለወጠውም ሐሳብ የሚሻልና የሚበልጥ ሲሆን የፊቱ የሰይጣን የኋላው የመንፈስ ቅዱስ ምልክት መሆኑን ለማረጋገጥ አስቀድሞ አጥብቆ ይጸልይ፡፡ ከዚያም ብዙ ሐሳቦቹን በብዙ ዕጣ ይጠቅልላቸው፡፡ በመቀጠል ሐዋርያት በይሁዳ ፈንታ እግዚአብሔር የወደደውን ሐዋርያ እንዲመርጥላቸው እንዳደረጉ እርሱም ከሐሳበቹ አንዱን በዕጣ ይቁረጠው፡፡ የቆረጠው ሐሳብ ክፉ ቢሆን እግዚአብሔር የፈረደበት መሆኑን ዐውቆ በትዕግሥት ይቀበለው፤ በጎም ቢያገኘው እርሱን አመስግኖ ይቀበለው፡፡ አንተም ይህን ካላደረግክ ከሁለቱ ዐይነት ሐሳብ በላይ ያለው ሐሳብ ለማስጨነቅና ተስፋ ለማስቆረጥ ከሰይጣን የሚመጣብህ ጾር ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር በጸሎትህ ምርሐኒ እግዚኦ ፍኖተ እንተ ባቲ አሐውር እያልክ ቆራጥ ልቡናን ከፈጠሪ ለምን፡፡” (ፍኖተ አእምሮ)
3.  ልቡናውን ሰብስቦ መጸለይ አልችል ያለው ደቀመዝሙር አረጋዊውን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡- “አባቴ! የጸሎት መጽሐፍ ይዤ ሳነብ ልቡናዬ አይሰበሰብልኝም፡፡ አፌ ቢያነብም ልቡናዬ አይተረጕምም፡፡ እርስዎ እንደነገሩኝ ደግሞ ቅዱሳን በፍጹም አሳባቸው እያሰቡና እያራቀቁ እንባንና ጸጸትን እየጨመሩ የደረሱትን እኛ በልባችን ሌላ እያሰብን በአፋችን ብቻ እንደነርሱ ብንናገር እንደ ገደል እንደ ዋሻ ሆነን በእግዚአብሔር እንደመቀለድ ነው፡፡ ጸሎትም አይሆንልንም፡፡ እንግዲህ ያፍ ጸሎቴ ቅድመ እግዚአብሔር የማይደርስ ከሆነ ጸሎቴን ብተወው ይሻላል ወይስ ባልተወው ይሻላል?” እርሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፡- “ዕውር ሰው በዘንጉ ምድር እየመታ ሲሄ ከመንገድ ላይ ያለ እባብ ለጊዜው ድምጹን ሰምቶ ይመታኛል ብሎ እንደሚሸሽለት ሁሉ አንተም አስተውለህ ባትጸልይም ባፍህ ውስጥ የቃለ እግዚአብሔርን መንኳኳት እየሰሙ አጋንንት መሸሻቸው አይቀርምና ምንም ቅድመ እግዚአብሔር ባይደርስም ጸሎትህን አትተው፡፡ አጋንንትንም ማባረር ጥቅም ነውና፡፡ ብዙ ከምትጸልየውም አንዳንድ ጊዜ ልብህ የሚወድቅባት ቃል ተጠራቅማ ወደ እግዚአብሔር እንድትደርስልህ ምንም ዝርወ ልብ ብትሆንም አፍህም ፍጥረቱ ነውና አንተው በዳይ አንተው አኵራፊ እንዳትሆን ባፍህም ብቻ ቢሆን መነጋገሩን አትተወው፡፡” (ፍኖተ አእምሮ)
4.  አንተ ክብረ ንጽሕናህን ጠብቀህ የምትኖር ድንግል ብትሆን ዝሙት በሚሠራው ወንድምህ ላይ አትፍረድበት፤ እንዲህ ካልሆነ ግን አንተም ራስህ ሕገ እግዚአብሔርን የምታፈርስ ትሆናለህ፡፡ አትዘሙ ያለው አምላክ እርሱ አትፍረድም ብሏልና፡፡አባ ጴሜን
5.  እውነተኛ ክርስቲያን አባቱ ክርስቶስን ይመስላል፡፡ ይሰደዳል እንጂ አያሳድድም፡፡ ይሰደባል እንጂ አይሳደብም፡፡ የጠፉትን ፍለጋ ይደክማል እንጂ ይባስ ብሎ አይገፈትርም፡፡ በወንድሙ ውድቀት ያለቅሳል እንጂ አይደሰትም፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን አባቱ ሌላ ነው፡፡
6.  ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ምስጋና በጊዜውም ያለጊዜውም ሊሆን ይገባል፡፡ ባገኘን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ባጣንም ጊዜ፤ ባለጤና በሆንን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በታመምንም ጊዜ፤ ሲሳካልን ብቻ ሳይሆን ባልተሳካልንም ጊዜ ማመስገን መለማመድ አለብን፡፡ የምስጋናችን ምንጭ የሁኔታዎች መለዋወጥ ሳይሆን ስለ አምላካችን ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ ስንለማመድ በክብር ላይ ክብር ይጨመርልናል፤ እንደ አባታችን ኢዮብ የዲያብሎስን አፍ እንዘጋለን፡፡
7.  ተአምራትን ማድረግ ትፈልጋላችሁን?” እንኪያስ "በዘፈን የደነቆረን ጀሮ መዝሙር እንዲሰማ አድርጉት፡፡ ሴትን በመመኘት የታወረው ዐይን ፈጣሪውን እንዲያይ አድርጉት፡፡ በስርቆት የሰለለ እጅ በምጽዋት እንዲዘረጋ አድርጉት፡፡ ወደ ኃጢአት ቤት በመሄድ ሽባ የሆነውን እግር ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲሮጥ አድርጉት፡፡ ሐሜትን በማውራት ዲዳ የሆነውን ከንፈር መልካም ንግግርን እንዲናገር አድርጉት፡፡ ከተአምራት ሁሉ የበለጠ ተአምር ይሄ ነው፡፡" .ዮሐንስ አፈወርቅ

No comments:

Post a Comment