Pages

Wednesday, May 14, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - የመጨረሻው ክፍል



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት ፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
5. እስክንገለጥ ድረስ ተሰውረናል

  ከማይበሉ የዓሣ ዝርያ ውስጥ የሚመደብ “ኦይስተር” የተባለ ዓሣ አለ፡፡ በሰውነቱ ውስጥም ለጌጣ ጌጥ የሚያገለግል ቅርፊት አለው፡፡ ነገር ግን ይኽ ዓሣ እስካልተገለጠ ድረስ ይኽ ክብሩ አይታይም፡፡ የእኛም እንደዚኹ ነው፡፡ ክርስቶስ እስካልተገለጠ ድረስ ክብራችን አይገለጥም፤ የተሰወረ ነው፡፡ ሕይወታችን ገና ያልተገለጠና የተሰወረ ከኾነ በዚኽ ዓለም መኖር ያለብን እንደሞተ ሰው ነው፡፡ ለምን? ሕይወታችን ክርስቶስ በክብር ሲገለጥ እኛም በክብር እንገለጥ ዘንድ፡፡
 
 ትናንት ሥልጣናቸውን ለማንም ሳያጋሩ ሕዝቡን ቀጥ አድርገው ሲገዙ የነበሩ ኃያላን ዛሬ በቦታቸው ላይ የሉም፡፡ ባላቸው ሃብትና ንብረት ሲመኩ የነበሩ ባለጸጐች ዛሬ በዚያ ስፍራቸው የሉም፡፡ ድምጻቸው ከፍ ብሎ ሲሰማ የነበሩ “ዝነኞች” ዛሬ ድምጻቸው አይሰማም፡፡ ብዙ ሲሮጡ የነበሩ “ብርቱዎች” ዛሬ ደክመዋል፡፡ ሥልጣኑ፣ ሃብቱ፣ ንብረቱ፣ ዝናው፣ ብርታቱ ኃላፊና ጠፊ ነው ማለት ነው፡፡ የተገለጡት ድሮውም የእነርሱ ባልኾነ አገላለጥ ነበር ማለት ነው፡፡ ለእነዚኽ “ኃያላን”፣ “ባለጸጐች”፣ “ዝነኞች”፣ “ብርቱዎች” ለጊዜውም ቢኾን ብዙዎች ጐንበስ ቀና ብለውላቸዋል፡፡ ኃይላቸው፣ ሃብታቸውና ንብረታቸው ከእነርሱ እየራቀ ሲኼድ ግን “ጐንበስ ቀና” ሲሉላቸው የነበሩ ሰዎችም ለእነርሱ ያላቸው አመለካከት ይቀየራል፡፡ ስለዚኽ ጐንበስ ቀና ሲሉ የነበሩት ሰዎች ሲያከብሩት የነበረው ኃያላኑን፣ ባለጸጐቹን፣ ዝነኞቹን፣ ብርቱዎቹን ሳይኾን ሌላ ነገራቸውን ነበር ማለት ነው፡፡ ሰዎቹ ሲያከብሩት የነበረው በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሰው ሳይኾን አፈርና ትቢያ የኾነውን ነገር ነበር ማለት ነው፡፡ ታድያ ከዚኽ በላይ ምስኪንነት ምን አለ? ምንም የለም፡፡ ክብራችን ሞገሳችን ሃብት ወይም ንብረት፣ ሥልጣን ወይም ዝና ሳይኾን እግዚአብሔር ከኾነልን ግን ክብራችን መቼም ቢኾን አይደበዝዝም፡፡ ይልቁንም እየደመቀ ይኼዳል እንጂ፡፡ ስለዚኽ መገለጫችን ባልኾነ መንገድ አንገለጥ፤ እስክንገለጥ ድረስ ተሰውረን እንቈይ እንጂ፡፡
 ወገኖቼ! በዚኽ ወራት የምናሳልፈው ጊዜ የዕረፍት ጊዜ አይደለም፡፡ ይኽ ወራት ገና ስንዠምር እንደተነጋገርነው ነፍሳችን እንደምን ካለ ቀንበር እንደተላቀቀች፣ ዳግመኛም በመንግሥተ ሰማያት የምታገኘውን ተድላና ደስታ የምናስብበት ወደዚያም ለመድረስ የምንቻኰልበት እንጂ ድጋሜ በድንዛዜ የምንያዝበት ወራት አይደለም፡፡ ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን ክርስቶስ ካጸዳው በኋላ ድጋሜ የምናቆሽሽበት ወራት አይደለም፡፡ አሮጌው ሰውነታችን እንደሞተ የምናስቀጥልበት እንጂ አዲሱን ሰውነታችን ከተነሣበት የምንጥልበት ወራት አይደለም፡፡ በሰማያዊ ስፍራ የተቀመጠው እኛነታችን፥ ሕይወታችን ክብራችንና ደስታችን ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ሰውረን የምናቆይበት እንጂ የእኛ ባልኾነ አገላለጥ የምንገልጥበት አይደለም፡፡
 ይኽን እስከ መጨረሻ አጽንተን እንድንቆይ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፤ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment