Pages

Friday, May 2, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - ክፍል ፫

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፳፭ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
2.    ተነሥተናል
   ሐዋርያው፡- “ሞታችኋልና” ብሎ አላቆመም፤ ጨምሮም፡- “እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ” በማለት እንደተነሣንም ነገረን እንጂ፡፡ በጥምቀት ውኃ ሞቱን በሚመስል ሞት ስንሞት፥ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ግብጻውያን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ አዲሱ ሰውነታችን ግን እስራኤላውያን ባሕሩ ተከፍሎላቸው እንደተሻገሩ ተሻግሯል (ተነሥቷል)፡፡ ብልየት ያለበት የቀዳማዊ አዳም ሰውነታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተቀብሮ አዲሱ ሰውነታችን ሕይወትን አግኝቶ ተነሥቷል፡፡ መሬታዊው ሰዋችን ሞቶ ሰማያዊው ሰዋችንን ለብሰን መንፈሳውያን ኾነናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን ተመልሰናል፡፡


አኹን ከእኛ የሚጠበቀው ይኽን ተፈጥሯችን ሳናቆሽሽ መጠበቅ ነው፤ እንደተነሣን መዝለቅ ማለት ነው፡፡ ይኽን ለማድረግ ከእኛ የሚጠበቀው ተራራ መውጣት አይደለም፤ የባሕር እሳት መሻገርም አይደለም፡፡ ይኽን ጠብቀን እንድንቈይ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ፈቃዳችንን ብቻ ነው፤ የሚሠራው እርሱ ነውና /ዮሐ.፲፭፡፭/፡፡ ይኽ በእኛ ዓቅም እንደማይቻል የሚያውቀው እግዚአብሔር መጽንዒ መንፈስ ቅዱስን ያደለንም ስለዚኹ ነው፡፡ አዲሱን ሰውነታችን ለብሰን ከተነሣን በኋላ እንደ ቀድሞ ምልልስ የምንጓዝ ከኾነ ግን ተመልሰን ወድቀናል፤ አዲሱ ሰዋችንን አውልቀን አሮጌውን ሰው ድጋሜ ለብሰነዋል፡፡ በእኛነታችን ውስጥ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሲመት፣ ፍትወትም ካለ አዲሱ ሰውነታችን ከእኛ ጋር የለም፡፡
በኃጢአት የመቃጠል ስሜት፣ ዝሙት፣ ርኵሰትና ክፉ ምኞት ከእኛ ዘንድ ካለ አሮጌው ሰው ኾነናል፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ አላደረግንም፡፡ ፋሲካን ማክበራችንም ትርጕም የለውም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ፋሲካ ማለት መሻገር ማለት ነው፤እግዚአብሔር ወልድ እኛን ከወደቅንበት አንሥቶና ተሸክሞ ከዚኽ ምድር ወደ ሰማያት ተሻግሯልና (ተነሥቶ ዓርጓልና)፡፡ ተወዳጆች ሆይ! የምናመልከውን አምላክ መስለን ካልተሻገርን የመሻገር በዓልን (ፋሲካን) ማክበራችን ምን ጥቅም አለው? ከጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን ሥራ፣ ከፍቅረ ዓለም ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ካልተሻገርን ፋሲካን ማክበራችን ምን ረብሕ አለው? ብዙዎቻችን ፋሲካን አክብረናል፡፡ ነገር ግን ከዚኽ ዓለም ወደ አባታችን በሕይወት ሳንሻገር ነው፡፡
ክርስቲያን ኾኖ ሰማያዊውን ፋሲካ ሳይኾን ምድራዊ ፋሲካን የሚያከብር ካለ ከምስኪኖች ኹሉ ይልቅ ምስኪን ነው፡፡ ይኼ ማለት የዲያብሎስ ዓለም ተመችቶታል፤ ከዚኽ በላይም መሻገርን አይሻም ማለት ነው፡፡ ታድያ ከዚኽ የባሰ ምስኪንነት ምን አለ?
እንኪያስ ተወዳጆች ሆይ! ፋሲካን እናክብር፡፡ እስከ አኹን በኃጢአት ውስጥ ካለን ወደ ብርሃን እንሻገርና የመሻገር በዓልን እናክብር፡፡ ከክፉ ሥራ ወደ ጽድቅ ሥራ እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከኃይል ወደ ኃይል እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ይኽን ዓለም የሚያሰነካክል ፈርዖን (ዲያብሎስ) ተሰነካክሏልና እንሻገር፡፡ ተሻግረንም ሰማያዊውን ፋሲካ እናክብር፡፡ በግብጽ የነበሩት እስራኤላውያን የበጉን ደም በጉበኑና በኹለቱም መቃን ሲቀቡት አጥፊው ከቤታቸው አልፏል፡፡ ይኸውም በጉ በራሱ ያንን የማድረግ ኃይል ስለነበረው አይደለም፤ ደሙ የክርስቶስ አምሳል በመኾኑ ነው እንጂ፡፡ እኛ ግን የአማናዊውን በግ ደም በልቡናችን፣ በአስተሳሰባችንና በሰውነታችን ኹሉ እንቀባና እንሻገር፡፡
ይኽን ስናደረግ በእባቡና በጊንጡ ማለትም በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ሥልጣን ይኖረናል /ሉቃ.፲፡፲፱/፡፡ የምንበላው በግ ራሱ ሕይወት ስለኾነ ሞት በእኛ ላይ አይነግሥም /ዮሐ.፲፬፡፮/፡፡ በዚኽ ዓለም ሳለን ከዚኽ ደስታ ተካፋዮች ከኾንን (የመዠመሪያውን ትንሣኤ ልቡና ከተነሣን) በሚመጣው ዓለምም ይኽን ደስታ ሊገለጽ በማይችል አኳኋን እንካፈላለን (ኹለተኛውን ትንሣኤ እንነሣለን) /ሉቃ.፳፪፡፲፭-፲፮/፡፡ አባቶቻችን ይኽን ቀኖና የቈነኑልን ይኽን ፋሲካ እንድናከብር ነውና በእውነት እናክብረው፡፡ ብንወድቅ እንኳን መልሰን በመነሣት እናክበረው፡፡ አለመነሣት የእኛ የክርስቲያኖች ተፈጥሮ አይደለምና ከተፈጥሯችን ውጪ አንመላለስ፡፡
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment