Pages

Monday, May 5, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - ክፍል ፬



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፳፯ ቀን፣ ፳፻፮ ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!


3. ተቀምጠናል

 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አኹን በክበበ ትስብእት ያለው በምድር ሳይኾን በሰማያዊው ስፍራ ነው፡፡ ክርስቶስ ያለው በባሕርይ አባቱ ዕሪና ተቀምጦ ነው፡፡ እኛም፡- “ወአንሥአነ ወአንበረነ ምስሌሁ በሰማያት በኢየሱስ ክርስቶስ - ከእርሱ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” እንዲል ከእርሱ ጋር ተዋሕደን ስለተነሣን ያለነው በሰማያዊ ስፍራ ነው ማለት ነው /ኤፌ.፪፡፯/፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀመጠ መባሉ የእኛን መቀመጥ መናገሩ ነው፤ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ስንወለድ የእርሱ ሕዋሳት ኾነናልና፡፡ ስለዚኽ ከክርስቶስ ጋር ተዋሕደን ለመኖር ትንሣኤ ልቡናን ከተነሣን በኋላ ሰማያዊ ግብራችንን ትተን በምድራዊ ግብር ብቻ መያዝ ክርስቲያናዊ ተፈጥሯችን አይደለም፡፡ ክርስቲያናዊ ተፈጥሯችንን ካልለቀቅን በስተቀር ይኽን ማድረግ አንችልም፡፡  

የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ እንደኾነ ብዙ ጊዜ ተምረናል /ኤፌ.፭፡፳፫/፡፡ ታድያ የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን) ራስ ክርስቶስ በሌለበት ስፍራ ሰውነቱ ማለትም ክርስቲያኖች እንደምን ሌላ ቦታ (ምድራዊ ግብር) ላይ ሊቀመጡ ይችላሉ? ራስ በሌለበትስ ሌላው የሰውነት ክፍል ሕይወት ሊኖረው ይችላል ወይ? አይችልም! ታድያ ሰው ሕይወት በሌለበት ስፍራ እንደምን መቈየትን ይመርጣል? አንድ ሰው ራሱ (ጭንቅላቱ) ሌላ ቦታ፥ ሌላው የሰውነት ክፍሉም ሌላ ቦታ ኾኖ በሕይወት መኖር አይችልም፤ ይኽ የተፈጥሮ ሕግ ነውና፡፡ የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወትም እንደዚኹ ነው፡፡ ምንም እንኳን ለጊዜው በዚኽ ምድር የምንቈይ ብንኾንም ዘለዓለማዊ ስፍራችን (መኖሪያችን) ግን እዚኽ አይደለም፡፡ መጻተኞች ነን፡፡ አንድ መጻተኛ (ስደተኛ) በካምፕ ውስጥ ኾኖ ብዙ ንብረትን ስለማፍራት ሊያስብ ይችላልን? በፍጹም! ባይኾን አገሩ ከገባ በኋላ ሊያደርገው ስለሚገባው ነገር ሊያስብ ይችላል፡፡ የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወትም እንደዚኹ ነው፡፡ ልናስብ የሚገባው አገራችን (መንግሥተ ሰማይ) ከገባን በኋላ ልናገኘው ስለሚገባን ክብር ነው፡፡ አኹን ተጓዦች ነን፡፡ ተጓዥ ደግሞ ስንቅ እንጂ ብዙ ሃብትና ንብረት አይፈልግም፤ ንብረቱ ከብዶት ጉዞውን ሊያሰነካክልበት ይችላልና፡፡ ንብረቱ ለጉዞው አጋዥ ከኾነ ግን ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ የእኛም እንደዚኽ ነው፡፡ 
እግዚአብሔር ትምህርት እንድንማር ሲያደርገን ለጉዞአችን የሚኾን ስንቅን እንድናገኝበት ነው፡፡ ስንማር ገንዘብ እናገኛለን፡፡ ክኂል እንቀስማለን፡፡ በገንዘባችን ደግሞ ራሳችንን ሳይኾን ወንድማችንን እናገለግልበታለን፡፡ በክኅሎታችን ወንድማችንን፣ ቤተ ክርስቲያንን እናገለግልበታለን፡፡ ይኽን ስናደርግ በሰማያዊው ስፍራችን እስከ መጨረሻው እንዘልቃለን፡፡ ሐዋርያው፡- “እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፡፡ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” የሚለንም ይኽን ሲያሳስበን ነው፡፡ ሞተናል፤ ተነሥተናል፤ ተቀምጠናልም፡፡ ሕይወታችን ሕይወት የሚኾነው ይኽን ሳንረሳ የዘለቅን እንደኾነ ብቻ ነው፡፡
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment