Pages

Friday, July 11, 2014

ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ ፭ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓል ኹለቱም ታላላቅ ሐዋርያት በሰማዕትነት ያረፉበትን በዓል ነው፡፡ ይኽ ዕለት በየዓመቱ አይለዋወጥም፡፡ የሐዋርያትን ጦም ከጨረስን በኋላ የምናከብረው ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋም በትምህርቷም ኹሉ እነዚኽን ታላላቅ ሐዋርያት ታነሣለች፤ ታወድሳለች፤ ሰማዕትነታቸውንም ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡ ምንም እንኳን በእነዚኽ ሐዋርያት ስም የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን በብዛት ባይገኝም በአዲስ አበባ ግን “ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ” የሚባል ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡
 ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ስንሔድ ይኽ ዕለት “ሓወርያ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ስያሜውም የእነዚኽን ሐዋርያት ሰማዕትነት ለመግለጥና ለማሰብ የተሠጠ ነው፡፡ እረኞች ጅራፋቸውን ገምደው በቡድን በቡድን እየኾኑ ያስጨኹታል፡፡ የጅራፉ ጩኸት የእነዚኽ ሰማዕታት መገረፍ፣ መቁሰል፣ መሰየፍ፣ መሰቃየት፣ መሰቀል የሚያስታውስ ነው፡፡ አባቶቻችን ክርስትናውን ማንበብና መጻፍ ወደማይችለው ማኅበረ ሰብእ ምን ያኽል እንዳሰረጹትም ከዚኽ እንገነዘባለን፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ለተማረው ማስተማር ይቅርና አባቶቻችን የሠሩትን እንኳን መጠበቅ አቅቶናል፡፡

 እነዚኽ ኹለቱም ታላላቅ ሐዋርያት የሚያመሳስላቸውም የሚያለያያቸውም ብዙ ነጥብ አለ፡፡ እስኪ አስቀድመን የሚያለያዩአቸውን ነጥቦች በጥቂቱም ቢኾን እንመልከት፡፡
 ቅዱስ ጴጥሮስ፥ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም - እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እያለ ስለ ክርስቶስ ሲመሰክር ሰምተው ክርስቶስን ከተከተሉት የመጀመሪያዎቹ ኹለት ሐዋርያት አንዱ ነው /ዮሐ.1፡29-38/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ከዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያትም ኾነ ከሰባ አርድዕት ወገን አይደለም፤ የተጠራውም ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ከኢየሩሳሌም 273 ኪ.ሜ. ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ በመሔድ ላይ ሳለ ነበር /ሐዋ.9፡1-4/፡፡ የተጠራውም ከሐዋርያት ኹሉ መጨረሻ ላይ ነበር፡፡ የደከመው ግን ቀድመው ከተጠሩ ሐዋርያት በላይ ነበር፡፡ አዎ! ከእኛ መካከል ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት የዘገየ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ስለ መዘግየቱ ማንም አይዘን፡፡ አኹን መጥቶም ቢኾን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ከሌሎች አገልጋዮች ይልቅ ብርቱ ኾኖ ማገልገል ይቻለዋል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ከነቢያት ኹሉ የመጨረሻው ነበር፡፡ ነገር ግን ሴቶች ከወለዷቸው ይልቅ እንደርሱ ያለ ነቢይ አልተነሣም /ማቴ.11፡11/፡፡ አውግስጢኖስ የተባለ ሊቅ፡- “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! አንተን ለመውደድ ምን ያኽል ዘገየኹ?” ብሏል፡፡ ሊቁ እንዲኽ ቢዘገይም ግን በሚልዮን የሚቈጠሩ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መንጋ ጨምሯል፡፡ እጅግ በርካታ መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡
 ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ባለች ቤተሳይዳ በተባለች ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ወላጆቹም በቅፍርናሆም ይኖሩ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የተወለደው በንግዷ በታወቀችና የኪልቂያ ዋና ከተማ በምትኾን በጠርሴስ ነበር፡፡ ማንኛውም አይሁዳዊ ልጅ ከ5 ዓመት ዠምሮ የሚማረውን ትምህርት (ከፈሪሳዊው አባቱ) እየተማረም አደገ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከዚኽም በተጨማሪ ከአባቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ፣ የግሪክና የሮም የሌሎችንም በጠርሴስ ከተማ የሚኖሩትን ልዩ ልዩ አሕዛብን ቋንቋና የድንኳን ስፌት እየተማረ አደገ፡፡ ለሐዋርያነት በተመረጠ ጊዜ አሕዛብን ለማስተማር የረዳውና የጠቀመው እነዚኽ በጠርሴስ ሳለ ቋንቋቸውንና ልማዳቸውን እየተማረና እያየ ማደጉ ነው፡፡ ዛሬ እኛ የምንማረው ቋንቋ ለምን አገልግሎት ነው? ቋንቋ ይችላል ለመባል? ሥራ ለማግኘት? ውጪ አገር ሔደን ላለመቸገር? ወይስ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ለወንጌል አገልግሎት? የምዕራባውያንን ባሕልና ልማድ የምናየውስ ለምን ይኾን? ክርስቲያናዊ ባሕላችን ትተን ወደነርሱ ለመሔድ? ወይስ በጥበብ እነርሱን ወደ ክርስትና ለማምጣት?
 ቅዱስ ጴጥሮስ ባለ ትዳር ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ድንግል ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አገልግሎቱን የዠመረው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅርን በማሳየትና በማመን ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ከክርስቶስ ጋር የተዋወቀው ቤተ ክርስቲያንን በማሳደድ ነበር፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ያልተማረና ዓሣ አጥማጅ ነበር /ሐዋ.4፡13/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን በዓለማዊ ትምህርት በተርሴስ ዩኒቨርሲቲ፤ በመንፈሳዊው ደግሞ ዕድሜው 15 ዓመት ሲሞላው በአባቱ ፈቃድ ወደ ትውልድ ሀገሩ በመመለስ በኢየሩሳሌም ከነበረው የታወቀው የገማልያል ትምህርት ቤት ተምሯል። በዚያም የአይሁድን ሕግና ሥርዓት እየተማረ ለ15 ዓመት ቆይቷል። ገማልያል ፈሪሳዊ ስለ ነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይኽን ፈሪሳዊነት ተቀብሎታል። በ30 ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አካል ኾኖ ተቈጥሯል፡፡
 ከዚኽ መረዳት እንደምንችለው እግዚአብሔር አምላካችን ኹላችንንም እኩል እንደሚወደን ነው፡፡ በትዳር ብንኖር፤ በድንግልና ብንኖር፤ የተማርን ብንኾን ያልተማርን ብንኾን እኩል ለጌታ እናስፈልጓለን፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ የእኛ ፈቃደኝነት ነው፡፡ ባለ ትዳር መኾናችን ክርስትያን ከመኾን አያግደንም፤ ድንግልም ብንኾን ክርስቲያን መኾንን አይከለክለንም፡፡ የተማርን ብንኾን በተማርነው ትምህርት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንችላለን፡፡ ያልተማርንም ብንኾን በደረጃችን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንችላለን፡፡
 ቅዱስ ጴጥሮስ የሕዝብ ሐዋርያ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የአሕዛብ ሐዋርያ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሽማግሌ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ወጣት ነበር፡፡ አዎ! ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን ብቻ አትፈልግም፤ ሽማግሌውም ያስፈልጋታል፡፡ ሽማግሌውን ብቻ አትፈልግም፤ ወጣቱም ያስፈልጋታል፡፡ ዛሬ ወደ ቅዱስ ቁርባን የሚቀርበው ማን ነው? ወጣቱ ይቀርባልን? ተወዳጆች ሆይ! እስኪ እናስተውል! ወጣትነት ኃጢአት ለመሥራት የተፈቀደ የሚመስል ዕድሜ አልኾነምን? ክርስቶስ ግን የኹሉም እንጂ የሕፃናት ወይም የሽማግሌዎች ብቻ አይደለም፡፡ እዚኽ ጋር የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ቃል ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ሊቁ እንዲኽ ይለናል፡- ትዳር አለኝ፤ ልጆችን አሳድጋለኹ፤ የቤት አባወራ ስለኾንኩኝ ይኽንን ማድረግ አልችልም፡፡ ወጣት ነኝ፤ ገና መሮጥ አለብኝአትበሉኝ፡፡ ከእናንተ የሚፈለገው ፈቃዳችኁ ብቻ ነውና፡፡ ዕድሜም ቢኾን፣ ባለጸግነትም ቢኾን፣ ማጣትም ቢኾን፥ ሌላም ቢኾን ይኽን ኹሉ ከማድረግ አይከለክላችኁምና፡፡ እንዴት? ሽማግሌዎችም፣ ወጣቶችም፣ ሚስቶችም፣ ሕፃናት አሳዳጊዎችም፣ ዕደ ጥበቦኞችም፣ ወታደሮችም ይኽን ኹሉ ፈጽመውታልና፡፡ ዳንኤል ወጣት ነበር፤ ሠለስቱ ደቂቅ ሕፃናት ነበሩ፤ ዮሴፍ ባርያ ነበር፤ ሉቃስ ሐኪም ነበር፤ ሊድያም ሐር ሻጭ ነጋዴ ነበረች፤ ጳውሎስንና ሲላስን በወኅኒ ሲጠብቅ የነበረውም ፖሊስ ነበር፤ ቆርነሌዎስ ደግሞ ዐሥራ አለቃ ነበር፤ ጢሞቴዎስ በሽተኛ ነበርነገር ግን ይኽን ከማድረግ የከለከላቸው አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡ እነዚኽ እንደ እኛ ሴቶች፣ እንደ እኛ ወጣቶች፣ እንደ እኛ ሽማግሎች፣ እንደ እኛ ነጋዴዎች፣ እንደ እኛ አሠሪዎች፣ እንደ እኛ ሠራተኞች፣ ወታደሮችና ሲቪል ነበሩ፡፡”
 ከቅዱስ ጴጥሮስ ይልቅ ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል፡፡ ኹለቱም ወንጌላውያን ቅዱስ ማርቆስና ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ፡፡ ኹለቱም ጳጳሳት ጢሞቴዎስና ቲቶ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ፡፡ እኛስ ማንን አፈራን? ኧረ ማፍራቱ ቀርቶብን ራሳችንን ባዳንን?  
ቅዱስ ጳውሎስ 100 ምዕራፍ ያሏቸው 14 መልዕክታትን ጽፏል፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ኹለት መልዕክታትን ጽፏል፡፡
የቅዱስ ጴጥሮስ አስተምህሮ ቀለል ያለና በርሱ መጠን የቀረበ ነው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ አሰባበክ ግን እጅግ ጥልቅ የኾነ የነገረ መለኮት ትምህርትን የያዘ ነው፡፡ በውስጡ በእንተ ግዝረት ወጥምቀት፣ በእንተ ክህነተ ብሉይ ወሐዲስ፣ በእንተ መሥዋዕተ ብሉይ ወሐዲስ፣ በእንተ ሙሴ ወክርስቶስ፣ ስለ እምነትና ጸጋ በስፋትና በጥልቀት አስተምሯል፡፡
 ቅዱስ ጴጥሮስ ችኩል ነበር፡፡ በዚኽም አንዳንድ ጊዜ ተመስግኖበታል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ተወቅሶበታል፡፡ ስለ ጌታችን የባሕርይ አምላክነት ለመመስከር፣ አትሰቀል ለማለት፣ ሰቃልያነ ክርስቶስን ለመግደል ሰይፍ ለማንሣት ችኩል ነበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስ፡፡ ይኽ ችኩልነቱ ግን የጌታ ደቀ መዝሙር ከመኾን አላስከለከለውም፡፡ እንደዉም ይኽ ችኵልነቱ በበዓለ ሓምሳ 3,000 ምእመናን ወደ ክርስቶስ እንዲመልስበት አድርጐታል፡፡ እግዚአብሔር ከእነ ማንነታችን እንደሚጠቀምብን ታስተውላላችኁን? ከመራሩ ጣፋጭ ማውጣት እንደሚችልበት ትገነዘባላችኁን? ቅዱስ ጳውሎስ ግን ምንም ለሃይማኖቱ ቀናተኛ ቢኾንም ችኵል አልነበረም፡፡
ምንም እንኳን እነዚኽ ታላላቅ ሐዋርያት ከላይ በጠቀስናቸውና በሌሎች ነገሮች የተለያየ ስብዕና ያላቸው ቢኾኑም በሰማዕትነታቸውና በሌሎች በርካታ ቁምነገሮች ግን የተመሳሰሉ ናቸው፡፡ እስኪ ከሚያመሳስልዋቸው ነገሮች ጥቂሶችን እንጥቀስ፡-
ኹለቱም አይሁዳውያን ነበሩ /ፊልጵ.3፡5/፡፡ ኹለቱንም የጠራቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ራሱ ነው /ማቴ.4፡18-20፣ ሐዋ.9፡1-4/፡፡ የኹለቱንም ስማቸው የለወጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ የቀድሞ ስሙ ኬፋ ሲኾን /ዮሐ.21፡15/፥ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ሳውል ይባል ነበር /ሐዋ.9፡4/፡፡
መንፈስ ቅዱስ ሲያድርባቸው ኹለቱም በአዲስ ቋንቋ ተናግረዋል /ሐዋ.2፣ 1ኛ ቆሮ.14፡18/፡፡ ኹለቱም እጃቸውን በመጫን በአዲስ አማንያን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ያስድሩ ነበር /ሐዋ.8፡17፣ 19፡5-6/፡፡ ኹለቱም ብዙ ተአምራትን አድርገዋል /ሐዋ.19፡11/፡፡ ኹለቱም ሙታንን አስነሥተዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታ የተባለች ብላቴናን ሲያስነሣ /ሐዋ.9፡36-41/፤ ቅዱስ ጳውሎስም አውጤኪስ የተባለውን ጐበዝ አስነሥቷል /ሐዋ.20፡7-12/፡፡
ኹለቱም ቀናተኞች ነበሩ፡፡ ወንጌል ለማስተማር ትጉሃን ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ምኵራብም ከአይሁድ ምኵራብ ውጪም ይመሰክር ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም፣ በልዳ፣ በኢዮጴ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር /ሐዋ.9፡22-31/፡፡ ከኢዮጴ ወደ ቂሳርያ በመሔድም ቆርነሌዎስን አጥምቋል /ሐዋ.10/፡፡ በተለያዩ ሀገራት ማለትም በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያ፣ በቢታንያ ተበታትነው ለነበሩ አይሁድ አስተምሯል /1ኛ ጴጥ.1፡1/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ከሐዋርያት ኹሉ ይልቅ እጅግ እንደ ደከመ ራሱ ተናግሯል /1ኛ ቆሮ.15፡10/፡፡ በኢየሩሳሌም አስተምሯል፤ በአንጾክያ አስተምሯል፡፡ መላ ግሪክን በወንጌል ያዳረሳት ርሱ ነው፡፡ በዐራት ታላላቅ ሐዋርያዊ ጕዞዎች መላ እስያን፣ አውሮጳን እስከ ስፔን ድረስ በየብስ በእግሩ፣ በባሕር በመርከብ እየሔደ አስተምሯል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን መሥርቷል፡፡ በአንደኛው ሐዋርያዊ ጕዞው ብቻ ወደ 2000 ኪሎ ሜትር በእግር ሔዷል፡፡ በየቤቱ እየዞረ አስተምሯል፡፡ በአርዮስፋጐስ አደባባይ አስተምሯል፡፡ ወደ ምኵራብ እየገባ አስተምሯል፡፡ በነገሥታት ፊት አስተምሯል፡፡ በእስር ቤት ውስጥ አስተምሯል፡፡ አቤት የእኛ ስንፍና? ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአንድ ወቅት እንዲኽ ብሎ ነበር፡- “ወይ እንደ ቅዱሳን ለመትጋት ሞክሩ፤ ካልኾነ ግን በስንፍና አልጋ ተይዛችኁ ሳለ ለመታበይ ያኽል ብቻ የቅዱሳን ዘር ነኝ አትበሉ፡፡”
ኹለቱም “መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ - የሰውን ፊት አይተው የማያዳሉ ገሳጽያን መምህራን” ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ብሎ ለሊቀ ካህናቱ መመለሱ ይኽን ያመለክታል /ሐዋ.5፡29/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በነገሥታት ፊት ስንኳ ለመመስከር ጥቡዕ (ደፋር) ነበር፡፡ ፊልክስ የተባለው ገዢ ጳውሎስን “ፈራው” የተባለውም ስለዚኹ ነው /ሐዋ.24፡25/፡፡ በንጉሥ አግሪጳ ፊት እስረኛ ኾኖ ሳለ እንኳን ምንም ሳይፈራና ሳያፍር ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር የነበረውም ስለዚኹ ነው /ሐዋ.26፡27-29/፡፡ በሌላ ጊዜም እንደዚኽ አድርጓል /ሐዋ.22፡25-29፣ 25፡10-12/፡፡ ዛሬስ ምን እየተሠራ ይኾን? ከነገሥታቱ ጋር መመሳሰል ወይስ …? 
ኹለቱም ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ወደ ኋላ አይሉም ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን ለማታለል የሞከሩትን አናንያንና ሚስቱ ሰጲራን እንዲሞቱ አድርጓል /ሐዋ.5፡4-9/፡፡ ይኽን ያደረገው ቤተ ክርስቲያን በእንደዚኽ ዓይነት ጕዳይ ላይ ቸልተኛ ልትኾን እንደማይገባት ሲያስረዳ እንጂ ከሰዎቹ ጋር የግል ጥላቻ ኑሮት አልነበረም /ሐዋ.5፡11/፡፡ ሲሞን መሰርይንም እንደዚኽ ገስጾታል /ሐዋ.8፡18-22/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ልክ በእንደዚኽ ዓይነት መንገድ ገስጿቸዋል /1ኛ ቆሮ.5፡3-5፣13/፡፡ በርያሱስ (በሌላ ስሙ ኤልማስ) ለተባለ ጠንቋይም በድፍረት “አንተ ተንኰል ኹሉ፥ ክፋትም ኹሉ የሞላብኽ የዲያብሎስ ልጅ የጽድቅም ኹሉ ጠላት የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታፍርምን” ብሎ ገስጾታል /ሐዋ.13፡10/፡፡
 ምንም እንኳን እንዲኽ መገሥጻን ቢኾኑም፥ ኹለቱም ሐዋርያት ግን እጅግ ትሑታን ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን፡- “ኃጥእ ነኝና ከእኔ ራቅ፤” በሌላ ጊዜም “እግሬን አታጥበኝም” ሲለው የነበረው ስለዚኹ ስለ ትሕትናው ነበር /ሉቃ.5፡8/፡፡ በዛሬው ዕለት ሰማዕትነት ሲቀበል እንኳን ሐምሌ 5 የሚነበበው ስንክሳራችን እንደሚነግረን “እንደጌታየ ሳይኾን የቁልቁሊት ስቀሉኝ” ያለውም ከትሕትናው የተነሣ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እንደዚኹ ራሱን፡- “ተሳዳቢ፣ አሳዳጅ፣ አንገላች ነበርኩ” ይላል /1ኛ ጢሞ.1፡13/፡፡ ከሐዋርያት ኹሉ እንደሚያንስም ተናግሯል፤ ራሱንም “ጭንጋፍ” እያለ ጠርቷል /1ኛ ቆሮ.15፡8-9/፡፡ እንግዲኽ ከገማልያል እግር ስር ኦሪትን ከጌታችንም ወንጌልን ጠንቅቆ የተማረ፣ 14 መልዕታትን የጻፈ፣ እስያን አውሮጳን ግሪክን ሮምን በእግሩ አካልሎ አብያተ ክርስቲያናትን የተከለ፣ ለ42 ዓመታት ያኽል በባሕርና በእግር እየተመላለሰ ወንጌልን ሌት ተቀን ያስተማረ፣ በ12ቱንም ሐዋርያት ሀገረ ስብከት እየገባ ወንድሞቹን ያገዘ፣ ለመጓዝ አመቺ ጊዜ ሲያገኝ በአካል፥ ሲታሠርና መንቀሳቀስ ሲከለከል ደግሞ ጣቶቹ ብዕር ጨብጠው እየጻፈ መልእክቶቹን በየሀገረ ስብከቱ የላከ፣ ቀን እያስተማረ ሌሊት ደግሞ ድንኳን እየሰፋ ወጪውን በራሱ የሸፈነ፣ በመጨረሻም የሰማዕትነትን አክሊል የተቀበለ ታላቅ ሐዋርያ “እኔ ጭንጋፍ ነኝ” ካለ አንድ ወይም አምስት መጻሕፍትን ጻፍን፥ በአንድ ደብር ላይ ቁጭ ብለን ወንጌል አስተማርን፥ በእግር ሳይኾን በአውሮፕላን ወደ ክፍላተ አገራት ተጕዘን ለአንድ ወይም ለኹለት ቀን ወንጌል አስተማርን ብለን ራሳችንን ከፍ ከፍ የምናደርግ የዘመኑ አገልጋዮች፥ ከዚኽ ሐዋርያ ምን እንማር ይኾን? “በዚኽ ዘመን እግዚአብሔር እኔን ባያስነሣ ኖሮ” ብለን የምንታበይ መንፈሳዮች (መንፈሳውያን የምንመስል አስመሳይ አገልጋዮች) ከእነዚኽ ቅዱሳን ሐዋርያት ምን ትምህርት እንቀስም ይኾን?
ኹለቱም ብዙ መከራ ተቀብለዋል፤ ብዙ ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ሊገደሉ ተብለው በኋላ ግን በገማልያል አስታራቂነት እንደተረፉ በግብረ ሐዋርያት መጽሐፍ ተጽፏል /ሐዋ.4፡1፣ 5፡32-41/፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ወኅኒ ተጥሎ እንደ ነበር ተጠቅሷል /ሐዋ.12፡3-4/፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ስደትና መከራማ በቍጥር አይታወቅም፡፡ ሐዋርያው ራሱ በሮሜ ክታቡ ላይ “ስለ አንተ ቀኑን ኹሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን” ያለውም ስለዚኹ ነው /ሮሜ.8፡36/፡፡ በሌላ ስፍራም “ብዙ ጊዜ ደከምኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ተገረፍኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ታሰርኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ለሞት የሚያበቃ መከራ ተቀበልኩ፡፡ አይሁድ አንዲት ስትቀር አርባ አርባ አምስት ጊዜ ገረፉኝ፡፡ መልሰው መላልሰው በበትር ደበደቡኝ፡፡ አንድ ጊዜ በድንጋይ ወገሩኝ፡፡ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሠበረች፤ ተንከራተተች፡፡ ሦስት ሌሊትና ሦስት ቀን ሙሉ በባሕር ውስጥ ስዋኝ ውዬ ስዋኝ አደርኩ፡፡ በመንገድም ኹል ጊዜ መከራ እቀበል ነበር፡፡ በፈሳሽ ውኃ ሽፍቶች መከራ አጸኑብኝ፡፡ ዘመዶቼ እስራኤል መከራ አጸኑብኝ፡፡ በከተማ መከራ ተቀበልኩ፡፡ በበረኻ መከራ ተቀበልኩ፡፡ በባሕር መከራ ተቀበልኩ፡፡ ቢጽ ሐሳውያን መከራ አጸኑብኝ፡፡ በቀዊም፣ በሰጊድ፣ በትግሀ ሌሊት፣ በራብና በጽምዕ፣ በብዙ ጦም፣ በብርድና ዕራቁት በመኾን መከራ ተቀበልኩ፡፡ ኹል ጊዜ ከዚኽ ሌላ ያገኘኝ መከራ ብዙ ነው፡፡ ዕለት ዕለት የሚከብደኝ ግን የአብያተ ክርስቲያናት ጕዳይ ነው” ብሏል /2ኛ ቆሮ.11፡23-27/፡፡ ትንሽ ከደከምን በኋላ እኛን የሚያሳስበን ስለምን ይኾን? ስለምንበላው የመብል ዐይነት? ስለሚያዝልን የሆቴል ዐይነት? ወዮ! ወንድም እኅቶቼ! እባካችኁ የእነዚኽ ቅዱሳን ዓጽም እንዳይወቅሰን ራሳችንን እናስመርምር (ንስሐ እንግባ)፡፡ ለሕመማችንም ወደ ሐኪም ቤት (ወደ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን) እንሒድ፡፡ ዓምደ ሃይማኖት የተባለው ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፡- “የትዕቢት እብጠት አስቸግሮኻልን? እንኪያስ ወደ ምሥጢራት ቅረብ፡፡ እኔ በልቤ ትሑት ነኝ ያለው ጌታም ትሕትናን ይሰጥኻል” ያለውን እናስታውስ፡፡  
ኹለቱም ሐዋርያት ያረፉት በሰማዕትነት ነው፡፡ ኹለቱም ያረፉት በ67 ዓ.ም. ኔሮን ቄሣር በቤተ ክርስቲያን ላይ መራር ትእዛዝን ሲያስተላልፍ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተዘቅዝቆ በመሰቀል፥ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በ74 ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሰይፎ ክብረ ሰማዕትነት ተሸልመዋል፡፡ 

 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት ከማረፉ በፊት ለጊዜው ለልጁ ለጢሞቴዎስ ለፍጻሜው ግን ለኹላችንም ያስተላለፈውን መልዕክት በመጥቀስ የዛሬውን ትምህርታችን እናጠቃልል፡፡ ሐዋርያው በእስር ቤት ኾኖ፥ የሞት ድግስ በተዘጋጀለት ዋዜማ እንዲኽ ነበር ያለው፡- “ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! በሐዋርያነት ጸንተኅ፣ በዝግታ በጸጥታ ኾነኅ ታስተምር ዘንድ እዳኝብኻለኹ፡፡ ዓላውያን መከራ በሚያፀኑብኅ ጊዜ፣ ዓላውያን መከራ በማያፀኑብኅ ጊዜ፤ አንድም የምእመናን ጀሯቸው ተከፍቶ ልቡናቸው ነቅቶ ትምህርቱን በሚቀበሉበት ጊዜ፣ አዕምሯቸው ፈዝዞ ጀሯቸው ደንዝዞ ትምህርቱን በማይቀበሉበት ጊዜ ታስተምር ዘንድ እዳኝብኻለኹ፡፡ ፀሐይ የሚሞቀኝ የለም ብላ መውጣቷን፣ ውኃም የሚጠጣኝ የለም ብሎ መፍሰሱን እንደማይተው ኹሉ፥ አንተም የሚሰማኝ የለም ብለኅ አገልግሎትኅን፣ ማስተማርኽን አታስታጕል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት ብሎ በጠራራ ፀሐይ ጕባኤ እንደዘረጋ አትዘንጋ፡፡ ለአንድ ኒቆዲሞስ ብሎ ማታ ማታ ያስተምር እንደ ነበር አትርሳ፡፡ ለአንድ ዘኬዎስ ብሎ ወደ ቤቱ እንደገባ አትርሳ፡፡ ለአንድ ቶማስ ብሎ ለሐዋርያት ዳግም እንደታያቸው አትዘንጋ፡፡
 
 እኔ ተልዕኮየን ፈጽሜአለኹ፡፡ የማርፍበት ጊዜም ደርሷል፡፡ በጐ ገድልን ተጋደልኹ፡፡ ቅድድሜንም ጨረስኩ፡፡ ሃይማኖቴንም ጠበቅኹ፡፡ እንግዲኽ ወዲኽ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ እግዚአብሔር በዕለተ ሞት በዕለተ ምጽአት የሚሰጠኝ ዋጋዬ ይቈየኛል፡፡ ይኽ የሚቈየኝ ዋጋም ጊዜአዊ የአበባ ጕንጉን አይደለም፤ ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው እንጂ፡፡ ይኽን የዘለዓለም አክሊል ስቀዳጅ በዙርያ ኾነው የሚያጨበጭቡልኝ የዚኽ ተውኔታዊ ዓለም ሰዎች አይደሉም፤ ንዑዳን ክቡራን ቅዱሳን መላዕክት ናቸው እንጂ፡፡ በዚኽ ዓለም የሚያገኙት ሹመት ሽልማት ተሎ ያልፋል፤ ደስታውም እንደዚኹ፡፡ ተልዕኮኅን ፈጽመኽ የምታገኘው ሹመት ሽልማት ግን እስከ የሌለው፥ ከጊዜ ቀመርም ውጪ የኾነ ደስታ ነው፡፡ በዚያ ኹሌ ማሸብረቅ አለ፡፡ በዚያ ኹሌ ክብር አለ፡፡ በዚያ … ኹሌ ልዕልና አለ፡፡ አዎ! ልሒድ፤ ከክርስቶስ ጋር ለመኖር ናፍቂያለኹ፡፡ መስጠቱም ለእኔ ብቻ አይደለም፤ የሱን መምጣት ለሚወዱ ክርስቲያኖች ኹሉ ነው እንጂ፡፡ ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! ይኽን ኹሉ ዘርዝሬ የምነግርኅ ለውዳሴ ከንቱ፣ ለተርእዮ እንዳልኾነ ዕወቅ፤ ተረዳም፡፡ ይኽን ኹሉ ዘርዝሬ የምነግርኅ የክርስትና ዋጋው፥ የአገልግሎት ዐስቡ እንደምን ታላቅ እንደኾነ እንድትነገዘብ አንተም ይኽን ከእኔ ተምረኽ እንድትበረታ ነው፡፡ እኔ መምህርኽ ያለ ወንጀሌ ብዙ መከራ ከተቀበልኩ ከላይ በገለጽኩልኽ መንገድም ተልዕኮየን ከፈጸምኩ፥ አንተም ምን ዕዳየ ብለኽ ሳታጉረመርም ተልዕኮኽን ፈጽም፤ እስከ መጨረሻ ጽና፡፡ በክርስትናዊ ምልልስኅ ኹሉ ደስተኛ ኹን እንጂ ኀዘንተኛ አትኹን፡፡ ለምን? በጐውን ገድል ተጋድያለኹና፡፡ በጐውን ገድል የምልኽም ከላይ የዘረዘርኩልኽን ጸዋትወ መከራዎቼ ስለ ጌታዬ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዬ የተቀበልኳቸው ስለኾኑ ነው፡፡ ልጄ ወዳጄ! የተጠበቀልኅን ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ታገኝ ዘንድ ተልዕኮኅን ፈጽም” /2ኛ ጢሞ.4፡6-8/፡፡
 የእነዚኽን ከዋክብተ ቤተ ክርስቲያን፣ የእነዚኽን ብርሃናተ ዓለም ሐዋርያት በረከታቸውና ረድኤታቸው በእውነት በኹላችን ላይ ይደር፡፡ በጥቂቱም ቢኾን እንድንመስላቸው የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!   
  

No comments:

Post a Comment