Pages

Saturday, September 6, 2014

አዲሱ ዓመት - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ፫)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጳጉሜ ፩ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የቀጠለ…                       
 ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን መውቀስም አለ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “እንዴት ብሎ? ርግጥ ነው ብዙውን ጊዜ ሠራተኞቻችንን እንወቅሳለን፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ መውቀስስ እንደምን ያለ ነው?” አዎ! የሚሰክር ወይም የሚሰርቅ ሠራተኛ ወይም ጓደኛ ብናይ ወይም ከዘመዳችን አንዱ ወደ ተውኔት ቤት፣ ወይም ለነፍሱ ምንም ረብሕ ወደማያገኝበት ሥፍራ ሲሮጥ፣ በከንቱ ሲምል፣ የሐሰት ምስክርነትን ሲሰጥ፣ ወይም ሲዋሽ፣ ወይም ሲቈጣ ብናየው ዠርባችንን ብንሰጠውና ብንገሥፀው ወቀሳችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡

 ዳግመኛም አንድ ሰው ቢበድለን፣ ርሱ ራሱ የሠራውንም ጥፋት በእኛ ቢያመካኝ ስለ እግዚአብሔር ብለን ይቅር ልንለው ይገባል፡፡ ብዙዎቻችን ግን ለጓደኞቻችን፣ ለሠራተኞቻችን የዚኽ ተቃራኒውን ነው የምናደርገው፡፡ ጓደኞቻችን ወይም ሠራተኞቻችን ቢበድሉን እናንባርቃለን፤ ይቅርታ የሌለው ፍርድም እንፈርድባቸዋለን፡፡ እኛው ራሳችን እግዚአብሔርን በገቢር ስንሰድብ አንድም ስናሰድብ ወይም ነፍሳችንን ስንጐዳ ግን እንደበደልን አይሰማንም፡፡ ይኽ ግን በአዲሱ ዓመት ልናስተካክለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ዕለት ዕለትም ልንለማመደው ይገባል፡፡  
 የበደሉንን ሰዎችስ ወዳጅ ማድረግ ይገባልን? አዎ! ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል የበደሉንን ሰዎች ወዳጅ ማድረግ ይገባናል፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል ሰውን ጠላት ማድረግስ? አዎ! ይቻላል፡፡ ለመኾኑ ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን ወዳጅና ጠላት ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው? ሰውን ወዳጅ ማድረግ ሲባል ያንን ሰው ከገንዘባችን፣ ከማዕዳችን እንዲካፈል በእኛም እንዲደገፍ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ አንድን ሰው እውነተኛ ወዳጅ ኾንነው አንድም አደረግነው የሚባለው ነፍሱን እንዳይጐዳ ብንገሥፀውና ብንመክረው፣ ቢበድል (በበደሉ የሚጐዳው ርሱ ራሱ ነውና) እንደ ጠላት ሳይኾን እንደ ወዳጅ ቀረብ ብለን የሚረባውን ብንነግረው፣ ከወደቀበት የኀጢአት አረንቋ እንዲነሣ ብናደርግ ለዚኽም ዘወትር በጸሎት ብንረዳውና ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርብ ብናደርግ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን ጠላት ማድረግም ይፈቀዳል፡፡ ይኽን ከዚኽ በፊት ያላከናወንነው ከኾነም ከአኹኑ አዲሱ ዓመት መዠመር እንችላለን፤ ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ሰውን ጠላት ማድረግ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጋጠ ወጥ፣ ክፋትን የተመላ፣ ንግግሩ (ትምህርቱ) ኹሉ በምንፍቅና መርዝ የተለወሰ፣ ዘወትር ነፍሳችንን የሚያውካትና የሚጐዳት ሰው ካለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቀኝ ዓይንኅም ብታሰናክልኽ አውጥተኽ ከአንተ ጣላት” እንዳለ /ማቴ.5፡29/ እነዚኽን ሰዎች መራቅ ጠላትም ማድረግ ይፈቀዳል፡፡ እነዚኽ ሰዎች ቀኝ ዓይን ተብለው መጠቀሳቸውም ምንም እንኳን እንደ ዓይናችን የምናያቸው ወዳጆቻችን ቢኾኑም ነፍሳችንን የሚጐዷት ከኾነ ከእኛ ዘንድ ልናርቃቸው ይገባል፡፡
 ንግግራችንም ዝምታችንም ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብሎ መናገር ሲባል ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ከአንድ ጓደኛችን ጋር ቁጭ ብለን ስንጨዋወት “ማን ሥልጣን ላይ ወጣ፣ ማን ወረደ፣ ማን አለፈ፣ ማን ምን ክብር አገኘ” እያልን ከምንጨዋወት ይልቅ ስለ ነገረ ሃይማኖት፣ ስለ ገሃነመ እሳት፣ ስለ መንግሥተ ሰማያት ብንጨዋወት መናገሩ ጥቅምን ይሰጣል፡፡ ነፍሳችንን በማይጠቅማት ነገር አላስጨነቅናትምና፡፡ ይኽን ዓይነት ኅብረት ባንተወዉም አንጐዳንም፡፡ በኋለኛው ቀን ላይ ይኽ ኹሉ ማድረጋችን አንዳች ጥቅም ይሰጠናልና፡፡ ስለዚኽ ለነፍሳችን አንዳች የሚጠቅም ነገር በሌለው ስብስብ መካከል መቀመጡና ማውራቱ ለእኛ ጉዳት እንጂ ረብሕ የለውም፡፡ የዚኽ ስብስብ መንፈስ ለውጦ ስለ ነገረ እግዚአብሔር ማውራቱም ስለ እግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል፡፡ ዝምታችንም ለእግዚአብሔር ክብር መኾን ይገቧል፡፡ ምንም ሳንበድለው ክፉ ለሚያደርግብን ሰው፣ ሳንወቅሰውና ሳናንጐራጉርበት በትዕግሥት ዝም ብንል ዝምታችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡
ማመስገንና መገሠፅ፣ ወይም ከቤት ውስጥ መኾንና አለመኾን ወይም መናገርና አርምሞ ብቻ አይደለም፤ ኀዘናችንም ደስታችንም ስለ እግዚአብሔር ክብር ሊኾን ይገባል፡፡ አንድ ወንድማችን ኀጢአት እየሠራ ብናየው ወይም እኛው ራሳችን በበደል ስንወድቅ ብናለቅስና ብናዝን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የኾነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፣ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና” /2ኛ ቆሮ.7፡10/ ኀዘናችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡ አንድ ወንድማችን መልካም ነገርን ስላገኘ ልክ ለእኛ እንደተደረገ አድርገን እግዚአብሔርን ብናመሰግንም ደስታችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡ ከዚኽ ደስታም እጅግ ብዙ ጥቅምን እናገኝበታለን፤ እንኪያስ ይኽን በአዲሱ ዓመት እንለማመደዋ!!!
 በወንድሙ ደስታ መደሰት ሲገባው ወንድሙ ስለ ተጠቀመ ብቻ በቅናት ከሚቃጠል ሰው በላይ አሳዛኝ ሰው ማን አለ? እስኪ ንገሩኝ! በወንድሙ ደስታ በማዘኑ የእግዚአብሔርን ፍርድ በራሱ ላይ በመጨመር በነፍስ በሥጋ ከሚጐዳ ቅናተኛ ሰው በላይ የሚያሳዝን ፍጥረት ማን አለ? ወንድማችን ስለ ተጠቀመ ብናመሰግን ወይም ብንደሰት፣ ወንድማችን ስለ ተጐዳም ብናዝን እና ብናለቅስ ይኽንንም ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ብናደርገው አንጠቀምምን?
  ፀጉርን ከማሳጠር በላይ ምን ትንሽ ነገር አለ? ነገር ግን ይኽም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሴቶች በፀጉራቸው ምክንያት ወንዶች የሚሰነካከሉ ከኾነና ይኽንን ዐውቀው ባይቈርጡትም ወንዶቹ በማይሰናከሉበት መንገድ ቢሸላለሙት፣ ደካማ ወንድሞቻቸው በማይሰናከሉበት መንገድ ራሳቸውን ቢያጌጡ ይኽን ለእግዚአብሔር ክብር አድርገዉታልና ሹመት ሽልማታቸው የበዛ ነው፡፡ የክፉ ምኞት ፍላጻን ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል አስቀርተዉታልና ዋጋቸው በሰማያት ዘንድ ታላቅ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ አንዲት ኩባያ ውኃን የሰጠ ሰው ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያገኝ ከኾነ፥ የምናደረግው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር ብለን የምናከናውነው ከኾነማ ሹመት ሽልማታችን እንደምን አይበዛ?
  ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ መሔድም አለመሔድም አለ፡፡ ምን ማለት ነው? ወደ ክፋት የማንሔድ ከኾነ፣ የቆነጃጅትን ውበት በማድነቅ ስም ልቡናችን በምኞት መንፈስ የማንጠመድ ከኾነ፣ አንዲት ቆንጆ ልጅ በፊታችን ብናይና እንደምታሰናክለን ተረድተን ዓይናችንን ከርሷ ዞር የምናደርግ ከኾነ ውበትን ለእግዚአብሔር ክብር አዋልነው ይባላል፡፡
 አለባበሳችንም ቢኾን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እጂግ ውድ የኾኑ አልባሳትን ባንለብስ፣ ሰውነታችንን እጂግ ሳናራቁት፣ በአጭሩ ሰውን የማያሰናክል አለባበስን ብንከተል አለባበሳችን ስለ እግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል (በነገራችን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአጸደ ሥጋ በዚኽ ዘመን ቢኖርና ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ የምናየውን የእኅቶቻችንን አለባበስ ቢያይ ምን ብሎ ሊገሥፅ እንደሚችል አስቡት፡፡ ምክንያቱም እኅቶቻችን በስመ ዘመናዊነት የሚለብሱት እጅግ በጣም አጭር ቀሚስ ወይም ሱሪ የብዙ ደካማ ወንዶችን ልብ በዝሙት ይፈታተናልና)፡፡
 የምጫማው ጫማ እንኳን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለሚያደርጉት ጫማ ከዓቅም በላይ ሲጨናነቁ አያለኹ፡፡ ፊታቸውን በተለያየ መንገድ ለማሸብረቅ የሚወዱትን ያኽል ስለ ጫማቸው ውበት እጂግ የሚጨነቁ ሰዎችን አያለኹ፡፡ ምንም እንኳን ይኽ እንደ ትንሽ ነገር አድርገን ብናስበውም ዘወትር በወንዶችም በሴቶችም የምናየው ነገር ነው፡፡ ስለዚኽ ጫማችን እንኳን ሳይቀር ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል ማለት ነው፡፡ በአካሔዳችንም፣ በአለባበሳችንም፣ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደሚቻል ሲናገር ጠቢቡ ምን እንደሚለን እስኪ እናድምጠው፡- “ከአለባበሱና ከአካሔዱ ከአሳሳቁም የተነሣ የሰው ጠባዩ ይታወቃል” /ሲራክ 19፡27/፡፡ ስለዚኽ በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ የምናደርገው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር የምናደርገው ከኾነ አሕዛቡም፣ መናፍቁም፣ ፈላስፋውም አስቦበት ሳይኾን እንዲኹ በእኛ ይደነቃል፡፡
 ትዳራችን እንኳን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ መኝታችን (በትዳር ውስጥ የሚደረገው ሩካቤ) ንጹሕ ማድረግ፣ ትዳርን ለብር ወይም ሌላ ምድራዊ ነገርን ለማግኘት ሳይኾን ነፍሳችንን ለማዳን፣ እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረግ ከኾነ ለእግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል፡፡ የትዳር አጋራችንን ከዘለዓለማዊ ሕይወት አንጻር እንጂ ከውበት፣ ከሃብት፣ ወይም ከሌላ ጊዜአዊ ጥቅም አንጻር የማንመለከት ከኾነ ትዳራችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡ በአዲሱ ዓመት ይኽን ልንለማመድ ይገባናል፡፡
 ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment