Pages

Sunday, September 7, 2014

አዲሱ ዓመት - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (የመጨረሻው ክፍል - ክፍል ፬)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጳጉሜ ፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የቀጠለ…
 እግዚአብሔር የሚወዳችኁ እናንተም የሚምትወዱት ልጆቼ! ይኽን ኹሉ በዝርዝር የምነግራችኁ ለምን ይመስላችኋል? ይኽን ኹሉ በዝርዝር መናገሬ በዘዴ ኹላችንም የምናደርገውን ማናቸውም እንቅስቃሴያችን ለእግዚአብሔር ክብር እናደርገው ዘንድ ስለምሻ ነው፡፡ በባሕር የሚነግዱ ነጋዴዎች ንብረታቸውን ወደ ከተማ ዳር መልሕቅ ካመጡ በኋላ መዠመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር በቀጥታ ወደ ገበያ ሥፍራ መሔድ አይደለም፡፡ ወደ ገበያ ሥፍራ ከመሔዳቸው በፊት ስለ ትርፋቸው ያስባሉ እንጂ፡፡ እኛም በምናደርገው ኹሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን ጥቅም ማሰብ አለብን፡፡

 ከእናንተ መካከል፡- “ኹሉንም ነገር ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ ማድረግ ግን የሚቻል አይደለም” የሚል ፈጽሞ አይገኝ፡፡ ጫማችንን ብንጫማ፣ ፀጕራችንን ብናስተካክል፣ ልብሳችንን ብንለብስ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ብንጓጓዝ፣ የቁመናችን አኳኋን፣ ንግግራችን፣ ስብስባችን፣ መግባታችን፣ መውጣታችን፣ መገሠፃችን፣ ማመስገናችን፣ መውቀሳችን፣ አለ መውቀሳችን፣ ሰውን ወዳጅ ወይም ጠላት ማድረጋችን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ የሚቻለን ከኾነ እኛ ከፈቀድን ለእግዚአብሔር ክብር ተብሎ የማይደረግ ምን ይቀራል?
 የወኅኒ አለቃ ከመኾን ምን የከፋ አለ? የወኅኒ ጠባቂ ሕይወት እጅግ የምትከብድ አትመስልምን? ነገር ግን የልቡና ፈቃደኝነት ካለን የወኅኒ አለቃም ተኩኖ ኹሉንም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻላል፡፡ እስረኞችን ማዳን ይቻላል፡፡ ያለ አግባብ የታሰሩትን መንከባከብ ይቻላል፡፡ ንጹሐን ሰዎችን አለ አግባብ ከሚያሰቃዩ ክፉዎች ጋር አለመተባበር ይቻላል፡፡ እስረኞችን እንደ አለቃ ሳይኾን እንደ ወንድምና እኅት ማገልገል ይቻላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሃይማኖት የመለሰውን የወኅኒ ጠባቂ ስንመለከት እንደዚኽ ዓይነት ሰው ነበር /ሐዋ.16፡25-40/፡፡ ስለዚኽ በአዲሱ ዓመት ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር እናድርገው ብንል ይቻለናል ማለት ነው፡፡
 እስኪ ንገሩኝ! ከነፍሰ ግድያ በላይ ምን የከፋ ነገር አለ? ነገር ግን በዚኽ የነፍስ ግድያ እንኳን የጽድቅን ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ አትደንግጡ! ግድያ እንኳን ለእግዚአብሔር ክብር ተብሎ ሊደረግ ይችላል፡፡ ከእናንተ መካከል “ነፍሰ ገዳይ ሰው እንዴት አድርጐ ነው በነፍሰ ገዳይነቱ ጽድቅ ሠራ ተብሎ ሊነገርለት የሚችለው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተመዘገበውን አንድ ታሪክ አንሥቼ ልነግራችኁ እወዳለኹ፡፡ አንድ ጊዜ ምድያማውያን ከእስራኤል ጋር ጦርነት ይገጥሙ ዘንድ እግዚአብሔርን ለቁጣ ቀስቅሰዉት ነበር፡፡ በጦርነቱም ልዕልናቸውን በማሳየት፥ የእግዚአብሔርን መልካም ፈቃድ ለማስቀረት አስበው ሴቶቻቸውን በማሳመር በድንኳኑ ፊት ቆመው ነበር፡፡ በዚኽም እስራኤላውያንን በዝሙት እስከ መሳብና ለጣዖት እንዲሰግዱ እስከ ማታለል ደርሰው ነበር፡፡ ይኽም ብቻ ሳይኾን እስራኤላውያን ሃይማኖት የለሽ እንዲኾኑ ፈልገው ነበር፡፡ ፊንሐስ ግን ይኽን ባየ ጊዜ በእጁ ሰይፍ ይዞ ኹለት ሲያመነዝሩ የተገኙትን ሰዎች ሆዳቸውን በሰይፍ ወግቶ ገድሏቸዋል፡፡ በዚኽም የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደኾነ አረጋግጧል፡፡ ፊንሐስ ያደረገው ነገር ሰውን መግደል ነው፡፡ የዚኹ ግድያ ዓላማ ግን እስራኤልን በጠቅላላ ማዳን ነበር፡፡ በመኾኑም ከግድያ እንኳን ጽድቅን ማፍራት ይቻላል ማለት ነው /ዘኅ.25/፡፡
ፊንሐስ በፈጸመው ግድያ እጁ አልረከሰም፡፡ ይልቁንም ያ “ነፍሰ ገዳዩ” ፊንሐስ እስራኤላውያንን ከዝሙት ጠንቅ ጠብቆ ንጹሐን አደረጋቸው እንጂ፡፡ ፊንሐስ እነዚያ ኹለቱንም የገደላቸው ጠልቷቸው አልነበረም፤ የተቀሩትን የእስራኤል ሰዎች ለማዳን እንጂ፡፡ ኹለቱንም ብቻ በመግደል እልፍ እስራኤልን በነፍስ በሥጋ ከመሞት ለመታደግ እንጂ፡፡ ይኸውም ሐኪሞች እንደሚያደርጉት ነው፡፡ ሐኪሞች አንድ በቁስል መበስበስ (በጋንግሪን) የተጠቃን የሰውነት ክፍል ቈርጠው ቢያስወግዱት የተቀረውን ሰውነት ለማዳን ነው፡፡ ፊንሐስም ያደረገው እንደዚኹ ነው፡፡ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት ይኽንን በተመለከተ ሲናገር፡- “ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፤ ቸነፈሩም ተወ፡፡ ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ኾኖ ተቈጠረለት” ብሏል /መዝ.106፡30-31/፡፡ ፊንሐስ ያደረገው ነገር ትክክል ነው ተብሎ እስከ ዘለዓለም ሲነገርለት ይኖራል፡፡ (በነገራችን ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አልመለስ ያሉትን መናፍቃን ከቤተ ክርስቲያን አውግዛ የምትለያቸው ቀሪውን ምእመን እንዳይበክሉ እንጂ ጠልታቸው አይደለም፡፡ በቅርብ ጊዜ የተወገዙት የተሐድሶ አራማጆች የተወገዙትም ከዚኹ አንጻር ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ውግዘቱ ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው፡፡)
  ዳግመኛም አንድ ሰው በመጸለዩ ምክንያት እግዚአብሔርን አስቈጥቷል፡፡ ምክንያቱም ጸሎቱ ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ አልነበረም፤ ርሱም ፈሪሳዊው ነው /ሉቃ.18/፡፡ ፊንሐስ ግድያን ስለ ፈጸመ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አገኘ፤ ፈሪሳዊው ደግሞ በአንጻሩ ስለ ጸለየ እግዚአብሔርን አስቈጣ፡፡ ስለዚኽ ማናቸውም የምናደርገው ነገር ምንም መንፈሳዊ ቢኾንም ለእግዚአብሔር ክብር እስካልተደረገ ድረስ ትርፉ ጉዳት ነው፡፡ ሥጋዊ ሥራም ብንሠራ ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ ሰውን ከመግደል በላይ እጅግ ክፉና ዘግናኝ ነገር ምን አለ? ነገር ግን ይኽ ለእግዚአብሔር ክብር የሚደረግ ከኾነ ከዚኹ ግድያ እንኳን ጽድቅን ማግኘት ይቻላል፡፡
 እንግዲኽ ከነፍሰ ገዳይ እንኳን እንዲኽ ዓይነት ጽድቅ ከተገኘ እያንዳንዱ ግብራችን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ አይቻለንም እንደምን ማለት ይቻለናል? የልቡና ፈቃደኝነት ካለን ግን ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ ብንገዛም ብንሸጥም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ ከአግባብ በላይ ዋጋን በመጨመር ሸማቹን ማኅበረ ሰብ ባለ ማስቸገር ንግዳችን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ አንድን ዕቃ በመደበቅ (አኹን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ኹኔታ ዘይትንና ስኳርን ማለት እንችላለን) አለአግባብ ለመክበር ብለን የምንደብቀው ከኾነ “እኽልን የሚያስቀር ሰው በሕዝቡ ዘንድ የተረገመ ነው” እንደተባለ /ምሳ.11፡26/ ንግዳችን እግዚአብሔር የከበረበት ንግድ አይደለም፡፡
 ከእናንተ መካከል፡- “አባታችን! አንድ ምሳሌ መስለኽ ልታስተምረን ስትችል ወደዚኽ ኹሉ ዝርዝር መግባት ለምን አስፈለገኽ?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ አንድ የሕንፃ ተቋራጭ አንድን ሕንፃ ለመገንባት የሚዠምረው መሠረት በመጣል ነው፡፡ ከዚያም ደረጃ በደረጃ የተቀረውን የሕንፃን ክፍል ይገነባል፡፡ በመጨረሻም ሕንፃው እጅግ የሚያምር እንዲኾን የቅብ (finishing) ሥራን ይሠራል፡፡ እኛም ይኽን ኹሉ በዝርዝር ማየታችን በክፍል 2 ትምህርታችን፡- ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለኽ? ነፍስኅ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋኽን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለኽ? አስቀድመኽ ቤቱን (ነፍስኽን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመኽ ለነፍስኽ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለኽ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለኽ አስብ እንጂ እንዲኹ ከአኹን (ከአዲሱ ዓመት) በኋላ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለኁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲኽ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚኹ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ /1ኛ ቆሮ.10፡31/፤” የሚለውን መሠረት ይዘን ነው፡፡
  ከእንግዲኽ ወዲኽ ብንጸልይም፣ ብንጦምም፣ ብንገሥፅም፣ ይቅር ብንልም፣ ብናመሰግንም፣ ብንወቅስም፣ ብንገባም፣ ብንወጣም፣ ብንሸጥም፣ ብንገዛም፣ ብንናገርም፣ ዝም ብንልም፣ ማናቸውን ነገር ብናደርግ ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ ይኽን ያልዠመርን ካለንም አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ እንዠምረው፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር የማናደርገው ከኾነ ግን አንሥራው፤ በማኅበር መካከል እንድንናገር ብንገፋፋም አንናገር፡፡ የትም ብንሔድ ይኽቺውን የሐዋርያው ቃል በልቡናችን ጽላት ጽፈን ይዘናት እንሒድ፡፡ ርሷም (ኃይለ ቃልዋ) የምናደርገው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር እንድናደርገው ታሳስበናለች፡፡ የምናደርገው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር የምናደርገው ከኾነም “ያከበሩኝን አከብራለኹ” ብሏልና /1ኛ ሳሙ.2፡30/ ከሰው እጅ ሳይኾን ከራሱ ከክብር ባለቤት ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ በዚኽም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ክብርን እንጐናጸፋለን፡፡ እንኪያስ ከእንግዲኽ ወዲኽ ክብር የክብር ክብር፣ አምልኮና ውዳሴ ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይገባዋልና በቃል ብቻ ሳይኾን በገቢር ጽድቅ በምግባር በትሩፋት ዘወትር እናክብረው፡፡ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን!!!
መልካም አዲስ ዓመት ይኹንላችኁ፤ ይኹንልን!!!

5 comments:

  1. yetenesaw haab melkam new gin tilket binorew tiru yihon neber

    ReplyDelete
    Replies
    1. ከክፍል አንድ ዠምረው ቢያነቡት የተሻለ ነው፡፡

      Delete
  2. i like the message.God bless you.if you don't mind can you tell us the source?

    ReplyDelete
    Replies
    1. You can easily Google it by saying: St. John Chrysostom Sermon on New Year.

      Delete