Pages

Wednesday, October 15, 2014

ለይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ የተሰጠ ምላሽ (ክፍል ኹለት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 5 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ምስጢረ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው!!!

 የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት እግዚአብሔር የገለጠው እውነት እንጂ የይሖዋ ምስክሮች እንደሚሉት ሰዋዊ ትምህርት አይደለም፡፡ ቃሉን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንፈልገው ብሎ መጠየቅ ግን የዕውቀት ማነስ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚፈለገው የትምህርቱ መኖር እንጂ የቃሉ መኖር አይደለምና፡፡ እንኳንስ ሥላሴ የሚለው ቃል ይቅርና መጽሐፍ ቅዱስ የሚል ቃል እንኳን በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኘውም፡፡

 ትምህርቱ ግልጽ የማይኾነውም ኹሉንም ነገር በአመክንዮ ለመቀበል ስለምንጨነቅ እንጂ ስለሌለ አይደለም፡፡ ገላጭ በኾነ ቃል “ሥላሴ” ብሎ የተናገረው ግን በ170 ዓ.ም. ቴዎፍሎስ ዘአንጾክያ ነው /Wikipedia.org/wiki/Trinity/፡፡ ከዚያ ትንሽ ቆይቶም ጠርጡለስ የተባለ ሊቅ “ሥላሴ” ብሎ ደጋግሞ በድርሳኑ ጽፏል /ANF03. Latin Christianity: Its Founder, Tertullian By Philip Schaff,  Against Praxeas, pp 1044/፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና ደረጃ ይኽ እምነቴ ነው ብላ የወሰነችው ግን በ381 በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ነው /Early Christian Doctrines, By J.N.D. Kelly, pp 88/፡፡ ምንም እንኳን እንዲኽ በቀኖና ባይገለጥም ትምህርቱ ግን ገና ከብሉይ ኪዳን አንሥቶ የነበረ መሠረተ ትምህርት ነው፡፡
 እስኪ ከብሉይ ኪዳን አንሥተን የተገለጠውን የሥላሴን ትምህርት በዘመናት ከፋፍለን እንመልከተው፡፡
የሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን
 ጐርጐርዮስ ገባሬ መንክራት የተባለ ሊቅ፡- “ከሰው ወገን ማንም አያውቃቸውም ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ዋሕድ ሰው ኾኖ አባቴ! እነሆ ስምኽን ለሰው ኹሉ ገለጥኩ፡፡ እኔንም የባሕርይ ልጅኽ እንደኾንኩ ያውቁ ዘንድ ዓለም ሳይፈጠር በነበረ ጌትነትኅ ግለጠኝ ብሎ ካስረዳ በኋላ ነው እንጂ” እንዳለው ወልድ ዋሕድ ሰው ኾኖ እስኪገልጠው ድረስ ሥሉስ ቅዱስን ማንም አያውቃቸውም ነበር” /ሃይማኖተ አበው ዘጐርጐርዮስ፣ 13፡9/፡፡ ይኽ ማለት ግን በብሉይ ኪዳን የሥላሴ ትምህርት አልተጻፈም ወይም አልተነገረም ማለት አይደለም፡፡ ወልደ እግዚአብሔር በለቢሰ ሥጋ መጠቶ እስኪገልጠው ድረስ ተሠውሮ ቈየ እንጂ፡፡ ይኽም የኾነበት ምክንያትም እስራኤላውያን ሕፃናተ አዕምሮ ስለኾኑ ትምህርተ ሥላሴ እንዳይከብዳቸውና ሦስት አምላክ ወደሚል የተሳሳተ መንገድ እንዳይሔዱ ነው፡፡
 በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ ምስጢረ ሥላሴ የሚናገር አንቀጽን ስንፈልግ ገና በመዠመሪያው መጽሐፍ በመዠመሪያው ቍጥር ነው የምናገኘው፡፡ “እግዚአብሔር በመዠመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል /ዘፍ.1፡1/፡፡ እዚኽ አንቀጽ ውስጥ እግዚአብሔር ተብሎ የተተረጐመው በዕብራይስጡ “ኤሎሂም” ነው የሚለው፡፡ ኢሎሂም ማለትም አምላኮች ማለት ነው፡፡ “አምላኮች” ስላለ ብዙ አማልክት እንደኾኑ እንዳናስብ ግን ወዲያውኑ “ፈጠረ” አለ፡፡ ይኽ ኤሎሂም የሚለው ብዙ ቁጥር ስንት እንደኾነ በጐላና በግልጥ የምናውቀውም በሐዲስ ኪዳን አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ተብሎ በተገለጠው ትምህርት ነው /ማቴ.28፡19/፡፡
 የይሖዋ ምስክሮች ይኽን ትምህርት ላለመቀበል “ይሖዋ አንድ ኾኖ ሳለ እንፍጠር፤ እንደባልቀው የሚሉ ቃላትን ሲናገር ታላቅነትን ወይም ግርማዊነትን የሚያመለክት አነጋገር ነው” ይላሉ፡፡ ይኽ ግን ፈጽሞ ስሕተት እንደኾነ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚነግረን እውነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ነገሥታት ራሳቸውን በብዙ ቁጥር ሲናገሩ አንመለከታቸውምና፡፡ ለምሳሌ፡-
·        ፈርዖን ዮሴፍን “ሾምኩኽ” አለው እንጂ “ሾምንኽ” አላለውም /ዘፍ.41፡41/፡፡
·        ዳርዮስ “አዝዣለኹ” አለ እንጂ “አዝዘናል” አላለም /ዕዝ.6፡12/፡፡
·        ናቡከደነፆርም እንደዚኹ “አዘዝኹ” አለ እንጂ “አዘዝን” አላለም /ዳን.4፡6/፡፡
 ስለዚኽ ይኽ የእግዚአብሔር አነጋገር የይሖዋ ምስክሮች እንደሚሉት የግርማዊነት አነጋገር አይደለም፤ የአንድነት የሦስትነት ነው እንጂ፡፡  
 ከላይ ከጠቀስነው በተጨማሪ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እጅግ ብዙ ትምህርቶች አሉ፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
Ø “እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ኾነ” /ዘፍ.3፡22/፡፡ ምንም እንኳን ይኽ አነጋገር “ከርስዋ በበላችኁ ቀን ዓይኖቻችኁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትኾኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” ተብለው /ዘፍ.3፡5/ በተታለሉት አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር የተናገረው የስላቅ ንግግር ቢኾንም ምስጢረ ሥላሴንም ቁልጭ አድርጐ ያስረዳል፡፡ ከእኛ እንደ አንዱ ኾነ ማለቱም የማክበር ንግግር አለመኾኑ በደምብ ያስገነዝባል፤ የማክበር ቢኾን ኖሮ እንደ እኛ ኾነ ማለት ነበረበትና፡፡
Ø “ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው” /ዘፍ.11፡7/፡፡ በዚኽ ውስጥ ተናጋሪው አብ ሲኾን እንውረድ ያላቸውም ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Genesis, pp 147/፡፡
Ø “ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ነው?” /ምሳ.30፡4/፡፡ ይኽ ኃይለ ቃል ደረቅ ሐዲስ ከሚባሉ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም የአብንና የወልድን ስም ግልጽ በኾነ አነጋገር ይነግረናልና፡፡ ይኽም በቀጥታ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ “ስሙና የአባቱ ስም” ካለው ጋር አንድ ነው /ራዕ.14፡1/፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስምም “የእግዚአብሔር መንፈስ” ብሎ ገና በዘፍጥረት 1፡2 ላይ ይናገራልና የሦስቱም አካላት ስም ገና ከብሉይ ኪዳን የታወቀ ነው ማለት ነው፡፡
የሥላሴ ትምህርት በሐዲስ ኪዳን
 እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጣት ሃይማኖት አንዲት ብቻ ናት /ኤፌ.4፡4/፡፡ ይኽቺውም ሃይማኖት አስቀድማ በዓለመ መላዕክት የነበረች በኋላም በአበው በነቢያት የቀጠለች ናት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ነቢያትና ሙሴ ይኾን ዘንድ ያለውን፥ … ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርኹት የለም” ብሎ እንዳስተማረ ሐዋርያትም በአበው በነቢያት ከተነገረው በቀር ሌላ እንግዳ ትምህርትን አላስተማሩም /ሐዋ.26፡22/፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በዚኹ የነቢያትና የሐዋርያት ትምህርት ተመሥርታ ስለ ሥላሴ ስታስተምር የኖረች ናት፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ አንተን ያከብርህ (ይገልጥህ) ዘንድ፥ በሥጋዊና በነፍሳዊ ኹሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው መጠን፥ ለሰጠኸው ኹሉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው (ግለጠው)። እውነተኛ አምላክ ብቻ የኾንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይኽች የዘለዓለም ሕይወት ናት” ብሏል /ዮሐ.17፡1-3/፡፡ ስለዚኽ አንድ ሰው ከምንም በፊት አብንና ወልድን ማመን አለበት፤ ይኽን አምኖ ያወቀም ጌታችን እንዳለ የዘለዓለምን ሕይወት ያገኛል፡፡ ነገር ግን አብንና ወልድን ብቻ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስንም ጭምር እንጂ፡፡ ጌታችን እንዲኽ ብሏልና፡- “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የኾነው አጽናኝ ርሱ ኹሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችኁን ኹሉ ያሳስባችኋል” /ዮሐ.14፡26/፡፡ ይኽን ቅዱስ መንፈስ ያልተቀበለ ሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው (የባሕርይ አምላክ ነው) ብሎ መመስከር አይችልም /1ኛ ቆሮ.12፡3/፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር፡- “ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት - በአካል ሦስት ሲኾኑ በመለኮት አንድ ናቸው” ብለን እንድንጸልይ ማድረጓም ከዚኹ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወስዳ ነው፡፡
በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተሰጠው የሥላሴ ትምህርት እጅግ ብዙ ቢኾንም ለጥቈማ ያኽል ግን የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡፡
v “እንግዲህ ሒዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” /ማቴ.28፡19/፡፡ እነዚኽ ከአንድ ቦታ ላይ ተደርድረው የምናነባቸው ስሞች አንድ አይደለም፤ ኹለትም አይደለም፤ አራትም አይደለም፡፡ ሦስት ስሞች እንጂ፡፡ ስም የሚወጣው በህልውና (በአኗኗር) አለ ተብሎ ለሚታሰብ ኗሪ ነው ብለናል፡፡ ለሌለ ነገር ስም አይወጣም፡፡ ከሌለ ምን ተብሎ ስም ይወጣለታል?
v “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችኁ አጽናኝ ርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል” /ዮሐ.15፡26/፡፡ እኔ አለ፤ አብ አለ፤ የእውነት መንፈስ በማለትም መንፈስ ቅዱስን በየራሳቸው አቋም ገለጸ፡፡
v “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከኹላችኁ ጋር ይኹን፡፡ አሜን” /2ኛ ቆሮ.13፡14/፡፡
v “እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስ እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት…” /1ኛ ጴጥ.1፡2/፡፡
v “የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ” /1ኛ ዮሐ.5፡7/፡፡
ስለዚኽ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ (በሥላሴ) ማመን የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣልና የይሖዋ ምስክሮች ዛሬውኑ ንስሓ ትገቡ ዘንድ ይገባል፡፡ በአሚነ ሥለሴ ያለንም በዚኹ እምነታችን ጸንተን በምግባር በትሩፋት ልናጌጥ ልናሸበርቅ ሙሽራውንም ለመቀበል የተዘጋጀን ልንኾን ያስፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ከሐዋርያነ አበው ዠምረን እስከ ጕባኤ ኒቅያ የነበሩት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምን ብለው እንዳስተማሩ እንማማራለን፡፡ 
ሰላም ወሰናይ!!!

No comments:

Post a Comment