Pages

Sunday, October 19, 2014

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል አራት)




(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 9 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!



ለ) ቅዱስ ትውፊት (Holy Tradition)


ትርጕም

 በሰዋስዋዊ ዘይቤው ሲፈታ፥ ትወፊት ማለት ስጦታ፣ ልማድ፣ ትምህርት፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ሥርዓት፣ ከጥንት ከአበው ሲያያዝ ሲወርድ፥ ቃል በቃል ሲነገር የመጣ ማለት ነው /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ፣ 397/፡፡ ጽርዓውያንም “ፓራዶሲስ” ይሉታል፤ አንድን ነገር እጅ በእጅ ለሌላ ሰው ማስረከብን ወይም ማቀበልንም ያመለክታል፡፡ ዕብራውያን ደግሞ “ማሳር - ማቀበል” እና “ቂብል - መቀበል” የሚሉ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡


 በቤተ ክርስቲያናዊ ትርጓሜው ስንመለከተው፥ ትውፊት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጠቅላላ በአበው፣ በነቢያት፣ በሐዋርያት፣ በጳጳሳት፣ በሊቃውንት፣ በካህናት በኵል የሚያስተላልፈው ሕያው (ሕይወትን የሚሰጥ) ቃል ማለት ነው፡፡ ይኽ ሕያው ቃል ቀደምት አበው ከእግዚአብሔር የተቀበሉትና ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት፥ ቤተ ክርስቲያንም በየጊዜው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የምትጠቀምበት ሕያው ትምህርት ነው፡፡

በቅዳሴያችን ጊዜ ቄሱ “ነዋ ወንጌለ መንግሥት - መንግሥተ ሰማያትን የምትሰብክ አንድም ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታገባ ወንጌል ይኽቺ ናት” ብሎ ለንፍቀ ካህኑ መስጠቱ፥ ንፍቀ ካህኑም “መንግሥቶ ወጽድቆ ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ - ጌትነቱንና ቸርነቱን የምትናገር የሰጠኝን ወንጌልን ሰጠኹኽ” ብሎ ለዲያቆኑ መስጠቱ ሐዋርያት ከሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ተቀብለው ለማስተማራቸው አምሳል ነውና ትውፊት ቅብብል፣ ውርርስ መኾኑን በግልጽ ያሳያል /ሥርዓተ ቅደሴ 10፡53፣ አንድምታው/፡፡

 በኹለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የነበረው ቅዱስ ሄሬኔዎስ፥ ፍሎሪነስ ለተባለ ጓደኛው ሲጽፍለት፡- “ነፍስ እስከማውቅና በሕይወቴ እስኪዋሐደኝ ድረስ በሕፃንነቴ የተማርኩትን አኹን ከምማረው በላይ ወለል ብሎ ይታየኛል፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሲቀመጥበት የነበረውን ቦታ፣ የትምህርት አሰጣጡ ዘዴ፣ እንዴት ይገባና ይወጣ እንደነበር፣ ክርስቲያናዊ ሕይወቱና የሰውነቱ መልክዕ፣ ለምእመናን ያስተማረውን ትምህርት፣ ከወንጌላዊ ዮሐንስና ከሌሎች ጌታችንን በዓይን ካዩት ደቀ መዛሙርት ጋር ስለነበረው ትውውቅ፣ ትምህርታቸውን እንዴት ያስታውሰው እንደነበር፣ ስለ ጌታ ከእነርሱ ምን እንደሰማ፣ ጌታችን ያደረጋቸውን ተአምራትና ያስተማረውን ትምህርት ይኽንና ይኽን የመሰለ ኹሉ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ከቃሉ አገልጋዮችና ምስክሮች እንደምን እንደተቀበለና ለእኛ እንዴት እንዳስተላለፈልን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አዋሕዶም እንዴት እንዳስተማረን አስታውሳለኁ፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት ረድቶኝ፥ በሕፃንነት አዕምሮዬ እነዚኽን ነገሮች ለመስማትና በወረቀት ሳይኾን በልቤ ጽላት እጽፋቸው ዘንድ ደግሞም ዘወትር አስባቸው ዘንድ እጅግ እጓጓ ነበር” በማለት ከቀደሙት አበው ስለተቀበለውና በኑሮ፣ በሕይወት ስለሚገለጡ፥ ግን ደግሞ ያልተጻፉ ትውፊቶች እንዳሉ አብራርቶ የተናገረበት አኳኋንም የትውፊትን ምንነት ፍንትው አድርጐ የሚተረጉምልን ነው /Fr. Tadros Y. Malaty, Tradition and Orthodoxy, pp 23 /፡፡
  ትውፊት ሲባል ስላለፈ ነገር ብቻ የሚናገር፥ ነገር ግን በአኹኑ ሰዓት ምንም ሕይወት እንደሌለው ተደርጐ የሚታሰብ አይደለም፡፡ አኹንም ሕይወት ያለው ብቻ ሳይኾን ሕይወትንም የሚሰጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ትንሽ ቆይተን በስፋት እንደምንመለከተው፥ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ትውፊት አንድ አካል ነው፡፡ ነገር ግን ስላለፈው ነገር ብቻ የሚናገር አይደለም፡፡ አኹንም ሕይወትን የሚሰጥ ነው፡፡ ስለዚኽ ትውፊትን መቀበል ያለፈውን ነገር የመጠበቅ ጕዳይ አይደለም ማለት ነው፤ የሕይወት ጕዳይ እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር የምንጠብቀው የሕይወት ጕዳይ እንደኾነ ስለሚገባን ነው ማለት ነው፡፡

 እግዚአብሔር በዚኹ ቅዱስ ትውፊት ሲናገር ስላለፈው ነገር ብቻ ሳይኾን ሰለአኹኑም ስለሚመጣውም ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡ ትውፊትን ቅዱስ ብለን መጥራታችንም የመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ስለማይለየው፥ አንድም ከክርስቶስና ክርስቶስ አድሮባቸው ከሚኖር ከቅዱሳን ስለተገኘ ነው /Georges Florovsky; Bible, Church, Tradition: An Eastern Orthodox View; Vol.I; pp 46/፡፡

 እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፥ እግዚአብሔር ከፍጥረት መዠመሪያ አንሥቶ በጽሑፍም ያለ ጽሑፍም የገለጠውን እውነት የምናገኘው በቅዱስ ትውፊት ውስጥ ነው፡፡ በመኾኑም የተጻፈውና ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ለድኅነታችን የሚኾን የእግዚአብሔርን መገለጥ የያዘ ስለኾነ እኵል አስፈላጊ ነው፡፡

 እንደ ምዕራቡ ቤተ ክርስቲያን (ካቶሊክ) ትርጕም ቅዱስ ትውፊት ማለት ያልተጻፈ ነገር እና በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍን ብቻ የያዘ ነው /J.N.D. Kelly, Early Christian Doctrines, pp 30-31/፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ግን ከላይ እንደገለጥነው ቅዱስ ትውፊት የተጻፈውም ያልተጻፈውም ኹሉ የሚያካትት ነው፡፡ በመኾኑም (ቅዱስ ትውፊት) በውስጡ መጽሐፍ ቅዱስን፣ የአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንና ቀኖናትን፣ የሦስቱን ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያትን (ጕባኤ ኒቅያ፣ ጕባኤ ቁስጥንጥንያ፣ ጕባኤ ኤፌሶን) እና ትእዛዛትን፣ መጻሕፍተ ቅዳሴያትን፣ ገድለ ቅዱሳንን፣ ቅዱሳት ሥዕላትን፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርና የሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸምን፣ ክርስቲያናዊ የአለባበስ፥ የአነጋገር እንዲኹም የአመጋገብ ሥርዓትን ሌላውንም ኹሉ ያካተተ ነው፡፡

            መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ትውፊት አንዱ አካል ነው!!!

  ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ የመዠመሪያውን ስፍራ የሚይዝ (የመዠመሪያ ስፍራ ይይዛል ስንልም ካልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ይልቅ በቀላሉ ለስሕተት የማይጋለጥ በመኾኑ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀኖና አንዴ ተወስኖ የቀረበ ነውና፡፡ በዚኽም ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት የሚመዘንበት ሚዛን ነው፡፡) ቢኾንም፥ ከሌላው የትውፊት አካል ግን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኹ ጽሑፍ አይደለም፡፡ ሊብራራና በሕይወት ሊተረጐም የሚገባው ነው፡፡ ይኽም የሚኾነው የእውነት ዓምድና መሠረት በምትኾን በቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ነው /1ኛ ጢሞ.3፡15/፡፡  የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ይኽን መጽሐፍ በስፋትና በጥልቀት የሚተረጕሙ እንጂ እንደ ተጨማሪ የሚታዩ አይደሉም፡፡ የቅዱሳኑ ገድላት በመጽሐፍ ቅዱስ የታዘዘውን እውነት በተግባር እንዴት እንደኖሩት የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላ ወንጌል አይደለም ማለት ነው፡፡ ቅዱሳት ሥዕላቱ በኅብረ ቀለማትና በጥበባዊ መንገድ ነገረ እግዚአብሔርን ማንበብ ለማይችል ሰው የሚያብራሩ ናቸው፡፡ ቅዳሴው፣ ሥርዓተ ጸሎቱ፣ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸሙ፣ ማዕጠንቱ፣ እና የመሳሰለው ኹሉ ሥርዓተ አምልኮው የሚፈጸምበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚኽ መጽሐፍ ቅዱስ እና ሌላው ቅዱስ ትውፊት ርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ ናቸው፡፡ አንዳቸው አንዳቸውን የሚተረጕሙ እንጂ የሚጣረሱ አይደሉም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፈው ሌላው ቅዱስ ትውፊት ነው የሚሞላው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እውነት ትክክለኛ ትርጕሙን የምናገኘው በሌላው ቅዱሱ ትውፊት ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰፊው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዋና ዋናውን የያዘ እንጂ ብቻውን የቆመ አይደለም፡፡ ወንጌል ከመጻፉ በፊት የነበረውንም ኹሉን በጽሑፍ የያዘ አይደለም /ዮሐ.20፡30-31/፡፡ ስለዚኽ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ትውፊት ብቻውን ፍጻሜ የለውም፤ ሌላው ቅዱስ ትውፊትም ያለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የለውም፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሌላውን ቅዱስ ትውፊት ከቅዱስ መጽሐፍ ጋር እኵል ሊቀበሉት የሚገባ የመለኮታዊ መገለጥ ምንጭ ነው ማለታችንም ከዚኹ የተነሣ ነው፡፡

ቅዱስ ትውፊት በዘመነ ብሉይ

 ትውፊት የምእመናን የዘወትር ሕይወት ነው፡፡ በመኾኑም ትውፊት ሰው ከመፈጠሩ አንሥቶ የነበረ ነው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን፡- “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለኽና” ብሎ ሲነግረው በጽሑፍ አልነበረም /ዘፍ.2፡17/፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት ለሰባት ዓመታት ሲኖሩ ይኽን ቅዱስ ትውፊት ጠብቀው ነው፡፡ እግዚአብሔርስ ይቅርና፥ ሰይጣን እንኳን አዳምንና ሔዋንን ያታለላቸው በጽሑፍ አልነበረም፤ ቅዱስ ባልኾነውና ከራሱ ካመነጨው ሐሰት እንጂ /ዘፍ.3/፡፡

 ቅዱሱ ትውፊት በአቤል በኵል ሲቀጥል፥ ዲያብሎስ ያስተዋወቀው ቅዱስ ያልኾነው ትውፊትም በቃየን በኵል ቀጥሏል፡፡ የአቤልና የቃየን ትውፊት ግን በቃል እንዲኹም በግብር እንጂ በጽሑፍ የወረሱት አልነበረም /ዘፍ.4/፡፡

 ኄኖክ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጐ ሞትን ሳይቀምስ የሔደው በቅዱሱ ትውፊት ሥርዓት መሠረት ስለኖረ ነው፡፡ ኖኅ በዚያ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጻድቅ ኾኖ የተገኘው፥ ባልተጻፈው በቅዱሱ ትውፊት እንጂ ከእግዚአብሔር በጽሑፍ ያገኘው ነገር ስለነበረ አይደለም፡፡ ኖኅ ንጹሐንና ንጹሐን ያልኾኑትን እንስሳት ለይቶ ያወቀው በጽሑፍ አልነበረም፡፡ አብርሃም እግዚአብሔርን አምኖ ከቤተሰቡ ተለይቶ ሲወጣም በጽሑፍ አይደለም፡፡ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይሠዉ ነበር፡፡ ነገር ግን በጽሑፍ የተሰጣቸው መመሪያ ስለነበረ አይደለም፡፡ ዮሴፍ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ማድረግ እንደማይገባ የተማረው ከቅዱስ ትውፊት በቃል እንጂ በጽሑፍ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ፥ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በ1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተነሥቶ መጽሐፍ እስኪጽፍ ድረስ፥ የእግዚአብሔር ሰዎች ከ4000 ዓመታት በላይ ሲመሩ የነበረው በጽሑፍ ሳይኾን በቃልና በተግባር በሚገለጠው ቅዱስ ትውፊት ነበር፡፡

ቅዱስ ትውፊት በዘመነ ሐዋርያት

  በዘመነ ሐዲስ ያለውን ስንመለከትም፥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ዓመት በላይ ሕዝቡን ደቀ መዛሙርቱን የነበረው በጽሑፍ አልነበረም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉት በወረቀት የተጻፈ ነገር አልነበረም፡፡ ወንጌላውያን ከጌታ በቃል ተምረው በተግባር አይተው ኋላ የሚጽፉትን እየዞሩ አስተማሩ እንጂ አስቀድመው ጽፈው ጠቅሰው አላስተማሩም፡፡ መጻሕፍት መጻፍ የተዠመሩት፥ ቤተ ክርስቲያን በይፋ ከተመሠረተች ከ8 ዓመታት በኋላ ነው (ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መዠመሪያ የተጻፈው መጽሐፍ የማቴዎስ ወንጌል ሲኾን ይኸውም በ41 ዓ.ም. ላይ ነው)፡፡ እስከዚኽ ጊዜ ድረስ ቤተ ክርስቲያን ስትመራ የነበረው በቃልና በተግባራዊ ምልልስ ሲተላለፍ በነበረው ቅዱስ ትውፊት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ወንጌል ከመጻፉ በፊት፥ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በቅዱስ ትውፊት ታውቋለች፡፡ ወንጌልን ስትኖረው ነበረች፡፡ 

 ከጌታችን ጋር ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት እየዋሉ፣ ካደረበት እያደሩ ሲያስተምር፣ ሲጸልይ፣ ሰዎችን ሲያጽናና፣ ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስንም በትምህርት ሲፈውስ፣ ሙታነ ሥጋንና ሙታነ ነፍስን ሕይወት ሲሰጣቸው ዐይተዋል፤ ሰምተዋል፡፡ ሥርዓተ ብሉይን አሳልፎ ሥርዓተ ሐዲስን ሲሠራ ተመልክተዋል፡፡ ነገር ግን ይኽን ኹሉ በትውፊት ለተላውያነ ሐዋርያት (Apostolic Fathers - ተላውያነ ሐዋርያት የሚባሉት ከሐዋርያት በቀጥታ የተማሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡) አስረከቡት እንጂ፥ እነርሱ ራሳቸው እንደነገሩን ኹሉንም አልጻፉልንም፡፡ የጻፉልን እጅግ ጥቂቱን ብቻ ነው /ዮሐ.21፡25፣ 1ኛ ዮሐ.1፡1/፡፡ “እንድጽፍላችኁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፡፡ ዳሩ ግን ደስታችኁ ፍጹም እንደኾነ ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልነግራችኁ ተስፋ አደርጋለኹ” እንዲል /2ኛ ዮሐ.12፣ 3ኛ ዮሐ.13-14/፥ እንኳንስ የጌታችን ይቅርና እነርሱ ራሳቸው ያስተማሩትን ትምህርት ያደረጉትንም ተአምራት በሙሉ አልጻፉልንም፡፡ በጽሑፍ የጻፉትም ቢኾን በቃል ያስተማርዋቸውን ምእመናን እንዲጸኑበትና አንዳንድ ቢጽ ሐሳውያን (ሐሰተኛ ወንድሞች) እውነቱን አዛብተው መጻፍ ስለዠመሩ እንዳይታለሉ ለመጠበቅ ጥቂቱን ነው /ሉቃ.1፡2/፡፡ ዋናው መሠረታቸው ግን ከላይ እንደገለጽነው በቃልና በተግባራዊ ሕይወት የተማሩት ትምህርት ነው፡፡

 ስለዚኽ ቅዱስ ትውፊት እያልነው ያለነው፥ እንዲኽ ዓይነቱን በገቢርና በቃል ዕለት ዕለት በቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት የሚገለጠውና አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠውን ሃይማኖት ነው /ይሁዳ ቁ.3/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽን በማስመልከት ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠኁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለኹና” /1ኛ ቆሮ.11፡23/፡፡ ከዚኽ የሐዋርያው ቃል እንደምንረዳው፥ ቅዱስ ትውፊት ማለት አንዳንድ የተሳሳቱ ሰዎች እንደሚሉት የአሮጊቶች ተረት ተረት ወይም ከሰው የተገኘ ውርስ ሳይኾን መለኮታዊ ስጦታ እንደኾነ ነው፡፡ “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችኁ ላያችኁ እናፍቃለኹና” /ሮሜ.1፡11/፡፡

 የቅዱስ ትውፊት ዋና ማዕከሉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ቅዱስ ትውፊት ወንጌል ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ ቢነገር ይወርዳል ይወለዳል ብሎ ነው፤ በዘመነ ሐዲስ ቢነገር ደግሞ ወረደ ተወለደ ብሎ የምሥራችን ለትውልድ ኹሉ በቃልም፣ በገቢርም፣ በጽሑፍም የሚያውጅ ነው፤ ቅዱስ ትውፊት፡፡ “ወንድሞች ሆይ! የሰበክኁላችኁን ደግሞም የተቀበላችኁትን በርሱም ደግሞ የቆማችኁበትን በርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለኹ፡፡ በከንቱ ካላመናችኁ በቀር ብታስቡት በምን ቃል እንደ ሰበክኁላችኁ አሳስባችኋለኹ፡፡ እኔ ደግሞ የተቀበልኹትን ከኹሉ በፊት ሰጠኋችኁ” እንዲል /1ኛ ቆሮ.15፡1/፡፡

ቅዱስ ትውፊት በሊቃውንት አስተምህሮ

 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ቅዱስ ትውፊት ምንነት እጅግ ሰፊ የኾነ ትምህርትን አስተምረዋል፡፡
ጥቂቶቹን ብቻ ለመጠቈም ያኽልም፡-
·        “በትወፊት አርባዕቱ ወንጌልን አወቅኁ፤ እነርሱም እውነቶች ናቸው፡፡” / Origen, (cc Fr. Tadros Y. Malaty) Tradition and Orthodoxy, pp 18/
·        “ሐዋርያት ‘በቃል በመናገርም እንጂ በጽሑፍ ብቻ እንዳላስተማሩ በቃላችንም ቢኾን ወይም በመልዕክታችን የተማራችኁትን ወግ (ትውፊት) ያዙ’ በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል ያመለክታል፡፡ ኹለቱም ማለት የተጻፈውና ያልተጻፈው ለትምህርተ ሃይማኖትና ለድኅነት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ስለዚኽ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት መታመን የሚገባው መኾኑ እውነት ነው፡፡” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፥ 2ኛ ተሰ. 2፡15ን ሲተረጕም/
·        “በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተጠብቀው ካሉት ትምህርተ ሃይማኖትና ስብከቶች አንዳንዶች በጽሑፍ፥ ሌሎች ግን በሐዋርያት ትውፊት የተሰጡን ናቸው፡፡ ኹለቱም ተመሳሳይ ሥልጣን አላቸው፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን መቋቋም በጥቂቱም ቢኾን የሚያውቅ ሰው ይኽን ሊቃወም አይችልም፡፡ ያልተጻፉትን ልማዶች ኹሉ ተገቢ እንዳይደሉ በቁጥር ብንጥላቸው በጣም አስፈላጊ የኾኑ የወንጌል ክፍሎችን እናጣለን፡፡ ትምህርታችንም ባዶ ይኾናል፡፡” /አውሳብዮስ ዘቂሳርያ፣  በእንተ መንፈስ ቅዱስ 27፡66/
·        “በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ኹሉ በትእምርተ መስቀል እንዲያማትቡ የት ተጻፈ? በምንጸልይበት ጊዜ ፊታችንን ወደ ምሥራቅ ማዞር እንዳለብን የት ተጻፈ? ወይኑንና ኅብስተ ቁርባኑን እንዲለውጥልን መንፈስ ቅዱስን ስለመጠየቅ (ስለ ቅዳሴ) ማን ጻፈ? በዚኽ መሠረት ወንጌል ወይም የሐዋርያት መጽሐፍ በጠቀሱት ብቻ አንወሰንም፡፡ በመስማትም የተማርነው ብዙ ነገር አለና፡፡” /ዝኒ ከማኁ/
·        “ለጥምቀት አገልግሎት ውኃን እንባርካለን፡፡ ተጠማቂውን ለመቀባት ዘይት እንባርካለን፡፡ ይኽ ኹሉ የት ተጻፈ? ይኽን የተማርነው በምስጢራዊው ትውፊት አይደለምን? በሜሮን እንድንቀባ የት ተጻፈ? ተጠማቂው 3 ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማድረግ የት ተጻፈ? ከጥምቀት ጋር ግኑኝነት ያላቸው ሌሎች ነገሮች፥ ሰይጣንንና መላእክቱን መካድ የት ተጻፈ?” /ዝኒ ከማኁ/

 እንደዚኹም መሠረተ ሐሳቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢኖርም ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሐዋርያት ትውፊት ነው፡፡ ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍትና ትንሣኤ እንዲኹም ፍልሰት የምናስተምረው ትምህርት ኹሉ ከሐዋርያት ትውፊት የተገኘ ነው፡፡

 መጽሐፍ ቅዱስን ስንተረጕም እንኳን የቅዱሳን አበውን አስተምህሮ የምንጠቅሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ትርጕም የምናገኘው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ስለኾነ ነው፡፡ በዚኹ ዙርያ “ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት መጻሕፍት አተረጓጐም ስልት” በሚል ርእስ በቀጣይ የምንመለስበት ይኾናል፡፡ 

ቅዱስ ትውፊት፥ ቅዱስ ካልኾነው ትውፊት እንዴት ይታወቃል?
    
  በቤተ ክርስቲያን ያለው ኹሉም በትውፊት የተገኘ ላይኾን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ነገርም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ መንፈስ ቅዱስ የሰጣት ነው ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዋዊ ነገሮችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እነዚኽ ከሰው የኾኑ ነገሮች በራሳቸው ኀጢአት ወይም ስሕተት ላይኾኑ ይችላሉ፡፡ ይልቁንም ለዋናው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ትውፊት ማቀላጠፊያ ወይም ማስተላለፊያ መንገዶች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ድምጽ ማጉያ፣ መቅረጸ ድምጽ፣ ሲዲ፣ ዲቪዲ፣ እና የመሳሰሉት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚኽ ዋናውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ጊዜአዊው ማቀላጠፊያውን ለይተን ልናውቅ ይገባናል፡፡

  ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ጉባኤ እንደመኾኗ መጠን፥ እነዚኽ ክርስቲያኖችም በተለያየ ግብረ ዓለም ሊያዙ ስለሚችሉ ይኽን የዓለም ሥራ ይዘው ቢመጡና ግብራቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቢያሠርፁ፥ ይኽ ክፉ ግብር እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ሊቈጠር አይገባውም፡፡
በመኾኑም ለቅዱስ ትውፊት ቀኖናዊ መመዘኛ እንዳለው ተረድተን ቅዱሱን ትውፊትና ቅዱስ ያልኾነውን ትውፊት ለይተን ልናውቅ ይገባናል /2ኛ ተሰ.2፡15/፡፡
  1. ትውፊት ኹሉ ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣና ሐዋርያዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ይዘት ያለው መኾን አለበት፤
  2.   ከጥንት ዠምሮ በየትም ቦታ፥ ኹልጊዜ በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን የታመነ የተጠበቀና በተግባር ላይ የዋለ መኾን አለበት፤ 
  3.  በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ መለወጥና መቋረጥ ያልተደረገበት መኾን አለበት፡፡

ይኽ ትምህርት የነገረ ሃይማኖት መሠረት ነው የምንልበት ምክንያትም ኹለት ምሳሌዎችን በማንሣት እናጠቃልለው፡፡
  1. እንደ ካቶሊካውያን አስተምህሮ ትውፊት ማለት የእምነት መሠረት ሲኾን ከዚኹም ውስጥ አዳዲስ ዶግማዎችን ማመንጨት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ስለ መካነ ንስሐ (Purgatory)፣ የፖፑ የበላይነት፣ ፖፑ አይሳሳትም ማለት የሚሉት ፍጹም የተሳሳቱ ትምህርቶች ከዚኹ የመነጩ ናቸው፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ግን ሃይማኖት የሚቀበሉት ተቀብለውም የሚኖሩት ለቀጣዩ ትውልድም ሳያፋልሱ የሚያስተላልፉት እንጂ በየጊዜው የሚጨመርበት ወይም የሚቀነስበት አይደለም፡፡
  2. በፕሮቴስታንቱ ዓለም ደግሞ ከካቶሊካውያኑ ፍጹም ተቃራኒ በመኾን ቅዱስ ትውፊትን አንቀበልም ይላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን በቂ እንደኾነ ያስተምራሉ፡፡ ነገር ግን ይኽም ቢኾን ፍጹም የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ እናንሣና ትምህርታቸው ምን ያኽል ስሕተት እንደኾነ እናሳይ፡፡ እሑድን እንደ ጌታ ቀን አድርገው ያከብራሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን እንዲከበር የታዘዘው ግን ቅዳሜ ነው /ዘጸ.20፡8/፡፡ ቅዳሜን ትተው እሑድን ማክበር ከየት አገኙት? ዳግመኛም የጌታችንን ልደት፣ ጥምቀት፣ ትንሣኤ እንዲኹም በዓለ ኃምሳ አብረዉን ያከብራሉ፡፡ ነገር ግን ይኽን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም አናገኝም፡፡ ሌላ ጥያቄ እንጨምር፡፡ ወደ ዓለም ኹሉ የተሰማሩት ሐዋርያት 12 መኾናቸውን ወንጌል ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ኹሉም ጽሑፍ አልጻፉም፡፡ አላስተማሩም ማለት ግን አይደለም፡፡ ታድያ ትምህርታቸው የት አለ? ትምህርታቸውን የምናገኘው በአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ብቻ ነው፡፡

  ስለዚኽ ቅዱስ ትውፊት መቀበል ግድ ነው፡፡ ለምን? የትናንቱን የቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ወደ ዛሬ የሚያመጣ፥ ዛሬ ላይ ያለውንም ወደ ነገ የሚያሻግር ቅዱስ ትውፊት ነውና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “የርሱን ግርማ ዐይተን እንጂ በብልሐት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችኁ” እንዳለ /2ኛ ጴጥ.1፡16/ ቅዱስ ትውፊት ሲባል እንዲኹ ከሰው የተገኘ ተረት ተረት እንዳልኾነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በትውፊት ያገኘነው መጽሐፍ ቅዱስም ተረት ተረት ማለታችን ነውና፡፡
ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ! በኹሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችኁ ወግን ፈጽማችኁ ስለ ያዛችኁ አመሰግናችኋለኹ” እንዳለን /1ኛ ቆሮ.11፡2/ የመጽሐፍ ቅዱስ አባት ራሱ ቅዱስ ትውፊት እንደኾነ ልናውቅ ይገባናል፡፡ “Sola Scriptura - መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” በሚለው የአንዳንዶች ስሕተትም ራሳችንንና ወንድማችንን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ 
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment