Pages

Saturday, October 25, 2014

እኔ ነኝ፥ አትፍሩ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በተመላለሰ ጊዜ ወደ ምኵራብ ገባ፡፡ እንደ ባለ ሥልጣንም ያስተምራቸው ነበር፡፡ ብዙዎች ግን ሰምተው ተገረሙና፡- “እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን?” እያሉ ይሰናከሉበት ነበር /ማር.6፡3/


ንጉሡ ሄሮድስም ተደናገጠ፡፡ ደግሞምመጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋልይል ነበር /ማር.6፡14/ ከሕዝቡ መካከል እንደ ቀደሙት እንደ ዳዊት ዓይነት ነቢይና ንጉሥ ይሹ ስለነበርኤልያስ ነውያሉ ነበር፤ ነቢይ ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁ ስለነበርከነቢያት አንዱ ነውይሉ ነበር /ማር.6፡15/፡፡
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሥጋዊና በደማዊ አእምሮአቸው እንደሚያስቡት ሳይኾን ለድኅነተ ሰብእ ብሎ ክብሩን እንደ መቀማት ሳይቈጥረው የባርያውን መልክ ይዞ የመጣ የባሕርይ አምላክ መኾኑን ይነግራቸው ዘንድ ኹለት ተአምራትን ያሳያቸው ዘንድ ወደደ፤ አሳያቸውም፡፡ እነርሱም፡
·        አንደኛው እሥራኤልን በምድረ በዳ ሰማያዊ መናን ይመግባቸው የነበረ፣ ዳግመኛም ዓለምን ኹሉ እየመገበ የሚኖር እርሱ ራሱ እንደኾነ ይረዱ ዘንድ በአምስት እንጀራና በኹለት ዓሣ ብቻ ሴቶችና ሕፃናት ሳይቈጠሩ አምስት ሺሕ ሕዝብን መገበ፡፡ መመገብ ብቻ አይደለም፤ ኹሉም ከጠገቡ በኋላም በሐዋርያቱ ልክ÷ ዓሥራ ኹለት መሶብ ሙሉ እንጀራንና ዓሣን አነሡ፡፡ በዚህም ነቢያት ኹሉየእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፥ ተነሥ፥ ተነሥ፥ ኃይልንም ልበስ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥእያሉ /ኢሳ.51፡9/ እየጮኹ ሲጠብቁት የነበረው አማናዊው መሲሕ እርሱ ራሱ መኾኑን ይነግራቸው ነበር /ማር.35-44/
·        ኹለተኛው ደግሞ “…በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር። እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥እንዲል /ማር.6፡47-49/ እምነታቸው በእርሱ ላይ ሊያኖሩ እንዲገባቸው፣መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም” /መዝ.77፡19/ ተብሎ የተጻፈለት ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር እንደኾነ ያሳያቸው ነበር፡፡ አስቀድሞ እንዲጮኹ፣ እንዲያለቅሱ፣ እንዲታወኩ፣ እርዳታን እንዲሹ አድርጐ በመጨረሻም እርሱ ራሱ መጥቶአይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩማለቱም አማናዊው እረኛቸው፣ ቸር ጠባቂያቸው እርሱ እንደኾነ እንዲያውቁ እንዲያምኑ ነበር /ሕዝ.34/፡፡

 ተወዳጆች ሆይ! ደቀ መዛሙርቱ በተጨነቁ ጊዜ ባሕሩን ጸጥ ያደረገላቸው አምላክ የእኔም የእናንተም አምላክ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሳሉ፣ ያውም የብስ ላይ ለመድረስ ምንም ተስፋ ባልነበራቸው ቦታ የደረሰላቸው አምላክ የእኔም የእናንተም አምላክ ነው፡፡ በፍርሐት በተነዋወጡ ጊዜአይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩያላቸው አባት የእኔም የእናንተም አባት ነው፡፡ ዙርያችን በጨለማ ተከበን ሊኾን ይችላል፡፡ ተስፋችን ተሟጥጦ ሊኾን ይችላል፡፡ እምነታችንን በእርሱ ላይ እስካደረግን ድረስ ግን የብርሃን ጌታ ብቅ ይልልናል፡፡ በዙርያችን ከቦን የነበረውን ጨለማ ይገፏል፡፡ ብርሃን ሊመጣ ሲል ቀድሞ ጨለማ ይመጣል /ዘፍ.1፡2-3/፡፡ እንኪያስ ወገኖቼ! ምንም ዓይነት ፈተና ውስጥ ብንኖርም እንኳ ጸንተን እረኛችንን እንጠብቀው፡፡ የነፍሳችን ብርሃን ክርስቶስ እስኪደርስልን ድረስ በአሚን በገቢር ቆመን እንጠብቀው፡፡
 አሁን ያለንበት ሁናቴ ከምን እንደመጣ ብቻ እናስተውለው፡፡ ከእኛ ኃጢአት፣ ከሰይጣን ፈተና ወይስ ከእግዚአብሔር ፈቃድ? ከእኛ ኃጢአት የተነሣ ከኾነ መመለስ ያለብን እኛው ነን፡፡
 ምንም ሳንበድል ጨለማ ውስጥ፣ ማጣት ውስጥ፣ ተስፋ በሚያስቈርጡ ኹኔታዎች ውስጥ ካለን ግን ኹኔታው ለጥቅማችን ነውና ተመስገን እንበል፡፡ እንዲህ ስንል ጠላት ይሸበራል፡፡ ፈታኙ እንደ ጢስ ተኖ ይጠፋል፡፡
ኹል ጊዜ እደ ልቦናችንን ወደ እግዚአብሔር እናንሣ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ዝም ያለን የሚመስለን በጸሎት ያልተጋን ጊዜ ነውና፡፡ እግዚአብሔር የሌለ እስኪመስለን ድረስ ዐፀባ የሚከበን በጸሎት እንድንተጋ ሲሻ ነው፡፡ እርሱ እየጠበቀን እኛ ተኝተን ሊኾን ይችላል፡፡ በመዳፉ ላይ ሳለን የተወን ሊመስለን ይችላል፡፡ እርሱ ግን በዝምታ ውስጥ ከአእምሮ በላይ የኾነ ሥራውን ይሠራል፡፡ ስለዚህ እናነጋግረው፡፡ የልጅነት ድምጻችንን ይናፍቋልና በጸሎት እንጥራው፡፡ እንደተናገርን እጃችንን ማንሣት ስንቀንስ ጨለማ ውስጥ ያለን ይመስለናል፡፡ እንኪያስ እጃችንን እናንሣና ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንውጣ፡፡
ዳግመኛም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አንቀጽ በተረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ይለናል፡- “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛው በጨለማ ጊዜ፣ በዛው ተስፋ በቈረጡበት ወቅት አስቀድሞ እርሱ ክርስቶስ መኾኑን ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው አይደለም፡፡ ወዲያውንም ማዕበሉን ያስወገደላቸው አይደለም፡፡ ለምን ያልከኝ እንደኾነም አስፈሪ ጊዜያትን መቋቋም ይለማመዱ ዘንድ፤ ዳግመኛም ሊመጣ ለሚችለው ማንኛውም ዓይነት ፈተና የተዘጋጁ ይኾኑ ዘንድ ነው ብዬ እመልስልሃለሁ፡፡ታድያ እያለማመደን ከኾነስ? እያስታጠቀን ከኾነስ? ደቀ መዛሙርቱ ፍርሐቱ የተወገደላቸው መቼ እንደኾነ ታስተውላላችሁን? “እኔ ነኝያላቸው ጊዜ ነው፡፡ እንኪያስ እኛም በቅዱስ ቃሉ እንስማዋ፡፡ ያኔ ፍርሐታችን ይርቃል፡፡ ይህን ያደረግን እንደኾነ ከመዝሙረኛው ጋር ኾነን፡- “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሔድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛልብለን የድል ዝማሬ እንዘምራለን /መዝ.23፡4/
ይህን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው አምላካችን ይርዳን አሜን!!!

1 comment: