Pages

Monday, October 27, 2014

ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ (መንደርደሪያ)



በዲ/ን ሳምሶን ወርቁ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በክርስትና ሕይወት ውስጥ ምዕመናን ስለመንፈሳዊነት ያላቸው ግንዛቤ ብዙ ጊዜ ያልተሟላ አንዳንዴ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነት ብለው የሚያስቡት መንፈሳዊነት ያልሆነውን ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙዎች መንፈሳዊያን ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች ሕይወት ተመልክተው መንፈሳዊነት እንዲህ ከሆነ ይቅርብኝ እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊነት ትርጉሙ ዓላማው ምስጢሩ የረቀቀ የጠለቀ ነው፡፡

መንፈሳዊነት ማለት መንፈሳዊ ልደትን በመወለድ የሚጀመር (ዮሐ ፫÷፮) ከስሜትና ከእውቀት በላይ የሆነ፣ ሰፊ ውጣ ውረድና ተጋድሎ ያለው፣ ከወሰኑ በኋላ ወደኋላ የማይባልበት ቁርጥ ውሳኔን የሚጠይቅ (ማቴ ፲፮÷፳፬) ፣ በጊዜ በቦታ በኑሮ ደረጃ የማይወሰን፣ እግዚአብሔርን ለመምሰል ያለማቋረጥ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የምንወጣበት ረጅም መሠላል ነው፡፡ መንፈሳዊነት መንፈሳዊ ልደትን መውሰድ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ኤፌ( ፬÷፲፭)
በስድስተኛው ክፍለ-ዘመን በግብፅ በረሀ ውስጥ ይኖር የነበረው ታላቅ አባት ቅዱስ ዮሐንስ ዘላዕላይ (ዮሐንስ ክላይማክስ) የመንፈሳዊ ሕይወትን ዕድገት በተመለከተ የጻፈው መጽሐፍ እስከ ዛሬ ድረስ በምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በስፋት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከዚህም የተነሣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ በብዛት የታተመ፣የተተረጎመና የተነበበ ታላቅ መጽሐፍ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ “ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መሠላል” በሚለው በዚህ መጽሐፉ ያዕቆብ በሎዛ ተኝቶ ሳለ በራዕይ ከምድር እስከ መንግሥተ ሰማያት ተዘርግቶ ያየውን መሠላል በመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት መስሎ ያስተምራል፡፡ 




መጽሐፉን እንደ አጠቃላይ በሦስት ዐበይት ክፍሎች ከፍለን ብንመለከት የመጀመሪያው ክፍል ከዓለማዊነት ስለመለየት፣ ዓለማዊነትን ስለመተውና ከዓለማዊነት ስለመውጣት በስፋት ይገልፃል፡፡ በሁለተኛው ክፍል ታዛዥነትን፣ ትዕግሥትን ፣ ተዘክሮ ሞትን፣ ህዝነትን ገንዘብ ስለማድረግ ይገልጻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ንዴትን ተንኮልን፣ ሐሰተኝነትን፣ ቀባጣሪነትን፣ ለፍላፊነትን፣ ሀሜተኝነትን፣ ስግብስግነትን፣ ዘማዊነትን ግዴለሽነትን፣ ፍሃትን፣ ከንቱ ውዳሴንና ጉራን እንዴት እንደምንተው ያስተምራል፡፡ በሦስተኛውና በመጨረሻው ክፍል ተመስጦና ጥልቀት ያለውን ጸሎትንና ፍቅርን ገንዘብ አድርገን እንዴት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንደምንሆን ያስተምረናል፡፡
ክርስቲያን በሀይማኖቱ ነቀፋ ጉድለት የሌለበት በአነጋገሩ በሥራው በሁለንተናው ክርስቶስን የሚመስል ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ “የሰው የሕይወቱ ግብ ወደ ሆነው ክርስቶስን ወደ መምሰል ለመድረስ ከምድር አስከ ሰማይ የተዘረጋውን መሠላል ደረጃ በደረጃ ልንወጣ ይገባል” ሲል ይመክረናል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ምናባዊ የመንፈሳዊ ሕይወት መሠላል በመጨረሻ ጫፍ ላይ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠላሉ ላይ ጉዞ የሚያደርጉትን ሊቀበል እጆቹ ተዘርግተው ይታያሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መልዐከ ብርሃናት ቅዱሳን ጸድቃን ሰማዕታት እነርሱ ያገኙትን ጸጋ እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ በመንፈሳዊ መሠላሉ እንድንወጣ ሲያበረቱን ሲደግፉን ይታያሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መልዐከ ጽልመት ሰይጣን ዲያብሎስ ደግሞ ሰዎች ወደ ደረጃው ፈጽመው እንዳይመጡና በመጡትም ላይ ቢሆን ደረጃውን እንዳይወጡ ጎትቶ ሊያወርድ ሲቃጣ ይታያል፡፡ በመሠላሉ ከፍታ ላይ መድረስን የምንሻ ከሆነ ዓይኖቻችን በደረጃዎቹ  ላይ ሳይሆን ሊረዳን ዘወትር ወደቀረበን፣ ከጌታ ላይ የማይነቀሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ በተለየ ዓይናችን በደረጃዎቹ ላይ የሚተያኩር ከሆነ በሥጋዊ ጥበብ ላይ የምንደገፍ ስለምንሆን በቀላሉ ተስፋ ወደመቁረጥ እንደርሳለን፤ ከዚህም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሳንደርስ በመንገድ ላይ እንቀራለን ማለት ነው፡፡
ስለዚህም ዘወትር ዓይናችን የመንገዳችን መሪ የሆነውን ዘለዓለማዊ ብርሃኑንና ተስፋ የምናደርገውን ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ለማየት የተገለጡ ሊሆኑ ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ስንረዳ የክርስትናን ዓላማን ብቻ ሳይሆን ዓላማችንን እንዴት ከግብ ልናደርስ እንደምንችል እንረዳለን፡፡ የመንፈሳዊ ሕይወት መሠላሉ አንድ ሁለት እያልን ለመውጣት እንግዲህ እራሳችንን እናዘጋጅ፡፡
 ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment