Pages

Wednesday, December 10, 2014

የንስሐ ልጆቼን እንዴት ላገልግል? (2)

በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 2 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጽሑፉ ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት፥ የግንቦት 2005 ዓ.ም. እትም ነው፡፡
የንስሐ ልጆች ጕባኤ
 አኹን አኹን የንስሐ ልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጐት ለማሟላት ጕዳይ እያሳሰባቸው የመጡ ካህናት የንስሐ ልጆቻቸውን የሚያሳትፍ ወርሐዊ ጕባኤ ያዘጋጃሉ፡፡ ቀሲስ አንተነህ ጌጡ ከእነዚኽ ካህናት አንዱ ናቸው፡፡ ቀሲስ አንተነህ በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም የትግበራ ቡድን አስተባባሪ ሲኾኑ በመደበኛ አገልግሎታቸው ተይዘው ዋነኛ የክህነት ተግባራቸውን ከፍጻሜ ሳያደርሱ እንዳይቀሩ በማለት 94 ለሚኾኑት የንስሐ ልጆቻቸው በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ላይ ወርኃዊ ጕባኤ ማዘጋጀት ከዠመሩ ሦስት ዓመት ሞላቸው፡፡ አዠማመሩን ሲገልጹ “የንስሐ ልጆቼ ጥቂት በነበሩ ጊዜ መገናኘት ቀላል ነበር፡፡ እየበዙ ሲሔዱ ግን አንድ በአንድ ዘወትር ማግኘት ይቸግራል፡፡ በዚኽ ጊዜ ደግሞ የንስሐ ልጆች መንፈሳዊ ሕይወት እንዳይጐዳ ለማድረግ በግለሰብ ደረጃ ያለውን ግንኙነት እንደ አስፈላጊነቱ በቀጠሮ እያደረጉ ኹሉን ደግሞ በቋሚ መርሐ ግብር በየወሩ በሚሠራ ጕባኤ ማከናወን ጥሩ አማራጭ ኾኖ ተሰማኝ፡፡”

 ወርሓዊው መርሓ ግብር ላይ መገኘት ግዴታ ነው፡፡ ይኽን ግዴታ ማክበር የማይችል ሰው ከመዠመሪያው በንስሐ ልጅነት አይያዝም፡፡ ስለዚኽ በየወሩ በሚካሔደው ጕባኤ ከዓቅም በላይ የኾነ ችግር ከሚገጥማቸው በስተቀር ኹሉም ይገኛሉ፡፡ በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ያሉት ከልጆቻቸው ጋር አብረው ይመጣሉ፡፡ ይኽም ሕፃናቱ ገና በለጋነት ዕድሜያቸው ቃለ እግዚአብሔር እንዲሰሙ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲማሩ ያደርጋቸዋል፡፡ “ይኽም ብቻ አይደለም” ይላሉ ቀሲስ አንተነህ፤ “የሕፃናቱ መገኘት የጕባኤው ልዩ ድምቀት ስለኾነ ሲቀሩ ደስ አይለንም፡፡”
 የዚኽ ጕባኤ መፈጠር ያስገኘው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ በመዠመሪያ ደረጃ ምእመናኑ ስለ ሃይማኖታቸው መሠረታዊ ዕውቀት እንዲጨብጡ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ በጕባኤው ላይ ታላላቅ አባቶችና ሊቃውንት ስለሚገኙ ከእነዚኽ አባቶች በሚገኘው ትምህርት የጕባኤው አባላት ተጠቃሚ ይኾናሉ፡፡ “በተለይ ሊቀ ትጉኀን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜንና ሌሎች የማኅበረ ቅዱሳን መምህራንን ባመሰግን ደስ ይለኛል፡፡ እነዚኽ ሊቃውንት ጊዜያቸውን መሥዋዕት አድርገው በመገኘት ለልጆቼ የሚገባውን ቃለ እግዚአብሔር አስተምረዉልኛል፡፡ ከሊቃነ ጳጳሳትም ብፁዕ አቡነ ሉቃስና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በተለይ ጕባኤው ዓመታዊ በዓሉን ሲያከብር እየተገኙ ጕባኤውን ባርከዋል፡፡ የንስሐ ልጆቼን በጐ አገልግሎት አበርትተዋል” ይላሉ በጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት፡፡ አንዱ የጕባኤው አስፈላጊነት ይኽ ነው፤ ካህናቱ የሌሎችን ሊቃውንትን ዓቅም ለመጠቀም አስችሏቸዋል፡፡ ምናልባት ከነርሱ ዓቅም በላይ የኾኑ ችግሮች ቢኖሩ ሌሎች ይራዷቸዋል፡፡
 ጕባኤው የአባላቱን ግላዊ ችግር በመፍታት ብቻ አልታቀበም፡፡ ከዚኽም አልፎ እየተጓዘ ነው፡፡ በምዕራብ ወለጋ፣ በጋሞ ጎፋ፣ በጂንካና በመሳሰሉት ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው ገጠራማና ጠረፋማ አህጉረ ስብከት የሚካሔደውን ስብከተ ወንጌል የማስፋፋት አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያን ሕጋዊና መዋቅራዊ አካላት ጋር በመኾን እስከ መደገፍ የዘለቀ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በዙርያቸው የሚያገኝዋቸውን ዓቅም በማጣት የተጐሳቆሉ ምስኪኖችንም የመርዳት ሥራ ይሠራል፡፡ ይኽ መኾን የቻለው በመሰብሰባቸውና በመነጋገራቸው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በማሳደግ የዠመረው የንስሐ አባትና ልጆች ግንኙነት ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ አገልግሎት መስጠት ችሏል፡፡ ይኽ የንስሐ ልጆች ጕባኤ የሚመራውን ኮሚቴ አዋቅሮ፣ ዓመታዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ የአባላቱን መንፈሳዊ ሕይወት እያጐለበተ፣ የበጐ አድራጐት ሥራ እየሠራና ቤተ ክርስቲያንንም እያገለገለ ይገኛል፡፡
 የቀሲስ አንተነህ የንስሐ ልጆች ጥቂቶቹ የንስሐ ሕይወትን ገና እየተለማመዱ ያሉ ቢኾኑም ብዙዎቹ ግን ለሥጋ ወደሙ በቅተው የሚኖሩ መኾናቸውን ስለነገሩኝ ይኽን ማድረግ እንዴት እንደቻሉ ጠየቅኋቸው፡፡
 “ሰው ማለት ራሱ የሚጠላውንና የሚፀየፈውን ኃጢአት ተሸክሞ የሚኖር ፍጡር ነው፡፡ አውጥቶ መጣል አቅቶት እንጂ ወዶት አይደለም አብሮት የሚኖረው፡፡ የንስሐ አባት እንድኾነው ፈልጎ ወደ እኔ የሚመጣውን ሰው በዋናነት የምመክረው ለራሱ ጊዜ ሰጥቶ ውስጡን እንዲያደምጥ ነው፡፡ በትምህርት፣ በሥራ፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በሌላ ተወጥሮ ራሱን የዘነጋ ሰው ውስጡን ማድመጥ ሲችል ከኃጢአት ለመራቅ ማንም እንዲወስንለት ሳይጠብቅ የገዛ ራሱን መክሮ ራሱን ለማዳን ይፈልጋል፡፡ ለውጡ ቅጽበታዊ ሳይኾን ሒደታዊ ነው፤ ኹሉን በአንዴ መናዘዝና መተው አይችል ይኾናል፡፡ ቀስ በቀስ ግን የደበቀውን ኹሉ ይናዘዝና እፎይታን ያገኛል፡፡ እኔም ወደዚኽ ደረጃ እንዲደርስ በዘዴ እየገፋሁ እረዳዋለኹ፡፡”
“አንድ ሰው የጨጓራ ሕመም ቢኖርበት ሕመሙን ለሐኪሙ ይነግራል፡፡ ከዚያም የታዘዘለትን መድኃኒት ይወስዳል፡፡ የተከለከለውንም ምግብ ያስወግዳል፡፡ ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የማያስተጓጉሉ የሥጋ ሕማማት አብረዉን እንዲኖሩ ካልፈቀድንላቸው፥ ከገነት መንግሥተ ሰማያት ከታላቁ ክብር የሚያስተጓጕል የነፍስ በሽታ የኾነን ኃጢአትንም አብሮን እንዲቆይ ሳንፈቅድ ንስሐ መድኃኒቱን ልናሳዝዝለት ይገባል” እያልኩ ነፍሱን የሚያቆስላትንና በቁስሏም ጥዝጣዜን እየጨመረ ሕመሟን የሚያባብሰውን ኃጢአትን መናዘዝና መተው አስፈሪና አሳፋሪ ሒደት ሳይኾን የመንፈስ ደስታን የሚሰጥና መጨረሻውም ፍፁም ፈውስ መኾኑን ስነግረው መዳኑን ለመፈጸም ይቸኩላል፡፡”
 ሌላው የቀሲስ አንተነህ ጠንካራ ጐን የገዛ ራሳቸውን መመርመር መቻላቸው ነው፡፡ “ኹልጊዜ እርምጃዬን እገመግማለኹ፤ የሰጠኹት የመፍትሔ ሐሳብ ምን ያኽል ውጤት አስገኝቷል? ብዬ አስባለኹ፡፡ በዕውቀትና በልምድ የሚበልጡኝን አባቶች አማክራለኹ” ይላሉ፡፡ የቀሲስ አንተነህ ራስን የማየት ልምድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሌሎችን ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልኾን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለኹ” ያለውን ያስታወሰናል /1ኛ ቆሮ.9፡27/፡፡
ይቀጥላል…

*** ውድ የመቅረዝ አንባብያን! የንስሐ አባቶቻችኁ ይኽን ጽሑፍ ላያነቡት ይችላሉ ብላችኁ ካሰባችኁ አትማችኁ እንድትሰጧቸውና ከዚኽ በጐ ልምድ ተነሥተው አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ የልጅነት ድርሻችኁን እንድትወጡ ስንል በእግዚአብሔር ስም እንለምናችኋለን፡፡

No comments:

Post a Comment