Pages

Monday, December 15, 2014

የንስሐ ልጆቼን እንዴት ላገልግል? (3)

በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ታኅሳስ 7 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጽሑፉ ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት፥ የግንቦት 2005 ዓ.ም. እትም ነው፡፡
ወጣቶችን ለንስሐ መጥራት
ለንስሐ አባትና ልጅ ግንኙነት እንደ አንድ ተግዳሮት እየኾነ ያለው ነገር የትውልድ ክፍተትና የባሕል ልዩነት ነው፡፡ በተለይ በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶችን ዘመን አመጣሽ ችግሮች ተገንዝቦ መፍትሔ መስጠት በዕድሜ ከፍ ላሉትና ከገጠሩ አከባቢ ለመጡት ካህናት አስቸጋሪ ነው፡፡
 ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ሌሎች ችግሮችንም ያወሳሉ፡- “የንስሐ ልጆች ከአባቶች ጋር ተገናኝተው ለመወያየት አመቺ ቦታም የሚጠፋበት ጊዜ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን አፀድ ስር እየተገናኘን ለመነጋገር ብንሞክርም በጕባኤ ሰዓት ወይም በሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሰዓት መወያየት ከባድ ይኾናል፡፡”
 ለዚኽ ችግር እንደ መፍትሔ ቢኾን ብለው ቀሲስ ፋሲል አንዲት ቢሮ ከፍተዋል፡፡ አራዳ ጊዮርጊስ አከባቢ የምትገኘው ቢሯቸው (በአኹኑ ሰዓት 5 ኪሎ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ውስጥ ነው) በመጠን አነስተኛ ብትኾንም በውስጧ በርካታ መጻሕፍትን የያዘች ናት፡፡ ቀሲስ ስለዚኽ ነገር ሲያስረዱ፡- “ተነሳሕያኑ ምክር ከተቀበሉ በኋላ ስለ ሃይማኖታቸውም ኾነ ስለ ግል መንፈሳዊ ሕይወታቸው ዕውቀታቸው እንዲዳብር የተመረጡ መጻሕፍትን አውሳቸዋለኹ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የንባብ ፍቅር ስለሚያድርባቸው ራሳቸው እየገዙ ማንበብ ይዠምራሉ፤ እንዲያውም ለእኛ ያመጡልናል” ይላሉ፡፡

 ቀሲስ ፋሲል የንስሐ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ዕውቀት እንዲዳብር ለማድረግ ሰርክ ጕባኤ እንዲካፈሉ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲሳተፉ፣ መንፈሳዊ ኰሌጅ ገብተው እንዲማሩ አድርገዋል፡፡ በተለይ ከልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ለሚመጡ ወገኖች ግን መርሐ ግብር እያዘጋጁ ራሳቸው ያስተምራሉ፡፡
 ምንም እንኳን ለንስሐ ልጆቻቸው የሚያዘጋጁት ወርሓዊ ጕባኤ ቢኖራቸውም የቀሲስ ፋሲል ልዩና ተጠቃሽ አገልግሎት በተለይ ወጣቶች ላይ ትኵረት የሚያደርገው፥ በከፈቱት ቢሮ አማካኝነት የሚሰጡት አገልግሎት ነው፡፡ “አገልግሎቱ ኹለት ዓይነት መልክ ያለው ነው” ይላሉ፡፡ “የመዠመሪያው መንፈሳዊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ለሚነሡ ችግሮች ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ምክር ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ ማኅበራዊ ይዘት ላላቸው ችግሮች የሚሰጥ የምክክር አገልግሎት ነው፡፡ ኹለተኛው ዓይነት አገልግሎት ራሱ ተመካሪውን ያሳተፈ ስለኾነ ረዘም ያለ ሒደት ነው፡፡ የመፍትሔውም ሐሳብ አልጭንበትም፡፡ ነገር ግን አብረን መፍትሔ እናፈላልጋለን፡፡ በረዘመ ሒደትም ቢኾን በእግዚአብሔር ርዳታ መፍትሔው ላይ እንደርሳለን፡፡”
 ቀሲስ ፋሲል በዚኽ ዓይነት መንገድ ማገልገል ከዠመሩ ሦስት ዓመት የሞላቸው ሲኾን በሒደትም በርካታ ወጣቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ኾነዋል (ሐምሌ 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰባተኛ ዓመታቸውን አክብረዋል)፡፡ ለቃለ መጠይቅ በሔድኩበትም ጊዜ ጥቂት ወጣቶች በቀጠሯቸው ተገኝተው ተራቸውን እየጠበቁ ነበር፡፡ ቀሲስ ፋሲል እንዳስረዱኝ በሳምንት ሦስት ቀን ለአንድ ተገልጋይ ከ40-45 ደቂቃ በመስጠት የምክርና የምክክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በዚኽም ምክንያት ብዙዎች ለሥጋ ወደሙ የበቁ ሲኾን ኹሉም ደግሞ ኃጢአታቸውን በመናዘዝ በንስሐ ሕይወት መመላለስ የዠመሩ ናቸው፡፡
 የቀሲስ ፋሲል ብዙዎች የንስሐ ልጆች በወጣትነት ዕድሜ የሚገኙ ናቸውና “ምን የተለየ ዘዴ ስለሚጠቀሙ ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ ቀሲስ ፋሲል ሲመልሱ፡- “ወጣቶች ከተለያየ ቦታ ሲመጡ የተለያዩ ችግሮችን ይዘው ነው፡፡ ችግሩ መንፈሳዊም ሥጋዊም ሊኾን ይችላል፡፡ እንደ ችግራቸውና እንደ ዝንባሌአቸው ኹኔታ እያየን ትኵረት በመስጠት መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ከተሰጣቸው ሥነ ልቡናቸውን በመንፈሳዊ መንገድ መቈጣጠር ይቻላል፡፡”
 “በሥጋዊውም ቢኾን ወጣትነት በብዙ ምድራዊ ችግሮች የተሞላ ስለኾነ ወጣቶች መንገድ የሚመራቸውን የሚፈልጉበት ጊዜ መኾኑ ሊረሳ አይገባም፡፡ አንዳንዱ ሙያ ያጣል፡፡ ሌላው ተምሮ ወይም ሠልጥኖ ሥራ ያጣል፡፡ በሥጋ ፈቃድ የሚፈተነው ጓደኛ እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ጓደኛ ያለው ጋብቻ የመያዝ ፍላጐት አለው፡፡ ይኽ ኹሉ ሲኾን ወጣቶች የሚመራቸው ባለማግኘት ይታወካሉ፡፡ ወይም ይጐዳሉ፡፡” ቀሲስ ፋሲል የወጣቶችን ችግር በመስማት ችግሮቻቸው የሚፈቱበትን መንገድ ስለሚፈልጉላቸው ወጣቶቹ ችግራቸውን ለመንገር ቅድሚያውን ለንስሐ አባታቸው እንዲሰጡ አድርገዋቸዋል፡፡
 “ከንስሐ ልጆች መካከል አንዳንዶቹ በባለሀብትነት ደረጃ ያሉ ሲኾን ሌሎቹ ደግሞ ቆሎ በመሸጥና ጫማ በመጥረግ ደረጃ ያሉ ይኾናሉ፡፡ መቅጠር የሚችለውን ሥራ ከሚፈልገው ጋር እንዲገናኝ አደርገዋለኹ፡፡ አንድ ሰው መማር ያልቻሉ ወገኖቹን ለማስተማር የሚችል ከኾነ ከንስሐ ልጆቼ መካከል ትምህርት የሚፈልጉትን አገናኛቸዋለኹ፡፡ በዚኽ መሠረት ችግራቸውን በጋራ እየፈታን ስለምንሔድ ቤተሰብ እንኾናለን፡፡ ከዚኽ ዓይነቱ የምክክርና የመደጋገፍ ሕይወት መራቅ የሚፈልግ አይኖርም፡፡”
 ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንደሚገባቸውም ቀሲስ ፋሲል እንደሚያስተምሩ ነግረዉኛል፡፡ ወላጆች ኦርቶዶክሳዊውን የልጆች አስተዳደግ ይማራሉ፤ በመዠመሪያ ራሳቸው መልካም ኾነው በመገኘት ለልጆቻቸው አርአያ እንዲኾኑ ይማራሉ፡፡ ቀጥሎም ልጆችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘው እንዲመጡ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲያስገቡዋቸው በማድረግ ሕፃናትም በቤተ ክርስቲያን እንዲያድጉ የሚያደርጉትን ጥረት አሳይተዉናል፡፡
  በመጨረሻም ለቀሲስ ፋሲል ያነሳኹላቸው ጥያቄ “ከካህናት አባቶች ምን ይጠበቃል?” የሚል ነው፡፡ እንደሚከተለው መልሰዋል፡-
ከአባቶች ምን ይጠበቃል?
·        ሓላፊነትን መወጣት፡- የካህናት ሓለፊነት ምእመናንን መጠበቅ ነው፡፡ ጌታችን የሰጠው ሓላፊነት “በጐቼን ጠብቅ” የካህናትን ዋና ሓላፊነት የሚገልጥ ነው፡፡ ቅዳሴው፣ ሰዓታቱ፣ ማኅሌቱና የመሳሰለው ኹሉ መንፈሳዊ ግዴታ እንጂ የክህነት ሓላፊነት አይደለም፡፡ ሓላፊነቱ መጠበቅ ነው፡፡
·        ትኵረት መስጠት፡- የንስሐ አባቶች ለአለባበስ ወይም ለሌላ ጕዳይ የሚጨነቁትን ያኽል ለዋና የእረኝነት ተግባራቸው አለመጨነቃቸው ከባድ ችግር ነው፡፡ የንስሐ ልጆችን አንድ በአንድ ማግኘትና ለእያንዳንዳቸው ሕይወት ትኵረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የንስሐ ልጅን “የት ነበር የማውቅህ?” ማለት በጣም ጐጂ ነገር ነው፡፡ የአንዱ መጥፋት የኹሉም መጥፋት ስለኾነ እያንዳንዱን መጠበቅ፣ የእያንዳንዱን የግል ኹኔታና ልዩ ችግር ልክ ሐኪሞች እንደሚያደርጉት መዝግቦ መያዝ ያስፈልጋል፡፡
·        ራስን ማጠናከር፡- በቤተ ክርስቲያናችን መማርና ራስን ማሳደግ የተለመደ ትውፊት ነው፡፡ ቅኔ የተማሩ ሊቃውንት መጻሕፍት ቤት ይገባሉ፡፡ የታችኛውን ቤት ትርጓሜ የተማሩት እንኳን “ደግሞ የላይኛውን ቤት እንየው” ይላሉ፡፡ በዚኽ ባሕል ውስጥ ያለፉ ካህናት ዘወትር መማር መትጋት ይገባቸዋል፡፡ ዘመናዊውንም ኾነ የአብነቱን ትምህርት በመደበኛም ኾነ በንባብ መማር የዘመኑን ኹኔታ በማጥናት ጊዜውን መዋጀት ለንስሐ አባቶች ጠቃሚ ግዴታ ነው፡፡
·        ልጆችን መመጠንና መከታተል፡- በጥንታዊው ሥርዓት የኾነ እንደኾነ አንድ አባት የንስሐ ልጆች ከ12 አይበልጡም፡፡ አኹን በምእመናን ከቦታ ቦታ መዘዋወር ምክንያት ይኽ ሊኾን የማይችልበት አጋጣሚ ቢፈጠርም ካህናት ግን ሊቈጣጠሩት ከሚችሉት በላይ የንስሐ ልጆችን ማብዛት አይገባቸውም፡፡ የሚይዟቸውንም ቢኾን በአግባቡ መዝግበው መያዝ አለባቸው፡፡ በቀጠሮ አማካኝነት መጐብኘት፣ የእያንዳንዱን ኹኔታ አስፈላጊውን መሠረታዊ መረጃ ለማስታወስ አመቺ በኾነ መልኩ መዝግበው መያዝ አለባቸው፡፡ ከዚያም ልጆቻቸውን በተለያየ ዘዴ እየተከታተሉ ለክብር ማብቃት ይኖርባቸዋል፡፡
 ይቀጥላል…

*** ውድ የመቅረዝ አንባብያን! የንስሐ አባቶቻችኁ ይኽን ጽሑፍ ላያነቡት ይችላሉ ብላችኁ ካሰባችኁ አትማችኁ እንድትሰጧቸውና ከዚኽ በጐ ልምድ ተነሥተው አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ የልጅነት ድርሻችኁን እንድትወጡ ስንል በእግዚአብሔር ስም እንለምናችኋለን፡፡

No comments:

Post a Comment