Pages

Friday, May 29, 2015

አንዲት/አሐቲ/ ሰንበት ትምህርት ቤት



በዲ/ን ሕሊና በለጠ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡-  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አንድወይምአንዲትየሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያናችን ከቁጥር መግለጫነቱ ባሻገር የጠለቀ ምሥጢራዊ ፍች ያለው ቃል ነው፡፡
ከምሥጢራት ሁሉ የረቀቀውን የሥላሴን ምሥጢር አባቶች ባስተማሩንና በተገለጠልን መጠን ስንገልጽ አንድምሦስትም መሆናቸውን እንመሰክራለን፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የምናመልከው አምላክ በባሕሪየ መለኮቱ አንድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስአንድ ጌታበማለት ይጠቁመናል፡፡ በእርሷ መንገድነት ካልሆነ በቀር ጌታን ማግኘት አይቻልምና ይሄ አንድ ጌታ የሚገኝባትን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖትን መጽሐፍ ቅዱስአንድ ሃይማኖትሲል ይጠራታል፡፡ ያመነና የተጠመቀ ነውና የሚድነው /ማር.1616/ የድኅነት መንገድ ወደሆነችው ወደዚህች ሃይማኖት መግቢያ በር የሆነውን ምሥጢረ ጥምቀትንም በመቀጠልአንዲት ጥምቀትሲል ይገልጸዋል፡፡/ኤፌ.45/ ሐዋርያት ልቡናቸውና ቃላቸው በአንድነት የተባበረ ነውና በኤፌሶን መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስአንድያላትን ሃይማኖት ሐዋርያው ይሁዳምለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽማ የተሰጠችይላታል፡፡ /ይሁ. 3/

መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ /ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች/ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱስ ሉቃስ ሲጠራልን ስሟን ከመጥቀስ ይልቅአንዲት ድንግልማለትን መረጠ፡፡ /ሉቃ.127/ ከመስቀሉ ሥር በአደራ ከጌታ የተቀበላት አቡቀለምሲስ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በራእዩአንዲት ሴትአላት፡፡ /ራእ.121/
የባልና የሚስት ምሥጢራዊ አንድነትም በመጽሐፍ ቅዱስባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸውበሚል የተብራራ ነው፡፡ /ማቴ.196 ማር.108/
እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በቤተክርስቲያናችን ሌሎች ብዙ ምሥጢራትምአንድበሚለው ቃል ይተነተናሉ፡፡ ነገር ግን ሥላሴ አንድ ናቸው ስንል ጌታ አንድ ነው ስንል ሃይማኖት አንዲት ናት ስንል ጥምቀት አንዲት ናት ስንል እመቤታችንን አንዲት ድንግል ወይም አንዲት ሴት ስንል አንድ/አንዲትየሚለው ቃል የገለጸው ቁጥርን ነው የምንል ከሆነ ሞኝነት ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃአንዲትበሚል ቃል የተገለጸ ሌላ ንባብን እንመልከት፤ በዘወትር ጸሎታችን ላይለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁየሚል ንባብ አለ፡፡ ከዚህ ዐረፍተ ነገርም በመቀጠልሦስተ ጊዜ በልየሚል ትዕዛዝ አለ፡፡ በጸሎት ጊዜ ይሄን ክፍል ስናነበው ሦስት ጊዜ እንለዋለን፡፡አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁእያልን ነገር ግን ሦስት ጊዜ እንሰግዳለን፡፡ ይህ የሚያሳየውአንዲትየሚለው ቃል ከቁጥር መለኪያነትም ባሻገር ጥልቅ ምሥጢርን ያዘለ መሆኑን ነው፡፡ /በዚህ ክፍልአንዲት ስግደትየተባለው የጸጋ ያልሆነ የባሕርይ፣ የአምልኮ ስግደት ነው፤ ለቅድስት ሥላሴ ብቻ የሚሰገድ ነውናአንዲትበሚል ቃል ተገለጸ/ በተመሳሳይ ከላይ የተገለጹትም በየዐውዳቸው ጥልቅ ትርጓሜ ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄን ሁሉአንድነት የያዘችው ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችንም ምሥጢረ ተዋሕዶን ወይም የመለኮትንና የሥጋን ተዋሕዶ/አንድነት/ ምክንያት በማድረግ ስያሜዋተዋሕዶ” /አንድነት/ ሆኗል፡፡
ከላይ በተብራራው ሐሳብ መሠረት አንዲት ሰንበት ትምህርት ቤት ስንልም አንድ የሚለው ቃል ቁጥርን /ብቻ/ የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህን ለመገንዘብ ባሕሪያተ ቤተ ክርስቲያንን ገልጾ ማለፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በባሕርይዋ አንዲት ቅድስት ሐዋርያዊት ኩላዊት ዘላለማዊት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንአንዲትናት ስንል ከላይ በሌሎቹ ምሥጢራት እንዳብራራነው የተለየ ትርጓሜ አለው፡፡ ይህ የቤተክርስቲያንአንዲትመሆን በሦስት ወገን ይፈታል፡፡ የመጀመሪያው አፈታት ቤተክርስቲያን የምንባል እኛ በክርስቶስ ቃል መሠረትነት የሚኖረን አንድነት ነው - ከጌታ ዕርገት በኋላ 120 ቤተሰብዕበአንድልብ ሆነው ይተጉ እንደነበር፡፡ /ሐዋ.114/ ሁለተኛው አንድነት በሕይወተ ሥጋ ያለነው በሕይወተ ሥጋ ከሌሉ ቅዱሳንና ከመላእክት ጋር የሚኖረን መንፈሳዊ አንድነት ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ ምንም እንኳን እርሱ ከሐዋርያት ዘመን ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ቢኖርም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ከሐዋርያት ጋር ያለውን አንድነት ሲገልጽ ከሐዋርያት ጋር ዛሬ ሥጋውን እንበላለን ደሙን እንጠጣለን ብሏል፡፡ ይህም ከቅዱሳን ጋር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለንን አንድነት የሚያመለክት ነው፡፡ ሦስተኛውና ለቀደሙትም ትርጉም የሚሰጠው አንድነት ፍጥረታት በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት ነው - “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ” /ዮሐ. 656/ እንዳለ፡፡ /ካቶሊኮች የቤተክርስቲያንን አንድነት ምሥጢራዊ ፍችን ችላ በማለት አንድነቱን አስተዳደራዊ እንደሆነ ያስተምራሉ፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ አንድነቱን ወዳጅነት/ፊሎውሺፕ/ ሲሉ ይተረጉሙታል/
ሰንበት ትምህርት ቤትም የቤተክርስቲያን አካል በመሆኗ፣ አንድም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ሰንበት ትምህርት ቤት የምትኖር ባለመሆኗ በቤተክርስቲያን ባሕርያት ትገለጻለች፡፡ አንዲት ሰንበት ትምህርት ቤት ስንል ለቤተክርስቲያን አንድነት ከዘረዘርነው ምሥጢር የላቀ ትንታኔ የምንሰጥ ሆኖ አይደለም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህየሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነትእንቅስቃሴ እየተካሔደ ያለውም ይህንን በተለይ እርስ በእርስ ያለንን የአገልግሎት አንድነት እናዳብርና ሰንበት ትምህርት ቤትን የሊቃውንትና የጳጳሳት እንዲሁም የቅዱሳን ማፍሪያ እናደርግ ዘንድ ነው፡፡ በአገልግሎታችን ቅዱሳን ተገኝተው አንድም ከቅዱሳን ማኅበር ተደምረን የአገልግሎት መሥዋዕታችን አምላክ የወደደው መሥዋዕት ይሆን ዘንድ መጀመሪያ በአንድነት መጽናት ያሻልናበአንዲት ሰንበት ትምህርት ቤትዓላማ በአንድነት መቆም አግባብ ነው፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ስንል አስተዳደራዊና ተቋማዊ አንድነትንም የሚጨምር ነው፡፡ ይህም ማለት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጥ ሥርዐተ ትምህርት እንዲኖራቸው፣ ወጥ ሥርዐተ መዝሙር እንዲኖራቸው፣ ወጥ ውስጠ ደንብ እንዲኖራቸው፣ ወጥ የአገልግሎት መርሕ እንዲኖራቸው ባጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድ አይነት መንፈሳዊ አካሔድ እንዲመሩ የሚያስችል እንቅስቃሴ ነው፡፡ እነዚህን መፈጸም ይቻል ዘንድም የአንድነት ሀገራዊ ዕቅድ ታቅዶ በየሀገረ ስብከቱ በመከፋፈል ከሀገረ ስብከትም ወደ ክፍለ ከተማና ወደ እያንዳንዱ ሰንበት ትምህርት ቤት በማውረድ አንድነቱ እንዲሠምር ጥቂት የማይባሉ ወንድሞች ብርቱ ጥረትን እያደረጉ ነው፡፡
የዚህ እንቅስቃሴ ውጤቶች ከሆኑትም ውስጥ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሥር የተካሔደውንና ብዙ ሺህ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮችን ያሳተፈውን የአንድነት መንፈሳዊ ጉዞና በሀገር አቀፍ ደረጃም በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሰሙን የሀገራችን የሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች በተገኙበት የሚካሔደውን ሀገር አቀፍ የአንድነት ጉባኤ መጥቀስ ይቻላል፡፡ /ይህ ጉባኤ ከተጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ከግንቦት 21-23 ድረስ በቤተ ክህነት አዳራሽ እየተካሔደ ይገኛል፤/
አንድነት ኃይል ነው፤ አንድነት ጉልበት ነው፤ አንድነት ጥንካሬ ነው፤ አንድነት ውበት ነው፡፡ 50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ 50 ሰው ጌጡ እንዲሉ ለአንድ ሰንበት ትምህርት ቤት ሸክም የሆነ የመምህራን እጥረት ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት ሲሸከሙት ግን ሸክምነቱ ያበቃና መንፈሳዊ ውበት ይሆናል፡፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር እንዲሉ አንድ አጥቢያን ወይም ሰንበት ትምህርት ቤትን እንደሚያገሳ አንበሳ እየዞረ ሊውጥ የሚንጠራራ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት ሲያብሩበት መፈናፈኛ ያጣል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በስብስብ ጉልበት አይደለም፡፡ ወንድሞች በኅብረት ቢሆኑ መልካም ነው በሚለው ቃል መሠረት እንጂ ብሎ በሥጋዊ ስሜት በመነሣት አይደለም፡፡ ከግል ጸሎት ይልቅ የኅብረት ጸሎት ከተናጠል አገልግሎት ይልቅ የአንድነት አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ስለሆነ እንጂ በስሌታዊ የሰው ኃይል ብዛት አይደለም፡፡ እኛ አንድነት ሲኖረን እኛ መንፈሳችን አንድ ሲሆን መግባቢያ ቋንቋችን አንድ ሲሆን ፈቃዳችን ሲስማማ ፍላጎታችን ከቅዱሳን ፍላጎት ጋር ሲጣጣም መንገዳችን የአባቶች ሲሆን ፍኖታችን የጥንቱ ሲሆን ኅብረታችን ሲጸና ቅዱሳን በመካከላችን ይገኛሉ - ቅዱሳን ከመካከላችን ይፈራሉ፡፡ እግዚአብሔር የአንድነታችን ራስ ይሆናል፡፡ አገልግሎታችንን ራሳችን እንደሚያዘን እንደ አንድ አካል ብልቶች እንከውናለን፡፡
በዘፍጥረት 11 ላይ ያሉ የሰናዖር ሰዎች አንድነት ነበራቸው፡፡ ኅብረት ነበራቸው፡፡ አንድነታቸውን ግን ለክፉ ሥራ ተጠቀሙበት፡፡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ አንድነታቸውን ገለጡ፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና እግዚአብሔር አምላክ ክፋታቸውን ዐይቶ የእነርሱን አንድነት ከመበተኑ በፊት ግን አንዲት ነገርን ተናገረእነሆ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፤ ለሁሉም አንድቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም፡፡ /ዘፍ.116/ ያሰቡትን ለመሥራት አይከለከሉም፤ ይችላሉ አለ፤ ምክንያቱም ቋንቋቸው አንድ ነውና፤ ኅብረታቸው አንድ ነውና፡፡ አንድነት በጸናበት ሁሉ ሥራ ቀላል ነው፡፡ መተባበር ባለበት ሁሉ ስኬት የቀለለ ነው፡፡ መግባባት ባለበት ሁሉ ግብ መምታት የሚጠበቅ ነው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ቋንቋቸው አንድ ነበርና ወደ ግባቸው ፈጥነው ገሰገሱ፡፡ ነገር ግን ግባቸው ክፉ ነበርና እግዚአብሔር የስኬት ሩጫቸው እንዲቆም አንድነታቸውን በተነው፡፡ ቋንቋቸውን ደባለቀው፡፡ አንዱ ጡብ ሲል ሌላው ውኃ አቀበለ፤ አንዱ አፈር ሲል ሌላው ድንጋይ አቀበለ፡፡ እነርሱም መግባባት ሳይችሉ የጀመሩትን አቋርጠው ተበታተኑ፡፡ መበተናቸውንም ለመግለጽ ባቢሎናውያን ተባሉ፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እንቅስቃሴ ቋንቋን አንድ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ ፍቅር የተባለ ቋንቋ፣ መንፈሳዊነት የተባለ ልሳን፣ ቅንዐተ ቤተክርስቲያን የተባለ መግባቢያ በሰንበት ትምህርት ቤቶችና በቤተ ክርስቲያን እንዲሰፍን ማድረግ፡፡ አንዱ ጾም ሲል ሌላው አብሮ እንዲጾም አንዱ ትምህርት ሲል ሌላው አብሮ እንዲማር አንዱ መዝሙር ሲል ሌላው አብሮ እንዲዘምር አንዱ ልማት ሲል ሌላው አብሮ እንዲያለማ አንዱ አፅራረ ቤተክርስቲያንን ሲቃወም ሌላው “…ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩየሚል ጥቅስን ካለቦታው ጠቅሶ እንዳይለይ፣ አንዱ የሬዳዊ ዜማ ሲል ሌላውምናለበትበሚል በሽታ እንዳይነጠልነገር ግን እግዚአብሔር በቀደሰው ሰማያዊ ኅብረት ሁሉም በአንድነት በመቆም እንዲጸድቅና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራን እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡
በተለይ የቤተክርስቲያን አካላትን በአመለካከት በዘር በአካባቢ በፖለቲካዊ አስተሳሰብና በተለያዩ ጉዳዮች ከፋፍለው የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት የሚፈልጉ ከሀድያን ሞሳኞችና ሌሎችም የተለያየ ዓላማ ያላቸው አካላት በበዙበት በዚህ ዘመን አንድ ሆኖ መገኘት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም የቤተክርስቲያናችንን ህልውና ፈጽመው የማይፈልጉ የተሐድሶ መናፍቃንንና ሞሳኞችን ለመከላከልና ለማጋለጥ ብሎም ለማጥፋት በአንድነት መታገል አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ጊዜ ባደረጓቸው የአንድነት እንቅስቃሴዎችም የውስጥ ጠላቶችና ሞሳኞች ከልክ በላይ ሲደናገጡ የታዩትም የአንድነቱ ኃይል ረብሿቸው ነው፡፡ ድንጋጤያቸው ለጥፋታቸው ንስሐን የሚያስመኛቸው ከሆነ እሰየው ካልሆነ ግን እንደ ካንሰር ሙሉ የቤተ ክርስቲያንን አካል እንዳይበክሉ መቆረጥ አለባቸውና አንድነቱ ይበልጥ እንዲጠነክር ያስፈልጋል፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቶች ከዕቅበተ እምነት ግዴታቸው ባሻገር ተተኪ ትውልድን ለማፍራት ከየትኛውም የቤተክርስቲያን ተቋማዊ አካል ይልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በመሆኑም አንድነቱን ማጠናከር ማለት የነገዋን ቤተክርስቲያን መቅረጽ ነው፡፡ የነገዎቹን ሊቃውንት ጳጳሳት ጻድቃን ሰማዕታት ለማፍራት ይቻል ዘንድ ሕፃናት የሚማሩባቸውን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማበርታት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ርምጃ አንድነቱን መደገፍ ነው፡፡
ባጠቃላይ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እንቅስቃሴ የአሐቲ ቤተክርስቲያን አካል የሆነችውን አንዲት ሰንበት ትምህርት ቤት ምሥጢራዊና ቤተክርስቲያናዊ የአሐቲነት ይዘቷን ጠብቆ እውነትን በፍቅር በመያዝ ወደ ክርስቶስ የማደግ /ኤፌ.415/ መንፈሳዊነትን የሚደግፍ መንፈስ ቅዱስ ያስጀመረው እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ ከተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር ዳገት ሆኖ እየታየ ያለው አስተዳደራዊ አንድነት ይመጣ ዘንድ ሁሉም ሰንበት ተማሪና እያንዳንዱ ቤተክርስቲያንን የሚወድ አካል መረባረብ አለበት፡፡ ከተቻለም በአገልግሎቱ ዐቅም በፈቀደው ሁሉ በመሳተፍ የታሪክ አካል ከመሆንም ባሻገር በረከትንም ማግኘት ይገባል፡፡ ከሰማያዊው አንድነት መደመርና የአንድነቱ አንድ አካል መሆንም ለመንፈሳዊ ሕይወት ታላቅ ስንቅ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አንድነታችንን ይባርክልን፡፡


2 comments:

  1. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን:: እንደ ሐዋርያቱ በአንድ ልብ እናስብ ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፤

    ReplyDelete
  2. Amen እግዚአብሔር አምላክ አንድነታችንን ይባርክልን፡፡

    ReplyDelete