Pages

Monday, June 1, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል አስር)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 25 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ አንባብያን! እንዴት ሰነበታችሁ? እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ዛሬም የትምህርተ ሃይማኖት ትምህርታችንን እንቀጥላለን፡፡ በዛሬው ክፍልም በክፍል ዘጠኝ የጀመርነውን የሥነ ፍጥረት ትምህርት ይኾናል፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ጥበቡን ያድለን፡፡ አሜን!!!

እግዚአብሔር ፍጥረትን ለመፍጠር የፈጀበት ቀን
      በዚህ ጕዳይ ላይ ብዙ ዓይነት አመለካከቶች ያሉ ሲኾን ዘፍ.2፡4ን በመጥቀስ በአንድ ቀን የሚሉ አሉ፤ መዝ.90፡4ን በመጥቀስ የማይታወቅ ብዙ ቀናት የሚሉ አሉ፤ እነ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ጨምሮ “ፀሐይና ከዋክብት የተፈጠሩት ረቡዕ ዕለት ስለኾነ ስንት ቀን እንደፈጀ ማወቅ አይቻልም፡፡ አሁን የምንኖረው እንኳን በሰባተኛው ቀን ነው” በማለት አንድ አፍታ ወይም ሚልዮን ዓመታት የሚሉ አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነው ግን እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን በስድስት ቀናት ውስጥ እንደፈጠረ ነው /ዘጸ.20፡11/፡፡
ለመኾኑ ጊዜ ምንድነው?
የሥነ ፍጥረትን ትምህርት ስናጠና የማይቀሩ ጥያቄዎች አሉ፡፡ “ጊዜ ምንድነው? መቼ ተፈጠረ? የራሱ የኾነ ህልውናስ አለውን?” የሚሉትና ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለዚህም ሦስት ዓይነት አመለካከት አለ፡-
1.  ፍጥረት ከመፈጠሩ በፊትም ጊዜ ነበረ፤
2.  ሌሎች ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ እግዚአብሔር ጊዜን ፈጠረ፤
3.  ሌሎች ፍጥረታትን ሲፈጥር እግዚአብሔር ጊዜንም አብሮ ፈጥሮታል የሚሉ ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነው ሦስተኛውን ነው፡፡ ይህ እንዴት እንደኾነም እንደሚከተለው እንመለከቷለን፡፡
እግዚአብሔር ለሥነ ፍጥረት መኖሪያና መመላለሻ አድርጎ ኹለት ነገሮችን ፈጥሯል፤ ጊዜና ቦታ፡፡ ከእነዚህ (ከጊዜና ከቦታ) አጥር ውጪ የሚኾን አንድም ፍጥረት የለም፡፡ እግዚአብሔር ግን ከእነዚህ አጥሮች (ድንበሮች) ውጪ ነው፡፡ በጊዜ አይለካም፤ በቦታም አይወሰንም፡፡
በዚሁ መሠረት ኹለት ዓይነት ጊዜያት እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ አንዱ ዘለዓለማዊነትን የሚያመለክት ሲኾን ሌላው ደግሞ ዘለዓለማዊነትን የማያመለክት፡፡
ዘለዓለማዊነትን የሚያመለክተው ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚነገር ሲኾን ትናንት፣ ነገ የሚል አቈጣጠር የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ጊዜ ኹሌ ዛሬ ወይም አሁን ነው፡፡ ይህ ዛሬ ወይም አሁን ብለን የምናገርለት አገላለጽ ራሱ የእኛ ዓይነት ዛሬ ወይም አሁን አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእኛ አሁን ወይም ዛሬ ከመቅጽበት ቅድም ወይም ትናንት የሚኾን ነው፡፡ ከላይ ይህን ጽሑፍ ስናነብ “አሁን” ብለን ስናገርለት የነበረው ጊዜ እንኳን አልፎ ይኸው “ቅድም” ኾኗል፡፡ የእግዚአብሔር “አሁን” ወይም “ዛሬ” ግን እንደዚህ የሚያልፍ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ኹሉም የታወቀ ስለኾነ እንደ ሰው ትዝታ ወይም ተስፋ የሚባሉ ነገሮች የሉም፡፡
ይህ ዘለዓለማዊነት ለዘለዓለማዊው አምላክ ብቻ የሚነገር ስለኾነ እንደ እኛ ዓይነት ጊዜ የሚለካ ወይም የሚሰፈር አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ስፍራ ይህን ግልጽ አድርጎት እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” /መዝ.2፡7/፤ “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” /ዮሐ.8፡58/ በሚሉት ኃይለ ቃላት ውስጥ “ዛሬ” እና “አለሁ” ሲል አንድ ወይም የተወሰነ ቀንን የሚያመለክት ሳይኾን ዘለዓለማዊነትን የሚያመለክት ነው፡፡
ምናልባት ከእናንተ መካከል፡- “የነበረ፤ የሚኖር ብለን በሐላፊና በመጻኢ አገላለጽ ለእግዚአብሔር እንናገር የለምን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ አዎ! እንዲህ ብለን እንናገራለን፤ ነገር ግን ቢቸግረን የምንናገራቸው እንጂ ስለ እግዚአብሔር በአግባቡ የሚገልጹ ኾነው እንዳልኾነ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ለእኛ የሚስማማውና ዘለዓለማዊ ያልኾነው ጊዜ ከመጀመሪያው ፍጥረት ጋር አብሮ የተፈጠረና የጀመረ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ብሎ እንደተናገረ ይህ ዘለዓለማዊ ያልኾነው ጊዜም በዛው ቅጽበት አብሮ የተፈጠረና የጀመረ ነው፡፡ ይህ የተፈጠረው ጊዜ ከዘለዓለማዊው ጊዜ የቀጠለ ሳይኾን ፍጡርና መጀመሪያ ያለው ነው፡፡ አሁን ካለንበት ቅጽበት አንሥተን ወደ ኋላ እያጠነጠንን ብንሔድ የምንደርስበት ጫፍ አለው፡፡
ይህ ዘለዓለማዊነት የሌለው ጊዜ መነሻ እንዳለው ኹሉ መጨረሻም አለው፡፡ መጨረሻውም በቃል መነገሩ፣ በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በመጣ ጊዜ ነው፡፡
የፍጥረት መገኛ
እግዚአብሔር ፍጥረታትን ያስገኘው ከኹለት ወገን ነው፡፡
1.  ካለ መኖር ወደ መኖር፡- 7 ናቸው፡፡ ብርሃን፣ መሬት፣ እሳት፣ ውኃ ፣ ነፋስ፣ መላዕክት፣ ጨለማ፡፡
2.  አስቀድሞ ከፈጠረው ፍጥረት (ግብር እምግብር)፡- ከውኃ ውኃ አደር ፍጥረታት፣ ከመሬትም የብስ አደር እንስሳትና የሰው ልጅ ተፈጥረዋል፡፡
እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ያስገኘበት ኹኔታ
እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ያስገኘበት መንገድ ኹሉን ቻይነቱ የሚያስረዱ ሲኾኑ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
1.  በሐልዮ (በማሰብ)፡- 7 ሲኾኑ እነርሱም አራቱ ባሕርያተ ሥጋ፣ ጨለማ፣ ሰባቱ ሰማያትና መላዕክት ናቸው፡፡
2.  በነቢብ (በመናገር)፡- 14 ሲኾኑ እነርሱም ብርሃን፣ ፀሐይ፣ ጠፈር፣ ጨረቃ፣ አዝርዕት፣ ከዋክብት፣ አትክልት፣ ውኃ አደር (እንስሳት፣ አራዊት፣ አዕዋፍ)፣ ዕፅዋት፣ የብስ አደር (እንስሳት፣ አራዊት፣ አዕዋፍ) ናቸው፡፡
3.  በገቢር (በተግባር)፡- 1 ሲኾን ርሱም የሰው ልጅ ነው፡፡
አራቱ ባሕርያተ ሥጋና ጠባያቸው
ባሕርይ ማለት የነገር ኹሉ ሥር፣ መገኛ መሠረት ማለት ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ሲቀጸል ዘለዓለማዊነቱን ምክንያትና መነሻ የሌለው መኾኑን የሚያስረዳ ሲኾን ለፍጥረታት ሲቀጸል ደግሞ የዚያ ፍጥረት የመገኘቱ ጥንተ አቋም የሚያስዳ ነው፡፡ እነዚኽ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ የምንላቸውም ከመላእክትና ከነፍስ በስተቀር ሌሎች ፍጥረታት ከእነዚኽ ስለሚገኙ ነው /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ ገጽ 14/፡፡
 አራቱም ባሕርያት የየራሳቸው ጠባይ አላቸው፡፡ ዳግመኛም፡-
1.  መሬት፡- ከውኃ ሳይለይ ጸብር (ጭቃ) ይባል ነበር፡፡ ለፍጥረት ማደሪያ ስለኾነም ምድር ተብሏል፡፡ ይቡስነት (ደረቅነት)፣ ጽሉምነት (ጥቁርነት)፣ ቆሪርነት (ቀዝቃዛነት) ጠባይ አለው፡፡ መሬት የእግዚአብሔርን ባለ ጸጋነት ያስረዳል፤ ሀብት ከመሬት ይገኛልና፡፡ ዳግመኛም ምድር ቻይ ናት፤ ፍጥረትን ኹሉ ችላ ትኖራለችና፡፡ “ለምን አረሱኝ፣ ለምን ቆፈሩኝ፣ ለምን ገረፉኝ?” አትልም፡፡ ጌታም ኹሉን ችሎ፣ ታግሦ፣ ሀብቱን ለፍጥረቱ ኹሉ ሳያዳላ ሰጥቶ ይኖራልና፡፡
2.  ውኃ፡- ብሩህነት (ብሩህ መኾን)፣ ርጡብነት (ርጥብ መኾን)፣ ቆሪርነት ጠባይ አለው፡፡ የእግዚአብሔርን የሚያነጻ መኾኑን ያስረዳል፡፡ ይኸውም ውኃ እድፍን ከአካል፣ አካልን ከእድፍ እንደሚለይ ኹሉ ጌታም ነፍስን በጥምቀት ውኃ ከኃጢአት፣ ኃጢአትንም ከነፍስ ይለያልና፡፡
3.  ነፋስ፡- ርጡብነት፣ ውዑይነት (ሙቅ መኾን)፣ ጽሉምነት ጠባይ አለው፡፡ ነፋስ የእግዚአብሔርን ፈራጅነት ያስረዳል /መዝ.7፡11-12፣ ማቴ.3፡12-13/፡፡ ይኸውም ነፋስ ገለባውን ከፍሬ እንደሚለይ ኹሉ እግዚአብሔርም ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያልና፡፡
4.  እሳት፡- ውዑይነት፣ ብሩህነት፣ ይቡስነት ጠባይ አለው፡፡ የእግዚአብሔርን ኃያልነት ያስረዳል፡፡ እሳት ኃያል ነው፡፡ ውኃ ካልከለከለው ቈላውን ደጋውን፣ ርጡቡን ደረቁን ልብላ ቢል ይቻሏል፡፡ እግዚአብሔርም ቸርነቱና ርኅራኄው ካልከለከለው ኹሉንም ማጥፋት ይችላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment