Pages

Friday, July 31, 2015

የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም መምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ትናንት፣ ዛሬና ነገ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 24 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም መምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ተቋም ከተመሠረተ ከ82 ዓመታት በላይ ኾኖታል፡፡ በእነዚህ አገልግሎት ዘመናቱም በርካታ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት፣ አባቶች መምህራንና ካህናትን አፍርቷል፡፡ ማሠልጠኛው ጥንታዊው የሀገራችን ቋንቋና ፊደል ግእዝና ትምህርቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ለትውልድም እንዲተላለፍ በማድረግ በኩል ታላቅ ድርሻ አለው፡፡ የቤተክርስቲያን አባቶችና ምእመናን ኹሉ የቤተ ክርስቲያን አለኝታና ቅርስ መኾኑን በኩራት የሚናገሩለት ተቋም ነው፡፡
ይኼው ማሠልጠኛ በረጅም ጊዜ አገልግሎት ለቤተክርስቲያንም ኾነ ለሀገር ከፍተኛ አገልግሎትና ጥቅም የሰጠ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የዚህን ት/ቤት ትናንት የነበረውን ገጽታ ዛሬ ያለበትንና ወደፊት የሚጠበቅበትን በዚህች አነስተኛ ጽሑፍ እንዳስሳለን፡፡

ጥቂት ስለ ገዳሙ
ዐፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ በኋላ ፍልውኃ አካባቢ አሁን ታላቁ ቤተ መንግሥት የተባለውን ለማሠራት አዲስ አበባ ከተማን ቆረቆሩ፡፡ ለጠዋትና ማታ ጸሎታቸው ማድረሻ አነስተኛ ሥዕል ቤት ከቤተ መንግሥታቸው አጠገብ አሠሩ፡፡ ይህች ሥዕል ቤት ዛሬ በታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ስትገኝ “ደብረ መንክራት ሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን” በመባል ትታወቃለች፡፡
የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ባሳተመው “የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ” ቁጥር 1፤ ነሐሴ 1992 ዓ.ም. መጽሔት ላይ የገዳሙን አመሠራረት በተመለከተ “የቤተክርስቲያኗን ታሪካዊ አመሠራረት መዘክራት እንደሚያስረዱት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ቅድስት ድንግል ማርያምን ዘወትር በጸሎት ይማጸኑዋት ነበርና ዕረፍታቸው እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ በገባችበት ታኅሣሥ 3 ቀን ኾነላቸው፡፡ ይህን ምሥጢር የሚያውቁት ልጃቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የሕዝብ እንደራሴዎች መክረውና አጥንተው የመልካም ሥራቸው መታሰቢያ፣ የዐጽማቸው ማረፊያ እንድትኾን የታእካ ነገሥት በአታ ለማርያምን ሕንፃ ቤተክርስቲያን በ191ዐ ዓ.ም መሠረቱን ጥለው በ192ዐ ዓ.ም ፈጸሙ” በማለት ተገልጿል /ገጽ 271/፡፡
ገዳሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ እምነት የተመሠረተ ባለታሪክ ገዳም ነው፡፡ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲሁም የሌሎችም ንጉሣውያን ቤተሰቦችና የግብጻዊው ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ዐጽም ያረፈበት፣ ጥንታውያን ንዋያተ ቅድሳት፣ የብራና መጻሕፍት፣ በርካታ ቅርሳ ቅርስ የሚገኝበት ታሪካዊ ገዳም ነው፡፡
ይህ ገዳም ሲመሠረት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ያሠሩት ንጉሠ ነገሥቱ፣ የቤተመንግሥቱ ሰዎችና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን የሚጠቀሙበት የኪዳነ ምሕረት ሥዕል ቤት ነበር፡፡ ከዐፄ ምኒልክ ሞት በኋላ ልጃቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሲነግሡ የአባቴ ዐጽም ያረፈበት ለአባቴ መታሰቢያ እንዲኾን ብለው የበአታ ማርያምን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለመተዳደሪያ ገንዘብ፣ ርስት፣ ሀብትና ንብረት ሰጥተው በ1910 ዓ.ም. በገዳምነት እንዲመሠረት አደረጉ፡፡ ገዳሙ ሲመሠረት አብረው የተቋቋሙ ሦስት ተቋማት በሥሩ ነበሩ፡፡ እነዚህም፡-
1.  የመምህራንና የቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት፤
2.  እናት አባት የሌላቸው ሕፃናት ተኮትኩተው የሚያድጉበት (እጓለ ማውታ)፤
3.  ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው የአረጋውያን መጦሪያ ናቸው፡፡

የገዳሙ መተዳደሪያ
 
ገዳሙን የመሠረቱት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከማይንቀሳቀሰው ንብረት፣ ርስት ሌላ ሦስት መቶ ሺሕ ማርቴሬዛ ብር የገዳሙ መተዳደሪያ እንዲኾን ሰጥተዋል፡፡ ገዳሙ ለዘለቄታው ራሱን ችሎ ሥራውን የሚያካሒድበት የእርሻ መሬት ርስት ጉልት፣ የከተማ ቦታና ቤት፣ ጥሬ ገንዘብ የሰጡ እንደነ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስና ሌሎች በጐ አድራጊዎች ነበሩ፡፡
      ጠቅላላ የገዳሙን ሥራ የሚያስተባብር መንፈሳዊውን አስተዳደር የሚመራው የቁምስና ማዕረግ ያለው “ሊቀ ሊቃውንት” ተብሎ የሚሾም አባት ነው፡፡ የገዳሙን ሀብትና ንብረት አጠቃላይ ገቢ በሚገባ እየተቈጣጠረ ለሚያስፈልገው ተግባር መዋሉን የሚከታተል፣ የገዳሙን አስተዳደር፣ ትምህርቱን፣ ፋይናንሱን ወ.ዘ.ተ. ሥራ የሚመራና የሚቈጣጠር በገዳሙ ሊቀ ሊቃውንት ሰብሳቢነት የሚሠራ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የሚገኙበት ባለአደራ ቦርድ ገዳሙን በበላይነት እያስተዳደረ ሥራውን ሲያካሒድ ቆይቷል፡፡

    የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም በዚህ ኹኔታ በሚያገኘው ገቢ በሥሩ ያሉትን የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት፣ ወላጅ የሌላቸውን ሕፃናት ማሳደጊያ፣ የአረጋውያን መጦሪያ እያስተዳደረ እንዳለ በ1967 ዓ.ም. በገጠር መሬት፣ በከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ የገዳሙ የእርሻ መሬቶች የከተማ ቤቶችና ሕንፃዎች በሙሉ ተወረሱ፡፡ ደርግ የገዳሙን ቦታና ቤቶች ከወረሰ በኋላ ለእጓለ ማውታ ማሳደጊያው፣ ለጡረታ ቤቱና ለአዳሪ ት/ቤት መተዳደሪያና ለሠራተኞች ደመወዝ የተወሰነ በጀት መደበ፡፡ /ሐመር-ሐምሌ/ነሐሴ 1993 ዓ.ም፤ ገጽ 19-2ዐ/፡፡ የባለአደራ ቦርዱ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ግንኙነት እያደረገ የተያዘለት በጀት ከገንዘብ ሚኒስቴር እየሰጠው ከበጐ አድራጊ ምእመን በስጦታ ከሚያገኘው ገቢ ጋር እየተቀናጀ በዚህ ዓይነት መተዳደሪያ ገዳሙ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እያከናወነ እስከ 1986 ዓ.ም. ድረስ ቆየ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የባለአደራ ቦርዱ አስደዳደር እንዲፈርስ ተወስኖ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከገንዘብ ሚኒስቴር የሚሰጠው በጀት ቀርቷል፡፡
    በቃለ አዋዲው መሠረት በሰበካ ጉባኤ እንዲተዳደር ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በየዓመቱ ከሚሰጠው ድጐማ ጋር ከንዋየ ቅድሳት መሸጫው፣ ከእህል ወፍጮና ከበጐ አድራጊ ምእመናን በስጦታ ከሚያገኘው ገቢ ጋር በማቀናጀት ጠቅላላ የገዳሙን መንፈሳዊ አገልግሎት የመምህራንና የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤቱን፣ እናት አባት የሌላቸውን ሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሁም የአረጋውያን መጦሪያ በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ አመሠራረት
   
በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሥር የሚተዳደረው የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት የተመሠረው፡- ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡትን ተማሪዎች በልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነቶች አስተምሮና አሠልጥኖ በዘርፉ ብቁ ካህናትና መምህራንን ለማፍራት፤ የሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋና ፊደል በተለይ የግእዝ ትምህርት ተጠብቆ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማስቻል፤ በገዳሙ አካባቢ የሚኖሩትን ሕፃናት እየተቀበለ መሠረተ ትምህርት፣ ንባብና ጽሕፈት እንዲሁም አምስቱን አዕማደ ምሥጢር በማስተማር በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ለማድረግ ታስቦ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያነት በ1925 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡
    ማሠልጠኛው ተቋቁሞ ትምህርቱ እየተሰጠ መምህራንና ካህናት እያሠለጠነ ቢቆይም ተማሪዎች ምግብና ልብስ እየተሟላላቸው በአዳሪነት እንዲማሩና ትምህርቱ በመደበኛ ኹኔታ በተጠናከረ መንገድ እንዲካሐየድ የተደረገው ከ195ዐ ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ማሠልጠኛው ትምህርቱን እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ቀጠለ፡፡
   በደርግ ዘመን ት/ቤቱ ተዳክሞ እንደ ነበር በወቅቱ የት/ቤቱን ኹኔታ ያወሳው “ዝክረ ምኒልክ” የተሰኘው የገዳሙ መጽሔት እንደሚከተለው አስፍሮታል፡፡ “ደርግ የገዳሙን ንብረት በሙሉ ወርሶ ለ17 ዓመታት በመንግሥት እጅ እንዲተዳደር ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ መንፈሳዊ ት/ቤቱ ምንም እንኳን መሠረታዊና መደበኛ የማስተማሩን ተግባር ባያቋርጥም ንብረቱ ስለተወረሰበት በበጀትና በቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት የተነሣ ወደፊት ሊራመድና ያልነበሩትን መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለማስፋፋት ያሉትንም ለማጠናከር አልቻለም፡፡ ይኹን እንጂ ከመንግሥት ተቆንጥሮ በተመደበለት አነስተኛ በጀት ነባር የኾኑ ትምህርቶችን በማስተማር በርካታ ሊቃውንትን ከማፍራት አልተገታም፡፡ ይህ ት/ቤት በወቅቱ የደረሰበትን ፈታኝ ተግዳሮት ተቋቁሞ ለ17 ዓመታት ሳያቋርጥ እያስተማረ ከቆየ በኋላ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ከገዳሙ የተወረሱትን ሕንፃዎችና የንግድ ቤቶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ለገዳሙ በአደራነት መለሰ፡፡ በዚህ አንጻር ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በሚሰጠው አነስተኛ ድጎማ እየተዳደረ ይገኛል” /ገጽ 132-133፤ 2006 ዓ.ም./፡፡
በማሠልጠኛው የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች

     በማሠልጠኛው ሰባት ዓይነት ጉባኤያት ይካሔዳሉ፡፡ እነዚህም፡- ብሉያትና ሐዲሳት ትርጓሜ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንት (ሃይማኖተ አበው፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቄርሎስ፣ 14ቱ ቅዳሴያት)፣ የቁጥር መጽሐፍ (አቡሻኽር)፤ መጻሕፍተ መነኮሳት (ማር ይስሐቅ፣ ፊልክስዮስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ)፣ ድጓ፣ ቅኔ፣ አቋቋምና ዝማሬ መዋሥዕት፣ ቅዳሴ ናቸው፡፡

የትምህርቱ ሒደትና የመደበኛ ተማሪዎች  አገልግሎታቸው
                                                   
በአሁኑ ወቅት መደበኛ ኾነው በማሠልጠኛው በአዳሪነት በኹሉም ጉባኤያት የሚማሩ 70 ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ የማሠልጠኛው መደበኛ የትምህርት ሰዓት ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ ቀኑ 1ዐ፡ዐዐ ሰዓት ድረስ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በክህነታቸው በኩል ይቀደሳሉ፣ ይዘምራሉ፡፡ ማኅሌት፣ ሰዓታት ይቆማሉ፡፡ ጠዋት ኪዳን ያደርሳሉ፤ ያሳጥናሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሙሉ አገልግሎት ይሳተፋሉ፡፡ በዐቢይ ጾም ዳዊት ያስተዛዝላሉ፡፡ ጾመ ድጓውን በዝማሜው በቁሙ የዕለት የዕለቱን በተሠራው ሥርዐት መሠረት ቀለሙን ያደርሳሉ፡፡ ሌሊት 1ዐ፡ዐዐ ሰዓት ደወል ሲደወል ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳሉ፡፡ ከዚያ ጀምረው እስከ 6፡ዐዐ ሰዓት ከቀኑ በቁመት ይቆያሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ቅዳሴ ዕጣነ ሞገር አለ፡፡ የማታ (የሠርክ) ጸሎትም 1ዐ፡ዐዐ ሰዓት ይደወላል፡፡ ተማሪዎቹ ከሞላ ጐደል ከመደበኛ የትምህርት ጊዜያቸው ውጪ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ይፈጽማሉ፡፡
የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ቀንና ሌሊት (24 ሰዓት) ጉባኤው ሳይቋረጥ የሚካሔድበት መንፈሳዊ ት/ቤት ነው፡፡ ከተለያዩ አድባራት በሥራ ላይ ኹነው ሙያቸውን (ዕውቀታቸውን) ለማሻሻል የሚመጡትን ኹሉ ያስተምራል፡፡ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልኾነ ተቋማት ሥራ ላይ ያሉትም የሥራ ሰዓታቸውን በማይነካ ኹኔታ ከመምህራቸው ጋር በመነጋገር አመቺ ሰዓት መርጠው በትርፍ ጊዜያቸው ይማራሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ በደጅ ጥናት ወደፊት ወደ ማሠልጠኛው ለመግባት እየተጠባበቁ ተመላላሽ ሆነው ሙሉ ቀን የሚማሩ አሉ፡፡
በትምህርቱ ሒደት ላይ በማሠልጠኛው የአሠራር ሥርዐት መሠረት ተገቢው ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ከጠዋቱ 2፡ዐዐ ሰዓት እስከ ቀኑ 1ዐ፡ዐዐ ሰዓት ባለው የመደበኛ ትምህርት ሰዓት ውጪ መምህራኑ ራሳቸው ጊዜያቸውን መሥዋዕት አድርገው ራበን፣ ጠማን፣ በረደን፣ ደከመን ሳይሉ ያስተምራሉ፡፡

የማሠልጠኛው ፍሬዎች፡-
   ከዚህ የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ተመርቀው በሀገራችን እንዲሁም በመላው ዓለም በመሰማራት በሊቀ ጳጳስነት፣ መንግሥታዊ በኾኑና ባልኾኑም ተቋማት በኃላፊነት፣ በመምህርነት ወ.ዘ.ተ. ለቤተ ክርስቲያንም ኾነ ለሀገራችን ከፍተኛ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙ በርካቶች ናቸው፡፡
በዚህ ዓመትም በአብነት ትምህርት (በከፍተኛ የዕውቀት ማስረጃ) ማለትም በቅዳሴ፣ በሐዲሳት ትርጓሜ፣ በብሉያት ትርጓሜ፣ በአቋቋም፣ በድጓ እና በቅኔ 27 ደቀ መዛሙርት፤ በተከታታይ የቅዳሜ ኮርስ (ሰርትፍኬት - እነርሱ ኆኀተ ስብከት ይሉታል) ደግሞ 39 ደቀ መዛሙርት ሐምሌ 25 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. ቅዱስ ፓትሪያርኩ በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጧቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ይካሔዳል፡፡  

ማሠልጠኛው ዛሬ
     እንደሚታወቀው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም የመምህራንና ካህናት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት እንደ ሌሎች ተቋማት በገዳሙ ሥር የሚተዳደር ነው፡፡ ገዳሙ በዓመት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ከሚሰጠው የበጀት መደጐሚያ፣ ከበጐ አድራጊ ምእመናን ስጦታና ከሌሎችም አገልግሎቶች ከሚያገኘው ገቢ የገዳሙን ካህናትና የአስተዳደር ሠራተኞች ደመወዝ፣ በመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛው ለሚገኙት መምህራን ደመወዝ፣ ለተማሪዎች የወር አበል ይከፍላል፡፡ እንዲሁም ለገዳሙ አገልግሎት የሚያስፈልገውን ኹሉ ያሟላል፡፡
ከማሠልጠኛው ምን ይጠበቃል?
    የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት የቤተ ክርስቲያን አለኝታ ነው፡፡ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ አስተምሮ ያስመረቃቸው ምሁራን እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በሊቀ ጳጳስነት፣ በቤተክርስቲያን አስተዳደር የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችና አገልግሎቶች፣ በመምህርነት ወ.ዘ.ተ. በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
   እነዚህን ሊቃውንት ያፈራ ማሠልጠኛ ትናንት በነበረበት ኹኔታ ላይ ዛሬ መገኘት የለበትም፡፡ ወደፊት በርካታ ነገር ይጠብቀዋል፡፡ ዘመኑ የመረጃ በመኾኑ በባለሙያ የተጠና ሥርዐተ ትምህርት መቅረጽ፣ የተሟላ ቤተ መጻሕፍት፤ ደረጃውን የጠበቀ የተማሪዎች መማሪያ፣ መኖሪያና ማደሪያ ቤቶች ያስፈልገዋል፡፡ ለመምህራኑ የተሻለ ክፍያ በመክፈል የመማር ማስተማሩን ሒደት ወደ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋምነት ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡ 
ይህ የቤተክርስቲያንና የሀገር ባለውለታ የኾነ ት/ቤት የሀገር  ቅርስ ነው፡፡ መተኪያና መለኪያ የማይገኝላቸውን የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርቶችን በተደራጀና አስተማማኝ በኾነ መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በሀገር ውስጥም ኾነ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኹሉ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን ሙያቸውን አቀናጅተው በጸሎታቸውም ጭምር ተባብረውና ተጋግዘው ይህን የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ታሪካዊነቱን እንደጠበቀ ድጋፍ ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲያድግ ሊያደርጉት ይገባል፡፡
© ምንጭ፡- የ2007 ዓ.ም. የደቀ መዛሙርት የምረቃ መጽሔት

No comments:

Post a Comment