Pages

Monday, August 3, 2015

ሆስፒታልና ቤተ ክርስቲያን በንጽጽር ሲታዩ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.):- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እግዚአብሔር የሚወዳችሁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ልጆቼ! ተጠራርታችሁ ወደ አባታችሁ ቤት ለመምጣት ያደረጋችሁትን ቅንአት ተመልክቼ ደስ ተሰኝቼባችኋለሁ፡፡ እኔም ይህን ቅንአታችሁን አይቼ ስለ ነፍሳችሁ ጤና ይበልጥ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቀዶ ጥገና የሚደረግባት ሐኪም ቤት ናት፡፡ የሥጋ ቀዶ ጥገና ግን አይደለም፤ የነፍስ ቀዶ ጥገና ነው እንጂ፡፡ የምናክመው የሥጋን ቁስል አይደለም፤ መንፈሳዊ ቁስልን እንጂ፡፡ መድኃኒቱም ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ መድኃኒት በምድር ላይ ከሚበቅሉት ዕፅዋት የተቀመመ አይደለም፤ ከሰማያት ከሚመጣው ቃል እንጂ፡፡ ይህን መድኃኒት በቁስል ላይ ለመጨመር ሐኪሞች አያስፈልጉም፤ የሰባክያነ ወንጌል አንደበት እንጂ፡፡ ቀዶ ጥገናውን ለማከናወን ብዙ ሰዓታትን አይፈጅም፡፡ ቀዶ ጥገናው ላይሳካ ይችላል ተብሎ የሚጠረጠር አይደለም፡፡ ከጊዜ በኋላ ወይም በሌላ ሕመም ምክንያት የተደረገው ቀዶ ጥገና ሊከሽፍ ይችላል ተብሎም አይገመትም፡፡ ሐኪሞች የሚሰጡን መድኃኒት እንዲህ ዓይነት ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ሐኪሞች የሚሰጡን መድኃኒተ ሥጋ ለጊዜው ብርቱ ነው፤ ሰውነታችን እያረጀ እንደሚሔደው ኹሉ መድኃኒቱም በጊዜ ሒደት ብርታቱን እያጣ ይሔዳል፡፡ ሌላ ደዌ ዘሥጋ ሲገጥመንም መቋቋም የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም መድኃኒቱን የቀመሙት ሰዎች ስለኾኑ፡፡ ከእግዚአብሔር የሚሰጠን መድኃኒት ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ምንም ያህል ጊዜ ቢቆይም አይበላሽም፤ ጊዜው አያልፍበትም፤ ኃይሉም ብርታቱም ያው ነው አይቀንስም፡፡

ሙሴ የተቀበለው ቃለ እግዚአብሔር በጊዜው የነበሩትን ሰዎች ፈውሷቸዋል፤ አሁንም ያ ቃል ይፈውሳል፡፡ የመፈወስ ኃይሉ ብርታቱ እስከ አሁን ድረስ አላጣም፤ ሌላ ምንም ዓይነት በሽታም አላሸነፈውም፡፡ ይህን መድኃኒት ለመግዛት ብር አይበቃውም፤ ቅን ልቡና ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ በዚህ መድኃኒት ባለጸጋውም ድኻውም እኩል ይታከማሉ፡፡ ወደ ምድራዊው ሆስፒታል ሲኬድ ባለጸጋው ብር ስላለው ያሻውን ሕክምና አግኝቶ ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ድኻው ግን ብር ስለሌለው መድኃኒቱንም መግዛት ስለማይችል ሳይታከም ከነሕመሙ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ይህ ከቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው መድኃኒት ግን በብር የሚገዛ አይደለም፡፡ ይህን መድኃኒት ለማግኘት የሚያስፈልገውም ብር ሳይኾን እምነትና ምግባር ነው፡፡ እምነትና ምግባር የከፈለ ሰው ይህን መድኃኒት ማግኘት ይቻሏል፡፡ እነዚህን የከፈለ ጤናውን አግኝቶ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ በመኾኑም ድኻውም ባለጸጋውም እኩል ታክመውበት ይሔዳሉ፡፡ እንደዉም ከባለጸጋው ይልቅ ድኻው በመድኃኒቱ ይበልጥ ተጠቅሞ ይሔዳል፡፡ ለዚህስ ምክንያቱ ምንድነው? ምክንያቱም ባለጸጋው ብር ስላለው በብዙ ሐሳብ የተያዘ ነው፡፡ ሀብታም ነኝ ብሎ ስለሚያስብ ትዕቢተኛ ነው፡፡ ሕይወቱን የሚመራው በቸልተኝነት ነው፡፡ በስንፍና ስለሚያዝ መድኃኒት የኾነውን ቃሉን ለማድመጥ ስልቹ ነው፡፡ ድኻው ግን በቅንጦትና በስንፍና ኑሮ ስለማይኖር፣ ጊዜውን በእንተ ፈንቶ ነገሮች ስለማያሳልፍ መድኃኒተ ነፍሱን ለማግኘት ንቁ ነው፡፡ ቃሉን ለማድመጥ ፈጣን ነው፡፡ ቸልተኝነት አይጠጋውም፡፡ የተባለውን ለማድመጥ ልቡናው ዘወትር ዝግጁ ነው፡፡ የሚከፍለው ክፍያ ብዙ ነው ማለት ነው፤ የሚያገኘውም መድኃኒት እንደዚያ ብዙ ነው፡፡

      ይህን ኹሉ ዘርዝሬ መናገሬ ግን ባለጸጋውን ኹሉ በደፈናው መኰነኔ አይደለም፡፡ ድኻውንም ኹሉ እንደሁ ማመስገኔ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሀብት በራሱ መጥፎ አይደለም፤ መጥፎ የሚያደርገው የእኛ አጠቃቀም ነው፡፡ ድኽነቱም በራሱ በጎ አይደለም፤ በጎ የሚያደርገው የኛ አጠቃቀም ነው፡፡ ባለጸጋው ነዌ ወደ ሲዖል የተወረወረው ሀብታም ስለነበረ አይደለም፤ ጨካኝና ሰብአዊነት የማይሰማው ክፉ ስለነበረ ነው እንጂ፡፡ አልዓዛርም በአብርሃም ዕቅፍ የተቀመተው እንዲሁ ድኻ ስለነበረ አይደለም፤ ድኻም ቢኾን አመስጋኝ ስለነበረ እንጂ፡፡
      ይህን በማስተዋል ታደምጡ ዘንድ እማልዳችኋለኁ፡፡ አንዳንድ መልካም የኾነ ነገር አለ፡፡ አንዳንድ መጥፎ የኾነ ነገርም አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ መጥፎም በጎም ጎን ያለው አለ፡፡ ሀብትና ድኽነት ግን በጎም ክፉም አይደሉም፡፡ ኹለቱም በጎ ወይም ክፉ የሚኾኑት እንደተጠቃሚው ሰው ነው፡፡ ሀብታችሁ ለበጎ አድራጎት የምትጠቀሙበት ከኾነ በጎ ነው፡፡ ከዚሁ በተቃራኒ ለክፉ ግብር የምታውሉት ከኾነ ግን ክፉ ነው፡፡ ክፉ ነው ማለቴ ግን ሀብቱ በራሱ ክፉ ኾኖ አይደለም፤ ክፉ ያደረገው የእናንተው አጠቃቀም ነው፡፡ ድኽነቱም ቢኾን እግዚአብሔርን ለማመስገን የምትጠቀሙበት ከኾነ ሹመት ሽልማታችሁ ብዙ ነው፡፡ በድኽነታችሁ አመካኝታችሁ እግዚአብሔርን የምታማርሩ ከኾነ ግን ድኽነታችሁ ክፉ ነው፡፡ ነገር ግን ሀብታችሁ በራሱ በጎ ወይም ክፉ እንዳልኾነ ኹሉ ድኽነታችሁም በራሱ ክፉ ወይም በጎ ኾኖ አይደለም፡፡ በጎ ወይም ክፉ የሚያደርገው የእናንተው አያያዝ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማመስገን ወይም ማማረር የሚመነጨው ከድኽነቱ ሳይኾን ከእኛ ነው፡፡ ሀብት መልካም ነው፤ መልካም የሚኾነው ግን ኃጢአት ላልሠራበት ሰው ብቻ ነው፡፡ ድኽነትም መጥፎ ነው፤ መጥፎ የሚኾነው ግን እምነት ለሌለው ሰው ነው፡፡ እምነት የሌለው ሰው አይጠግብም፤ ዘወትር እግዚአብሔርን ያማርራል፤ ዘወትር ብስጩ ነው፤ “እግዚአብሔር ስለምን ፈጠረኝ?” እያለ ይበሳጫልና ድኽነት እምነት ለሌለው ሰው መጥፎ ነው፡፡
      ስለዚህ ባለጸጎችን እንዲሁ በደፈናው አንውቀሳቸው፤ ድኽነትንም እንዲሁ አንጥላው፡፡ መውቀስ ካለብን እነዚህን ኹለቱንም በአግባቡ የማይጠቀሙባቸው ሰዎችን ነው፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኩት ድኽነት ወይም ሀብት በራሳቸው መጥፎ ወይም በጎ አይደሉምና፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን የሚሰጠው መድኃኒት ድኻውም ባለጸጋውም እኩል ታክመውበት ይሔዳሉ፡፡ ከባለጸጋው ይበልጥ ደግሞ ድኻው፡፡ የቃለ እግዚአብሔር ጥቅሙ መድኃኒተ ነፍስ መኾኑ ብቻ አይደለም፤ ጥራቱ በጊዜ ብዛትም አይበላሽም፡፡ በሌላ በሽታ  ተጨማሪ ጉዳትን አያመጣም፡፡ በነጻ የሚታደል ነው፡፡ የድኻውም የባለ ጸጋውም ዓቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ሌላም ጥቅምም አለው፡፡ እርሱስ ምንድነው? አንድ ታካሚ ለቀዶ ጥገና ወደዚህ በመጣ ጊዜ ቁስሉ ሌላ ሰው እንዲያየው አይደረግም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ወደኾነው ሆስፒታል ብትሔዱ ግን አንድ የቀዶ ጥገና ልዩ ባለ ሙያ (Specialist) አስቀድሞ የታካሚውን ቁስል ሳያይ የቁስል ፋሻን ማድረግ አይችልም፡፡
በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ አንደኛ በአንድ ጊዜ ብዙ ሕሙማን ይታያሉ፡፡ ኹለተኛ ሕክምናው የሚሰጠው በምሥጢር ነው፡፡ የእያንዳንዱን ኃጢአተኛ ኃጢአትን በአደባባይ አንናገርም፡፡ ከዚያ ይልቅ መጀመሪያ ኹሉንም አንድ ላይ እናስተምራለን፡፡ ከዚያም እያንዳንዱ ሰው ሕሊናውን እንዲያደምጥ እናደርጋለን፡፡ ከዚያም እያንዳንዱ ሰው ካስተማርነው ትምህርት እንደ በሽታው ዓይነት የሚስማማውን መድኃኒት እያነሣ ይወስዳል፡፡ ሰባኬ ወንጌሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማንና ቀኖናን ያስተምራል፡፡ በዚያም አብሮ ክፉ ምግባርን ይገሥፃል፤ በጎ ምግባርን ያወድሳል፡፡ ዋልጌነትን ይነቅፋል፤ ንጽህናን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ ትዕቢትን ይገሥጻል፤ ትሕትናን ያመሰግናል፡፡ መድኃኒተ ሥጋ በውስጡ ሕመሙን ማከም የሚችሉ ብዙ ንጥረ ነገርን እንደያዘ ኹሉ ከሰባኪው የሚወጣው ቃለ እግዚአብሔርም እንደዚሁ ለእያንዳንዱ ሰው የሚኾን ፈውስን ይዟል፡፡ ቃሉ ኹሉም እየሰማ ይነገራል፤ ወደ እያንዳንዱ ሕሊና እንዲገባ ይደረጋል፡፡ በምሥጢርም ሕክምናውን ያከናውናል፡፡ የታማሚው ቁስል ሳይገለጥ በስውር ጤናውን ይመልስለታል፡፡ …
     
      *** ታዲያ መድኒተ ሥጋን ለማግኘት የምንፋጠነው ያህል ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር፥ ተምረንም ከመስማት ባለፈ (አጋንንትም ይሰማሉና) በተግባር መድኃኒትነቱን ተጠቅመንበታልን?





1 comment: