Pages

Saturday, September 26, 2015

መስቀል ኃይል

በልዑል ገብረ እግዚአብሔር
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 15 ቀን 2008 ዓ.ም.)፦ በስመ አብ ወወልድ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

የአዳም ነገር……
በቀራኒዮ መሐል ቀጠሮ ተይዞለታል
የገመጣት ፍሬ መዘዝ ወልዳ
ከሰገነት……...ቁልቁል ሰድዳ
ብርሃን ልብሱ ተገፎበት
ልበ ምቱ……..ቀንሶበት
ክብሩን ሊመልስለት
…….የማይሻረው ቃልን ሰጥቶታል!

የእሳት አጥር ጉድጓድ ጨለማ ቤት ሰፍፎ
ለዚህ አልነበረም…….ተፈጥሮው
በሲኦል ከተማ መጋኛ ሊመታው
ያ የሰው በኩር የፊጥኝ ታስሮ
በዲያቢሎስ ቀንበር ተቀንብሮ
እሳቱን ሲያሳርሰው በጅራፍ ጀርፎ
ባርነትን ተፈራርመው
………………..ፀጋ ልብሱን ገፍፎ ገፍፎ!

ዋይ! ዋይ! ዋይ!
የሲቃ ድምፀት ምህረት የለሹ እኩይ ግዛት
አዳም እንጂ የተጎዳ…
እበላለው ብሎ የተበላ
…………..እወጣለው ብሎ የወረደ
በፍቃዱ …….
ከግዛቱ ወደ ግዞት ተሰደደ ተዋረደ


እንቁ ክብሩን…
…በርካሽ ዋጋ ተምኖ ሸጧት… ላያገኛት!

በእጁ የሰራው አሳምሮ አርብ ያቆመው
ያ…የአርያሙ የመሬቱ ጌታ
መራራት ባህሪው አይደል…?
የፈጠረው ወዶ የሰራው
……………አዳም ከነዘር ማንዘሩ
ትእዛዝ ቃልን ማፍረሱ
…………………በሲኦል ሲማግደው!

አይንን የሰራ እኮ………ያያል
ጆሮን የተከለ ታዲያ ይሰማል
ወደር የለሽ ፍቅሩን ሊገልጽለት ቃልን ሰጠው
ማህተሙን አትሞ ሸኘው
በተስፋ ብርሃን እንዲያገኘው
……………………………በቀራኒዮ ቀጠረው

ከንፁህ ዘር ከድንግሊቱ ከልጅ ልጅ ሊወለድ
መለኮት ..ከትስብእት ተዋህዶ
ከንግስቲቱ እንበለዘር ተወልዶ
በሥጋ ታየ ወልደ አብ ወልደ ማርያም
…………..በምድር በእግረ ሥጋ ሲራመድ!

የፍቅር ተፍጻሜት ነፍስን ለጠላቱ ማዋል
ያ ፈጣሪ ጠላቱን ወደደው
ንግስናውን የተሻማ
አምላክነቱን ያሻውን
‹‹ አዳም…አዳም….አዳም››
እያለ በፍቅር ቋንቋ ጠራው
ለካ…
ሲሰራው…..ሲያኖረው
ሲሳሳት …....ሲሸኘው
ትናንት ላይ……….…..ዛሬም ይወደዋል!

ያ ሰማይ ወምድር ’ማይሸከሙት
ክብሩን ለክተው……….ማያበቁት
ከዙፋኑ ወርዶ ሰውን ፍለጋ ….
ሊያነግሱት አልመጣ ንጉስ እንጂ
ሊያከብሩት አልወረደ ክቡር እንጂ
በምድር ……..ሌላ ዙፋን ቆየው
የፍቅሩን ነገር በመስቀል ገለፀው!

ያን የወንበዴ መፋረጃ አስፈሪውን ….
በፍቅር ስለፍቅር ሞቶ በደሙ ቀደሰው
እሱ ተዋርዶ አዳም ከበረ
እሱ ተገርፎ አዳም ተካሰ
እሱ ሞቶ አዳም ህይወት ዘራ
ከቃል ሽርፍራፊ ሳይጎድል ወደ ቤቱ መለሰው
እንደ ቀድሞ ልጄ ብሎ ፀጋ ልብሱን አለበሰው!

ይኸው ፍቅር! …..ይኸው ይቅርታ!
ኩራታችን ……
ከእንግዲህ ኃይል የእኛ ነው
ሥልጣን ተገላብጧል ኃይል በስሙ ላመኑት
…………………ዲያቢሎስ በተራው ባሪያ ሆኗል
ሰው በስልጣኑ በመስቀሉ አስሮ
በእሳት አውታር……….ወጥሮ
……………………………ወደጥልቁ ይሰድደዋል!
ሰላም ለመስቀለ ክርስቶስ
ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ!


ለሚፈሩህ ምልክት ሰጠሃቸው……
ከይሴ…….ተኩላ…….እባቡን ሊያንቀጠቅጡ
የጥንቱን ጠላት የዘራውን ሊያሳጭዱት
………….በኃይለ መስቀል ወጥረው ሊቀጡ!

ኃይልን ሰጠሃቸው….
የጨለመውን ሊያበሩ የጎበጠን ሊያቀኑ
ጋኔንን ሊሰድዱ..….ህሙምን ሊያድኑ!

ሥልጣን ሰጣሃቸው……
አንተ በሞትህበት..…..በተመሰቀለው እንጨትህ
ልጆችህ ልጅ ልጆችህ…
የኃይልህ መገለጫ ደም የፈሰሰበት ልዩ ፍቅርህ
ሥልጣን ሆኗቸዋል…..ሰለጠኑበት…ዲያቢሎስን
ኃይል ሆኗቸዋል ……አየሉበት……...ፀራቸውን
መድኃኒት ሆኗቸዋል...ተፈወሱበት…ደዌያቸውን!

ያንተ ቁስል አርፎበት
………………. ደምህ ዋጋ ሆናቸው
በአርብ ሰርተህ በአርብ ተሰቅለህ
…………..በፈቃድ ሞት አዳንሃቸው
ስብሐት ለከ ክርስቶስ!

ተካሰ…...አዳም ተካሰ……..እንባው ታበሰለት
በግርፋት መኣት የተላጠው ጀርባው
ዘይት ፈሶለት ተጠግኖ
ወገቡን ያጎበጠው የአመታት እዳው ተነሳለት!

ይህ ፍቅር …ወደር የለሹ መውደድ
ለደስታ ለሐሴት በቡሩክ እጁ ያኔ ሲሰራው
አስበኝ ሳይለው….አሰበው
ፍጠረኝ ሳይለው ፈጠረው
እንዲሁ ወዶታልና…
……….…በነፃ የመንግስቱ ገዢ አደረገው!

ቀራኒዮን ሳየው….
አናቱ ላይ የቀረ አደራ…
መስቀል ተመሳቅሎ
ጽሕፈት ተጽፎበት
ቅዱስ ደም ፈሶበት
‹‹ፍቅር…ፍቅር›› ይላል ንባቡ
………በአርባ በሰማንያ ላነበበው
ጎልጎታን ተከትሎ
……..ከእግረ መስቀል ለተገኘው!

ተአምረኛ!
ያ ክርስቶስ…… ቅድመ መስቀል
…………….ላዕለ ጉንደ መስቀል
………………….ድህረ መስቀል
……….…ተአምረኛ!…………...

ሬሳ ያስነሳ………….ከዋክብት ያረገፈ
ከሞት ሃገር መቃብር ድንጋይ የገፈፈ
ተአምረኛ!
መስቀለ ክርስቶስ…. ያ ቅዱስ ቀድሶታልና
…………..በተፍፃሜተ ፍቅረ አትሞታልና
ይህ መስቀል በፈንታው
ሙት አቆመ……ህይወት ሆኖ
አይን ከፈተ……ብርሃን ሰጥቶ!

ይህን ተአምረኛ ያስጌጡታል
ከፍ ….ከፍ….ያረጉታል…..እንጂ
ቆሻሻ ገንብተው…
………………የዝቃጭ ተራራ ይሰሩበታል…?

የቅናት ልብ ባለቤቱን በግፍ ሰቅሎ
በመስቀሉ አርሮ በቅናት ተቃጥሎ
…………………………..….ይቀብሩታል….?

መስቀል ዘበአማን…
መስቀል እውነት ነው
እውነት መስቀል ነው!

እውነት እስኪገለጥ በሐሰት ይሸፈናል
ቀን ሰዓቱን ለቅሞ በክብር ይገለጣል
የሰቃዮች ተንኮል….እሌኒ እስክትመጣ
በእምነት…..ተነስታ
ፍቅረ-መስቀል ሽታ
……………..ከተቀበረበት እስክታወጣ
እሌኒ ንግስት
ሀሰሰት መስቀሎ ለክርስቶስ!

እውነትን ፈላጊ እውነትን ተመኘ
መስቀልን ፈላጊ መስቀሉን አገኘ!

ኪርያኮስ ማ …………….. ጠቆመህ …?
ቆሻሻ ፎቅ ስር ያለ የሰም እውነት
…………መስቀሉ ተቀብሮ ወርቁ ታየህ!

እንግዲህ በእልልታ ይናጋ …
በመስቀሉ ላመነ ….ኃይል መጣ
ሐሰት ቆሻሻን ገልቦ
………..ወርቅ መስቀሉ ሲወጣ!

ሃሌ …..ሃሌሉያ!
አንደበት ይከፈት ……...የምስጋና ሰዓት ነውና
እጆች ይፋተጉ ….ይላተሙ ….ያጨብጭቡ
………………………….ኃይል ለሰው ሆኗልና!

ሽብሸባ …እልልታ ….ጭብጨባ ለመስቀሉ
ስብሐት ሲደርስ..…..ይደገም ‹ይደሉ›ይበሉ
ስብሐት ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ
ይደሉ…
ስብሐት ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ!


የመስቀሉ ነገር ….ላመን ኃይላችን ነው …
የጠላትን ጦር…………ጋሻ ሆኖ ‘ሚመክት
ክንዳችን ነው …
ኃያላንን ‘ሚያደቅቅ ዱቄት አርጎ ሚሸረክት!

መስቀል ቤዛችን ….
የብሉዩ መርገም በደም የጠፋበት
በአባት እዳ…ልጅ ‘ማይጠየቅበት!

መስቀል የነፍስ መፅናኛዋ…
ሰላም ነውና…..ሰላም ‘ሚሰጣት
ሀዘኗን ሽሮ በደስታ ‘ሚያቆማት!

የመስቀሉ ነገር …
ለናቁት …ለጣሉት ሞኝነት ነው
በዓለም ላለው ጥበቡ
…………በሰማይ ዋጋ ለሌለው!

መስቀል ህይወት…
በደም አጥቦ ነፍስን የዘራበት
ለቤቱ ጽኑዕ መሰረት የሆናት!

ይኸው መስቀል…..
ኩራትህ ነው………እሰረው በአንገትህ
ውበት ይታይበት መስቀልያ አጣፍተህ!

ካህናት……..
በሰሜን……በደቡብ
በምስራቅ በምእራብ
……………………….ባርኩበት
በግፋ የቆሸሸው ዓለሙ ይንፃበት!

አንተም……..
በስመ ሥልሴ…
ግንባር ልብህ…ግራ ቀኝህን አማትብበት
የሞተልህ አሰልጥኖሃልና…
………………..ዲያብሎስን ሰልጥንበት!

የፍቅር መሻትህን
በእምነት ስትደምረው
በደመራህ ታየዋለህ
መሻትህ……
መስቀሉን ጠቁሞህ
……..ደምረው!……

ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኃቸው
ከይሴ....ተኩላ…እባቡን ሊያንቀጠቅጡት
የጥንቱን ጠላት የዘራውን ሊያሳጭዱት
በኃይለ መስቀል......ወጥረው ሊቀጡት!

ኃይልን…..ሰጠኃቸው
በመስቀሉ አዳንኃቸው
ስብሐት ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ
……..…..ዘተቀደሰ በደሙ ክቡር!………….
…………………..=//=………..………….

No comments:

Post a Comment