Pages

Tuesday, September 22, 2015

ኆኅተ ብርሃን


በዲያቆን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 11 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ኆኅተ ብርሃን ማለት የብርሃን ደጅ፣ የብርሃን መውጫ ማለት ነው፡፡ አማናዊውን ብርሃን ክርስቶስን ስላስገኘች ኆኅተ ብርሃን የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፡፡ በዚህ ጽሑፍ ብርሃን በቤተ ክርስቲያን አነጋገር ምን እንደ ሆነ እመቤታችን ኆኅተ ብርሃን የመባሏን ምስጢር እግዚአብሔር አምላክ በገለጠልን መጠን እንመለከታለን፡፡
በትውፊታችን ብርሃን የሚለውን ቃል በብዙ መልኩ ተጠቅመንበታል፡፡ በዓላትን ስንጠራ ብርሃን የሚለውን ቅጽል ከፊት አስቀድመን ብርሃነ ልደቱ፣ ብርሃኑ ጥምቀቱ፣ ብርሃነ ትንሣኤው… ወዘተ እያልን እንጠራለን፡፡ የእግዚአብሔር መላእክትን የብርሃን መላእክት (አጋንንትን የፅልመት/የጨለማ መላእክት) እንላለን፡፡ ክፉ ነገር የበዛበትን ዘመን የጨለማው ዘመን፣ በስኬት የታጀበውን ደግሞ ወርቃማው /የብርሃን ዘመን (ዘመነ ብርሃን) በማለት እንሰይመዋለን፡፡ መልካም ሥራ የሠሩ ነገሥታትንና ሹማምንትን ስማቸው ላይ ‘ብርሃን’ን እንቀጽላለን እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዚኢትዮጵያ እንድንል፡፡ ቀለምን ለመቀበል የፈጠነና የሚመረምር አእምሮ ያለውን ሰው ብሩህ (ብርሃናማ/Bright) አእምሮ አለው እንላለን፡፡ ከብርሃን ጋር ባለው ትውፊትና ሥርዓት የሰማይ ብሩህ ሕይወታችንን እንዲመስልልን ሻማን በፀሎት ጊዜ እናበራለን፡፡ በቅዱሳት ሥዕላት ላይ ቅዱሳን ሲሣሉ በብርሃን ይከበባሉ፡፡ ወይም ብርሃን ከአካላቸው ሲወጣ ይታያል፡፡  ‘ማኅቶቱ ለሥጋከ ዐይንከ ውእቱ’ (የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ናት) እንዲል ወንጌል (ማቴ.6፡22)፡፡ ዐይኑ ማየት የተሳነውን ብርሃኑን አጣ እንለዋለን፡፡ ወላጆች ልጆችን ሲወልዱ ስኬት ካገኛቸው ወይም በልጆቹ ይሳካልናል ብለው ካሰቡ የልጆቹን ስም ብርሃኑ፣ ብርሃኔ….ወዘተ ብለው ይሰይማሉ፡፡ ለመሆኑ ብርሃን ምንድን ነው?

ብርሃን በዕለተ እሑድ ከተፈጠሩ ከ8ቱ ፍጥረታት አንዱ ነው፡፡ በዕለተ እሑድ መላእክትን ፈጥሮ ማን ፈጠረን ብለው በተሸበሩበት ጊዜ ከበስተምስራቅ በኩል በብርሃን እንደ ተገለጠላቸው መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘኤጲፋንዮስ ይገልፃል፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ዕለት ከተፈጠሩት መካከል እሳት አንዱ ነው፡፡
ከላይ የተገለፀውን የብርሃን አፈጣጠር ስንመለከት ከድኅነትና ከእውቀት ጋር ማዛመድ እንደሚቻል እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ መላእክት የዕውቀት ገላጭ ፈጣሪን ሳያውቁት ቆይተው በብርሃን ተገልፆ ዐወቁት፡፡ እነርሱ መርምረውት ሳይሆን እርሱ ተገልጦ አገኙት፡፡ ሳጥናኤል “እኔ ፈጠርኳችሁ” ብሎ በኃጢአት ጨለማ ሊያጠፋቸው ሲፍጨረጨር ብርሃነ መለኮቱን ገልፆ አዳናቸው፡፡ ስለዚህ ብርሃን  መጀመሪያ ሲፈጠር ከማሳወቅና ከሃይማኖት (ከድኅነት) ጋር ነው፡፡  የእውቀት ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን  ማወቅ፣ የሃይማኖት መጀመሪያ በፈጣሪ፣ በቅድስት ሥላሴ ማመን ነውና ይህ ሆነ፡፡ ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ነው፡፡ ካለመገለጥ ክርስትና የለም፡፡ ምክንያቱም አምላክ ራሱን እንደ ችሎታችን ካልገለጠ በቀር በምርምር፣ በሥጋዊ ጥበብ እርሱን ማወቅ አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው እንደ መላእክቱ፣ እንደነ ቅዱስ ገብርኤል መጀመሪያ ማመን ይቀድማል፣ ከዛ ዕውቀትን እርሱ ይገልጥልናል የምንለው፡፡ ከዚህ በመነሣት ምንም እንኳን በትውፊታችን ብርሃንን ለብዙ በጎ ነገሮች እየቀጸልን ብንጠቀምም በዚህ ጽሑፍ የብርሃንን ዕውቀትነትና ድኅነትነት ብቻ አንሥተን የእመቤታችንን ኆኅተ ብርሃንነት በአጭሩ እናያለን፡፡
ሰው ዐውቆ እንዳይጸድቅ ዘወትር የሚታትረው የድንቁርና አባት ዲያቢሎስ አዳም በዕፀ በለስ ላይ የነበረውን ዕውቀት በማሳሳት ከነበረው ብርሃናማ ሕይወት እንደ እርሱ በጨለማ እንዲኳትን አደረገው፡፡ የሰው ልጅም ከዚያ በኋላ ባለማወቅና በኃጢአት ጨለማ ባዘነ፡፡ ‘ሕዝቤ ዕውቀትን ከማጣት የተነሣ ጠፍቷል’ እንዲል ነቢዩ ሆሴዕ፡፡  (ሆሴ.4፡6)፡፡ የሰው ሕይወቱ የጨለማ ሕይወት (የጥፋት) ተባለ፡፡ እውነተኛው ብርሃን (አዳኝ) እስኪመጣ የሰው ልጅ ጽድቁ ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ሆነ፡፡ (ኢሳ.64፡6)፡፡ ነገር ግን ንስሐውን ዐይቶ ለአዳም እንደሚያድነው ቃል የገባለት ፈጣሪ፥ እንደ ሚወርድ እንደሚወለድ ለነቢያቱ ገለፀላቸውና እነሱም ይህን ተናገሩ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ በጨለማ ውስጥና በሞት ጥላ ያለ ሕዝብ ብርሃንን አየ ሲል ተነበየ፡፡ (ኢሳ.9፡2)፡፡ ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም ‘ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት ርእየ ብርሃነ ዐቢየ’ ያለው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ)፡፡
ጨለማ ውስጥ ያለውን የሰው ዘር ሊያድንና በታላቅ መገለጥ ራሱን ሊገልጥ (ሊያሳውቅ) ለአዳም ቃል እንደገባ፣ ነቢያትን  እንዳናገረ እውነተኛው ብርሃን እግዚአብሔር (ዮሐ.1፡4፣ ዮሐ.1፡9፣ 1ኛ ዮሐ.1፡5) ወደ  ዓለም መጣ፡፡ ለብርሃን  ጨለማ አይስማማውምና ከጨለማ ከተለየች ከድንግል ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆነ፡፡ በወንጌልም “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” አለ (ዮሐ.8፡12)፤ ዓለምን ከጨለማ ጥፋት ሊያድን ተገልጧልና/ ታውቋልና፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ‘ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኩሉ ሰብእ’ (ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን) አለው፡፡ በኒቂያ የተሰበሰቡ 318ቱ ሊቃውንትም ፀሐየ ፅድቅ ክርስቶስን  ‘ብርሃን ዘእምብርሃን’ (ከብርሃን የተገኘ ብርሃን) አሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ ወካዕበ ይቤ በአፈ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም ዘያበርህ ላዕለ ጻድቃን” (በዳዊት አፍ እንደ ተነገረ ብርሃን በሆነው በእግዚአብሔር ስም የሚመጣና በጻድቃን ላይ የሚያበራ የተባረከ ነው) ያለው ስለ ክርስቶስ በተናገረበት አንቀጽ ነው፡፡ ዳዊትም አስቀድሞ  ‘ፈኑ ብርሃነከ’ ብርሃንህን ላክልኝ ብሎ ዘምሮ ነበር፡፡ መዝ. 42/43፡3-4)፡፡
ከላይ ባየነው መልኩ መጻሕፍት ሁሉ ተባብረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ ብርሃንነት ይመሠክራሉ፡፡ እርሱን አምላክ ብለን ድንግልን ወላዲተ አምላክ፣ እርሱን ጌታ እርሷን የጌታ እናት፣ እርሱን ጌታ እርሷን እመቤት፣ እርሱን አምላክ ወሰብዕ እርሷን ድንግል ወእም እንደምንለው እርሱን ብርሃን ብለን እርሷን እመ ብርሃን እንላለን፡፡ እንደውም “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐ.8፡12) እንዳለ ቅዱሳኑንም “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” (ማቴ.5፡14) ብሏልና እርሷንም ብርሃን እንላታለን፡፡ በነገረ ማርያም ትምህርት ቴክታና ጴጥርቃ ስለተባሉ ከእመቤታችን ወደኋላ 7 ዘር ስንቆጥር ስለምናገኛቸው አያቶቿ በስፋት ይነገራል፡፡ ቴክታና ጴጥርቃ ሳይወልዱ ብዙ ቆይተው በሕልም ቴክታ እንቦሳ ስትወልድ፣ እንቦሳይቱ ሌላ እንቦሳ ስትወልድ፣ እንዲህ እያሉ እስከ 6 ድረስ ይሔዱና ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ያያሉ፡፡ ሕልም ፈቺም መልካም ሴት እንደሚወልዱ፣ እርሷም ሌላ መልካም ሴት እንደምትወልድ፣ እንደዚሁ እስከ ስድስተኛዋ ደርሰው ከፍጥረታት ሁሉ የምትበልጥ እንደምትወለድ ነግሯቸው የፀሐይ  ነገርን ግን አልተገለፀልኝም ይላቸዋል፡፡ ቴክታ ዴርዴን፣ ዴርዴ ሲካርን ፣ ሲካር ቶናን፣ ቶና ሔርሜላን፣ ሔርሜላ ሐናን ይወልዱና ጨረቃ የተባለችውን እመብርሃን ሐና ከኢያቄም ትወልዳለች፡፡ ጨረቃ የተባለችው እመቤታችንም ዘእንበለ ዘርአ ብእሲ (ካለ ወንድ ዘር) ፀሐይ የተባለውን እውነተኛውን ብርሃን ክርስቶስን ወለደችው፡፡ እመቤታችን አማናዊ ፀሓይ ክርስቶስን በመውለዷ ሊቃውንት አዲሲቷ ሰማይ ብለዋታል፡፡ ስለዚህ ድንግልን የብርሃን መገኛ፣ የብርሃን ደጅ - ኆኅተ ብርሃን እንላታለን፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞንም ስለ ጨረቃነቷ ስለ ብርሃንነቷ ሲናገር “መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ ሠናይት ከመወርኅ ወብርህት ከመፀሐይ” (ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ እንደጨረቃ የተዋበች፣ እንደ ፀሐይም የጠራች ዐላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማናት?) በማለት ገልጿታል፡፡ (መኃ.6:10 )፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም “ወአንሰ እትፌሣሕ በእንቲአኪ ኦ ሀገረ እግዚአብሔር ወእትሐሰይ ብኪ ኦ ኤዶም ገነት ነባቢት እንተ ርእዩኪ ነቢያት ከመጎሕ ድልው ለወሊደ ፀሓይ በከመ ይቤ ሰሎሞን አቡኪ አይ ይእቲ ዛቲ እንተ ታስተርኢ ከመጎሕ” (እንደ ተዘጋጀ ወገግታ ነቢያት ያዩሽ የምትናገሪ ኤዶም ገነት ሆይ ደስ እሰኝብሻለሁ፣ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትታይ ይኽቺ ማን ናት? በማለት አባትሽ ሰሎሞን  እንደተናገረ) በማለት አወድሷታል፡፡ (አርጋኖን ዘሠሉስ ምዕ. 5፡10-11)፡፡ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ፡
“ ዘካርያስ ርእየ ለወርኅ ሣባጥ በሠርቁ፤
ተአምረኪ ለዘይት ማእከለ ክልኤ አዕፁቁ፤
ማርያም ጽዮን ለብርሃን ትቅዋም ወርቁ፤
ዕዝራኒ በገዳም ከመ ወአለ ውዱቁ፤
ለሕብረ ገጽኪ ጽጌ ኅተወ መብረቁ፤”
(የብርሃን የወርቅ መቅረዙ ጽዮን ማርያም ነቢዩ ዘካሪያስ በኹለቱ የወይራ አዕጹቅ መኻከል በየካቲት ወር ምልክትሽን አየ፣ ዕዝራም በምድረ በዳ ወድቆ በዋለ ጊዜ (ሱባኤ በገባ ጊዜ)፣  ጽጌ (አበባ) የፊትሽ ደም ግባት ብልጭታው በፊቱ ብልጭ አለ (አንጸባረቀ)) ብሎ በብርሃን እናትነቷ ማብራቷን መስክሯል፡፡ (ማኅሌተ ጽጌ ቁጥር 27)፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ኆኅተ ብርሃን - የብርሃን መገኛ ናት፡፡
ዐይን መብራት እንደሚባል መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ (ማቴ.6፡22)፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ሔዋንን የታወረ የዓለም ግራ ዐይን ሲላት እመቤታችንን ደግሞ በብርሃን የተሞላ የዓለም ቀኝ ዐይን ይላታል፡፡ ሔዋን ወደ ጨለማ ዓለምን ስትመራ ብርሃናማዋ ዐይን ድንግል ደርሳ ዓለምን አዳነች፡፡ (Luminous eye, Sebastain Brock P. 70-73).

አስቀድመን  የብርሃንን ድኅነትነትና ዕውቀትነት ብቻ እንደምናይ ገልፀን ነበር፡፡ በአዳም ምክንያት ካገኘን ሞት የመዳን ሥራ የተፈፀመልን በአምላካችን በክርስቶስ ሲሆን ያዳነንም ከእመቤታችን ሰው  በመሆን ነው፡፡ ስለዚህ እመቤታችን አባቶች ምክንያተ ድኂን (የድኅነት/ የመዳን ምክንያት) ይሏታል፡፡ አዳኙ ብርሃን ከእርሷ ተገኝቷልና ኆኅተ ብርሃን መባሏም ለዚህ ነው፡፡ ከዕውቀት ጋር በተያያዘም “በነገረ መለኮት እንደ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዐዋቂ የለም” ይባላል፡፡ ይህ ሐዋርያ ዕውቀቱን ከየት እንዳገኘ አባቶች ሲጠቁሙም “እነኋት እናትህ (ዮሐ.19፡20) ብሎ ጌታ ድንግልን በእናትነት ከሰጠው በኋላ ለ15 ዓመታት አስተምራው ነው” ይላሉ፡፡ እመቤታችን ከዚህም በላይ ፍጡራን ሁሉ የማያውቁትን ምሥጢር ታውቃለች፡፡ በሠሉስ ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም ላይ እንደተጠቀሰው ከጌታ ዕርገት በኋላ እመቤታችንን ሐዋርያት ‘ጌታን እንዴት እንደወለድሽው ንገሪን’ ቢሏት እርሷ ግን  ‘ይህ ምስጢር ስንኳን ልናገረው ሳስበው ይጨንቀኛል፤ ተዉ፤ አይቻላችኹም፤ የረቀቀ ምስጢር ነው፤’ አለቻቸው፡፡ እነርሱ ግን “ግድ የለም ንገሪን” አሏት፡፡ እርሷም “ጊዜው ሠለስት ነበር ቅጽረ ቤተ እግዚአብሔር ለሦስት ተከፈለ፤ ጉምና ካፊያ ኾነ፤ ወትሮ የማውቀው መልአክ ቀርቶ የማላውቀው መልአክ መጣ “ወገሰሰ ዐጽፎ ዘየማን ወኮነ ኅብስተ ሕይወት ወገሰሰ ዐጽፎ ዘፀጋም ወኮነ ጽዋዐ ሕይወት፤ ቀኝ ክንፉን ቢባርከው ኅብስተ ሕይወት ሆነ በልቶ አበላኝ ግራ ክንፉን ቢባርከው ጽዋዐ ሕይወት ሆነ ጠጥቶ አጠጣኝ ብላ   ወደ ደገኛው ምሥጢር ልትገባ ስትል መልአኩ መጥቶ ግሩም ድምጽ ቢያሰማቸው  ሁሉም ደንግጠው ወድቀዋል፡፡ “እርሷ ለበቃችው ምስጢር እናንተ አልደረሳችሁም” ሲላቸው ነው፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ድኅነትና ዕውቀት የተገኙባት ብርሃን ናትና ኆኅተ ብርሃን ትባላለች፡፡
ለዓለም  የሚያበራውን እውነተኛውን ብርሃን ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስን የሰጠችን እመ ብርሃን፣ ኆኅተ ብርሃን ድንግል ማርያም በዓለም ጨለማ እንዳንዋጥ የምልጃዋን ጨረቃ ታበራልን ዘንድ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ይሁን፡፡
ይህ ጽሑፍ መታሰቢያነቱ ለውድ የመንፈስ እናቴ ለኆኅተ ብርሃን ሰንበት ምህርት ቤቴ ይሁንልኝ፡፡

No comments:

Post a Comment