በሥርጉተ ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 07 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ሰማዕትነቱ
ቅዱስ አግናጥዮስ የአንጾኪያ ቤተ
ክርስቲያን ጳጳስ በነበረበት ወቅት ቤተ
ክርስቲያን ከዓላውያን የሮማ ነገሥታት ከፍተኛ መከራና ስቃይ ይደርስባት ነበር:: በድምጥያኖስ ዘመነ መንግሥት ከነበረው የመከራ ማዕበል በጾም እና በጸሎት፣ በብዙ መንፈሳዊ ተጋድሎ፥ በተለይም ምእመናን መከራውን ተሰቅቀው ከሃይማኖት እንዳይወጡ ተግቶ በማስተማር እንደ መልካም ካፒቴን ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መርቶ አሻግሯል:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከትሕትናው የተነሣ ስለ ራሱ ሕይወት እውነተኛ የክርስቶስ ፍቅር ላይ ገና አልደረስኩም፤ እውነተኛ የደቀ መዝሙርነት ፍጽምና ላይ አልደረስኩም እያለ ያዝን ነበር:: በመሆኑም ሰማዕትነት የበለጠ ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርብ በማመን ለሰማዕትነት ክብር እንዲበቃ በእጅጉ ይመኝ ነበር::
በሮማ መንግሥታት ዙፋን ላይ የተተካው ንጉሥ ትርያዳን በጦርነት ድል ቢቀናው ልቡ በትዕቢት ተነፍቶ፥ “ለድል ባበቁት” አማልክት ተመክቶ በግዛቱ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ለጣዖታት እንዲገዙ አዘዘ:: ለሥራ ጉዳይ ወደ አንጾኪያ ጎራ ባለበት ጊዜም የክርስቲያኖች መሪ ቅዱስ አግናጥዮስ ተጠርቶ ወደ እርሱ እንዲቀርብ ተደረገ:: ንጉሡም:- “ትእዛዛችንን የምታፈርስ ሌሎችንም በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደሉ ዘንድ እንዲሁ የምታስተምር ‘ክፉ ሰይጣን’ አንተ ማን
ነህ?” ሲል ጠየቀው:: ቅዱስ አግናጥዮስ እንዲህ ሲል መለሰለት:-“ማንም ለባሴ- እግዚአብሔርን ሰይጣን ሊለው አይገባም፤ ክፉዎች አጋንንት ከእግዚአብሔር አገልጋዮች የራቁ ናቸውና:: ነገር ግን እኔ የእነዚህ ክፉ መናፍስት ጠላት ስለሆንኩ፥ ከሰማዩ ንጉሥ ከክርስቶስ የተነሣ ክፉ አሠራራቸውን ስለማጠፋ ከእነርሱ የተነሣ ክፉ ብትለኝ እስማማለሁ”:: ንጉሡ “ለባሴ-እግዚአብሔር ማን
ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ቅዱስ አግናጥዮስ “በልቡ ክርስቶስ ያለው” ሲል መለሰለት:: ቀጥሎም ንጉሡ “ታዲያ እኛስ የፈለግነው በጦርነት ጊዜ እርዳታቸው እግጅ ደስ የሚያሰኘን እና በኅሊናችን ያሉ አማልክት በአንተም እንዲኖሩ አይደል?” ሲለው በድፍረት እንዲህ አለው፥ “የአሕዛብ ሰይጣናትን አማልክት በማለትህ ተሳስተሃል:: ሰማይና ምድርን፥ በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ የፈጠረ አንድ እግዚአብሔር፤ በመንግሥቱ በደስታ እኖር ዘንድ ተስፋ የማደርገው የአብ አንድያ ልጅ አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ አለና”:: ንጉሡ:- “በጴንጤናዊው ጲላጦስ የተሰቀለውን ማለትህ ነው?” አግናጥዮስ:- “ማለቴ ኀጢአቴን ከአስገኝዋ ጋር የሰቀለውን፤ እርሱን በልባቸው ለተሸከሙት [ለክርስቲያኖች] ሰይጣንን ከነማታለያው ከእግራቸው በታች የቀጠቀጠውን ማለቴ ነው” አለው:: በመጨረሻም ትርያዳን በመዘባበት “ታዲያ የተሰቀለውን እርሱን በውስጥህ ተሸክመሃላ!?” ሲለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‘በወንጌል አላፍርምና’ [እንደ ሰው ሰውኛ ሽንፈት የሚመስል ነገር ግን የእግዚአብሔር ኀይል የሆነ ነገረ መስቀሉን - ክርስቶስ ታመመ: ሞተ: ተሰቀለ ብዬ ማስተማርን አላፍርም] እንዳለ እርሱም በልበ ሙሉነት “አዎን እውነት ነው፤ ‘በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ’ ተብሎ ተጽፏልና” አለው (2ቆሮ. 6፥16):: ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከአንጾኪያ ወደ ሮም ተወስዶ በዚያ በስታድየም በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለአናብስት ተጥሎ እንዲበላ ትእዛዝ አስተላለፈ:: ሰማዕትነት ጥንቱንም የሚመኘው ነበርና ቅዱስ አግናጥዮስ ይህንን ፍርድ ሲሰማ በደስታ እንዲህ ሲል ጮኸ:-
“ኦ ጌታ ሆይ አመሰግንሃለሁ! በፍጹም ፍቅርህ አክብረኸኛልና ልክ እንደ ሐዋርያህ ጳውሎስ እጆቼ በብረት ሰንሰለት እንዲታሰሩ አድርገሃለና”:: እጆቹን በደስታ ለሰንሰለት ካስረከበ በኋላ በጨካኝ ወታደሮች እየተዳፋ ጉዞ ወደ ሮም ሆነ::
ሰርምኔስ እንደ ደረሰ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እግር ሥር አብሮት የተማረውን አሁን የሰርምኔስ ጳጳስ የሆነው የሚወደው ጓደኛው ፖሊካርፕስን አግኝቶ ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎች ተለዋወጡ፤ የአብያተ ክርስቲያናትን አደራም ሰጠው:: በጉዞው ወቅት ብዙ ከተሞችን እያቆራረጠ ሲሄድ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት እርሱን ለማግኘት ከየአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት ይጎርፉ ነበር:: ለእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መላእክታትን የጻፈውም በዚሁ ጉዞ ላይ ሆኖ ነው:: ሰዎች ሁሉ በየመንገዱ እየተከተሉ እርሱን ለማግኘት ሲሽቀዳደሙ እና ፍቅራቸውን ሲገልጹ ተመልክቶ ምናልባት ይህ ፍቅራቸው የተከፈተለትን የሰማዕትነት በር እንዳይዘጋበት ሰግቶ ለሮም ክርስቲያኖች እንዳይከለክሉት ጻፈላቸው:: በአድርያቲክ ባሕር በመርከብ ሲጓዝ “ፑቲዮሊስ”ን (ሐዋ. 28፥13-14) ሲያይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተመሳሳይ ታስሮ ወደ ሮም የሄደበትን የጉዞ መስመር ተከትሎ ይሄድ ዘንድ ወደደ:: ነገር ግን ማዕበል ስለ
ተነሣ በዚያ መሄድ አልተቻለም:: ሮም እንደ ደረሰ በዚያ ያሉት ወንድሞች እርሱን በማየታቸው ደስ ቢላቸውም ሊሞት ስለ
ሆነ ደግሞ አዝነው በተቀላቀለ ስሜት ሆነው ተቀበሉት:: እርሱም ካረጋጋቸው እና ለአብያተ ክርስቲያናቱ ሁሉ ከጸለየ በኋላ በሮማ ስታድየም የሚካሄደው ፌስቲባል እየተገባደደ ስለነበር ሕዝቡ ሳይበተን ለማድረስ በወታደሮች እየተቻኮለ ወደ ትያትር ቦታው ተወሰደ:: በዚያም ለአንበሶች ተጥሎ “ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች” እንደ ተባለ (ምሳ. 10፥24) የክርስቶስ ሰማዕት ለመሆን በተመኘው መሠረት ምኞቱን አገኘ:: ከአንበሶች የተረፈው ተረፈ ዐጽሙም ተሰብስቦ ለአንሶኪያ ቤተክርስቲያን ተላከላት::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለቅዱስ አግናጥዮስ ያስተማረው ትምህርት
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ትምህርት ያስተማረው የቅዱስ አግናጥዮስ መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ ለተገኙ የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ነው:: በቅዱስ አግናጥዮስ መንፈሳዊ ፍሬዎች ከመደመሙ የተነሣ የትኛውን አስቀድሞ የትኛውን እንደሚያስከትል ግራ እንደ
ተጋባ በመግለጽ ትምህርቱን ይጀምራል:: በመጀመሪያ ስለ ጵጵስናው ክብር፥ በራሳቸው በሐዋርያት ስለ መሾሙ በሰፊው ካብራራ በኋላ ቀጥሎ ስለ ሰማዕትነቱ እና ከዚህም የተነሣ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ስላገኘችው ክብር በመጨረሻም ዘወትር ወደ መቃብሩ በእምነት በመምጣት በረከት ማግኘት እንደሚገባ ያስተምራል:: ትምህርቱን በአጭሩ እነሆ::
በዚህ ቅዱስ ሰው ነፍስ ውስጥ ስላሉ እጅግ ብዙ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የተነሣ የትኛውን አስቀድመን የትኛውን እንደምናስከትል ግራ ተጋብተናል:: በመጀመሪያ የቱን እንናገር? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለቤተ ክርስቲያን መጋቢነት ባስተማረው መመሪያ መሠረት በጥንቃቄ መቆሙን? “መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል” ሲል ሰምቶ (ዮሐ. 10፥11) ይህንኑ ማድረጉን? ከሐዋርያት ጋር ቃል በቃል መነጋገሩን እና ከመንፈሳዊ ምንጮች መጠጣቱን፣ ይህንኑም በሕይወቱ በሙሉ መተርጎሙን? በመልካም ምግባራት ቆራጥና ጥንቁቅ መሆኑን . . .? ሰማዕት? ጳጳስ? ሐዋርያ? ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከእያንዳንዳቸው ሌሎች ብዙ አክሊላት የሚመነጩባቸው ሦስት አክሊላትን ደፍቶለታልና::
ለታላቁ የጵጵስና ክብር የተገባ ስለ ሆነ ብቻ አልደነቅም፤ ይህንን ሹመት ከሐዋርያት ከራሳቸው ስላገኘው፥ የከበረ ራሱንም በቅዱሳት እጃቸው በአንብሮተ እድ ስለዳሰሱት ነው እንጂ:: የሾሙት እነርሱ ስለሆኑና የበዛ የመንፈስ ቅዱስን ኀይል ስላሳደሩበት ብቻም አይደለም:: የምግባራት ሁሉ መከማቻ መሆኑን ራሳቸው ስለ መሰከሩለት ጭምር ነው እንጂ:: ይህም እንዴት ነው ያላችሁኝ እንደ ሆነ አሁን አሳያችኋለሁ:: ቅዱስ ጳውሎስ ለቲቶ ጳጳሳትን በተመለከተ ጽፎለታል:: ጳውሎስ ስል ስለ እርሱ ብቻ መናገሬ አይደለም፤ ስለ ጴጥሮስ፣ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ ዮሐንስ እና ስለ ሌሎችም ሐዋርያት ነው:: ሰዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም ትምህርታቸው አንድ ነው፤ አስገኚው እና መንፈሳቸውን የሚያነቃቃ መንፈስ ቅዱስ አንድ ስለ ሆነ:: ታዲያ ጳውሎስ ጳጳስ ምን አይነት ሰው መሆን እንዲገባው ለቲቶ ሲጽፍ እንዲህ አለ:- “ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና” (ቲቶ. 1፥7-9):: ለጢሞቲዎስም እንዲሁ ጽፎለታል:- “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው።እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን።በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል”(1 ጢሞ. 3፥1-7):: ቅዱስ ጳውሎስ ከጳጳሳት ምን ያህል የምግባር ጥንቃቄ እንደ ፈለገ አያችሁ? የንጉሥን ምስል በጥንቃቄ እንደሚስል እንደ አንድ ጎበዝ ሰዓሊ:: ያ ከእርሱ የሚቀዱ ስዎች ሁሉ በትክክል ኮፒ እንዲያደርጉ ብዙ የተለያዩ ቀለማትን ቀይጦ ንድፍ እንደሚሰራ ጳውሎስም የአንድን ጳጳስ ባሕርይ ከብዙ ምግባራት ቀይጦ ትክክለኛ ንድፍ ሠራ:: አግናጥዮስ የዚህን ንድፍ ሁሉንም ክፍል በመያዝ በሕይወቱ በትክክል የተረጎመ ነው:: ለዚህም ማረጋገጫችን እነዚህን ነገሮች የተናገሩት፥ ሌሎችም ጳጳሳትን ሲሾሙ እንዲህ አይነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያስተማሩ ሐዋርያት ራሳቸው ቅዱስ አግናጥዮስን ስለ ሾሙት ነው:: እነርሱ ራሳቸው በእነዚህ ነገሮች ቸልተኛ ሆነው የማይገባውን ሰው ሊሾሙ ስለማይችሉ:: እነዚህ ሁሉ ምግባራት በዚህ ሰማዕት ነፍስ ተተክለው ባያዩ ለዚህ አገልግሎት ባልመረጡትም ነበርና:: ስለዚህም ጳውሎስ የማይገባውን ሰው ፈጥኖ የሚሾም በኋላ ተሿሚው ሰው ለሚያደርሰው ጥፋት በሙሉ ተጠያቂ እንደሚሆን ሲያስጠነቅቅ ጢሞቴዎስን “በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፥ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር” ብሎታል (1ጢሞ.5፥22)::
ሌላው ከጵጵስናው የሚገኝ አክሊል በዚያ አስቸጋሪና የስቃይ ዘመን ተሾሞ በጥበብ እና በብቃት ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደሩ ነው:: ብዙ ሰዎች በተመላለሱበት መንገድ መሄድና ማንም ባልሄደበት ባልተመነጠረ ጫካ ውስጥ መሄድ የተለያዩ እንደሆኑ ሁሉ በአሁን ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደርና በእርሱ ዘመን ማስተዳደር አንድ አይደለም:: አሁን ምእመናንን ለማሳመን ብዙ ጉልበት አይጠይቅም፤ ያን ጊዜ ግን ክርስትና ለብዙዎች ገና አዲስ ትምህርት ስለሆነ ለማሳመንም ለማጽናትም ከባድ ትግልን ይጠይቃል:: በዚያ ላይ ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ ከውጪ በዓላውያን ጣዖታውያን ነገሥታት ከፍተኛ መከራ ነበረባት:: ከጵጵስናው የተገኘ ሌላው አክሊል በታላቋ ከተማ አንጾኪያ መሾሙ ነው:: እጅግ ብዙ ምእመናን ያሉባት እግዚአብሔር ብዙ ሥራዎች የሠራላት ልዩ ከተማ ናት:: ለምሳሌ የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ የተሰጠው የዓለም መሪ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህች ከተማ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ አድርጓል:: ጴጥሮስ ከተነሣ ዘንድ ሌላ አክሊል ትዝ አለኝ:- በጴጥሮስ ወንበር የተተካ መሆኑ:: ጴጥሮስ ሲሄድ ጴጥሮስን የመሰለ ተተካ፤ ዓለቱ ሲሄድ መሠረቱ እንዳይናጋ ሌላ መሠረት ተተካ::
ሌሎች ብዙ አክሊላት ቢኖሩም ስለ ጵጵስናው ክብር ብቻ ስንነጋገር የሰማዕትነቱ ነገር እንዳያመልጠን ወደዚያው እንለፍ:: በወቅቱ በቤተ ክርስቲያን ጽኑ መከራ ነበረ፤ ክርስትያኖች ሊያሸልሟቸው፣ ሊያስከብሯቸው እና ሊደነቁባቸው ስለሚገቡ ሥራዎቻቸው ይቀጡና ይሰቃዩ ነበር:: ዲያብሎስ በነገሥታት አድሮ በተለይ ጳጳሳትን ያስገድል ነበር፤ ከሰው ተለይተው በረጅም ጉዞ እንግልት እንዲደክሙ ወደ ሩቅ ሀገር ተወስደው እንዲገደሉ ያደርግ ነበር:: በዚሁ ምክንያት አግናጥዮስን ከአንጾኪያ ሮም እንዲወሰድ አደረገው:: ክርስቶስ አብሮት እንደሚሰደድ አብሮት እንደሚጓዝ ባለማወቅ በብቸኝነት: በጉዞ ድካም: በቀናት ብዛት ልቡ እንዲዝል ዲያብሎስ ይህን አደረገ:: ነገር ግን አብያተ ክርስቲያናት በጉዞው በአንድነት ተሰበሰቡ:: በሩጫ ውድድር ጊዜ ደጋፊዎች አብረው እያሯሯጡ አትሌቶችን እንደሚያበረታቱ ሁሉ በጉዞው ወቅት በየመንገዱ ያሉ ከተሞች በሚያስፈልገው ሁሉ እየረዱ በጸሎት እና ምልጃ አበረታቱት:: ሰማዕት ለመሆን ካለው ዝግጁነትና ደስታ የተነሣ ጉዞው ከዚህ ዓለም ወጥቶ ወደ ሰማያት ለመውጣት የሚደረግ ረጅም ጉዞ እንጂ የሞት ጉዞ አይመስልም ነበር:: ይህም ለምእመናን ታላቅ መጽናኛ ነበር:: በሮም ብቻ ሳይሆን በየመንገዱ ላሉ ከተሞች እንደ ፀሐይ ከምሥራቅ (አንጾኪያ) ወጥቶ ወደ ምዕራብ (ሮም)፥ ቁሳዊ ሳይሆን ጨለማ የማይጋርደው መለኮታዊ ብርሃንን እያበራ ይሄድ ነበር:: ሞቱ ለመላው ሮም አስተማሪ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መጨረሻውን በዚያ አደረገ:: ከእርሱም በፊት ጴጥሮስና ጳውሎስ በዚሁ ሰማዕት እንዲሆኑ አደረገ:: አንድም በጣዖታት የረከሰችው ምድር እንድትቀደስ አንድም ሥራቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ምስክር እንዲሆን:: ሰማዕታት ሀገራቸውን፣ ዘመዶቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውን፣ ቤት ንብረታቸውን ትተው፣ የዚህ ዓለም ሕይወትን ራሱ ንቀው ከደስታ ይልቅ መከራን መምረጣቸው ክርስቶስ ከሞት በኋላ ያለውን ኀይል ያስረዳል:: በመላዋ ሮም የሚኖሩ ሁሉ የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት እንደሆነ ያውቁ ዘንድ ሞቱን በስውር ስፍራ ሳይሆን በአደባባይ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደረገ:: ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ተለየ፤ በበለጠ ክብር እንደገና አገኛችሁት:: ጳጳስ ልካችሁ ሰማዕት ተቀበላችሁ:: በእንባ ላካችሁት: ከብዙ አክሊላት ጋር ተቀበላችሁት:: ዓጽሙ ከሮም ሲመጣ የነበረው ደስታ ምን እንደሚሆን እስኪ አስቡት . . . ጎበዝ አትሌት አሸንፎ ሲገባ እንደሚደረገው አቀባበል፤ በትክሻቸው ተሸክመው በከተማው እንደሚያዞሩት::
ዛሬ ብቻ ሳይሆን ዘወትር ወደ እርሱ እየመጣን ከመፈሳዊ ፍሬዎቹ እንልቀም:: ዓጽሙን መቃብሩን በመሳለም በምልጃው በረከት ለመጠቀም በእምነት እንቅረብ:: የኤልሣዕ መቃብር ሙት ካስነሣ ይልቁንም ጸጋ በበዛበት በዚህ ዘመን የአግናጥዮስ ከዚህ የበለጠ ተአምር እንዴት አያደርግ:: የቅዱሳን ዓጽማቸው ብቻ አይደለም መቃብራቸውም መንፈሳዊ ጸጋን የተመላ ነው:: ስለዚህ እለምናችኋለሁ በሕመም፣ በችግር፣ በማንኛውም ሁኔታ ያላችሁ፣ በጥልቅ ኀጢአት ውስጥ ያላችሁ ወደ እርሱ በእምነት ኑ፤ ሁሉንም ያስወግድላችኋል መቃብሩን በማየት ብቻ በብዙ ደስታ ትመለሳላችሁ::
እኛንም በአማላጅነቱ የምንጠቀም ያድርገን አሜን!!!
ምንጮች:-
Ø ሃይማኖተ አበው
Ø ስንክሳር
Ø ANF01: The Apostolic Fathers with Justin Martyr and Irenaeus
NPNF1-09:
St. Chrysostom: On the Priesthood; Ascetic Treatises; Select Homilies and
Letters; Homilies on the Statutes
ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ መንግስተሰማያትን ያውርስልን የአገልግሎት ዘመንዎን እግዚአብሔር አምላክ ይባርክልን፡፡
ReplyDeleteAmen
ReplyDeleteAmen
ReplyDeleteለሂወት ያሰማለን
ReplyDelete