Monday, December 28, 2015

ስለ በርለዓም ሰማዕት



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 18 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
    በርለዓም ሰማዕት በዲዮቅልጥያኖስ ጊዜ በአንጾኪያ የነበረ እጅግ ጥቡዕ ክርስቲያን ነው፡፡ መምለክያነ ጣዖት ለጣዖት ይሠዋ ዘንድ ባስገደዱት ጊዜ ያሳየው ጽናት እስከ ምን ድረስ እንደ ኾነ፣ የዲያብሎስ የማታለል ሥራ እንዴት በየጊዜው እንደሚቀያየር፣ ሊቁ ያስተምራቸው የነበሩት ምእመናንም ከዚህ ሰማዕት ምን ሊማሩ እንደሚገባቸው ሰማዕቱ ወዳረፈበት መቃብር ወስዶ ያስተማራቸው ነው፡፡ መታሰቢያዉም እ.ኤ.አ. ሕዳር 19 ነው፡፡
† † †

     (1) ዛሬ ንዑድ ክቡር የሚኾን በርለዓም ወደ ቅዱስ በዓሉ ጠርቶናል፡፡ ነገር ግን እንድናመሰግነው አይደለም፤ እንድንመስለው ነው እንጂ፡፡ ሲያመሰግን እንድንሰማውም አይደለም፤ የደረሰበትን ቅድስና ዐይተን እርሱን መስለን እዚያ የቅድስና ማዕርግ ላይ እንድንደርስ ነው እንጂ፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ወደ ሥልጣን ሲወጡ ሌሎች ሰዎች ልክ እንደ እነርሱ ታላላቅ ኾነው ማየትን በፍጹም አይወዱም፤ ቅንአት ውስጣቸውን ይተናነቃቸዋል፡፡ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ፍጹም ተቃራኒ ነው እንጂ፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት ክብራቸውን ከምንም በላይ ከፍ ብሎ የሚያዩት ደቀ መዛሙርቶቻቸው እነርሱን አብነት አድርገው ከእነርሱ በላይ የተሻሉ ኾነው ሲመለከቱአቸው ነው፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ሰማዕታትን ማመስገን ቢፈልግ እነርሱን ሊመስል ይገቧል፡፡ አንድ ሰው የእምነት አትሌቶችን ማሞገስ ቢፈልግ እነርሱን መስሎ ምግባር ትሩፋትን ሊሠራ ይገቧል፡፡ ይህ ነገርም እነርሱ ካገኙት ሹመት ሽልማት በላይ ሰማዕታቱን ደስ ያሰኛቸዋል፡፡ በእርግጥም ያገኙትን ሹመት ሽልማት ከምንም በላይ የሚያጣጥሙትና የተሰጣቸው ክብር ምን ያህል ታላቅ እንደ ኾነ የሚገነዘቡት እኛ እነርሱን መስለን የሔድን እንደ ኾነ ነው፡፡ ይህንንም በማስመልከት ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ የተናገረውን አድምጡ፤ እንዲህ ያለውን፡- “እናንተ በጌታችን ጸንታችሁ ብትቆሙ አሁን እኛ በሕይወት እንኖራለን” /1ኛ ተሰ.3፥8/፡፡ ከዚህ በፊትም ብፁዕ ሙሴ እንዲህ ብሏል፡- “አሁንም ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር ትላቸው እንደ ኾነ ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ” /ዘጸ.32፥32/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “እነርሱ ከተጎዱ የእኔ ክብር ምንም አይደለም፤ የምእመናን ሙላት ማለት የአካል መገናኘትም ነውና፡፡ ታዲያ ራስ የሕይወት አክሊልን አግኝቶ እግር ቢቀጣ ምን ጥቅም አለው?”

     (2) “ጊዜው የስደት ጊዜ አይደለም፡፡ ታዲያ አሁን ሰማዕታትን ልንመስላቸው የምንችለው እንዴት ነው?” ብላችሁ ጠይቃችኋል፡፡ አዎ! የስደት ጊዜ እንዳልኾነ ዐውቃለሁ፡፡ የስደት ዘመን ባይኾንም የሰማዕትነት ዘመን ግን ነው፡፡ በዘመነ ሰማዕታት እንደ ነበረው ዓይነት የተጋድሎ ጊዜ አይደለም፤ ነገር ግን የአክሊል የሽልማት ጊዜ ነው፡፡ ሥጋውያንና ደማውያን ሰዎች በማሳደድ ሥራ ላይ አይደሉም፤ አጋንንት ግን ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ዐላውያን ነገሥታት ክርስቲያኖችን እያሳደዱ አይደሉም፤ ከማንኛውም ዐላዊ ንጉሥ የከፋው ዲያብሎስ ግን ብዙዎችን እያሳደደ ነው፡፡ ከፊት ለፊታችሁ የተቀጣጠለ እሳት ላታዩ ትችላላችሁ፤ የፍትወት እሳት ግን እያያችሁ ነው፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት በሚንቀለቀል እሳት ላይ ተጨመሩ፤ በኣፍአ በሚታየው የእቶን እሳት ላይ ተጣዱ፡፡ ከተናጣቂዎችና ከጨካኝ የበረኻ አውሬዎች ጋር ተጋደሉ፡፡ እጅግ መራራ መከራዎችን ታገሡ፡፡ በእናንተ ልቡና ውስጥ ያበጠውን ክፉና ክርስቲያናዊ ያልኾኑ ሐሳቦችን ድል አደረጉ፡፡ እነዚህን ቅዱሳን ሰማዕታት የምትመስሉአቸው በዚህ መንገድ ነው፡፡ “ሰልፋችን ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር ከክፋትም መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” /ኤፌ.6፥12/፡፡ ፍትወት እሳት ነው፤ ያውም የማይጠፋና ዘወትር የሚኖር እሳት! ፍትወት ማለት እንደ ተበከለና ዕብድ ውሻ ነው፡፡ ምንም ያህል ከእርሱ እንሽሽ ብትሉም ኹልጊዜ ወደ እናንተ ፈጥኖ ይመጣል፤ ይህን ማድረጉም መቼም መች አያቋርጥም፡፡ የእቶን እሳት ክፉ ነው፤ የፍትወት እሳት ግን ከእቶን እሳት ይልቅ አረመኔ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ውስጥ የተኩስ ማቆም ስምምነት የሚታሰብ አይደለም፡፡ በሕይወተ ሥጋ እስካለን ድረስ ከዚህ ውጊያ ውጪ ኾኖ መኖር የሚገመት አይደለም፡፡ ዘወትር ውጊያ አለ፡፡ ይህ የሚኾነውም ሽልማቱም ታላቅ ይኾን ዘንድ ነው፡፡ ብፁዕ ጳውሎስ ኹልጊዜ የሚያስታጥቀንም ለዚሁ ነው፤ ውጊያው ኹልጊዜ ስለ ኾነ - ጠላት ኹልጊዜ ንቁ ስለ ኾነ፡፡
     (3) ፍትወት ከእሳት ባልተናነሰ መልኩ እንደሚያቃጥል መማር ትወዳላችሁን? ሰሎሞንን አድምጡት፤ እንዲህ ያለውን፡- “በፍም ላይ የሚሔድ እግሮቹ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሳይቀጣ አይቀርም” /ምሳ.6፥28-29/፡፡ እንግዲህ የፍትወት እሳት ከተፈጥሮ እሳት ጋር እንደሚነጻጸር ታያላችሁን? እሳትን የሚነካ ሰው ሳይቃጠል መመለስ አይቻለውም፡፡ የቆነጃጀትን ፊት ዐይቶ የሚመኝ ሰውም ከዚያ እሳት በላይ ነፍሱን ያቃጥላል፡፡ አንድን ሰው በዝሙት ዓይን መመልከት ለሰውነት እንደ ላምባ (እንደ ጋዝ) ነው፡፡ ስለዚሁ ምክንያት እኛም የዚህ ዓለም ነገሮችን በዚህ መልኩ ልንመለከታቸው አይገባንም፤ የፍትወት ነዳጆች ናቸውና፡፡ ከዚያ ይልቅ በንጹህ ሐሳብ በመያ’ዝ፣ ከዚህም በላይ፥ የሚቀጣጠለውን እሳት በመግታት የልቡናችንን ጽናት እንዳያነዋውጽብን በኹሉም ረገድ ልንጥለውና ልናጠፋው ይገባናል እንጂ፡፡ እንደ እውነቱ ከኾነ፥ ፍትወት በሚመጣበት ጊዜ አንድ ሰው እያንዳንዱን ፍላጎቱን በትዕግሥትና በእምነት ኾኖ መጋደል ካልቻለ ልቡናው ከኣፍአዊ እሳት በላይ (በፍትወቱ) ይቃጠላል፡፡ የክርስቶስ አትሌት የሚኾን ተወዳጅ በርለዓምም ያደረገው ይህንን ነው፡፡ በቀኝ እጁ ላይ የእሳት ክምር ቢመለከትም ትኩረቱን ስቃዩ ላይ አላደረገም፤ ከሐወልታት ይልቅ ጸንቶ ቆመ እንጂ፡፡ ስቃዩ ተሰምቶታል፤ ሕመሙ ተሰምቶታል፡፡ ምክንያቱም ሰውነቱ ስቃይና ሕመም የሚስማማው እንጂ ብረት አይደለምና፡፡ ነገር ግን ስቃዩን ናቀው፡፡ ሕመሙን ናቀው፡፡ በመዋቲው ሰውነቱ እንደ ኢ-መዋትያን ኃይላት ኾነ፡፡
     (4) ታሪኩ ይበልጥ ግልፅ እንዲኾንላችሁ ግን፥ የሰማዕትነቱን ነገር ከመጀመሪያው አንሥቶ ከዚህ ጋር እያያዝኩኝ እነግራችኋለሁ፡፡ የዲያብሎስ ተንኰልንም በደንብ ታስተውሉት ዘንድ እለምናችኋለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹን ቅዱሳን ወደ እሳት ጕድጓድ ጣላቸው፤ አንዳንዶቹንም ከእሳትም ወደ ከፋ ወደ ፈላ ውኃ ውስጥ ጨመራቸው፡፡ አንዳንዶቹንም ጀርባቸውን ገረፋቸው፤ ሌሎቹን ወደ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፡፡ አንዳንዶቹን ለበረኻ አውሬ ሰጣቸው፤ ሌሎቹንም ወደ እቶን ጨመራቸው፡፡ አንዳንቹን ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው፤ ሌሎቹንም ገና በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ቆዳቸውን ገፈፋቸው፡፡ አንዳንዶቹ ላይ በደም በጨቀየ ሰውነታቸው ላይ ፍም ጨመረባቸው፤ ሌሎቹንም በቆሰለው ሰውነታቸው ላይ ከበረኻ አውሬ ይልቅ ጨክኖ በስለት አሰቃያቸው፡፡ ሌሎቹንም እጅግ የሚዘገንን ስቃይን አበዛባቸው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ይህን ኹሉ ስቃይ እንደ ናቁት ባየና ድል እንዳደረጉት በተመለከተና በዙሪያ ስቃያቸውን ለሚያዩ ሰዎችም ይበልጥ ብርታትን እንደሚሰጡአቸው ባስተዋለ ጊዜስ ምን አደረገ? አዲስ የማታለያ ዘዴን ፈጠረ፡፡ ይኸውም ተሰምቶ የማያውቀውና ያልተለመደው ስቃይ ልቡናውን ያነዋውጸው ዘንድ አስቦ ነው፡፡ “አሃ! ይህ ዓይነቱ ስቃይ ከዚህ በፊት የተደረገና የሚቻል ነው፡፡ ምንም እንኳን ስቃዩ ከባድ ቢኾንም፥ ከዚህ በፊት ስለ ሰማው እንደ ኢምንት በመቍጠር ንቆታል፡፡ ይህ አዲሱ ግን ያልተለመደና ከዚህ በፊት ያልተሰማ ስለ ኾነ ቀላል ቢኾንም እንኳን ከምንም በላይ የማይችለው ነው፡፡ ስለዚህ የውጊያው ስልት አዲስ ይኹን፡፡ ሴራው እንግዳ ይኹን፡፡ ይህ የኾነ እንደ ኾነም በአዲሱና በእንግዳው መከራ አትሌቱን አነዋውጾ ማሸነፍ ይቻላል፡፡”
     (5) እናስ ምን አደረገ? ቅዱሱ ከታሰረበት ወኅኒ ቤት እንዲወጣ አደረገ፡፡ በእርግጥ ይህን ያደረገው ስለ ተንኰሉ ነበር፡፡ ገና ከመጀመሪያው አንሥቶ ውጊያዉን አላከበደበትም፡፡ እጅግ የሚሰቀጥጡ ስቃዮችን ከመነሻው ጀምሮ አላደሰበትም፡፡ ቀላል ቀላል የኾኑ ጥቃቶችን አደረሰበት እንጂ፡፡ ስለ ምን ምክንያት? እነዚያ የሚጋደሉ ድል ተደርገው ቢኾን ሽንፈታቸው ያሳፍር ነበር፤ ቀላሉን መሰናክል እንኳን ማለፍ አልቻሉምና፡፡ በጥቃቅኑ ፈተና ሰይጣንን እየካዱና ድል እያደረጉት ቢመጡ ግን ከባድ ፈተና ሲገጥማቸው በቀላሉ ድል ይደረጋሉ፡፡ በመኾኑም ቀላሉን መሰናክል መጀመሪያ አመጣባቸው፤ ይችላቸው ወይም አይችላቸው እንደ ኾነ ያውቅ ዘንድ፤ እንዳያመልጡት አስቦ፡፡ “በዚህ ድል ያደረግኳቸው እንደ ኾነ እሳለቅባቸዋለሁ፡፡ ድል ባላደርጋቸውም ግን ቢያንስ ሊመጣ ካለው አዳክማቸዋለሁ፡፡” ስለዚህም ከወኅኒ ቤት አስወጣው፡፡ በርለዓም ግን ብዙ ጊዜ በትግል ትምህርት ቤት እንደ ተለማመደ ብርቱ አትሌት ኾነ፡፡ ለሰማዕቱ ወኅኒ ቤቱ እንደ ትግል ትምህርት ቤት ነበር፡፡ እዚያ ቦታ በኅቡእ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር የውጊያ ስልቶችን ከእርሱ ይማር ነበር፤ በእንደዚህ ዓይነት ወኅኒ ቤት ውስጥ ክርስቶስም አብሮ አለና፡፡
     (6) በመኾኑም በወኅኒ ቤቱ ረጅም ጊዜ ስለ ቆየ እጅግ ብርቱ ኾኖ ወጣ፡፡ ከወጣም በኋላ ዲያብሎስ በጭፍሮቹ አማካኝነት ወደ አደባባይ አወጣው፡፡ ይህን ሲያደርግም በካቴና አላሰረውም፡፡ የሞት ፍርዱን የሚያስፈጽሙ ሰዎችንም በዙሪያው አላሰማራም፡፡ ምክንያቱም በርለዓም እነዚህን ነገሮች እንደ ናፈቀ ዐይቷልና፤ ጭፍሮቹንም ለብዙ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ሲያለማምዳቸው ነበርና፡፡ ከወኅኒ ቤቱ ይልቅ ወደ ሰገነት አወጣው - ለየት ያለና እንግዳ፣ እንዲሁም ምንም ያልተጠበቀ የስቃይ ዘዴ! በቀላሉ ሊጥለው ፈልጎ ነው፡፡ ዲያብሎስ በቅዱሳን ላይ የሚያደርገው እንደዚህ ነው፡- ከሚያደርስባቸው ስቃይ በላይ እነርሱን ማነዋወጽ! ከዚያስ ተንኰሉ ምን ነበር? ከጣዖቱ መሠዊያ በላይ የእጅ መዳፉን ወደ ላይ አድርጎ እንዲዘረጋ አዘዘና ወታደሮቹም በእጁ ላይ እሳትንና ዕጣንን እንዲጨምሩበት አደረገ፡፡ ይኸውም በርለዓም እሳቱ ሲያቃጥለው የእጁን መዳፍ ወደ ታች እንዲገለብጥና ለጣዖት መሥዋዕት እንዳቀረበ እንዲቈጥረው፣ በዚያም (በርለዓም) እንደ በደለ እንዲያስብ ነው፡፡ ዲያብሎስ ምን ያህል ተንኰለኛ እንደ ኾነ ታያላችሁን? መልካም! “ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል” የተባለው እግዚአብሔር ደግሞ ተንኰሉን እንዴት ኃይል አልባ እንደሚያደርግበት ተመልከቱ /ኢዮ.5፥13/፤ የተንኰሉ ብዛትና ዓይነት ለሰማዕቱ እንደ ምን የበዛ ክብርን እንዲጨምርለት እንደሚያደርግለት ዕዩ፡፡ ተቃዋሚዎቹ ለመቍጠር የሚታክት የተንኰል ሥራ በአንድ ቅዱስ ላይ ቢያደርሱ ተሸንፈው ይሔዳሉ፤ እርሱ ግን ይበልጥ ከፍ ከፍ ይላል፡፡ አሁንም የኾነው እንደዚህ ነው፡፡ ንዑድ ክቡር የሚኾን በርለዓም ከብረት እንደ ተሠራ ኾኖ እጁ ምንም ሳይንቀሳቀስና ሳይገለበጥ ቆመ፡፡ እጁ ተገልብጦ ቢኾኖ ኖሮ እንኳን ሰማዕቱ ለጣዖት መሥዋዕትን ሠዋ አንለውም፡፡
     (7) እዚህ ጋር በደንብ ታዳምጡኝ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ እጁ ተገልብጦ ቢኾን ኖሮ እንኳን ድርጊቱ እንደ ሽንፈት አይቈጠርም ነበር፡፡ ለምን? ጀርባቸውን ተገረፉ፤ ወይም በሌላ መንገድ ተሰቃዩ ባልናቸው ቅዱሳን ላይ የተናገርነውን እዚህም ላይ እንደግመዋለን፡፡ ወደ ጣዖት ቤቱ ገብተው መሥዋዕት ቢያቀርቡ ኖሮ ችግሩ የእነርሱ ነው ማለት በቻልን ነበር፤ ስቃዩን ሊታገሡ ባለመቻላቸው ሠዉ ማለት በቻልን ነበር፡፡ በስቃዩ ጸንተው ቢቆሙና በሚደርስባቸው መከራ ቢያቃስቱና ሃይማኖታቸውን ባይክዱ ግን አቃሰቱ ብሎ ሊወቅሳቸው የሚችል ማንም የለም፡፡ ምንም እንኳን በስቃይ ውስጥ የነበሩ ቢኾኑም ጸንተዋልና - እምነታችንንም አንክድም ብለዋልና እንቀበላቸዋለን፤ ይበልጥም እናደንቃቸዋለን፡፡ እዚህ ላይም፥ ብፁዕ የሚኾን በርለዓም የእሳቱን ቃጠሎ ሳይታገሥ ቀርቶ መሥዋዕትን ቢያቀርብ ኖሮ ድል ተደረገ ባልነው ነበር፡፡ ነገር ግን ላቅርብ ብሎ ሳይኾን በቃጠሎው ምክንያት እጁ ቢገለበጥ ችግሩ የሰማዕቱ የራሱ አይደለም፡፡ ይህ የኾነው በልቡናው ድክመት ሳይኾን በነርቩ ድካም የተነሣ ነውና፤ እጁ ሳይታዘዝለት ቀርቶ በመታጠፉ ምክንያት የኾነ ነውና፡፡ ይኸውም ጀርባቸውን የተገረፉ ቅዱሳን ቆዳቸው ቢገፈፍ እንደማንወቅሳቸው ማለት ነው፡፡ እስኪ ቀረብ የሚል ሌላ ምሳሌ መስዬ ላስረዳችሁ፡፡ በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቢያንቀጠቅጣቸውና እጃቸው ዝልፍልፍ ቢል ማንም አይወቅሳቸውም፤ ይህ የኾነው ከእነርሱ ድክመት ሳይኾን ከበሽታው ባሕሪይ የተነሣ ነውና፡፡ ልክ እንደዚሁ ይህ ቅዱስም እጁን ቢገለብጥ ማንም የሚወቅሰው የለም፡፡ ወባ እንኳን የታማሚውን እጅ እርሱ ሳያስበው እንዲዝለፈለፍና እንዲጠመዘዝ የሚያደርግ ከኾነ፥ ሰማዕቱ ወዶና ፈቅዶ ባያደርገውም በእጅ መዳፍ ላይ የተቀመጠ የሚነድ እሳት ደግሞ ይበልጥ እንዲህ ያደርጋል፡፡
     (8) ይህን ቢያደርጉበትም ግን አልተቻላቸውም፡፡ ይኸውም፥ የእግዚአብሔር ቸርነት አትሌቱን ልታበረታው ከእርሱ ጋር እንደ ነበረች፣ በእርሱ ላይ ጉዳት የሚያደርሰው ነገር ለእርሱ ጥቅም ያደርግለት እንደ ነበር ትማሩ ዘንድ ነው፡፡ በመኾኑም በዚህ መልኩ አልተሰቃየም፤ ንቅንቅ እንደማይል ግንብ ኾኖ ምንም ሳይገለበጥ ጸና እንጂ፡፡ በዚያ ሰዓት ይህን እያዩ የማይደነቁ እነማን ናቸው? የማይንቀጠቀጡስ እነማን ናቸው? መላእክት ከላይ ኾነው ይህንን ዐዩ፤ ሊቃነ መላእክትም እንደዚሁ ተመለከቱ፡፡ ሰዎች እንደዚህ ሲጋደሉ፥ ነገር ግን እንደ ሰውነታቸው ባሕርይ ምንም ሳይሰቃዩ ሲቀሩ ማየትን የማይወድ ታዲያ ማን ነው? አንድ ሰው ብቻዉን ምሥዋዕ፣ መሥዋዕትና መሥዋዕት አቅራቢ ሲኾን ማየትን የማይወድ ማን ሰው ነው? ከዚያ የሚወጣው ጭስ ኹለት ዕጥፍ ነበር - ከዕጣኑና ከሰውነቱ ቃጠሎ የተነሣ፡፡ ኹለተኛው ግን ከመጀመሪያው ይልቅ ደስ ያሰኛል፤ ከአንደኛው ይልቅ መዓዛው ያውዳል፡፡ በሐመልማላዊቷ ዕፅ የኾነውም ልክ ይህን ዓይነት ነበር /ዘጸ.3/፡፡ ምክንያቱም ሐመልማሏ ውስጥ ነበልባል ነበር፤ ሐመልማሏን ግን አላቃጠላትም፡፡ እዚህም ላይ ልክ እንደዚሁ ነው - እጁ ይቃጠል ነበር፤ ነፍሱን ግን አላቃጠለውም፡፡ ሰውነቱ እየተቃጠለና እያለቀ ነበር፤ እምነቱ ግን አልጠፋም ነበር፡፡ ሥጋው አለቀ፤ ትጋቱ ግን አላለቀም፡፡ የእሳቱ ፍም በእጁ መዳፍ ላይ ሲቀጣጠልና ሕመሙም ሲሰማው የነፍሱ ብርታት ግን አልጠፋም ነበር፡፡ አዎ! እጁ እሳቱ ፈጅቶት ወድቋል፤ ሥጋ እንጂ ጽኑ ግንብ አይደለምና፡፡ ነፍሱ ግን ኹለተኛዉን እጁን ወደ ማየት ዞረች፤ ይኸውም በእርሷም ጽናቷን ታሳይ ዘንድ ነው፡፡ አንድ ጀግና ወታደር ጠላቶቹን በሚያጠቃበት ጊዜ የተቃዋሚዎቹን ሰልፍ ከበተነና በሰይፍ አድርጎ በተከታታይ ምት ከመታቸው በኋላ፥ ቀጥሎ የሚያደርገው ነገር በዙሪያው ሌሎች ያሉ እንደ ኾነ ወደ መፈለግ ነው፤ ምክንያቱም ጠላቶቹን ኹሉ ገድሎ አልጨረሳቸውምና፡፡ እዚህም ላይ የብፁዕ በርለዓም ነፍስ የአጋንንትን ማኅበር ስትጨርስ እጁ ከነደደች በኋላ ሌላዉን እጁን ወደ ማየት ዞረች፡፡ ይኸውም በእርሷም ትጋቱን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡
     (9) አንድ እጁን ብቻ ለእሳቱ እንደ ሰጠ አድርጋችሁ አትንገሩኝ፡፡ ይልቁንም ከዚያ በፊት ይህንን አስቡ፡- እጁን ወዶና ፈቅዶ የሰጠ ሰው ራሱንም (ከአንገት በላዩንም) ቢኾን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ጀርባዉንም ለእሳትና ለበረኻ አውሬዎች ይሰጣል፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ያለ ነገር ከዚያች ቀን በፊት የመቀበል ልምዱ ባይኖረዉም ባሕርና ገደል፣ መስቀልና መንኰራኩር፣ ሌላውም ማንኛውም ዓይነት ስቃይ ወዶና ፈቅዶ ይቀበላል፡፡ በሌላ አነጋገር፥ ሰማዕታቱ የሚቀበሉት ስቃይ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገለጥ አይደለም፤ ተነግሮ የማያውቅ የስቃይ ዓይነት ነው፡፡ ምክንያቱም የአሰቃዮቻቸውን ሕሊና (ፈቃድ) መቈጣጠር አይችሉም፤ ወይም ስቃዩ ከዚህ በላይ መኾን የለበትም የማለት መብቱ የላቸውም፡፡ የሚደርስባቸው ስቃይ በስቃይ አድራሹ ኢ-ሰብአዊና አረሜኔአዊ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡ ሰውነታቸው ካላለቀና የስቃይ አድራሹ ፈቃድ ካልረካ በስተቀር አይቆምም፡፡ በመኾኑም የበርለዓም ሰውነቱ ተጨማደደ፤ ፈቃዱ ግን ከሚነድደው እሳት በላይ ያበራና ይንቦገቦግ ነበር፡፡ ይኸውም በዚያ ከሚነድደው እሳት ይልቅ መንፈሳዊ እሳት በዚያ ውስጥ ያበራ ስለ ነበር ነው፡፡ ስለዚሁ ምክንያትም በርለዓም ከኣፍአ ይነድ የነበረውን እሳት ልብ አላለዉም፤ የሚያቃጥለው የክርስቶስ ፍቅር በልቡ ይንቀለቀል ስለ ነበር ከውጭ የነበረውን እሳት አላስተዋለውም፡፡   
     (10) ተወዳጆች ሆይ! እኛም እነዚህን ነገሮች የምንሰማ ብቻ አንኹን፤ እነርሱንም እንምሰላቸው እንጂ፡፡ ገና ስንጀመር የተነጋገርነውን አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ ሰማዕቱን በዚሁ ሰዓት ብቻ የምታደንቁት አትኹኑ፡፡ ኹሉም ሰው ወደ ቤቱ ሲሔድ ቅዱሱን አብሮ ይዞት ይሒድ፡፡ ወደ ቤቱ ይዞት ይግባ - ከዚህም በላይ የነገርኩትን እያስታወሰ ወደ ልቡናው ያስገባው፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው እንኳን ደኅና መጣህ በሉት፡፡ እጁ እንደ ተዘረጋም በልቡናችሁ ላይ አስቀምጡት፡፡ የድል አክሊል የተቀዳጀውን እንኳን ደኅና መጣህ በሉት፤ ከልቡናችሁ ወጥቶ ይሔድ ዘንድም አትፍቀዱለት፡፡ ወደ ሰማዕታቱ መቃብር እንድትመጡ ያደረግንበት ዋናው ምክንያቱም ይኼው ነው - ከማየትም ጭምር ምግባር ትሩፋትን ለመሥራት እንድትበረቱ እንዲሁም ልክ እንደ እነርሱ ጉጉት ያድርባችሁ ዘንድ፡፡ አንድ ወታደር መስማት ብቻ ወኔ የሚያሳድርበት ከኾነ ማየት ደግሞ ይበልጥ ያበረቷል፡፡ በተለይም የወታደር ካምፕ ውስጥ ሲገባ፣ የአንድ ወታደር ሰይፍ በደም ጨቅይቶ ሲመለከት፣ የጠላት ራስ እዚያ ተጋድሞ ሲያይ፣ ከጠላት የተማረከውን መሣሪያ ተንጠልጥሎ ሲያስተውል፣ ድል ባደረገው ሰው እጅ የጠላት ትኩስ ደም ሲመለከት፣ ጦሩንንና ጋሻዉን እንዲሁም ቀስቱንና ሌሎች የጦር መሣሪያዎቹን በየሥፍራው ሲመለከት እጅግ ወኔ ያድርበታል፡፡ እኛም እዚህ የተሰበሰብነው ስለዚሁ ምክንያት ነው፡፡ የሰማዕታት መቃብር ማለት የወታደር ካምፕ ማለት ነውና፡፡ ዓይነ ልቡናችሁን ብትገልጡ እዚህ ካምፕ ውስጥ የጽድቅ ጥሩርን፣ የእምነት ጋሻን፣ የመዳንን ራስ ቍር፣ የወንጌል ጫማን፣ የመንፈስንም ሰይፍ የዲያብሎስን ራስ ወደ ምድር አምዘግዝጎ ሲጥለው ታያላችሁ /ኤፌ.6፥14-17/፡፡ የአጋንንት መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች በሰማዕታቱ መቃብር አጠገብ ወድቀውና በተደጋጋሚም ራሳቸውን ሲቧጥጡ የምታዩአቸውም ሌላ ነገር አይደለም፤ የተቈረጠ የክፉው ዲያብሎስ ራስ ነው እንጂ፡፡ አሁንም ቢኾን እነዚህ መሣሪያዎች ለእነዚህ የክርስቶስ ወታደሮች አሉላቸው፡፡ ነገሥታት ጀግና ባሪያዎቻቸው ሲሞቱ ከነመሣሪያዎቻቸው እንደሚቀብርዋቸው ኹሉ፥ ክርስቶስም እንደዚሁ እነዚህ ሰማዕታት ከነመሣሪያቸው እንዲቀበሩ አድርጓል፡፡ ይኸውም ከትንሣኤ ዘጉባኤ በፊት የቅዱሳን ክብራቸውና ኃይላቸው እንዴት እንደ ኾነ ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ መንፈሳዊ መድፎቻቸውን ተማሩ፤ ደስ የሚያሰኝ ሽልማትንም ይዛችሁ ትሔዳላችሁ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እናንተም ከዲያብሎስ ጋር - ያውም ታላቅና ብዙ እንዲሁም የማያቋርጥ - ጦርነት አለባችሁና ይህንን ተማሩ፡፡
     (11) ስለዚህ ልክ እንደ እነርሱ ድል ታደርጉ ዘንድ ተጋድሎአቸው እንዴት እንደ ነበረ ተማሩ፡፡ ሀብትንና ገንዘብን እንዲሁም ሌላው የዚህን ዓለም ብልጭልጭ ነገርን ናቁ፡፡ ባለጸጋ የኾኑ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን እንደኾኑ አድርጋችሁ አታስቡአቸው፤ ንዑዳን ክቡራንስ ሰማዕታት ናቸውና፡፡ ንዑዳን ክቡራን የሚባሉት በቅምጥልነት ሕይወት የሚኖሩት አይደሉም፤ ሰውነታቸውን በእሳት ጋን ውስጥ የሚያኖሩት ናቸው እንጂ፡፡ ብፁዓን የምንላቸው የተከመረን የምግብ ዓይነት ለመብላት የተቀመጡትን አይደለም፤ በፈላ ውኃ ውስጥ የሚጨመሩትን ነው እንጂ፡፡ በየቀኑ ገላቸውን የሚታጠቡትን አይደለም፤ በየመቃብሩ ያሉትን ነው እንጂ፡፡ በየመዓልቱ የሽቱን ዓይነት የሚቀቡትን አይደለም፤ ከሰውነታቸው ላይ ጭስንና ላብን የሚያወጡትን ነው እንጂ፡፡ ይህ ጥዑም መዓዛም ከዚያኛው ይልቅ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ሽቱውን የሚጠቀሙ ሰዎች ወደ ቅጣት ይመራቸዋል፤ ይህኛው (የሰማዕትነቱ) ግን ወደ ላይኛው አክሊል ሽልማት ይወስዳል፡፡ ቅምጥልነት፣ ሽቱን መቀባባት፣ ያለ ልክ ወይንን መጠጣት፣ አብዝቶም መብላት እንደ ምን ክፉ እንደ ኾነ መማር ትወዳላችሁን? እንኪያስ ነቢዩን አድምጡት፤ እንዲህ ያለውን፡- “ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለሚተኙ፣ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ፣ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ፣ በጽዋ የቀላ ወይንን ለሚጠጡ፣ እጅግ ባማረ ሽቱም ለሚቀቡ ወዮላቸው” /አሞ.6፥4-6/፡፡ እነዚህ ነገሮች በዘመነ ብሉይ የተከለከሉ ከነበሩ፥ ትምህርቱ በሰፋበት በጸጋው ዘመን (በዘመነ ሐዲስ) ደግሞ ይበልጥ ይከለከላሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች የምናገራቸው ለወንዶችም ለሴቶችም እኩል ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያት ለኹሉም ናትና፡፡ የክርስቶስ ወታደር ለመኾን ጾታ መሥፈርት አይደለምና፤ ማኅበሩም አንድ ነውና፡፡ ሴቶችም በሰማዕትነት ጊዜም ኾነ በሌላ ደፍሮ መናገርም በሚያስፈልግበት ሰዓት የጽድቅ ጥሩርን መልበስ፣ ጋሻን ማንሣት፣ ጦርንም መወርወር ይቻላቸዋል፡፡ አንድ የሠለጠነ ቀስተኛ ሰው አነጣጥሮና ወደሚፈልገው ዓላማ የሚወረውር ከኾነ የጠላቱን ሰልፍ ትርምስምሱን ያወጧል፡፡ ልክ እንደዚሁ የዲያብሎስን የማታለል ሥራን የሚዋጉ ቅዱሳን ሰማዕታትና የእውነት ወታደሮችም ቃላቸውን ከአንደበታቸው አነጣጥረው ልክ እንደ ቀስቱ አድርገው ይወረውራሉ፡፡ እነዚህ እንደ ቀስት በአየር ላይ የሚወረወሩ ቃላትም በማይታየው የአጋንንት ጉልበት ላይ ያርፋሉ፤ የጦርነት ሰልፋቸውንም ይበትኑታል፡፡
     (12) ብፁዕ በሚኾን በበርለዓም የኾነውም ይኸው ነው፡፡ ልክ እንደ ቀስት ቃሉን ብቻ በመወርወር የዲያብሎስን ሠራዊት አወደመው፡፡ እኛም ይህን እናድርግ፡፡ የቲያትር ትርኢትን ያሳዩ ሰዎች ከመድረኩ ሲወርዱ እንዴት ልዝብ እንደሚኾኑ አይታችኋልን? ይህ የሚኾኑበት ምክንያትም በመድረኩ ላይ በትኩረት ይሠሩ ስለ ነበር ነው፡፡ ከመድረኩ ከወረዱ በኋላም ቢኾን ያ ነገር በሕሊናቸው ስለሚቀረጽ ዓይኖቻቸውን እዚህም እዚያም ያሽከረክራሉ፤ እጆቻቸውን ያወዛውዛሉ፤ እግሮቻቸውን ያዟዙራሉ፤ በዚያ በመድረኩ የነበረውን ኹሉንም ነገር ከመድረኩ ከወረዱ በኋላም ቢኾን ያደርጉታል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ነፍሳቸውን የሚጎዳ ነገር ይህን ያህል በሕሊናቸው የሚያዩት ከኾነና በመድረኩ የተከናወነውን ነገር ምንም የማይረሱት ከኾነ፥ እዚህ ቅዱሳን ሰማዕታትን በመምሰላችን ከቅዱሳን መላእክት ጋር የምንነጻጸረው እኛ’ማ ቢያንስ የእነዚህ ተዋንያንን ያህል የተነገረንን ነገር ለመያዝ ፍላጎት ከሌለን ምን ዓይነት ሰነፎች ብንኾን ነው? እማልዳችኋለሁ፤ እለምንማችኋለሁ! ስለ ድኅነታችን እንዲህ ቸልተኞች አንኹን፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታቱን በእሳት ከሚጠበሰው ሥጋቸው፣ በፈላ ውኃ ውስጥ እንደ ተጨመሩ፣ ከነሌላ ስቃያቸውም ጭምር ዘወትር በልቡናችን ውሳጤ እናስቀምጣቸው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ሠዓልያን በጭስ፣ በጥቀርሻና በጊዜ ብዛት የወየበ ሥዕልን እንደሚወለውሉት ኹሉ እናንተም ይህን ለማድረግ ሰማዕታቱን አስቡአቸው፤ በኃጢአት ጥቀርሻ የወየበ ልቡናችሁን ለማጽዳት እነዚህን ሰማዕታት አስታውሱአቸው፡፡ ይህንን በልቡናችሁ ዘወትር የምታስቡ ከኾነም ሀብት ንብረትን አታደንቁም፤ በድህነታችሁ አታለቅሱም፤ ክብርንና ሹመትን አታወድሱም፤ በአጠቃላይ በሰዋዊ ጉዳዮች ደስታን እንደማታገኙ ምንምም የሚያስቀና ነገር እንደሌለ ትገነዘባላችሁ፡፡ ይልቁንም ከእነዚህ ነገሮች ኹሉ በላይ ትኾናላችሁ፤ ይህ በልቡናችሁ የተሣለ ሥዕልም ዘወትር ወደ ምግባር ወደ ትሩፋት ይመራችኋል፡፡ ሰዎችን እንደ ወታደር ኾነው በጦር ሜዳ ላይ የሚመለከት ሰው የቅምጥልነት ሕይወትን አይመኝም፤ ምቾትንና ድሎትን የተመላ ሕይወትን አያደንቅም፤ ከዚያ ይልቅ ያ ሸካራ ሕይወት - ያ ውጥረት የተመላበትና ዘወትር በፍልሚያ የኾነን ሕይወት ያደንቃል እንጂ፡፡ ሲጀምርስ አብዝቶ መጠጣትንና መጋደል፣ አብዝቶ መብላትንና ወታደር፣ ሽቶና የጦር መሣሪያ፣ ጦርነትና መዝናናት ምን አንድነት አላቸው? ተወዳጆች ሆይ! እናንተም የክርስቶስ ወታደሮች ናችሁ፤ ስለዚህ መሣሪያችሁን እንጂ ሽቱን አታንሡ፡፡ እናንተ አትሌቶች ናችሁ፤ ስለዚህ እንደ ሯጮች እንጂ ትርኢት እንደሚያሳዩ ሰዎች አትኹኑ፡፡ በዚሁ መንገድም እነዚህን ቅዱሳን እንምሰላቸው፡፡ በዚሁ መልኩም የእምነት አርበኞቹን፣ የክብር አክሊል የተቀዳጁትን፣ የእግዚአብሔርም ወዳጆችን እናክብራቸው፡፡ እነርሱ ያገኙትን አክሊል ሽልማት እናገኝ ዘንድ እነርሱ በሔዱበት ፍኖት እንሒድ፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር የባሕርይ ገንዘቡ የኾነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ እነዚህን በረከቶች እናገኝ ዘንድ ይርዳን፡፡ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን!!!
© ይህ ጽሑፍ በቅርቡ ወደ እናንተ ወደ አንባቢያን እጅ ከሚደርሰውና ሙሉ ገቢው በመቀሌ ሀገረ ስብከት የዐይናለም ደብረ ኃይል ቅዱስ ጊዮርጊስ የመነኮሳይያትና የአረጋውያን አንድነት ገዳም መርጃ እንዲውል ከተረጎምሁት አዲስ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡

5 comments:

  1. Kale hiwot yasemaln Yeagelgilot zemnachihun yabizalin

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን የሰማእቱን በረከት ያድልልን፡፡

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount