Pages

Friday, January 29, 2016

ዕረፍተ ድንግል



በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(ከመጽሐፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 20 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ይዞ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እመቤታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የሔደው የዕረፍቷ ጊዜ መድረሱን ለማብሠር ነበር፡፡ የድል ምልክት የሆነውን ፍሬው የተንዠረገገ የቴምር ፍሬ የሚያፈራውን ዘንባባ ይዞ ለሁለተኛ ጊዜ እርሷ ወዳለችበት ይዞ ገብቶ ደስ ይበልሽ ሲላት አሁንም እየሰገዳና እጅ እየነሣ ነበር፡፡ ጌታችን እንዳዘዘውም "ልጅሽና ጌታሽ እናቴ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ጊዜው ደርሷል ብሏል፡፡ ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ቅድስት ሆይ ስለዚህም ለሁለተኛ ጊዜ ይህን መልካም የምሥራች እነግረሽ ዘንድ ላከኝ፡፡ ብፅዕት ሆይ በምድር የሚኖሩትን ሁሉ በደስታ እንደሞላሻቸው አሁን ደግሞ በዕረፍትሽና በዕርገትሽ ምክንያት የሰማይ ኃይላት በደስታ ይሞሉ ዘንድ በሰማይ ያሉ ነፍሳትም ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በክብር ያበሩ ዘንድ ምክንያት ትሆኛለሽ፡፡ ደስተኛይቱ ፍስሕት የሚል ማዕረግ ለዘላለም ተስጥቶሻልና ስታዝኝና ስታለቅሽ በኖርሽው መጠን ደስ ይበልሽ፡፡ ጸሎቶችሽና አስተብቁዖቶችሽ በሙሉ በልጅሽ ፊት ወደ ሰማይ ዐርገዋል፤ ስለዚህም ይህን ዓለም ትተሽው ወደ ሰማይ ትሔጅና ፍጻሜ በሌለው የዘላለም ሕይወት ከልጅሽ ጋር ትኖሪ ዘንድ አዝዟል" ብሎ ዘንባባውንም በእጇ ሰጣት፡፡

የነበረውን ትውፊት ሁሉ አሰባስቦና አጠናቅሮ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በግሪክ ቋንቋ ሕይወቷንና ተጋድሎዋን በተሻለ ሁኔታ የጻፈው መክሲሞስ ዘኢየሩሳሌም እንደመዘገበው እመቤታችን የመልአኩን ብሥራት በሰማች ጊዜ እጅግ ተደስታ እንደ ቀድሞው ሁሉ በፍጹም ትሕትና "እነሆ የእግዚአብሔር አገልጋዩ፤ አሁንም እንደቀድሞው እንደቃልህ ይደረግልኝ አለችው" ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ አሁን በዚህ ጽሑፍ የማልገልጻቸው እጂግ ብዙ ገቢረ ተአምራት ተፈጽመዋል፡፡ እመቤታችን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የሰጣትን ዘንባባ ይዛ በደብረ ዘይት ተራራ ሔዳ ከጸለየች በኋላ መጀመሪያ ዮሐንስ መጥቷል፡፡ ከዚያም ቤት ከተመለሰች በኋላ ሐዋርያትና ብዙ ተላውያነ ሐዋርያት ደንገት አንድ ጊዜ በደመና ደረሱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከደመናው ከተቀበላቸው በኋላ ወደ እርሷ ይዟቸው ገባ፡፡ ሁሉም አንድ በአንድ እየሆኑ በፊቷ እያለፉ ተሳለሟት፤ እርሷም አነጋገራቸዋለች፡፡ ከአርድእት አንዱ የሆነው ተላዌ ቅዱ ጳውሎስ የሆነውና ከፍልስፍና የተመለሰው የአቴናው ዲዮናስዮስ ከተገኙት አርድእት መካከል እርሱ ቅዱስ ጤሞቴዎስና አንድ ቅዱስ ሔሮቴዎስ እንደነበሩና ቅዱስ ጴጥሮስን፤ ቅዱስ ጳውሎስንና ሌሎቹን ሐዋርያት ስታናግራቸው እንዳየና ራሱም በፊቷ አልፈው እማሔ ካደረጉት መካከል መሆኑን ለጢሞቴዎስ በላካት መልእክት ላይ መዝግቦታል፡፡ ከዚያም በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወርዶባቸው ሁሉም ሐዋርያትና አርድእት መንፈስ ቅዱስ እንደሰጠው መጠን ተሰምቶ የማያውቅ ልዩ ምስጋና ማቅረባቸውን መዝግቧል፡፡ ከዚህም በኋላ የተደረጉት ተአምራት የጌታችን ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር መውረድ እን ሙሴ እነዳዊት በአንድነት ከአእላፋት መላእክት ጋር ሲዘምሩና የሰማይ ሠራዊት በደስታ ሲጥለቀለቁ ጽዮንም ስትናወጥ የነበሩት ሐዋርያትና አርድእት ሁሉ መስክረዋል፡፡
 
የአካላዊ ቃልን ወደዚህ ዓለም መምጣት ማብሠር እንደተሰጠህ የድንግሊቱንም ወደዚያኛው መሔድ ማብሠር ድጋሜ የተሠጠህ የታመንህን የከበርክ ገብርኤል ሆይ እባክህ መልካም ነገር እያለ የራቀውን የእኛን ትውልድም ከመልካሙ ነገር አገናኝልን፤ መልካሙን አሰማን፡፡ ከድንግሊቱና ከደስተኛይቱ እናታችን በረከትም አድርስልን፡፡ እንግዲያውስ ቅዱሳኑን ተከትለን እኛም እየዘመርንና እያመሰገንን የሰው ዘር መመኪያ የሆነችውን የእናታችንና የእመቤታችን የንጽሕተ ንጹሐን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያምን በዓለ ዕረፍት በተከበረው ትውፊታችን መሠረት እናክብር፡፡
እንኳን ለበዓለ ዕረፍታ ለንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም አደረሳችሁ፡፡

5 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያስማልን፤ከእመቤታችን ረድኤት፣በረከት ያሳትፈን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ በእድሜ በፀጋ ያቆይልን፤ ከእናታችን ከድንግል እናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከቱን ያድልልን አሜን።

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ በእድሜ በፀጋ ያቆይልን

    ReplyDelete
  4. ቃለ ሕይወት ያስማልን፤ከእመቤታችን ረድኤት፣በረከት ያሳትፈን ።

    ReplyDelete