Pages

Friday, February 5, 2016

የክርስቲያን መከራው


በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ለአንድ ክርስቲያን መከራው ለጥቅሙ የሚሰጠው ነው፡፡ ለአንድ ክርስቲያን  መከራን መቀበል ማለት ከሰማያዊ ክብር መሳተፍ ነው፡፡ ይህስ እንደ ምን ነው ያልከኝ እንደ ኾነም እንዲህ ብዬ እመልስልኻለሁ፡- ስንፍናንና ክፉ ፈቃድን የሚያርቅ፣ ዓለማዊ ግብርን መውደድን፣ ውዳሴ ከንቱ መውደድን የሚያርቅ ነውና የክርስቲያን መከራው ክብርን ያስገኛል፡፡ ነፍስን የሚረዳ፣ በክብር ላይ ክብርን የሚያገኝ ነውና የክርስቲያን መከራው የሚያሳዝን መከራ አይደለም ብዬ እነግርኻለሁ፡፡

የቅዱሳኑ ክብራቸው እንዲህ ደምቆ ልናየው የቻልነው ከምን የተነሣ እንደ ኾነ እንመልከተው፡፡ ስላገኛቸው መከራ አይደለምን? ፈቃድህ ከኾነ ገና ከመነሻው ጀምረን እንቍጠራቸው፡፡ አዎ! ከአቤልና ከኖኅ ጀምረን እስኪ እንቍጠራቸው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን በዚያ ለመቍጠር እንኳን በሚታክቱ ክፉዎች ሰዎች መካከል እየኖሩ ያለ መከራ ክብርን ማግኘት አልተቻላቸውም፤ እንዲህ እንደ ተባለ፡- “ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኘው” /ዘፍ.6፥9/፡፡ ተመልከት! ለእኛ አብነት የሚኾኑን እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች አሉን፡፡ ብዙ አበውን፣ ብዙ ሕፃናትን፣ ብዙ መምህራንን አብነት አድርገን መከራ እንቀበላለን፡፡ በሰብአ ትካት መካከል ኾኖ መከራ ስለ ተቀበለው ስለ ኖኅ ምን ማለት ይቻለናል? በዙሪያው ስለ ነበረው እንግዳና አስደናቂ ዝናብ ምን ማለት እንችላለን? ወይስ አብርሃም ከአገር አገር ሲሰደድ መኖሩን፣ ሚስቱን እንደ ቀሙት፣ ጦርነትና ረሃብ እንዳገኘው እናገር ዘንድ ይገባኛልን? ወይስ እጅግ አስጨናቂ ነገሮች ስላገኙት፣ ከቦታ ቦታ ስላሳደዱት፣ ድካሙ ከንቱ ይኾንበት ስለነበረው፣ በድካሙ ላይ ሌሎች ሰዎች ይጠቀሙበት ስለ ነበረው ስለ ይስሐቅ ልናገርን? ወይስ ስለ ያዕቆብ ልናገርን? ያዕቆብ ያገኘውን መከራ እዘረዝር ዘንድ አይገባኝም፤ እርሱ ራሱ ለፈርዖን የተናገረውን ምስክር አድርጌ ላቅርብ እንጂ፤ እንዲህ ያለውን፡- “የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ኾኑብኝ፡፡ አባቶች በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያኽሉም” /ዘፍ.47፥9/፡፡ ወይስ ስለ ዮሴፍ ልናገር ይገባኛልን? ወይስ ስለ ሙሴ ወይስ ስለ ኢያሱ ወይስ ስለ ዳዊት ወይስ ስለ ኤልያስ ወይስ ስለ ሳሙኤል ወይስ ስለ ነቢያት ኹሉ ልናገር ይገባኛልን? እነዚህ ኹሉ በመከራ እንደ ከበሩ አታውቅምን? አንተ ሰው ሆይ! ከዕረፍትና ከቅምጥል ሕይወት ክብርን ልታገኘ ትሻለህን? እኔ እነግርሃለሁ፤ በፍጹም አታገኘውም፡፡
ወይስ ስለ ሐዋሪያት ልናገርን? እነዚህስ ከኹሉም በላይ መከራ ተቀበሉ፡፡ ጌታችን ክርስቶስም እንዲህ ብሏልና፡- “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” /ዮሐ.16፥33/፤ “እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፡፡ ዓለም ግን ደስ ይሏል” /ዮሐ.16፥20/፤ “ወደ ሕይወት የምትወስደው በር እጅግ ጠባብ መንገዷም ቀጭን ናትና የሚገቡባትም ጥቂቶች ናቸው” /ማቴ.7፥14/፡፡ ታዲያ እስኪ ንገረኝ! ጌታችን መንገዷ ጠባብ ናት እያለ አንተ ሰፊውን መንገድ ትፈልጋለህን? ይህስ እንደ ምን ሊኾን ይችላል? በሌላ መንገድ የምትሔድ ከኾነም ወደ ሕይወት አትደርስም፤ እንደ ምርጫህ ምረረ ገሃነም ያገኝኻል እንጂ፡፡

2 comments: